July 21, 2017 

 ነጥብ አንድአንድ ነገር ታዝባቹሃል ? በግብር ዙሪያ ሕዝቡ ተቃውሞ ሲያሰማ የዳያስፕራ ግርግርና ወሬ ጸጥ ነው ያለው። ሁልጊዜ የምንለው ይሄንን ነበር። ትግሉ ያለው አገር ቤት ነው። አገር ቤት ያለው ህዝብ መንቀሳቀስ ከጀመረ ብቻ ነው የለውጥ መጀመሪያ የሚሆነው። ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ እንደሚባለው ዳያስፖራ ቢንጫጫ ወያኔዎች ከመሳቅና ከመሳለቅ ውጭ ከመጣጤፍም አይቆጥሩትም።

ነጥብ ሁለትከዚህ በፊት በኦሮሚያ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች የሌላውን ማህበረሰብ ጥያቄዎች ያጣጣሙ አልነበሩም። በመሆኑም በኦሮሚያ ባሉ ትላልቅ ከተሞች እምብዛም ድጋፍ አላገኙም። አዲስ አበባ፣ አዳማ/ናዝርሬት.፣ ደብረ ዘይት፣ ጂማ፣ አሰላ ዝዋይ ..በመሳስሉት ቦታዎች የ”ኦሮሞ ተቃዉሞ” ብዙ ገፍቶ ሊሄድ አልቻለም። በአዲስ አበባ ሰልፍ ጠርተው ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መቶ ሰው አይሞላም ሰልፍ የወጣው። በአዳማም ከ400 ሺህ ሰው በመቶ የሚቆጠሩ ናቸው አደባባይ የወጡት። በአብዛኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች። ትላልቅ ከተሞችን ያላቀፈ እንቅስቃሴ ደግሞ ዉጤት አያመጣም። ለዚህም ነው አገዛዙ እንቅስቃሴዉን መቆጣጠር ችሎ የነበረው።

አሁን በአምቦ የተጀመረው ተቃዉሞ ግን እንደከዚህ በፊቱ አይደለም። የሁሉንም ዜጎች ጥያቄ ያነገበ ነው።በግብር ስም መንግስታዊ ዘረፋ ይቁም የሚል። ይሄ ጥያቄ የኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጎች ነው። ለዚህም ነው በቀላሉ በአዲስ አበባ በበርካታ ቦታዎች ሱቆች እየተዘጉ ያሉት። አጀንዳችን አንድ ሆኖ ከቀጠልን ግፈኞች ሊቋቋሙን አይችሉም።

አንድነት ሃይል ነው። ከተከፋፈልን እንሸነፋለን። ከተባበርን ድሉ የኛው ነው። የግለሰብ መብቶች ከተከበሩ ፣ የቡድን ፣ የብኄረሰብ መብቶችም ይከበራሉ። በመሆኑ ለዜጎች መብት በጋራ መታገላችንን እንግፋበት።

ነጥብ ሶስት –  በዚህ መልኩ በትቂት ቀናት ውስጥ እየሰፋ የመጣው ተቃዉሞን ሰዎቹ እንዴት አድርገው መቆጣጠር እንደሚችሉ አላውቅም። ለአሥር ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ወታደራዊ አገዛዝ ተግባራዊ አድርገው፣ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩትን አስረው፣ በሺሆች የሚቆጠሩትን ገድለው ፣ ያሰሯቸውን ደግሞ “አይደግመኝም” የሚል ከኔቴራ በማልበስ አዋርደው፣ “ሁሉ ነገር ሰላም ነው” እያሉ በሜዲያቸው ሲፎክሩብን ይኸው እንደገና ተቃዉሞ አገርሽቷል።

ሰዎቹ ይህ አይነት ተመሳሳይ ቀዉስ ውስጥ መግባታቸው ትምህርት ሆኗቸው፣ በቶሎ አገራዊ መፍትሄ ቢፈልጉ ጥሩ ነበር። እግዜር ትንሽም ቢሆን ማስተዋል ከሰጣቸው።

ከዚህ ዘገባ ጋር የምታዩት አዲስ አበባ ሳሪስ አከባቢ፣  የንግዱ ማህበረሰብ ሱቆቹን ጥርቅም አድርጎ በመዝጋት ከአቅም በላይ የተጫነበትን ግብር መቃወሙን የሚያሳዩ ናቸው።