የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅም ታሪኳ የጥቃት ነፋሳት ሲነፍሱባት፥ የአፍራሽ ዝናማት ሲዘንሙባት፥ ምንም ነገር እንዳልደረሰባት ሆና እኛ ዘመን የደረሰችው፥ መሠረቷ በዐለት የሚመሰሉ ጠንካራ ቅዱሳን ገዳማት ስለሆኑ ነው። ከዋናዎቹ ገዳማት አንዷ የግሑሣንና የግሑሣት እናት ቅድስት ዋልድባ ናት። መሥራቿ ኮከበ ገዳም ከተባሉት ሰባት ሳሙኤሎች አንዱ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሳሙኤል ከቅድስናቸው የተነሣ የዱር አራዊት ይታዘዟቸው ነበር። ጾም ጸሎት ስግደት ስላደከማቸው፥ መንፈሳዊ ተልእኳቸውን የሚያደርሱት አናብስትን ፈረሳቸው አድርገው ነበር። አቡነ ሳሙኤል ሲጸልዩ እመቤታችን ትገለጽላቸው እንደነበረ በተአምረ ማርያም ተመዝግቧል። በዚሁ ልምድ ከዕለታት አንድ ቀን ተገልጻላቸው እንዲህ ብላቸዋለች፤”ወዛቲ፡ ጸሎት፡ ዘትጼሊ፡ ወቅዳሴየ፡ ኢትኅድግ፡ በመዋዕለ፡ ሕይወትከ፡ ወለደቂቅከኒ፡ እምድኅሬከ፡ አዝዝ፡ ከመ፡ ኢይኅድጉ፡ እስመ፡ ዘይጼውዓኒ፡ በዝንቱ፡ ቅዳሴ፡ አፈቅሮ፡ በኲሉ፡ ልብየ” (“ይቺን የምትጸልያትን ጸሎትና ቅዳሴየን በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምንጊዜም እንዳትተዋቸው። የመንፈስ ልጆችህም እንዳይተዋቸው እዘዛቸው። በዚህ ቅዳሴ ስሜን የሚጠራውን በሙሉ ልቤ እወደዋለሁ”) ብላቸዋለች። “ይኸውም ሊታወቅ ዛሬ በዋልድባ በቃሉ ያጠና በቃሉ፥ በቃሉ ያላጠና በመጽሐፍ ቅዳሴ ማርያም ሳይደግም የሚውል የለም” ይላል የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ መቅድም።

ትርጓሜ ው፥ “ቅዳሴ ማርያምን ከተከዜ ወዲህ ማን አምጥቶልናል?” ይልና ሲመልስ ” . . . ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ (ሳሙኤል ዘገዳመ ዋሊ) ነው” ይላል። እነዚህን ጥቅሶች በአንድነት ስናያቸው፥ “ራሱን ቅዳሴ ማርያምን የደረሰልን እንደሚባለው አባ ህርያቆስ ኤጲስ ቆጶስ ዘሀገረ ብህንሳ ሳይሆን አባ ሳሙኤል ዘገዳመ ዋሊ ናቸው” ወደማለት ይመራናል። አባቶቻችን ከትሑትነታቸው የተነሣ ድርሰታቸውን ለሌላ አባት እንደሚሰጡ ወይም ስማቸውን ደብቀው “አንድ ስሙን ያልተናገረ ርቱዐ ሃይማኖት የደረሰው” ብለው እንደሚያልፉት የርቱዐ ሃይማኖት ድርሰቶችና ሌሎቹ ቅዳሴዎች ይመሰክራሉ። ትሑታን አባቶቻችን የሚፈልጉት ሥራቸውን አምላካቸው ብቻ እንዲያውቅላቸው ቢሆንም፥ ታላላቅ የድርሰት አስተዋፅኦ ያደረጉ አባቶቻችን እነማን እንደነበሩ ብናውቃቸውና ብንኮራባቸው ክብራቸው ለኛም ይተርፋል እንጂ አይቀነስም።

ይህ ጥቅስ የሚያስታውሰን ሌላው ቁም ነገር እንደ ዋልድባ ያሉ ገዳማት ኢትዮጵያን የሚጠቅሟት በጸሎታቸውና ነገሥታቱ ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲያድርባቸው መገሠጽ ብቻ ሳይሆን የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ምንጭም መሆናቸው ነው። ገዳማቱ ከፊደል ቆጠራ እስከ ዩኒቨርስቲ ደረጃ የሚገመቱ ትምህርቶች ይሰጥባቸው ነበረ። መምህራኑ ያስተምራሉ፥ ድርሰት ይደርሳሉ፤ ግብጽ፥ ሶርያ ድረስ ሄደው፥ ቅዱሳት መካናትን ተሳልመው፥ በሰላም ከተመለሱ እዚያ የሚገኙትን አዳዲስ ድርሰቶች ወደግዕዝ ተርጒመው ያመጡልናል። ኢትዮጵያን ከጥንት ሀገሮች አንዷ ያደረጋትና በዕውቀት ምንጭነት በዓለም ፊት ያስከበራት የነዚህ ገዳማት መነኮሳት ጥረት ነው። ለኢትዮጵያ የሚያስብ መንግሥት የእነዚህን ገዳማት ብሔራዊ ውለታ ተገንዝቦ ተንበርክኮ እጅ ነሥቶ ይንከባከባቸዋል እንጂ፥ እንደ ጠላቶቻቸው ሲያጠቃቸው አምላካቸው ዝም አይልም። ለገዢዎች ቢጸልዩም፥ “ወአምላክነሂ፡ ኢያረምም፡” (አምላካችን ይኸን በደል እያየ ዝም አይልም) የሚለውን ጸሎት ዳዊት ሲደግሙ አይዘሉትም። “ዝም አይልም” ማለት ይበቀላል ማለት ነው።

የዋልድባ ገዳም መንፈሳዊ ጥንካሬ የተመሠተችበት ቦታ ነው። እንደሚታመነው፥ ቅድስት ማርያም፥ ቅዱስ ዮሴፍና ሰሎሜ ሕፃኑን ክርስቶስን ከንጉሥ ሄሮድስ ቁጣ ወደግብፅ ያሸሹ ጊዜ ወደኢትዮጵያም መጥተው ነበር፤ ያረፉትም ዋልድባ ነበር ።

የገዳም ኑሮ ሥጋን በመበደል ነፍስን ማዳበር ቢሆንም፥ አቡነ ሳሙኤል ለዋልድባ ገዳም ያቋቋሙት ሥርዓተ ብሕትውና ለላቀ ለመጠቀ ፍጹምነት ምሳሌ ሆኗል። ለገዳሙ የመረጡት ቦታ ፍጹም ቆላ ነው። በወጣትነት እድሜየ አንድ ጊዜ እንኳን ደርሼ የተመለስኩት በብዙ ድካም ነው። ግራኝ ብዙ ገዳማትንና ያቀፉትን ብሔራዊ ቅርስ ሲዘርፍና የቀረውን የእሳት እራት ሲያደርግ፥ ዋልድባ መድረስ ያልቻለው ቦታዋ በቀላሉ የማይበገር ስለሆነ ነው። የእቃ ቤቱ እንደሚያሳየው ጥንታዊ መጻሕፍትም ተርፈዋል። ትርጓሜ ዳዊት በግዕዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት እዚህ ገዳም ውስጥ ነው።

የመነኮሳቱ ዋና ምግባቸው ቋርፍ የሚባል ስር ነው። ከምርረቱ የተነሣ፥ ለቅምሻ የጎረስኩትን መዋጥ አልቻልኩም ነበር። መነኮሳቱ ግን የድንች ያህን ይመገቡታል። “በዋልድባም ይዘፈናል” የሚባለውን ተረት ማንም ያውቀዋል። ግን ተረቱ ዋልድባን የትሕርምት መጨረሻ እንዳደረጋት ብዙ ሰው ልብ አይለው ይሆናል። “እዚያ ትሕርምት እበዛበት ቦታ እንኳን” ለማለት ነው።

ስለ ትሕርምቱ ጽናት ለምሳሌ ያህል፥ የዋልድባና የሌላ ገዳማት ሰዎች ከሰጡት ምስክርነት ውስጥ በቅርቤ ያገኘሁትን ልጥቀስ፤
1. አንድ ጊዜ፥ አባ ከናፍረ ክርስቶስ የሚባሉ የደብረ ውቅሮ መምህር ከዞጋ አበምኔት ከአቡነ አካለ ክርስቶስ ዘንድ ሄደው እንዲህ ሲሉ ኀጢአታቸውን ይናዘዛሉ፤ “አባቴ ሆይ፤ በፍርድ ቀን፥ በዚያች በእግዚአብሔር ቀን፥ በዚያች በቀላል ደስታ ቀን፥ በዚያች በማያልቅና በማያልፍ ከባድና አስደንጋጭ የኀዘን ቀን የሚደርስብኝን የሥጋ መቅሠፍትና የነፍስ ሞት አንድ ሌሊት ትዝ ሲለኝ፥ ከሀገሬ ተነሥቼ እየገሠገሥኩ ከገዳመ ድባ ዘዕፀ ዋሊ (=ከዋልድባ ገዳም) ገባሁ። የገዳሙ ጽናት በጣም ስላስጨነቀኝ ወደኋላ ተመለስኩ። “ዕርፍ ይዞ ወደኋላ የሚያርስ የለም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀጥታ ናትና” (ሉቃስ ምዕራፍ 9፤ ቊጥር 62) ያለውን ተላለፍኩ። አባቶችም፥ “አንድ ሰው ከመነኮሰ በኋላ ወደዘመዶቹ አይመለስ፤ አገር ላገርም አይዙር፤ አገር ላገር የሚዞር መነኲሴ ሐሳዊና የአጋንንት ረዳት፥ የክርስቶስን ስም ሻጭም ነው” ይላል። ከአሁን ጀምሮ ወደዋልድባ መመለስ ባልችልም ከዓለማውያን ጋር መኖር አልፈልግም ። አንተ በዚች በገዳምህ አኑረኝ። ብሞትም እዚሁ ቅበረኝ።” ሲሉ ተናዘዙ።

2. የደብረ ዞጋ አበምኔት አቡነ አካለ ክርስቶስም የምንኩስና ሕይወታቸውን ሲጀምሩ ወደዋልድባ ለመሄድ ተነሥተው እንደነበረ ታሪካቸው እንዲህ ሲል ይናገራል፤የአቡነ አካለ ክርስቶስን አባትነት በማድነቅ ብዙ ሰው ሲከባቸው በመበሳጨት እንዲህ አሉ። “ከብዙ ሰው ማህል መኖር ምን ይጠቅመኛል? ኅሊናየ እግዚአብሔርን ከማሰብ ሰዎችንና ፍቅራቸውን ወደማሰብ ይሳብ የለምን? ሞትን ከማሰብ የዓለም ደስታንና ረጅም ዕድሜ ወደመጓጓት ይሳብ የለምን? ከአሁን ጀምሮ ወደ ገዳመ ድባ ዘዕፀ ዋሊ (ወደ ዋልድባ ገዳም) ሄጄ በብሕትውና ኃጢአቴን እያስታወስኩ መኖር አለብኝ” አሉ። ይኸንን ሐሳብ ለብቻቸው ሆነው ከወሰኑ በኋላ ጉዟቸውን ጀመሩ። ለማልሞ ከሚባል የሀገር በር ሲደርሱ፥ እንዲህ የምትለው ድምፅ ከሰማይ ሰሙ፤ “ያልታዘዘልህን ሌላ ገዳም አትፈልግ፥ አትመኝ። በፊት ወደነበርክባት ገዳምህ ተመልሰህ ሂድ፤ ወደሰማያዊት ርስትህ እስክትሄድ ድረስ ምድራዊት ክፍልህና ርስትህ እሷ ናት።” ይኸን ቃል ሲሰሙ ወደገዳማቸው ተመልሰው፥ በጾም በጸሎት በብዙ ትሕርምት ነፍሳቸውን ሲያደክሟት ቆይተው፥ ማኅደረ ማርያም ወደምትባለዋ ገዳም ሄደው የምንኩስና ልብሳቸውን በጻድቁ በአባ ህርያቆስ እጅ ለብሰው አንድ ጊዜ እንኳን በምንም ምክንያት ከዘጉት በአታቸው ሳይወጡ ኖሩ።

3. የአቡነ አካለ ክርስቶስን ገድል የጻፉላቸው አባ ኢሳይያስም የዋልድባን ሕይወት ቀምሰውታል፤ እንዲህ ሲሉ ጽፈውልናል፤ “ከዚያ በኋላ ወደ ገዳመ ድባ ዘዕፀ ዋሊ(ደብረ ዋልድባ) ሄጄ፥ ራሴን ለማኅበሩ አለቆች ለታዛዥነት አቀረብኩ። በተቻለኝም መጠን ታዘዝኳቸው። ግን እግዚአብሔር እዚያ መኖርን ሳይፈቅድልኝ፥ መሬቷንም ክፍሌ ሳያደርግልኝ ጊዜ፥ ወደ ሰይኮ ገዳሜ ተመልሼ ብዙ ዘመን ኖርኩ።

4. አንድ የዞጋ ገዳም ደቀ መዝሙር ለጉብኝት ከዋልድባ ገዳም ወደመጡ መነኮሳት ዘንድ ሄዶ እንዲህ አላቸው፤ “አባቶቼ ሆይ፥ ወደ ዋልድባ ገዳም ስትመለሱ አብሬያችሁ ለመሄድና እዚያ ለመኖር፥ በመጨረሻም ዕረፍቴና መቃብሬ እዚያ እንዲሆን እፈልጋለሁ” አላቸው። እነዚያ መነኮሳት እንዲህ አሉት፤ “ይቺ ገዳመ ዋልድባ አስጨናቂ ናት፤ የሚቀርቧትን እንደ እሳት ታቃጥላለች፤ እንደ በረዶ ትቀዘቅዛለች። የሚርቋትን ደግሞ በልባቸው ውስጥ ታድርና እንዲመኟት እያደረገች ምኞት ሆና ትቀራለች። እዚያች ገዳም ውስጥ መኖር አይቻልህም” አሉት። እሱም፥ “አባቶቼ ሆይ፤ ልቤን አትስበሩብኝ፤ እግዚአብሔር ያስችለኝ ይሆናል” አላቸው። እነሱም፥ “እንዲህ ካስገደድከንስ፥ በል ከገዳም አባትህ አስፈቅድ። ከፈቀዱልህ አብረኸን ትሄዳለህ” አሉት። በዚህ ማህል የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ተወልደ መድኅን ደቀ መዝሙሩን ጠርተው እንዲህ አሉት “ልጄ ሆይ፥ የምትፈልገውና የምትመኘው ነፍስህን ስለ ንጽሕት ንስሐ ለማስጨነቅ ከሆነ፥ እዚያ ሄደህ ቋርፍ በመብላት ፈንታ እዚሁ የዘንጋዳ ዳቤ ጋግርና በመጠኑ ቅመስ፤ ውሐም በመጠኑ ለክተህ ጉሮሮህን አቀዝቅዝ። እንዲህ አድርገህ ሆድህን ከተቆጣጠርክ ተስፋ ይኖርሃል” አሉት።

የዋልድባ ገዳም መቸ እንደተመሠረተ አስተማማኝ ታሪካዊ ሰነድ ባይኖርም፥ ስመ ጥርነቷ በገድለ አቡነ ዓቢየ እግዚእ፥ በገድለ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ፥ በገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፥ በገድለ አቡነ ፊልሞና እና በሌሎች ቅዱሳን ገድላት ውስጥ ተመዝግቧል።

ገዳማቱ የቤተ ክርስቲያኗ መሠረት የመሆናቸውን ያህል፥ ቤተ ክርስቲያንም የመንግሥት ዓምድ ነበረች። ስለዚህ የመንግሥቱና የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሥልጣኖች ሀገር የሚመሩት አብረው በመመካከርና በመተሳሰብ ነበረ። በዚያ ሰላማዊ ግንኙነት ዘመን የመኳንንቱ ታላቁ ትሩፋታቸው ለገዳማቱ ጉልት (ሪም) መጎለትና በቅዱሳኑ መነኮሳት መባረክና በጸሎታቸው መተማመን ነበር። ገዳማቱ ርስቱን ከሁለት ጥቅም ላይ ያውሉታል። አርሰው አምርተው የምርቱን አንዱን ክፍል ለኑሯቸው ያደርጉታል፤ ሁለተኛውን ክፍል ደግም ቊጥራቸው ከፍ ያለ ድኩማን ይረዱበታል። የዛሬዎቹ የመንግሥት ባለሥልጣን ለገዳማቱ ርስት ጎልተው በቅዱሳን አበው መባረክ ባይፈልጉም፥ ዘመናዊውን የምርት አመራረት አስተምረዋቸው የተለመደውን የድኩማን እርዳታቸውም በይበልጥ እንዲያስፋፉት ማድረግ ብሔራዊ ግዴታቸው ነበር። እነሱ ግን ይኸን በማድረግ ፈንታ ጉልታቸውን ቀምተው ለራሳቸው መበልጸጊያ አደረጉት፤ ሌላውን የሕዝብ መሬት እየቀሙ ለውጪ ሀገር ቱጃሮች ርስተ ጉልት አደረጉት። ይህ መቅሠፍትን በራስ ላይ ማምጣት ነው።

እግዚአብሔር የትዝኅርተኞችን ልቡና መልሶልን ያሰበውን መቅሠፍት እንዲመልሰው እንጸልያለን። ዋልድባም እንደነ ወጺፍ ስሟ ብቻ እንዳይቀር አምላኳን እንማፀናለን።