June 28, 2017

በአራት ተከታታይ ፅሁፎች “ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት የሚደረገው ትግል ከየትና እንዴት መጀመር አለበት?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የተለያዩ ሃሳቦችን ለመዳሰስ ተሞክሯል። ከወቅታዊ የሀገራችን ፖለቲካ አንፃር ሲታይ በአብዛኞቹ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ ቅድሚያ የተሰጠው በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትግል ስልት ነው። ይሁን እንጂ፣ “ብሔርተኝነት” በሚል መሪ ቃል፤ በክፍል አንድ ህዝብን ወደ ጦርነትና ጨቋኝ ስርዓት እንደሚወስድ፣ በክፍል ሁለት የሰው ልጅን ወደ አውሬነት እንደሚቀይር፣ በክፍል ሶስት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት እንደማይጠቅም፣ እንዲሁም በክፍል አራትበስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት የተካነበት የትግል ስልት እንደሆነ ለማሳየት ተሞክሯል። ከዚህ በመቀጠል ደግሞ “ነፃነት” በሚል መሪ ቃል በነፃነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሁሉንአቀፍ የሰላማዊ ትግል አማራጭን በተከታታይ ክፍሎች እንመለከታለን።

እርግጥ በነፃነት መኖር የማይፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም። ይሁን እንጂ፣ “የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም” እንዲሉ ነፃነት’ም ካላወቁት አይናፍቅም። ነፃነትን የማያውቅ ሰው የነፃነትን ትርጉምና ፋይዳ አይረዳም። የራሱን ነፃነት አያስከብርም፣ የሌሎችን ነፃነት አያከብርም።ስለ ነፃነት ሙሉዕ ግንዛቤ የሌለው ሰው የሕይወትን ትርጉምና ፋይዳ እንኳን መገንዘብ አይችልም።

በመሰረቱ ነፃነት የሕይወት ትርጉም እና ፋይዳ ነው። የሰውልጅ ለሕይወት ያለው ስሜት አንፃራዊ ነፃነቱን ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት የሚገለፀው ባለው አንፃራዊ ነፃነት ነው። ሀብት እና ድህነት፤ መፈለግ እና አለመፈለግ፤ ሃይል እና ተገዢነት፤ ጤና እና በሽታ፤ ባህል እና አላዋቂነት፤ ሥራ እና ምቾት፤ ጥጋብ እና ረሃብ፤ መልካም እና መጥፎ፣ ሁሉም አንፃራዊ የነፃነት ማነስ እና መብዛት ውጤቶች ናቸው።

የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ነፃነት” የሚለውን ቃል፤ “1ኛ፡ሌላውን ሳይነኩ የፈለጉትን ነገር የመስራት፥ የመናገር፥ የመፃፍ፣ … መብት። 2ኛ፡በባዕድ መንግስት ወይም በሌላ ሰው ቁጥጥር ስር አለመሆን። 3ኛ፡ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት ስልጣን፥ መብት” እንደሆነ ይጠቅሳል። ሰው (person) ማለት ደግሞ በሃሳብ ወይም በተግባር ራሱን ወይም የሌሎች ሃሳብና ተግባር ወክሎ የሚንቀሳቀስ ነው። በራስ ወይም በሌሎች ሰዎች ፍላጎት መሰረት እየሰሩ፥ እየተናገሩ፥ እየፃፉ፣… በራስ ወይም በሌሎች ፍቃድ እየተንቀሳቀሱ እና ራስንበራስ እያስተዳደሩ ወይም በሌሎች እየተመሩ መኖር ደግሞ “ሕይወት” ይባላል።

በዚህ መሰረት፣ ሕይወት ማለት እንደ ራስ ፍላጎትና ፍቃድ ወይም በሌሎች ፍላጎትና ፍቃድ መሰረት የሚተውኑባት ቤተተውኔት ወይም ቲያትር (theatre) ናት! በሕይወት ውስጥ እያንዳንዱ ግለሰብ ተዋናይ (Actor) ነው። በእንግሊዘኛ “person” የሚለው ቃል ሥርዖ ቃሉ “persona” የሚለው የላቲን ቃል ሲሆን በመድረክ ላይ ያለ ሰው ውጫዊ ገፅታ ወይም መልክ “outward appearance of a man, counterfeited on the stage” የሚል ፍቺ አለው። ስለዚህ፣ ሰው (person) በሕይወት ትያቲር ላይ የራሱን ወይም የሌላን ሰው ገፀባህሪ በመወከል የሚተውን (personate) ነው።

ሰው የተፈጥሮ (Natural Person) እና ሰውሰራሽ (Artificial person) በሚል ለሁለት ይከፈላል። የተፈጥሮ ሰው በራሱ የተውኔቱ ደራሲ (author) እና ተዋናይ (actor) ሊሆን ይችላል። “ሰውሰራሽ” ሰው ግን የተፈጥሮ ሰዎች ገፀባህሪን በመወከል የሚተውን ተዋናይ (actor) ነው። “Thomas Hobbes” የተፈጥሮ እና ሰውሰራሽ ሰዎች በሕይወት ቲያትር ውስጥ ያላቸውን ሚና እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡

Of persons artificial, some have their words and actions owned by those whom they represent. And then the person is the actor, and he that owneth his words and actions is the author, in which case the actor acteth by authority. So that by authority is always understood a right of doing any act; and done by authority, done by commission or license from him whose right it is.” Leviathan – Thomas Hobbes, Page 84

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ “authority” የሚለው ቃል ሥርዖቃሉ “author” የሚለው ቃል ነው። ስለዚህ፣ በአማርኛ “ስልጣን” (authority) ማለት አንድን ነገር ለማድረግ፣ ለመስራት፣ ወይም ለማሰራት የሚያስችል መብት ነው። “ባለስልጣን” ማለት ደግሞ፤ “አንድን ነገር ለማድረግ፥ ለመስራት፥ ወይም ለማሰራት ኣመራርን ለመስጠት፥ ለመወሰን የሚያስችል መብት ያለው ግለሰብ ወይም ድርጅት” ማለት ነው። በአጠቃላይ፣ “ስልጣን” ማለት በተፈጥሮ ወይም በውክልና የተሰጠና አንድን ነገር ለማድረግ፣ ለመስራት፣ ወይም ለማሰራት የሚያስችል “መብት” (right) ነው።

የመንግስት ስልጣን ከእያንዳንዱና ከሁሉም ዜጎች በውክልና የተሰጠ ሀገሪቷንና ሕዝቡን ለመምራት የሚያስችል መብት (authority) ነው። እንደ “Thomas Hobbes” አገላለፅ፣ “መንግስት” ማለት እያንዳንዱ ዜጋ ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በመስማማት፤ “1ኛ፡የሌላውን መብት ሳይነካ የፈለገውን ነገር እየሰራ፣ እየተናገረና እየፃፈ በሰላም በሀገሩ እንዲኖር፣ እና 2ኛ፡በባዕድ ሀገር መንግስት ወይም በሌላ ሰው በኃይል ተገዢ እንዳይሆን ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግለት፣ 3ኛ ላይ የተጠቀሰውን “ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት ስልጣን፥ መብት”ን በውክልና ለተወሰኑ ሰዎች በመስጠት የፈጠረው አካል ነው።

በመጨረሻም ወደ ፅኁፉ ዋና ነጥብ ስንመለስ፣ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት በተለይ ባለፉት አስር አመታት የባሰ ጨቋኝና አምባገነን እየሆነ መምጣቱ እርግጥ ነው። በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በኃይል ታፍኗል። በመሆኑም፣ ይህን ጨቋኝና አምባገነን መንግስት ከስልጣን በማስወገድ የዜጎች ነፃነትና እኩልነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት አለበት የሚል አመለካከት በሰፊው ይንፀባረቃል። ነገር ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት ሆነ ሌላ ማንኛውም መንግስት ከእያንዳንዱና ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ከተሰጠው ፍቃድና ውክልና ውጪ ምንም ነገር የማድረግ ስልጣን የለውም።

በመሰረቱ፣ የኢህአዴግ መንግስት በሕዝብ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ የሆነ ተግባር መፈፀም አይችልም። ሕገመንግስት ደግሞ በሀገሪቱ ሕዝብና በመንግስት መካከል የተፈረመ የውል ሰነድ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ሰው (person) እንደመሆኑ መጠን በራሱ ፍላጎት መሰረት እየሰራ፥ እየተናገረና እየፃፈ እና በራሱ ፍቃድ እየተንቀሳቀሰ ለመኖር እንዲችል ራሱን በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት መብትና ስልጣኑን ለመንግስት አሳልፎ ሰጥቷል። የኢህአዴግ መንግስት እንዲያስከብር የተሰጠውን ስልጣን የዜጎችን በነፃነት የመስራት፣ የመናገር፣ የመፃፍና የመንቀሳቀስ መብት ለመገደብ አውሎታል። የኢህአዴግ መንግስት ላለፉት አስር አመታት በሕገመንግስቱ መሰረት ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ውጪ ሲንቀሳቀስ ውክልና የሰጠው የኢትዮጲያ ሕዝብ ምን ዓይነት እርምጃ ወሰደ?

በእርግጥ የኢህአዴግ መንግስት እንደ መንግስት በእያንዳንዱና በሁሉም ዜጎች ተፅፎ የተሰጠውን ቲያትር ከመተወን ባለፈ አዲስ ተውኔት የመፃፍና የመተውን ስልጣን የለውም። ነገር ግን፣ ለምሳሌ፣ የፀረሽብር ሕጉን ሲያፀድቅና በዚህም በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ለእስር፣ ለስቃይና ለስደት ሲዳርግ የኢትዮጲያ ህዝብ “በውል ከተሰጠህ ስልጣንና ኃላፊነት ውጪ አዋጅና መመሪያ አውጥተሃል” በሚል ውክልናውን አነሳ? በውሉ መሰረት ለመንግስት የሚከፍለውን ግብር አቋረጠ? ጥቂቶች ሺህዎች ለሞት፥ እስርና ስደት ሲዳረጉ ብዙ ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጲያ ሕዝብ መብትና ነፃነቱን ለማስከበር ምን ያህል እርምጃ ተራመደ።

ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል መብትና ነፃነቱን አውቆ በራሱና ለራሱ ማስከበር እስካልቻለ ድረስ የኢህአዴግ መንግስት ተቀየረ፥ አልተቀየረ ምን ፋይዳ አለው? የደርግ ሆነ የኢህአዴግ መንግስት መብትና ነፃነቱን ከማረጋገጥ ይልቅ በደልና ጭቆና ሲፈፅሙበት አሜን ብሎ የተቀበለ ማህብረሰብ ሌላ መንግስት ቢመጣባይመጣ ምን ለውጥ አለው? ትላንትና ዛሬ መብትና ነፃነቱን መብትና ነፃነቱን በራሱ ማስከበር የተሳነው ማህብረሰብ የኢህአዴግ መንግስት ከስልጣን ቢወገድባይወገድ ምን የተለየ ነገር ይኖራል። መብትና ነፃነቱን እንዲከበር ሆነ እንዳይከበር ያደረገው መንግስት ሳይሆን ዋናው የስልጣን ባለቤት “ሕዝብ” ነው። ጨቋኝ ስርዓት ባለበት ሀገር ጭቆናን አምኖ የተቀበለ ማህብረሰብ አለ። በእርግጥ “ጨቋኝ” መባል ያለበት ጭቆናን ፈቅዶ የተቀበለ ነው። ሰጪ በሌለበት ተቀባይ አይኖርም። ስለዚህ፣ ጨቋኝ ህዝብ እንጂ ጨቋኝ መንግስት ብሎ ነገር የለም።

በአጠቃላይ፣ መንግስት ሕዝብ እንደፈቀደለት ነው የሚሆነው። ለመብቱና ነፃነቱ የሚከራከር ጠያቂ ማህብረሰብ ባለበት መንግስት ወዶ ሳይሆን በግዱ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል። አለበለዚያ ሕዝብ ውክልናውን ስለሚያነሳበት የስርዓቱ ሕልውና ያከትማል። ስለዚህ፣ ዋናው ነገር መንግስትን መቀየር ሳይሆን ሕዝብን መቀየር ነው። ቁም ነገሩ ያለው ሕዝብ መብትና ነፃነቱን አውቆ በራሱ እንዲያስከብር ማድረጉ ላይ ነው። ሕዝብ ስለ መብቱና ነፃነቱ ያለውን ግንዛቤ በመቀየርና ጠያቂ የሆነ ማህብረሰብ መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ መንግስት መቀያየሩ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” የሚሉት አይነት ነው።

ዛጎል