June 22, 2017

ቃል የተገባው የድብልቅ የምርጫ ሥርዓት ጥያቄ ውስጥ ወድቋል

ሌሎቹን ክልሎች ብንተወው ኢህአዴግ በቀጣዩ ምርጫ ኦሮሚያና አማራ ክልል ላይ ሙሉ በሙሉ እንደማይመረጥ ያውቀዋል፤ ሕዝቡም ያውቃል፤ ይህ እውነት ነው። በዚህ መነሻ የምርጫ ህጉን ወደ ተመጣጣኝ ውክልና ይቀይራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ” ሲሉ ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁና ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆነ የዩኒቨረስቲ መምህር ተናገሩ። “ሰለዚህም” አሉ መምህሩ ” ስለዚህ የሚደረገው ድርድርም ሆነ ምክክር ዋጋ የለውም። ኢህአዴግ የምርጫ ህጉን ቀይሮ በራሱ አንገት ላይ የተሳለ  ካራ ያስቀምታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ” በአጭር የጽሁፍ መልስ ድርድሩን አስመልክቶ ከዛጎል ለቀረበላቸው ሁለት ጥያቄዎች መልስ የሰጡት እኚሁ መመህር ” ኦሮሚያ ላይ እንዴት ሰው ለኢህአዴግ ድምጽ ይሰጣል?” ሲሉ ነው መልሳቸውን የጀመሩት። የፈሰሰው ደም፣ ያለቀው ሕዝብ፣ እስር ቤት የታጎረው ወገን …. ብዙ መዘርዘር ያቻላል” ካሉ በሁዋላ” ጊዜው ሩቅ አይደለም። በቀላሉም የሚረሳ አይሆንም። ከሁሉም በላይ ማህበራዊ ሚዲያውና ዘመኑ ቀውሱን በየመንደሩ አዳርሶታል”
ድርድር ሰጥቶ መቀበል መሆኑንን ያመለከቱት አስተያየት ሰጪ ” አሁን እየሆነ ያለው ውይይት እንጂ ድርድር አይባልም ” በመሆኑም የወይይቱ ተሳታፊዎች የሆኑና ከኢህአዴግ ጋር ንክኪ የሌላቸው ካሉ ወደ ምርጫው ስራ ከአሁኑ ትኩረት ቢሰጡና ህዝቡን የማደራጀት የቤት ለቤት ስራ ቢሰሩ እንደሚመረጥ ጠቁመዋል። ማህበራዊ ሚዲያዋቹም ምርጫው ላይ በማተኮር ቢሰሩ የተሻለ እንደሚሆን መክረዋል።

ዝርዝር ጉዳዮችን ሳያስቀምጡ በጥቅሉ ምላሻቸውን የሰጡት መምህር ” ኢህአዴግ ሲጀመር ውይይት እንጂ ድርድር ሊባል እንደማይችል ተናገሮ ነበር። እንዳለውም ዋና መነጋገሪያ ጉዳዮችን እንደማይቀበል ይፋ አድርጓል። እናም የቀረው ቀሪ የውይይት መርሃ ግብር በመሆኑ ምርጫውን ኢላማ አድርጎ መስራት ብቸኛ አማራጭ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል። ድርድሩ ገና ሲጀመር ቀልድ እንደሆነና ኢህአዴግ ለጊዚያዊ ማረጋጊያ፣ እንዲሁም የለጋሽ አገሮችን ወቅታዊ እይታ ለማንሸዋረር ያደረገው እንደሆነ ተነግሮ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ድርድሩ ውጤታማ መሆኑና አለመሆኑ ሳይታወቅ አስቀድሞ ድምዳሜ ላይ መድረስና ማጣጣል አግባብ እንዳልሆነ የሚሞግቱ ክፍሎች ባይበዙም ይሰሙ ነበር።
በዓመቱ መጀመሪያ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ የፓርላማ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ የምርጫ ህጉን ጨምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎች እንደሚካሄዱ የመንግስታቸው እቅድ እንደሆነ ቃል ገብተው ነበር። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተለይ የምርጫውን አፈጻጸም ወደ ተመጣጣኝ ውክልና አሰራር እንደሚቀየር ሲያረጋግጡ ቆይተዋል። 
ዞሮ ዞሮ ራሳቸውን ካገለሉት ዋንኛ ፓርቲዎች ወጪ፣ ብዙም የማይታወቁ፣ በመሰንጠቅ ጉልህ ፓርቲዎችን አክስመው ስም ብቻ ይዘው የተቀመጡ፣ ራሱ ኢህአዴግ የሚረዳቸው የሚባሉ፣ ነጻ ፓርቲ ለመምሰል የሚውተረተሩ፣ ህዝብ ጆሮና ትኩረት የነፈጋቸውን ፓርቲዎች ሰብስቦ ራሱ አጀንዳ አደራጅ ሆኖ ኢህአዴግ በቀጠሮ ያስኬደው ድርድር መጨረሻው ከጅምሩ የተሰጠው ግምት ላይ እንደወደቀ አስተያየት እየተሰጠ ነው። በመጨረሻው ድርድር ኢህአዴግ ” አገሪቱ ውስጥ የህሊናና የፖለቲካ እንዲሁም በመጻፉ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም” ሲል የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ የቀረበውን አጀንዳ ሰርዞታል። የአሰብ ወደብን በተመለከተ ” የሌለንን ወደብ ከየት አምጥተው ሊሰጡን ነው?” ሲል ተቃዋሚ የሚባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች አስተሳሰብ ቅዠት እንደሆነ አድርጎ መልስ በመስጠት ዘግቶታል።ወደብ ፍለጋ የሚዳክረው ኢህአዴግ ስለ አሰብ ወደብ ሲነሳ የሚያንገሸግሸው ለምን እንደሆነ እንደማይገባቸው በተደጋጋሚ አስተያየት የሚሰጥበት ጉዳይ ነው። ሟቹ መለስን ጨምሮ የተለያዩ ሃላፊዎች አስብን በተመለከተ የሚሰጡት መልስ የህዝብን ስሜት እንኳን ባከበረ መልኩ አለመሆኑ ሁሌም የሚያሳዝን እንደሆነ፣ ይህ የህዝብን ስሜት በሚጎዳ መልኩ የሚቀርበው ምላሽ ” ራሱን የቻለና ጊዜን ጠብቆ የሚተገበር ዓላማ ስለመኖሩ አመላካች ነው” ለሚሉት ወግኖች እንደማረጋገጫ የሚወሰደ እንደሆነ የሚጠቁሙ ጥቂት አይደሉም።

በድርድሩ ኢህአዴግን የወከሉት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ” የድንበር ጉዳይ በሁለት መንግስታት መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው” ሲሉ ለሱዳን ተቆርሶ የሚሰጠውን መሬት ጉዳይ ተቃዋሚዎችን አያገባችሁም በሚል ቀርቅረውታል። በዚሁ መሰረት ድንበርን አስመለክቶ ድርድር መቀመጥ ብሎ ነገር የለም። ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ውይይት ሊደረግበት ከመቻሉ ውጪ ለድርድር የሚቀርብ አይሆንም ተብሏል። ህገ መንግስቱ እስከማሻሻል እንደሚዘልቅ ሲወተውት የነበረው ኢህአዴግ ይህንኑ አስመልክቶ የቀረበውን የህገመንግስት አንዳንድ አንቀጾች የማሻሻል አጀንዳ በስተመጨረሻ ” ሕገ መንግሥት የሚሻሻለው ሀገመንጋስታዊ ድንብ ተከትሎ ብቻ ነው” በማለት አጀንዳውን ውድቅ አድርጎታል። የተስማማበት ጉዳይ ቢኖር የምርጫ ሕጎችን ማሻሻል፣ ሌሎች ሕጎችን ማሻሻል (የፀረ ሽብር ሕጉን፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅን፣ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ)፣ የፍትሕ አካላትን አደረጃጀት፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን በተመለከተ፣ ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ የቀረቡትን ነው።በሌላ በኩል ግን ገዥው ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ዙሪያ እንደማይደራደር በመግለጹ ቃል የገባው ተመጣጣኝ ውክልና ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንደገባ ሪፖርተር ጉዳዩን አስመለክቶ በወጣው ዘገባ ግምቱን ሰጥቷል።

ድርድሩ ” ፌክ ” ነው !! የሕዝብ ጥያቄዎችን የሚመልስ አይደለም  ይህንኑ ድርድር መድረክ/ ኦፌዴንና ሰማያዊ ፓርቲ ከልብ ያልሆነ መሆኑን ገልጸው ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል። ይህንኑ አስመልክተው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ ”  ቢነገር የማይሰማ፣ የሚገርም፣ ሞራል የሌለው ፣ በሙስና የሸተተ፣ …. ” ሲሉ ኢህአዴግን ክፉኛ በመዝለፍ ከድርድሩ የወጡበትን ምክንያት ማስረዳታቸው የሚታወሰ ነው። ኢህአዴግ በበኩሉ አገሪቱ አሁን የተረጋጋችና አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት መሆኑን በማመልከት የሚቀርብበትን ወቀሳ እንደማይቀበል ነው የሚገልጸው። ሙስናና ኪራይ ስብሳቢነት የአገሪቱ ችግር በመሆኑ ጥልቅ ተሃድሶ በማካሄድ የህዝብን ጥያቄ መመለሱን ነው የሚያበስረው። ኢህአዴግ ይህን ቢልም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ስለመኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እየገለጹ ነው። ከዚያም በላይ ጥቃቱን የሚፈጽሙት ክፍሎችም ጉዳት ማድረሳቸውን በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው።

ፎቶ ሪፖርተር