ፀጋው መላኩ

አልጀዚራ የኤርትራ መንግስት በዜጎቹ ላይ እያደረሰ ያለውን ስቃይ በተመለከተ ያሰራጨውን ዘገባ ተከትሎ የኤርትራ መንግስት በሚዲያው ላይ ክሱን አሰምቷል። አልጀዚራ በዚሁ ባሰራጨው ዘገባ ሀገሪቱ በአንድ ፓርቲ አገዛዝ የወደቀች መሆኗን ከማሳየቱም ባሻገር በዜጎቹ ላይ የሚያደርሰውንም ጭቆና ለማሳየት ሞክሯል። የኤርትራ መንግስት ዜና ወኪል አቶ ጳውሎስ ነታአባይ በዚሁ ውዝግብ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ አልጀዚራ ኤርትራን በተመለከተ እያሰራጨ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ሥም የማጥፋት ፕሮፖጋንዳ እንዲያቆም በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ጥያቄውን ባለመቀበል በድርጊቱ የገፋበት መሆኑን አመልክተዋል። በኳታር መንግስት ባለቤትነት የሚተዳደረው አልጀዚራ ኤርትራ በሳዑዲ የሚመራውን ቡድን መደገፏን ተከትሎ በሀገሪቱ ላይ አሉታዊነት ያላቸው ዘገባዎችን ያሰራጨ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

 የኤርትራ መንግስትም አልጀዚራ መሰል መረጃን ከማሰራጨት እንዲቆጠብ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየ መሆኑን የሱዳን ትሪብዩን ዘገባ ያመለክታል። ኤርትራና ጂቡቲ በኳታር ላይ ማዕቀብ የጣለውን በሳዑዲ የሚመራውን ቡድን መደገፋቸውን ተከትሎ ኳታር በሁለቱ ሀገራት መካከል የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው የራስ ዱሜራ ደሴትና ተራራ የሰላም አስከባሪ ጦሯን ማስወጣቷን ተከትሎ በጂቡቲና በኤርትራ መካከል ወታደራዊ ፍጥጫው እንደቀጠለ ነው። ኤርትራ ከዚህ ቀደም ከኳታር የተለያዩ አርዳታዎችንና ድጋፎች ሲደረግላት የቆየች ሀገር ብትሆንም ሀገሪቱ የያዘችውን አቋም ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከመቋረጥ ባለፈ እሰጣ አገባ ውስጥ ገብቷል።

ስንደቅ