Filed under: News Feature,ነፃ አስተያየቶች |

የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 1 ፅኁፍ በብሔርተኝነትና በራስ-የመወሰን መብትን መሰረት ያደረገ የትግል እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚጀመር የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎችንና የትግራይ አማፂያንን በማሳያነት በመጥቀስ ተመልክተናል። በዚህ ፅኁፍ ደግሞ የደርግና እንግሊዝ ጦር ሰራዊት ከአማፂያኑ የደረሰባቸውን ያልተጠበቀ ሽንፈትና ውርደት ተከትሎ በነፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀሙትን በደልና ጭቆና እንመለከታለን። ከዚያ በመቀጠል፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውጊያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት የአማፂያኑ መሪዎች/ልሂቃን ከጦርነቱ ጎን-ለጎን ለራሳቸው ማንሳት የነበረባቸው “መሰረታዊ ጥያቄ” ምን እንደሆነ እንመለከታለን።

ስዩም ተሾመ

በክፍል አንድ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የደቡብ አፍሪካ ነባር ነጭ ሰፋሪዎች እና የትግራይ ሕዝብ የትጥቅ ትግል የጀመሩት በራስ-የመወሰን መብታቸውን ለማረጋገጥ ነው። በዚህ መልኩ የተጀመረውን የትጥቅ ትግል ለማክሸፍ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእንግሊዝ እና የደርግ ወታደሮች ተሰማርተው ነበር። የሁለቱም ጦር ሰራዊት በአማፂያኑ ከተደቀነባቸው አሳፋሪ ሽንፈትና ውርደት ራሳቸውን ለማዳን በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። እስኪ እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች የፈፀሙትን ጭፍጨፋ እና ደርግ በትግራይ፥ ሃውዜን ላይ የፈፀመውን ጭፍጨፋ የምክንያት-ውጤት ተያያዥነትና ተመሳሳይነት በአጭሩ እንመልከት።

1. በትግል ወቅት የተፈፀመው ጭፍጨፋ

1.1 በደቡብ አፍሪካ፡ “መሬቱን በእሳት መለብለብ” 

እ.አ.አ በ1899 ዓ.ም የእንግሊዝ ጦር አዛዦች በደቡብ አፍሪካ የነጭ ሰፋሪዎች ግዛትን “Boers Republic” ለመቆጣጠር ሲዘምቱ ለሽምቅ ተዋጊዎቹ ዝቅተኛ ግምትና ከፍተኛ ንቀት ነበራቸው። ሽምቅ ተዋጊዎቹን “ኋላ-ቀር፣ ቀሽሞች እና የጫካ ሽፍቶች” በማለት ያጣጥሏቸው ነበር። በእርግጥ የነጭ ሰፋሪዎች ጠቅላላ የሕዝብ ብዛት ከ300 ሺህ አይበልጥም ነበር። ከዚህ ውስጥ ግን 27000 የሚሆኑ የሽምቅ ተዋጊዎች ነበሯቸው። በአንፃሩ በጦርነቱ የተሳተፈው የእንግሊዝ ጦር ሰራዊት ጠቅላላ ብዛት 500 ሺህ ይደርስ ነበር።

የደቡብ አፍሪካ ሽምቅ ተዋጊዎች ውጊያው በተጀመረ የመጀመሪያ ሁለት አመታት ውስጥ በእንግሊዝ ጦር ላይ ያልተጠበቀ ድል ተቀዳጁ። እንግሊዝ ከአሰማራቻቸው የወታደሮች አንፃር 5% የሚሆኑት የደቡብ አፍርካ ሽምቅ ተዋጊዎች 22000 የሚሆኑ የእንግሊዝ ወታደሮችን ገደሉ። በዚህም እንግሊዝ ከ1815 – 1915 ዓ.ም ባሉት መቶ አመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማታውቀው አሳፋሪ ሽንፈትና ውርደት ተከናነበች

አብዛኛው የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች በሽምቅ ውጊያው ተሳታፊ ናቸው። ወደ ጦር ሜዳ ሳይሄዱ የቀሩት በአብዛኛው እናቶች፥ ሕፃናት ልጆችና አዛውንቶች ነበሩ። የእንግሊዝ ጦር በሽምቅ ተዋጊዎቹ የሚደርስበት ጥቃት ራሱን ለማዳን “ተዋጊዎቹን ለማጥፋት “መሬቱን በእሳት መለብለብ” (Scorched-earth) የተባለውን የውጊያ ስልት ተግባራዊ አደረገ። ተዋጊዎቹ በሚንቀሳቀሱበት አከባቢ ያሉ መኖሪያ ቤቶች ሙሉ-ለሙሉ በእሳት ቃጠሎ እንዲወድሙ ተደረገ።

በዚህ ምክንያት፣ ከመቶ ሺህ በላይ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎችን በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ። ወደ ማጎሪያ ካምፕ ከገቡት ውስጥ 28000 የሚሆኑት በርሃብና በበሽታ ሲሞቱ፣ ከእነዚህ ውስጥ 22000 (81%) የሚሆኑት ከ16 አመት በታች ሕፃናት ናቸው።  ለአንድ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪ ውርደት ማለት ሴቶች፣ ሕፃናትና አዛውንቶች በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታጉረው በርሃብና በበሽታ ሲያልቁ እያዩ ምንም ማድረግ አለመቻል ነው። ከዚህ ሰቆቃ የተረፉት ነጭ ሰፋሪዎች እ.አ.አ በ1948 ዓ.ም እንግዝ ለቅቃ ስትወጣ “ከዳኒኤል ፍራንኮይስ ማለን” (Daniel Francois Malan) መሪነት የአፓርታይድ ስርዓትን መሰረቱ።

1.2 በኢትዮጲያ፡ “ባህሩን በቦምብ ማድረቅ” 

እ.አ.አ በ1979 ዓ.ም ወታደራዊ ደርግ መንግስት በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የሚንቀሳቀሱትን አማፂያን በኃይል ለመደምሰስ ቆርጦ ተነሳ። ለዚህ ዓላማ ሁለተኛውን አብዮታዊ ጦር ከፍተኛ ትጥቅ ያለው ከ70ሺህ በላይ ወታደሮች አሰማራ። ከአንድ አመት በኋላ በመጋቢት ወር 1980 ዓ.ም ግን ከ15000 የማይበልጡ የሻዕቢያ ተዋጊዎች ወደ 10000 የደርግ ወታደሮችን በመግደል አሸነፉ። በቀጣዩ ሚያዚያ ወር 1980 ዓ.ም ደርግ ሦስተኛን አብዮታዊ ጦር በማደራጀት በትግራይ የሚንቀሳቀሱ አማፂያንን በኃይል ለመደምሰስ በለገሰ አስፋው መሪነት ተንቀሳቀሰ።

ሦስተኛን አብዮታዊ ጦር በትግራይ በአማፂያኑ ቁጥጥር ስር የወደቁትን ቦታዎች ለማስለቀቅ እና የኤርትራ-ትግራይ መስመርን ለማስከፈት ያደረገው ጥረት በሕውሓት የውጊያ ስልት በተደጋጋሚ ከሸፈ። የደርግ ሰራዊት በኤርትራ ካጋጠመው አሳፋሪ ሽንፈት በኋላ ሻዕቢያን ለማሸነፍ በቅድሚያ ሕወሓትን መደምሰስ እንዳለበት ወስኖ ነበር የመጣው። ነገር ግን፣ የአማፂያኑን ይዞታ መልሶ ለማስለቀቅና የአዲስ አበባ – አስመራ መንገድን ለማስከፈት ባደረጋቸው ውጊያዎች ተደጋጋሚ ሽንፈት ገጠመው።

በመጨረሻም፣ በትግራይ አማፂያን እየደረሰበት ያለው ተደጋጋሚ ሽንፈት ከትግራይ በተጨማሪ ኤርትራንም እያሳጣው እንደሆነ ሲውቅ የወሰደው እርምጃ በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ እልቂት አሰከተለ። በደቡብ አፍሪካ የሸምቅ ተዋጊዎች የተደቀነባቸውን አሳፋሪ ሽነፈት ለማስቀረት ተግባራዊ እንደተደረገው የ¨Scorched-earth” ፖሊሲ፣ የደርግ ሰራዊት “ዓሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ” በሚል ሃውዜን ላይ የአየር ድብደባ ፈፀመ። የሕውሃት መስራችንና የቀድሞ አመራር የነበሩት አረጋዊ በርሄ የሃውዜን ጭፍጨፋንና በትግራይ ሕዝብ ስነ-ልቦና ላይ ያሰከተለውን ጉዳት እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“…On on 22 June 1988, that Legesse ordered the aerial bombardment of Hawzien. This attack, conducted by helicopter gunships and MiGs, resulted in 1,800 civilian deaths, the worst single atrocity of the war since the start of the ELF insurrection in 1961…. Many elderly parents who had been reluctant to let their children join the Front were now not only encouraging them but also themselves requesting to be armed and join the militia forces. While the numbers of TPLF brigades grew to more than 20,000 fighters, the Dergue’s forces were dwindling.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Amsterdam 2008, Page 184 – 317.

ከላይ ከተገለፀው ክስተት በኋላ የደርግ ሰራዊት በሽንፈት ላይ ሽንፈት ማስተናገድ ቀጠለ። በየካቲት ወር 1981 ዓ.ም የሕወሃት ታጋዮች በእንዳ-ስላሴ የተደረገውን ውጊያ ካሸነፉ በኋላ በቀጣዩ አንድ ሳምንት ውስጥ 20000 የደርግ ሰራዊትና የመንግስት ሰራተኞች ትግራይን ለቀው ወጡ። ይህን ተከትሎ መላው ትግራይ በሕወሃት ቁጥጥር ስር ወደቀ። ግንቦት 20/1983 ዓ.ም የደርግ መንግስት ተገረሰሰ።

በአጠቃላይ፣ እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ የፈፀሙትን በደልና ጭፍጨፋ የደርግ መንግስት በትግራይ ሕዝብ ላይ ፈፅሞታል። ከዚህ በመቀጠል ደግሞ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውጊያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት የአማፂያኑ መሪዎች/ልሂቃን ከጦርነቱ ጎን-ለጎን ለራሳቸው ማንሳት የነበረባቸው “ጥያቄ” ምን እንደሆነ እንመለከታለን።

2. በትግል ወቅት ያልተመለሰው ጥያቄ

ለአንድ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪ ወራሪውን የእንግሊዝ ጦር ለማስወጣት በሚደረገው የትጥቅ ትግል መሳተፍ ትክክለኛ ተግባር ነው። በተመሣሣይ፣ ለአንድ የትግራይ ተወላጅ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ከስልጣን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል መሳተፉ አኩሪ ተግባር ነው። በአጠቃላይ፣ ከኢምፔራሊዝም ወራሪ ሆነ ከአምባገነናዊ ስርዓት ነፃ ለመውጣት የሚደረገው የትጥቅ ትግል አግባብነቱ አጠራጣሪ አይደለም።

ነገር ግን፣ “Edward Said” የተባለው” ምሁር “Frantz Fanon” የተባለ የአልጄሪያ የነፃነት ታጋይን በመጥቀስ፣ የትግል መሪዎች/ልሂቃን የትጥቅ ትግሉን ከመምራት ባለፈ አንድን ጥያቄ መጠየቅና መመለስ እንዳለባቸው ይገልፃል፡-

“This is defensive nationalism of course, yet as Frantz Fanon analysed the situation during the height of the Algerian war of liberation against the French, going along with the approving chorus of Algerian nationalism as embodied in party and leadership is not enough. There is always the question of goal which, even in the thick of battle, entails the analysis of choices. Are we fighting just to rid ourselves of colonialism, a necessary goal, or are we thinking about what we will do when the last white policeman leaves? According to Fanon, the goal of the native intellectual cannot simply be to replace a white policeman with his native counterpart, but rather what he called the invention of new souls.”  REITH LECTURES 1993: Representations of an Intellectual, Lec.2: Holding Nations and Traditions at Bay, 1993.

ከላይ እንደተገለፀው፣ ለነፃነት የሚደረገው ትግል ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት፣ ጦርነቱ ተፋፍሞ የሰማዕታቱ ቁጥር እየጨመረ በሄደበት፤ እንደ ደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች ወይም እንደ ትግራይ ሕዝብ በንፁሃን ላይ በደልና ጭፍጨፋ ሲፈፀም፣ በዚህም ምክንያት የታጋዮች ሕዝባዊ ወገንተኝነትና የጨቋኙ ስርዓት ጠላትነት በናረበት ወቅት፣…የትግሉ መሪዎችና ልሂቃን “የትግላችን የመጨረሻ ግብ ምንድነው?” ብለው መጠየቅና ለዚህም ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት አለባቸው።

ይህን መሰረታዊ ጥያቄ ለራስ አለመጠየቅ ወይም በሌሎች ታጋዮች ዘንድ እንዲነሳ አለመፍቀድ እና በትግሉ የመጨረሻ ግብ ላይ ግልፅ የሆነ ግንዛቤና አቅጣጫ ማስቀመጥ አለመቻል በሚታገሉለት ሕዝብ እና በትግሉ ሰማዕታት ላይ ክህደት መፈፀም ነው። በትግል ወቅት ይህን ጥያቄ ራስንና ሌሎች ታጋዮችን በመጠየቅ፣ በጉዳዩ ዙሪያ የተለያየ ሃሳብና አስተያየት እንዲሰጥ በማድረግ፣ በውይይት የዳበረ ግንዛቤና የጋራ መግባባት ካልተፈጠረ በስተቀር የነፃነት ትግሉ ፋይዳ የለውም። ምክንያቱም፣ ጨቋኙ ስርዓት በተወገደ ማግስት እንደ አልጄሪያ፥ ቦስኒያ፥ ደቡብ ሱዳን፥…ወዘተ የእርስ-በእርስ ጦርነት ይከተላል። ወይም ደግሞ እንደ ኤርትራ የሻዕቢያ መንግስት፥ እንደ ኢትዮጲያ የኢህአዴግ መንግስት፥ እንደ ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት፥ …ወዘተ የትግሉ መጨረሻ የቀድሞው ስርዓት ጭቁኖችን አዲስ ጨቋኝ ስርዓት እንዲመሰርቱ ማስቻል ይሆናል።

እንደ አልጄሪያዊው የነፃነት ታጋይና ልሂቅ “Frantz Fanon” አገላለፅ፣ የትጥቅ ትግል የመጨረሻ ግብ “አዳዲስ ነፍሶችን መፍጠር ነው” (the invention of new souls)። በመሰረቱ፣ የዘር/ብሔር አፓርታይድ የትጥቅ ትግል መሪዎችና ልሂቃን ለራሳቸው አሮጌ ነፍስ ይዘው አዲስ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመመስረት ሲያጣጥሩ የሚፈጥሩት ሌላ ጨቋኝ ስርዓት ነው። ነገር ግን፣ እነዚህን አዳዲስ ነፍሶች ምንድን ናቸው? እንዴትስ መፍጠር ይቻላል? ከቀድሞ ጨቋኝ ስርዓት ጋር የትጥቅ ትግል ለመጀመር የተፈጠሩ አሮጌ ነፍሶች ምን ዓይነት ናቸው? በአሮጌ ነፍሶች ውስጥ ሆኖ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት ይቻላል? ለምንና እንዴት? እነዚህን እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በቀጣይ ክፍሎች በዝርዘር እንመለከታለን።