ማሳሰቢያ፡-
(በዚህ ፅሁፍ “የትግራይ ህዝብ” በሚል የሚቀርበው ሃሳብ በዋናነት “የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የትግል መሪዎችንና ልሂቃንን የፖለቲካ አመለካከት፥ ዓላማና ስልት የሚያመለክት እንጂ የብዙሃኑን የትግራይ ሕዝብ ሃሳብና አመለካከት አይወክልም!)


ስዩም ተሾመ

1: የአፓርታይድ ስርዓት አመሰራረት
“የዘር/ብሔር አፓርታይድ” በሚል ርዕስ ባቀረብናቸው አምስት ተከታታይ ፅሁፎች፣ የትግል መሪዎችና ልሂቃን ትግሉም ለማስጀመር በማህብረሰቡ ውስጥ ያሰረፁትን የብሔርተኝነት ስሜት እና በጦርነት ወቅት የተፈጠረውን የጠላትነት ስሜት ከማህብረሰቡ ስነ-ልቦና ውስጥ ማስወገድ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ለዚህ ደግሞ የትጥቅ ትግል መሪዎችና ልሂቃን ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ከራሳቸውና ከትግል ጓዶቻቸው ጋር በግልፅ በመወያየት የጋራ ግንዛቤ መፍጠር አለባቸው።

የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች አማፂያን ከእንግሊዝ ጋር የሚያደርጉት ጦርነት በተፋፋመበት ወቅት የትግል መሪዎቹ/ልሂቃን ይህን ጥያቄ ባለመጠየቃቸው በእንግሊዝ ወታደሮች ላይ እያደረሱት ያለው ያልተጠበቀ ጥቃትና ሽንፈት በሚታገሉለት ማህብረሰብ ላይ የሚስከትለውን ጉዳት እንዳይገነዘቡ አድርጓቸዋል። በተመሳሳይ፣ በራስ-የመወሰን መብትን ተስፋ በመስጠትና የብሔርተኝነት ስሜትን በማቀጣጠል የትጥቅ ትግል የጀመረው ሕውሃት ከከፍተኛ አመራሮች እስከ ተርታ ታጋዮች ድረስ የተለየ ሃሳብና አመለካከትን ማንሳት እንደ ጥፋት ይቆጠር እንደነበር የቀድሞ ድርጅቱ አመራርና መስራች አረጋዊ በርሄ ይገልፃል፡-

“Utilizing ethnic nationalism as the core method of mobilization with its anticipated achievement of self-determination the TPLF began to establish ‘movement hegemony’ in the rural areas of Tigrai. …In the name of ‘democratic centralism’ and with no less harsh measures of dealing with its rival forces, internal dissent in the TPLF was suppressed, for it was considered counter-revolutionary activity that could ruin the whole organization.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Amsterdam 2008, Page 151 – 152

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ በጦርነት ወቅት በመሪዎችና ልሂቃን ዘንድ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የማስተናገድ ድርጅታዊ ባህልና አሰራር ከሌላቸው ከትግል በኋላ፤ አንደኛ፡- በትግል ወቅት በማህብረሰቡ ውስጥ የሰረፀው የብሔርተኝነት ስሜት ወደ ጭፍን ወገንተኝነትና የተበዳይነት ስሜት ይቀየራል፣ ሁለተኛ፡- በጦርነት ወቅት የተፈጠረው የጠላትነት ስሜት ወደ ፍርሃትና አለመተማመን ይቀየራል። ይህ ሲሆን ከትግል በኋላ የሚመሰረተው መንግስታዊ ስርዓት ምን እንደሚመስል ስለ መንግስት መዋቅርና ባህሪ ትንታኔ በመስጠት ግንባር ቀደም የሆነው ፈረንሳዊው ምሁር “Montesquieu” እንዲህ ይገልፀዋል፡-

“In a republic the principle of action is virtue, which, psychologically equates with love of equality; and in a tyranny, the principle of action is fear. …This natural love of equality includes love of others as well as love of self, and egoism, loving one’s self at the expense of others, is an unnatural and perverted condition. …The Sovereign must, therefore, treat all its members alike… If it leaves the general for the particular, and treats one man better than another, it ceases to be Sovereign”

The Social Contract and Discourses

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በፍርሃት የሚመራ የፖለቲካ ስርዓት እንደ ቀድሞው ስርዓት “ጨቋኝ” ይሆናል። በጨቋኝነቱ ላይ የአንድን ብሔር/ዘር መብትና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ዓላማ ካለው ደግሞ “አፓርታይድ”(Apartheid) ይባላል። ከዚህ ቀጥሎ በደቡብ አፍሪካ በነበረው “የዘር አፓርታይድ” እና በኢትዮጲያ ባለው “የብሔር አፓርታይድ” መካከል ከዓላማና ስልት አንፃር ያላቸውን ተመሳሳይነት በዝርዝር እንመለከታለን።

2: የአፓርታይድ ስርዓት ዓላማ
2.1: በደቡብ አፍሪካ 
የደቡብ አፍሪካ ነባር ነጭ ሰፋሪዎች በራስ-የመወሰን መብታቸውን የማጣት አደጋ የተጋረጠባቸው የሌላ ዘር (ሀገር) ተወላጅ በሆኑ አዲስ ነጭ ሰፋሪዎች አማካኝነት ነው። ይህ ከእንግሊዞች ጋር ወደ ጦርነት እንዲያመሩ አድርጓቸዋል። በጦርነቱ ወቅት በነባር ነጭ ሰፋሪዎች ላይ እጅግ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ተፈፅመባቸው። ስለዚህ፣ እ.አ.አ. በ1948 እንግሊዝ ደቡብ አፍሪካን ለቅቃ ስትወጣ በዘር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ የአፓርታይድ ስርዓት ዘረጋ። የስርዓቱ መሰረታዊ ዓላማዎች፤ 1ኛ፡- የነጮችን በራስ-የመወሰን መብት በማረጋገጥ ፖለቲካዊ መብታቸው እንደ ቀድሞ በሌላ ዘር (ሀገር) ተወላጆች የመዋጥ አደጋን ማስቀረት፣ እና 2ኛ፡- በእንግሊዞች የተፈፀመው አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ዳግም ተመልሶ እንዳይመጣ ማድረግ ናቸው።

2.2: በኢትዮጲያ
የትግራይን ሕዝብ በቀዳማዊ ወያነ እና በሕወሃት ዘመን በራስ-የመወሰን መብቱን ለማረጋገጥ ባደረገው የትጥቅ ትግል “በአብዛኛው” ከሌላ ብሔር በተወጣጣ የጦር ሰራዊት ለማዳፈን ጥረት ተደርጓል። በዚህም፣ የአፄ ኃ/ስላሴ መንግስት የቀዳማይ ወያኔ እንቅስቃሴን ለመደምሰስ በወሰደው የኃይል እርምጃ፣ እንዲሁም የደርግ መንግስት ከሕወሃት ጋር ባደረገው 17 ዓመት የፈጀ ጦርነት በጣም ብዙ ሺህ የትግራይ ተወላጆች ለሞትና የአካል ጉዳት ተዳርገዋል። ስለዚህ፣ የደርግ መንግስት ከተገረሰሰ በኋላ በሕወሃት ጠንሳሽነት የተመሰረተው የኢህአዴግ መንግስት በብሄር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ የአፓርታይድ ስርዓት ዘረጋ። የስርዓቱ መሰረታዊ ዓላማ፤ 1ኛ፡- የትግራይ ሕዝብን በራስ-የመወሰን መብት በማረጋገጥ ፖለቲካዊ መብታቸው እንደ ቀድሞ በሌላ ብሔር ተወላጆች እንዳይጨፈለቅ ማድረግ፣ እና 2ኛ፡- በቀድሞ ስርዓት የተፈፀመው በደልና ጭፍጨፋ ዳግም ተመልሶ እንዳይመጣ ማድረግ ናቸው።

3. የአፓርታይድ አተገባበር ስልት 
3.1 በደቡብ አፍሪካ 
ብዙውን ግዜ በደቡብ አፍሪካ ስለነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ሲነሳ በቅድሚያ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው በዘርና ቀለም የሚለያይ ስርዓት መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ስርዓቱ የሀገሪቱን ዜጎች “ነጭ፥ ጥቁር፥ “ከለርድ” (colored) እና ህንዳዊያን” በማለት ለአራት ይከፍላቸዋል። ነገር ግን፣ በዘር-ልዩነት ላይ ተመስርቶ መከፋፈል በነጭ ሰፋሪዎች ላይ የተጋረጠውን በሌላ ዘር ተወላጆች የመወጥ አደጋን አያስቀረውም።

የደቡብ አፍሪካ ነጮች በሌላ ዘር ተወላጆች የመዋጥ አደጋን ማስቀረትና በራስ-የመወሰን መብታቸውን ማስከበር የሚችሉት በሀገሪቱ አብላጫ (majority) የሆኑትን ጥቁሮች በመከፋፈል እና የፖለቲካ ተሳትፏቸውን በመገደብ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ፣ በዘርና ቀለም ላይ የተመሠረተ መከፋፈል በተጨማሪ፣ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችን በአከባቢ መከፋፈል ያስፈልጋል። ስለዚህ፣ የአፓርታይድ ስርዓት የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮችን በአስር የተለያዩ ክልሎች ለመከፋፈል “The Promotion of Bantu Self-Government Act of 1959” የተባለውን አዋጅ አወጣ። የዚህ አዋጅ መሰረታዊ ዓላማና አተገባበር የታሪክ ደህረ-ገፅ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡-

“The Promotion of Bantu Self-Government Act of 1959 created 10 Bantu homelands known as Bantustans. Separating black South Africans from each other enabled the government to claim there was no black majority, and reduced the possibility that blacks would unify into one nationalist organization. Every black South African was designated as a citizen as one of the Bantustans, a system that supposedly gave them full political rights, but effectively removed them from the nation’s political body.”

ከላይ እንደተገለፀው፣ የአፓርታይድ ስርዓት ጥቁሮች የሚኖሩባቸውን ግዜቶች ለአስር የተከፋፈለበት መሰረታዊ ምክንያት በእያንዳንዱ ክልል ጥቁሮች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ሳይሆን በሀገሪቱ ውስጥ ያላቸውን አብላጫ ድምፅ ለማስቀረትና የተቀናጀ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ነው። በዚህ መሰረት፣ እያንዳንዱ ክልል ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ስልጣን ይኖረዋል። በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ጥቁሮች ግን በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ተደራጅተው እንዳይንቀሳቀሱ “በሌላ ክልል ውስጥ ጣልቃ መግባት ነው” በሚል ሰበብ ተከልክሏል። ስለዚህ፣ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ጥቁሮች በሀገሪቱ ውስጥ ያላቸውን አብላጫ ድምፅ በማሳጣት የነጮችን በራስ-የመወሰን መብትን ለማረጋገጥ የተዘረጋ ስርዓት ነው።

በአጠቃላይ፣ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን አፓርታይድ ስርዓትን ከዘር-ልዩነት አንፃር ብቻ ማየት በብዙሃኑ ጥቁሮች ላይ የተፈፀመውን አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና በግልፅ አያሳይም። የአፓርታይድን ስረዓት ለማስወገድ ከፍተኛ ትግል የተካሄደው በጥቁሮችና በነጮች መካከል ነበር። ምክንያቱም ከዘር መድልዎ በተጨማሪ፣ ከላይ የተጠቀሰው አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና ከዘረኝነት የባሰ ጨቋኝና ጎጂ ስለነበረ ነው።

በደቡብ አፍሪካ በዘር-ልዩነት ላይ የተመሰረተው የአፓርታይድ ስርዓት እንደ ቀድሞው በሌላ ዘር (ሀገር) ተወላጆች የመዋጥ አደጋን በማስቀረት የነጮችን በራስ-የመወሰን መብት ለማስከበር ጥቁሮችን በመከፋፈልና የጋራ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን በመገደብ ተግባራዊ መደረጉን ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪ፣ “በእንግሊዞች የተፈፀመው አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ዳግም ተመልሶ እንዳይመጣ ለማድረግ ደግሞ የአፓርታይድ ስርዓት ጠንካራ የሆነ ወታደራዊ አቅም ገንብቶ እንደነበር ይታወቃል። በዚህ ረገድ ስርዓቱ የኒኩለር ቦምብ ለመስራት ተቃርቦ የነበረ መሆኑ የሚጠቀስ ነው።

3.2 በኢትዮጲያ
ሕወሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት የመሰረተው በብሔር ልዩነት ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ ስርዓት የተመሰረተባቸውን ሁለት መሰረታዊ ዓላማዎች ለማሳካት ተመሳሳይ የአተገባበር ስልቶች ነበሩት። አንደኛ፣ “የትግራይ ሕዝብን በራስ-የመወሰን መብት በማረጋገጥ ፖለቲካዊ መብታቸው እንደ ቀድሞ በሌላ ብሔር ተወላጆች እንዳይጨፈለቅ ማድረግ” የሚለውን ዓላማ ለማሳካት ሀገሪቱን በዘጠኝ ብሔራዊ ክልሎች ከፋፍሏታል።

በእርግጥ “እያንዳንዱ ክልል ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አለው” ተብሏል። ነገር ግን፣ ከዓመታዊ በጀት ምንጭና አመዳደብ፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እና ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮችን አንፃር ሲታይ ክልሎች የፌዴራሉ መንግስት ጥገኞች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ እንደ ደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ከጠቅላላው የኢትዮጲያ ሕዝብ 60% የሚሸፍኑት የአማራና ኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸውን አብላጫ ድምፅ እንዲያጡ፤ በሀገራዊ ጉዳዪች ላይ የጋራ አቋም እንዳይኖራቸው እና የተደራጀ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ተደርገዋል። በዚህም የፖለቲካ ልሂቃን በብሔር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ስለሚያራምዱና የጋራ የሆነ ሀገራዊ አጀንዳ ስለማይኖራቸው የትግራይ ሕዝብን በራስ-የመወሰን መብት ማረጋገጥ ይቻላል። የክልሉ ተወላጆች ፖለቲካዊ መብት እንደ ቀድሞ በሌላ ብሔር ተወላጆች የመጨፍለቅ አደጋ የለበትም።

እንደ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓት “The Promotion of Bantu Self-Government Act of 1959” የተሰኘው አዋጅ፣ በኢትዮጲያ የተለያዩ ብሔር ተወላጆችን የጋራ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመገደብ የወጣው አዋጅ ¨A PROCLAMATION ON ANTI-TERRORISM PROCLAMATION NO. 652/2009” በመባል ይታወቃል። የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተከራካሪዎችን፣ እንዲሁም በተራ የተቃውሞና አመፅ እንቅስቃሴ የተሰማሩ ወጣቶችን ሳይቀር ለማሰርና ለማሰቃየት ያገለግላል። በዚህ አዋጅ ከተከሰሱ ከአሸባሪዎች ይልቅ የፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ቁጥር እጅግ ብዙ እጥፍ የበለጠበት ምክንያት የጸረ-ሽብር ሕጉ ለምን ዓላማ እየዋለ እንደሆነ በግልፅ ያሳያል።

በመጨረሻም፣ “በቀድሞ ስርዓት የተፈፀመው በደልና ጭፍጨፋ ዳግም ተመልሶ እንዳይመጣ ማድረግ” የሚለውን ሁለተኛውን ዓላማ ለማሳካት ደግሞ የሀገሪቱን የመከላከያ ሰራዊት፣ ፖሊስ፣ ደህንነትና ሌሎች ተያያዥ መስሪያ ቤቶች ላይ በኃላፊነት የሚመሩት በዋናነት የክልሉ ተወላጆች ናቸው። ለዚህ ዓላማ የሚውል ጠንካራ የዕዝ-ሰንሰለት፣ የፋይናንስ አቅምና የመረጃ አቅርቦት ስርዓት ተዘርግቷል።

በአጠቃላይ፣ የአንድን ሕዝብ በራስ-የመወሰን መብት ለማረጋገጥ የሚወሰድ እርምጃ መለሶ የሌሎችን መብትና ነፃነት የሚገድብ ከሆነ “ስህተት” ነው።  በዚህ መሰረት፣ በደቡብ አፍሪካ የነጭ ሰፋሪዎች በራስ የመወሰን መብትን ለማረጋገጥ ሲባል በዘር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ የአፓርታይድ ስርዓት መዘርጋት፣ በዚህም አማካኝነት ጥቁሮችን በመከፋፈልና የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን መገደብ ፍፁም ስህተት ነው። በተመሣሣይ፣ የትግራይ ሕዝብን በራስ-የመወሰን መብት ለማረጋገት ሲባል በብሔር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ የአፓርታይድ ስርዓት፣ በዚህም አማካኝነት የኢትዮጲያ ሕዝብን በብሔር መከፋፈልና የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን መገደብ ፍፁም ስህተት ነው።

 የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 5፡- ማን ነው ተጠያቂው፡ ሕዝብ የጨፈጨፈው ወይስ ያስጨፍጫፈው?

 

 

 

 

 

 

 

 

ስዩም ተሾመ

በክፍል አራት በዝርዝር እንደተገለፀው፣ የሽምቅ ውጊያ ሕዝብን እንደ “ባህር” በመጠቀም አማፂያኑ እንደ “ዓሣ” በውስጡ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ስልት ነው። ጨቋኝ መንግስት ደግሞ “በአማፂያኑና በተቃዋሚዎች ላይ ከከዚህ በፊቱ የበለጠ ፍርሃትና ሽብር የሚፈጥር የኃይል እርምጃ በወሰድን ቁጥር የሽምቅ ተዋጊዎቹ ጥቃትና ድጋፍ ይቀንሳል” በሚል መርህ የሚመራ ነው። ነገር ግን፣ ከበፊቱ የበለጠ የኃይል እርምጃ በተወሰደ ቁጥር ጨቋኙ ስርዓት ለውድቀት፣ የሽምቅ ተዋጊዎቹ ደግሞ ለስኬት ይንደረደራሉ።

ስዩም ተሾመ

በዚህ መሰረት፣ እንደ ደርግ አምባገነናዊ የሆነ መንግስት የአማጺያኑን ጥቃትና ድጋፍ ለማስወገድ በሚወስደው የኃይል እርምጃ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈፅመው በደልና ጭፍጨፋ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ ሄዶ በመጨረሻ ለውድቀት ሲዳረግ፣ እንደ ሕወሃት ያሉ የሽምቅ ተዋጊዎቹ ደግሞ የመንግስት ስልጣን የመያዝ ፍላጎታቸው ይሳካል። ነገር ግን፣ ከውድቀት እና ስኬት በስተጀርባ ያለው ሃቅ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው በደልና ጭፍጨፋ ነው። ለዚህ ተጠያቂው ማን ነው? አስቃቂ በደልና ጭፍጨፋ በመፈፀሙ ምክንያት ለውድቀት የተዳረገው አምባገነናዊ መንግስት ወይስ አስቃቂ በደልና ጭፍጨፋ በመፈፀሙ ምክንያት ለስኬት የበቃው የአማፂ ቡድን?

በእርግጥ የደርግ መንግስት ሲዋጋ የነበረው በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሆን አማፂኑ ደግሞ ደርግን የመገርሰስ ዓላማ ነበራቸው። ስለዚህ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በዋናነት የመንግስትን ስልጣን ለመቆጣጠር ነበር። ከዚህ አንፃር፣ “በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ በመፈፀሙ ምክንያት ከሁሉም በፊት ተጎኚው ከስልጣን የተወገደው መንግስት፣ ተጠቃሚ ደግሞ የታገለለትን ስልጣን በእጁ ያስገባው አማፂ ነው” ሊባል ይችላል። ነገር ግን፣ ከውድቀትና ስኬት ባሻገር፣ በንፁሃን ላይ ለተፈፀመው በደልና ጭፍጨፋ ተጠያቂው ማን እንደሆነ በግልፅ ተለይቶ መታወቅ አለበት። ለዚህ ደግሞ የሁለቱንም ወገኖች እንቅስቃሴ ከጦርነት በፊት፣ በጦርነት ወቅት እና ከጦርነት በኋላ በሚል ከፋፍሎ ማየት ያስፈልጋል።

1፡ ከጦርነት በፊት፡ መነሻ ምክኒያት
በክፍል አንድ በዝርዝር ለመግለፅ እንደ ተሞከረው፣ ፖለቲካዊ ስርዓቱ የአንድን ማህብረሰብ እኩልነት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማያረጋገጥ ከሆነ፣ የሀገሪቱ መንግስት ስራና አሰራሩን በማሻሻል ለማህብረሰቡ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ መስጠት ከተሳነው፣ የአመፅና ተቃውሞ መቀስቀሱ የማይቀር ነው። የፖለቲካ ልሂቃን ደግሞ ማህብረሰቡ ዘንድ ያለውን የለውጥ ፍላጎት ወደ “አብዮት” (revolution) ለመቀየር እና የትግል ስልቱን ከአመፅና ተቃውሞ ወደ ትጥቅ ትግል ለማሸጋገር የብሔርተኝነት ስሜት ማስረጽ እና በራስ-የመወሰን መብትን እንደ ግብ ማስቀመጥ የግድ ነው።

የአንድን ማህብረሰብ እኩልነት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚፈፀም ማንኛውም ዓይነት ተግባር በራሱ ሆነ በዓላማው “ትክክል” ነው። በአንፃሩ፣ የሕዝብን መብትና ነፃነት ለመገደብ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ተግባር “ስህተት” ነው። የሕወሃት መስራች ታጋዮች የትግራይን ሕዝብ መብትና ነፃነት ለማስከበር የትጥቅ ትግል መጀመራቸው ትክክል ነበር። በአንጻሩ የቀድሞው የአፄ ኃ/ስላሴ ዘውዳዊ አገዛዝ ሆነ የደርግ ወታደራዊ መንግስት ሕዝቡ ያነሳቸውን የእኩልነት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ተቀብለው ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በተደጋጋሚ በኃይል ለማፈን መሞከራቸው ስህተት ነው። ስለዚህ፣ የአፄ ኃ/ስላሴ እና የደርግ መንግስት ኤርትራና በትግራይ የትጥቅ ትግል እንዲጀመር መነሻ ምክኒያት እንደመሆናቸው “ተጠያቂ” ናቸው።

2፡ በጦርነት ወቅት፡ እኩል ተጠያቂነት  
በጦርነት ወቅት የተፈፀሙ ተግባርን ከጦርነት በፊትና በኋላ (በሰላማዊ ሕይወት) እንደሚፈፀሙ ተግባራት በቀላሉ “ትክክል” ወይም “ስህተት” ብሎ መፈረጅ አይቻልም። ምክንያቱም፣ በጦርነት ውስጥ የሚፈፀሙ ተግባራት ምርጫና አማራጭ በሌለበት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የሚፈፀሙ ናቸው። “Immanual Kant” የሞራልና ሕግ መርሆችን በሚተነትንበት “THE SCIENCE OF RIGHT” በተሰኘው መፅሃፉ በአስገዳጅ ሁኔታ (Necessity) ውስጥ የሚፈፀም ተግባርን ከሞራልና ሕግ አግባብ መፈረጅ የማይቻልበትን አጣብቂኝ መርህ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡- “Necessity has no law. And yet there cannot be a necessity that could make what is wrong lawful.” በዚህ መሰረት፣ የሕልውና አደጋ የተጋረጠበት ሰው ራሱን ለማዳን በሚወስደው የኃይል እርምጃ (an act of violent self-preservation) ተጠያቂ ሊሆን እንደማይችል ይገልፃል፡-

“There can, in fact, be no criminal law assigning the penalty of death to a man who, when shipwrecked and struggling in extreme danger for his life, and in order to save it, may thrust another from a plank on which he had saved himself. For the punishment threatened by the law could not possibly have greater power than the fear of the loss of life in the case in question. Such a penal law would thus fail altogether to exercise its intended effect; for the threat of an evil which is still uncertain- such as death by a judicial sentence could not overcome the fear of an evil which is certain, as drowning is in such circumstances.”  THE SCIENCE OF RIGHT by Immanual Kant, tran. by W. Hastie, Part-1, Page 6-7.

ከላይ እንደተገለፀው፣ በኢትዮጲያ በደርግ እና በትግራይና ኤርትራ ነፃ-አውጪ አማፂያን፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ በእንግሊዞችና በነጭ ሰፋሪዎች መካከል በተካሄደው ውጊያ አንዱ በሌላው ላይ የፈፀመውን ተግባር “አግባብነት” መታየት ያለበት በአስገዳጅ ሁኔታ መርህ ነው። በሁለቱም ሀገራት የሚንቀሳቀሱት አማፂያን ከሽምቅ ውጊያ በስተቀር እነሱን ለመደምሰስ የተሰማራውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር ሰራዊት በመደበኛ የጦርነት ስልት መቋቋም አይችሉም። በዚህ መሰረት፣ እ.አ.አ. ከ1899 – 1901 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ነጮች ታጋዮችና በእንግሊዞች ወታደሮች፣ እንዲሁም ከ1979 – 1981 ዓ.ም በደርግ ወታደሮችና በሕወሓት ታጋዮች መካከል ሲካሄድ በነበረው ጦርነት የተፈፀመውን አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ “ትክክል” ወይም “ስህተት” ብሎ መፈረጅ አይቻልም።

ስለዚህ፣ በደቡብ አፍሪካና በኢትዮጲያ የሚገኙ አማፂያን እያንዳንዳቸው 22000 የእንግሊዝና የደርግ ወታደሮችን የገደሉት ምርጫና አማራጭ በሌለበት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነው። ነገር ግን፣ ምንም ያህል አስገዳጅ ቢሆን 22ሺህ ወታደሮችን በሦስት አመት ውስጥ መግደል “ትክክል” ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም፣ የተገደሉት ወታደሮች እንደ ማንኛውም ሰው ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ 22ሺህ ወታደሮች በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ መግደላቸው በደርግና በእንግሊዝ ጦር ሰራዊት ላይ የሕልውና አደጋ ፈጥሯል። ይህ ደግሞ በተራው በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ እንዲፈፅሙ ምክንያት ሆኗል። ነገር ግን፣ ምንም ያህል አስገዳጅ ቢሆን፣ በትግራይ ሕዝብና በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ የተፈፀመው በደልና ጭፍጨፋ “ተቀባይነት” ሊኖረው አይችልም።

በአጠቃላይ፣ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ከተፈፀመባቸው ንፁሃን ዜጎች በስተቀር በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት ሁለቱም ወገኖች እኩል ተጠያቂ ናቸው።  ምክንያቱም፣ የደርግና እንግሊዝ ጦር አዛዦች በአጭር ግዜ ውስጥ 22ሺህ ወታደሮች ባይገደሉባቸው ኖሮ በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ እንዲፈፅሙ የሚደርጋቸው አስገዳጅ ሁኔታ አይፈጠርም ነበር። በመሆኑም፣ የደርግና የእንግሊዝ ወታደሮች ምንም ያህል በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ በንፁሃን ዜጎች ላይ ለፈፀሙት አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ተጠያቂ ናቸው። በተመሣሣይ፣ የሕውሓት እና የደቡብ አፍሪካ ሽምቅ ተዋጊዎች ምንም ያህል በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ በነፁሃን ዜጎች ላይ በደልና ጭፍጨፋ እንዲፈፀም ምክንያት በመሆናቸው በዚያው ልክ ተጠያቂ ናቸው።

በክፍል ሦስት ጦርነቱ በተፋፋመበት፣ የብሔርተኝነትና ጠላትነት ስሜት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት፣ የአማፂያኑ መሪዎችና ልሂቃን መጠየቅ ያለባቸው መሰረታዊ ጥያቄ እዚህ’ጋ እናንሳ፤ “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?”

በክፍል ሁለት በዝርዝር እንደተጠቀሰው፣ የእንግሊዝ ጦር በደቡብ አፍሪካ “መሬቱን በእሳት መለብለብ” Scorched-earth” በሚል ተዋጊዎቹ በሚንቀሳቀሱባቸው አከባቢዎች የነበሩትን መኖሪያ ቤቶች በእሳት በማውደም፣ ሕፃናት፣ እናቶችና አዛውንቶችን በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ አስገብቶ በርሃብና በበሽታ ያለቁበት ለምድነው? የሽምቅ ተዋጊዎቹ በሦስት አመት ውስጥ ከ22ሺህ በላይ የእንግሊዝ ወታደሮችን በመግደል የሰራዊቱ ሕልውና አደጋ እንዲወድቅ ስላደረጉ። በተመሳሳይ፣ የደርግ መንግስት “ዓሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ” በሚል በዋናነት የሕውሃት ሽምቅ ተዋጊዎች በሚንቀሳቀሱበት እንደ ሃውዜን ባለ ቦታ ላይ የአየር ድብደባ በመፈፀም በአንድ ቀን 1800 ንፁሃን ዜጎችን የጨፈጨፈው ለምንድነው? የኤርትራና የትግራይ አማፂ ቡድኖች በሶስት አመታት ውስጥ ከ22ሺህ በላይ የደርግ ወታደሮችን በመግደል የሰራዊቱ ሕልውና አደጋ እንዲወድቅ ስላደረጉ።

ስለዚህ፣ የትጥቅ ትግል መሪዎች ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ከራሳቸውና ከትግል ጓዶቻቸው ጋር በግልፅ ቢወያዩበት ኖሮ፤ አንደኛ፡- ከራሳቸው አልፎ በጠላታቸው ላይ እየፈጠሩት ያለው አስገዳጅ ሁኔታ በመመዘንና የጠላት ኃይል ምርጫና አማራጭ በሌለበት የሚወስደውን እርምጃና የሚያስከትለውን ጉዳት በመገመት፣ በማህብረሰቡ ላይ የደረሰውን በደልና ጭፍጨፋ ማስቀረት ወይም ጉዳቱን መቀነስ ይችሉ ነበር።

ሁለተኛ፡- በሽምቅ ውጊያ ሕዝብን እንደ ባህር ተጠቅመው እንደ ዓሣ በውስጡ እየተንቀሳቀሱ በአምባገነናዊ ወይም ወራሪ ጦር ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀም በማህብረሰቡ ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ እንዲፈፀም ጥሪ ማቅረብ ነው። በአጠቃላይ፣ በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች እና በትግራይ ሕዝብ ላይ ለተፈፀመው አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ የደርግና እንግሊዝ ሰራዊት በድርጊት ፈፃሚነት፣ የሕውሃትና የደቡብ አፍሪካ ሽምቅ ተዋጊዎች ደግሞ በምክንያትነት እኩል ተጠያቂ ናቸው።

3፡ ከጦርነት በኋላ፡ መንታ መንገድ 
አንደኛ፡- 1ከላይ በተራ ቁጥር 1 ላይ እንደተጠቀሰው፣ የብሔርተኝነት ስሜት የትጥቅ ትግል ለማስጀመር ሲባል በማህብረሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ የተደረገ መሆኑን ከተገነዘበ የመንግስት ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ በክፍል ሦስት ላይ በዝርዝር እንደተጠቀሰው አክራሪ ብሔርተኝነትን ከማህብረሰቡ ስነ-ልቦና ውስጥ በማስወገድ በእኩልነት፣ ነፃነትና የሕግ-የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ማህብረሰብ ለመፍጠር ይንቀሳቀሳል። ሁለተኛ፡- ከላይ በተራ ቁጥር 2 ላይ እንደተጠቀሰው፣ በጦርነት ወቅት አማፂ ቡድኑ በሚወክለው ማህብረሰብ ላይ ለተፈፀመው በደልና ጭፍጨፋ ምክንያት በመሆኑ ከቀድሞ ስርዓት እኩል ተጠያቂ መሆኑን ተገንዝቦ በጦርነቱ ወቅት የተፈጠረውን የጠላትነት ስሜት ለማስወገድ ጥረት ያደርጋል።

አማፂ ቡድኑ ከጦርነቱ በኋላ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ዋና ዋና ተግባራት በአግባቡ ከፈጸመ የሁሉም ዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ይችላል። በተቃራኒው፣ የተጠቀሱትን ተግባራት ተገንዝቦ በአግባቡ መፈፀም ከተሳነው ግን፤ አንደኛ፡- ለትጥቅ ትግል ማስጀመሪያነት በማህብረሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ የተደረገው የብሔርተኝነት ስሜት ከጦርነት በኋላ ወደ አክራሪ ወገንተኝነትና የተበዳይነት ስሜት ያድጋል፣ ሁለተኛ፡- በጦርነት ወቅት የተፈጠረው የጠላትነት ስሜት ከጦርነት በኋላ ወደ ፍርሃትና አለመተማመን ይቀየራል። አንድ በፍርሃትና አለመተማመን ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት እንደ ቀድሞ ስርዓት ጨቋኝ ይሆናል። በጨቋኝነቱ ላይ የአንድን ብሔር/ዘር መብትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ደግሞ የዘር/ብሔር አፓርታይድ ይባላል።

የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች አማፂያን በ1948 ዓ፣ም ከእንግሊዝ ቅኝ-አገዛዝ ነፃ በወጡ ማግስት ከላይ ከተጠቀሱት መንታ-መንገዶች የትኛውን እንደተከተሉ ይታወቃል። ሕወሃት መራሽ ኢህአዴግ ደርግን ከስልጣን ካወረደ በኋላ በየትኛው መንገድ ተጉዞ ዛሬ ላይ እንደደረስን በቀጣዩ ክፍል በዝርዝር እንመለከታለን።