July 22, 2017 21:27

መቼም ይህን ጉዳይ ሳነሳ የዘመኑ የኦሮሞ ምሁር ነን የሚሉ ኦሮሞን አውርደው አውርደው የማንም መጫወቻ ያደረጉት ኦሮሞ ገዥ ሆኖ አያውቅም በአበሾች ሲረገጥ የኖረ ነው ብለው ዛሬ እየሆነ ያለው አልቃሻነቱ ለቆት ወደ አባቶቹ ወኔ እንዳይመለስባቸው ነገሬን ይኮንኑታል፡፡ ኦሮሞ ጥንቱንም ኢትዮጵያዊ እንደሆነና ያው ዛሬ አበሻ አደለህም ተብሎ ሌላ ሥም ቢሰጠውም ሳይንሱም ታሪኩም ግን የኦሮሞን ጥንታዊ ኢትዮጵያዊነት በተለይም ደግሞ አበሻዊነት (ከሌቫንት ና ኢትዮጵያዊ መሠረት ካላቸው ነገዶች) ያለምንም ስህተት ነው እንደወረደ የሚናገሩት፡፡ መረጃዎቹ በአፍ እንደፈቀዱ የሚያወሩት ሳይሆን ደግሞ ዘመኑ ደረስኩበት የሚለው የመለዘር ጥናት(ጄኔቲክ አንሴስተሪ የሚነግረን ነው)፡፡ በዘር በአጭሩ ኢትዮጵያ አማራና ትግሬ ሐበሻ ከሆኑ ኦሮሞ ምንም አይነት ከእነሱ የሚለየው የዘር መሠረት የለውም፡፡ ይህን እውነት የኦሮሞ ታሪኮችና አብረውት ሲወረዱ ሲዋረዱ የመጡ እምነታዊና ባህላዊ እሴቶቹም ይገልጹት ይመስላል፡፡ ምን አልባትም ኦሮሞ በቀጥታ የኦሪት እምነትን ይዞ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ለተወሰነ ጊዜ በአንዱ የአገሪቱ ሥፍራ ሲኖር ቆይቶ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወድ መስፋፋት ደረጃ እንደደረሰ እንረዳለን፡፡ የኦሮሞን ኦሪታዊነት በተመለከተ የኢሬቻው ስርዓት አንዱ መገለጫ ሲሆን የገዳ ሥርዓቱ ራሱ በመጽሀፍ ቅዱስ ተጽፈው የምናነባቸው የጥንታዊያኑ የእነ ሙሴና ኢያሱ አይነት እንደሆነ እናያለን፡፡ ወደ ተነሳሁበት ከመግባቴ በፊት ስለ ኦሮሞ ኦሪታዊነት ማሳያዎች ጥቂት ማለት ፈለግሁ፡፡

አንዳንደ ሰዎች የኦሮሞ ኢሬቻን ሥርዓት ከጥንቱ የኖህ ከጥፋት ውሃ በኋላ የሆነውን ሥርዓት ማስታወሻ አይነት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህን ሥርዓት እውንም ስናያው የሰሜኑ ክርስትናን ቀድሞ የተቀበለውም ዘመን የሚለውጠው በክርስቶስ ልደት ሳይሆን በዚሁ ከኦሮሞ ኤሬቻ ጋር ተቀራራቢ በሆኑ ቀናቶች ነው፡፡ በትክክልም የኢትዮጵያን ዘመን መለወጫ መሠረት ስናይ ከኖሕ የጥፋት ውሀ መጉደል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ አይነት ሥርዓት ደግሞ በኢትዮጵያ ከክርስትናው በፊት በጣም ተንሰራፍቶ ስለነበር በክርስትናውም ዘመን ይሄው ጊዜ ለዓመተ ምህረት መቁጠሪያነት እንደመነሻ ቀን የሆነ ይመስላል፡፡ ሌላው የኦሮሞ ባህላዊ እምነት ተብሎ የሚጠራው ዋቄፈቻ(ታ) ትርጉም የሰማይ አምላክን ማምለክ ማለትን ይመስላል፡፡ ዋቃ ማለት እግዚአብሔር ማለት ሲሆን ሰማይ ማለትም ነው፡፡ ኢሬቻን ያስተዋለ እንግዲህ ከእንቁጣጣሽ ጋር ማወዳደር ነው፡፡ በእንቁጣጣሽ ለምለም ቄጤማ በየቤቱ ይበረከታል፡፡ በኤረቻም ይሄው ለምለም ቄጤማ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ልብ በሉ በእንቁጣጣሽ ለምለም ቄጤማ አበባየሆሽ በሚሉ ሰዎች ሳይሆን በመስከርም 1 ቀን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብትገኙ ሲታደል ታያላችሁ፡፡ አልፎ አልፎም ዲያቆናት በየሰፈሩ እየዞሩ የምስራች እያሉ ያድላሉ፡፡ ይሄ ሥርዓት በእርግጥም የኖህን የጥፋት ውሃ መጉደልን ለማብሰር ነው፡፡ ይሄው ትምህርትም በቤተክርስቲያኗ ይሰጣል፡፡

ከክርስትናው ታሪክ ጋ ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ከሌሎች ሁሉ የሚለያት የኦሪትንና ክርስትናውን በማዋሀድ እስከዛሬም መኖሯ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የኦሪት ሥርዓት በኢትዮጵያ ምን ያህል ተጽኖ እንደነበረው ነው፡፡ በቅርቡ ለብዙዎቻችሁ ያጋራሁት የኢትዮጵያውያን የመለዘር ጥናት(ጄኔቲክስ) ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በተለይ ደግሞ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አፋር፣ አማራ፣ የመሣሰሉት ፍጹም የዘር መሠረት አንደነትን ያሳያል አሁንም ሊንኩን እዚህ ልተውላችሁ፡፡ http://www.cell.com/ajhg/pdf/S0002-9297(12)00271-6.pdf ይህ እንግዲህ እንደወረደ የሚነግረን የኢትዮጵያውያንን የዘር መሠረት ነው፡፡

የዚህን ጥናት ውጤት ዘለግ ስናደርገው የሚናገረው በዚህች አገር በአንድ ወቅት አንድ የሆነው ሕዝብ ከቦታ ቦታ በዚችው አገር ክልል ውስጥ ሲንቀሳቀስ እርስ በእርስ እየተነጣጠለ የየራሱ ባህልና ቋንቋ እያዳበረ ከዛ ተመልሶ ሲገናኝ እንደ ባዕድ እየተያየ በጦርነትም በሰላምም እንደገና እየተዋሀደ የኖረ ሕዝብ እንደሆነ ነው፡፡ ላስተዋለው የጥንቱ ባህሉንና እምነቱን በተወሰነም ቢሆን አቆይቶ እናያለን፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ኦሪታዊነት ትልቅ ተጽኖ እንዳሳደረ እናስተውላለን፡፡ ኢሬቻና ራሱም የገዳ ሥርዓቱ ሌላ የሚመስለው ጥንታዊ እምነትም ሆነ ሥርዓት ለመኖሩ ዋቢ ያለ አይመስለኝም፡፡

ሆኖም ከኦሪታዊው ሥርዓት ጋር ግን ትልቅ መመሣሰል እንዳለው እናያለን፡፡ ኢሬቻን ከላይ በገለጽኩት መልኩ ነው፡፡ የገዳውን ሥርዓት ለተመለከተ በቀጥታ ትዝ የሚለው ከሙሴ እስከ ሳሙኤል (የሀና ልጅ) ያለው የእስራኤላውያንን ሥርዓት ነው፡፡ ልብ በሉ ከላይ ሌቫንት ብዬ የጠቀስኩት የኢትዮጵያውያን (የሁሉም) አንዱ ወገን አባት የሆነው በሊንኩም በግልጽ የምታዩት ጥንት እስራኤላውያን ይኖሩበት በነበረው ሥፍራ ይኖር የነበረ ሕዝብ ነው፡፡ ገዳ እንዴት የእነሙሴን ታሪክ መሰለ ካላችሁ፡፡ እስራኤል እስከ ሳሙኤል ድረስ ንጉስ አልነበራቸውም፡፡ ሕዝቡን ይመራ የነበረው ልዩ ሰው ነው፡፡ ካህን ነው ግን የግድ ከሌዊ ወገን አይደለም፡፡ ልብ በሉ በአጋጣሚ ሙሴ የአሮን ወንድም የሌዊ ወገን ነው፡፡ ከሙሴ ቀጥሎ እስራኤልን የመራው የነዌ ልጅ ኢያሱ(አውሴ) የኤፍሬም ነገድ ነበር እንጂ ከሊዊ አልነበረም፡፡ ይህ የመሪነት ኃላፊነት እስከ ሳሙኤል ድረስ ቀጥሎ በሳሙኤል የተቀባው ሳኦል የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉስ ነበር፡፡ የገዳን ሥርዓት አስተውሉት፡፡

ንጉስ አልነበረም፡፡ ሕዝቡን በማስተዳደርም ሆነ በጦርነት ወቅት በመምራት ግን ልዩ ሥርዓት ነበር ልክ እንደ እነ ሙሴና ኢያሱ አይነት አመራር ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የኦሪታዊ ተጽዕኖ ጉልህ ድርሻ ነበረው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ ኦሮሞም በሉት ሌላው ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደዛሬው ከመበረዙ ትንሽ ወደ ኋላ ምን ዓልባትም ከደርግ በፊት ያለውን እንኳን በደንብ ብናጤነው ኦሪታዊነትን የሚያሳዩን አኗኗር በግልጽ እናያለን፡፡ ልብ በሉ ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከክርስትናው ጋር ተዋህደው የምናገኛቸው ሥርዓቶችም ከላይ እንደጠቀስኩት የኦሪቱን እምነት በኢትዮጵያውያን ዘንድ የነበረውን ጉል ድርሻ ነው፡፡

ሌላው ዛሬ ኩሽቲክ ሴሜቲክ ምናምን እየተባለ የሚታወቀው ቋነቋም በቋንቋ ሊቃውንት የሚታወቀው አፍሮ ኤዢያቲክ በመባል ነው፡፡ ዛሬ እንደሚወራው አደለም፡፡ ለኦሮምኛ በሉት ዛሬ የኩሽ እየተባሉ የሚጠሩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ቢያንስ ከላቲን ሴም እየተባሉ ለሚጠሩት በጣም ይቀርባሉ፡፡ እውነታው ይሄ ነው፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ በኢትዮጵያ ምድር አያሌ ገዥ ሆነው የተነሱ ነገስታትም ዘራቸው ከአማራ ከትግሬ ከኦሮሞ ተብሎ የተጠቆመበት ጊዜ የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ የቀርቦቹ እስከ ኃይለሥላሴ ያሉትም በዘር አማራ ኦሮሞ ምናምን ተብለው አይተወቁም፡፡ ሌሎች የአበሻ ነገስታት ይሏቸዋል፡፡ በእርግጥም አዎ ልክ ነው፡፡ እነሱ ብዙዎቹ ራሳቸውን ሰሎሞናዊያን ነን ይላሉ፡፡ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ሁሉም ባይሆኑም፡፡ ለብዙዎች የቀዳማዊ ሚኒሊክ ታሪክ ተረት ተረት ነው፡፡ ከላይ ሊኒኩን ያስቀመጥኩት ሳይንሳዊ መረጃ ግን ይህን ታሪክ እውነት እንደነበር ይመሰክራል፡፡ ምን አልባትም ያኔ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድ ላይ ነበሩ፡፡ ከዛም በኋላ እንዳልተነጣጠሉ (በጊዘያዊነት ከሆነው በቀር) የዚሁ ጥናት ውጤት ያሳያል፡፡ ከዛ ጀምሮ መነጣጠሉ ቢኖር እንዲህ በዘር መመሳሰሉም ላይኖር ይችላልና፡፡ እንግዲህ የገዥነትን እውነት ከአነሳን የእከሌ ብሔር ገዛ የሚል የለም፡፡ ባይሆን የክርስቲያን ነገስታት ነበሩ፡፡ ያም ሆኖ ከጥቂቶቹ በቀር ማንንም ሰው በእምነቱ ላይ ተጽኖ አላሳደሩም፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ከጥንቱ ሙስሊሞችን ከተቀበለው እስከ አጼ ኃይለስላሴ፡፡ ጥቂቶች ለምሳሌ ዮሀኒስ ሁሉንም ክርስቲያ ለማድረግ እንደሞከሩ ባይካድም፡፡

በእነዚህ ታሪኮች ግን በተለይም ከ16መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ ኦሮሞ ልዩ የታሪክ ሥፍራ ነበረው፡፡ በሥልጣንም፡፡ በለሌች አስተዋፅኦዎችም፡፡ ከሌላ እንደመጣ በብዙዎች ሲነገር የነበረው የኦሮሞን የት መጣነት አሁንም ለትዝብት ከላይ ያለውን ሊንክ ይመልከቱ፡፡ ከማዳጋስካርም አልመጣ ከባህርም አልወጣ፡፡ አውነታው ከ16ኛው ክፍለ ዘመንም በፊት ይሄው ሕዝብ የአበሾቹ አንድ አካል ነበር፡፡ ከዚህ ዘመን ጀምሮ የዚህን ሕዝብ ልዩ ትኩረት እንዲኖረው ካደረጉት ጉዳዮች ዋነኛው ምን አልባትም ብቸኛው ቁምነገር ግን በጦርነት በተሰለፈባቸው ሁሉ በአገኛቸው ድሎችና ሥኬታማነቱ ነው፡፡ ልብ በሉ ከታች ከገላና (አባ ባሕሬ ከነበሩበት) እስከ ሰሜን ትግራይ ለመድረስ ከ50 ዓመት ያነሰ ጊዜ ነው የወሰደበት፡፡ ከዛም ቀጠለ በኢትዮጵያ የመሪነት ድርሻ ውስጥ ትልቁን ቦታ ይዞ ኖረ፡፡

ዛሬ ያለው የኦሮሞ ቁቤ ትውልድ እንደልብ በሚዘውሩት አእምሮው ባዶ ስለሆነ አይገባውም፡፡ የጎንደርን መንግስት ምንምን መጥቀስ ዛሬ ላለው ቁቤ የመከነና ማንም የሚነዳው ትውልድ እንዴት ቢነግሩት እውነታው እንደሚገለጥለት አላውቅም፡፡ እውነታው ኦሮሞ እስከደርግ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ የመሪነት ድርሻ ትልቅ ቦታ የነበረው ነው፡፡ ከዚህም በላይ ያለው እውነታ ኢትዮጵያን የመሯት ነገስታት አጼ ኃይለስላሴን ጨምሮ በዘር ከመጡ በግልጽ የሚታወቅ ዛሬ ኦሮሞ ከተባለው አበሻው ክፍል እንደሆኑ እናያለን፡፡ መቼም ኃይለስላሴ የታላቁና የብልሁ የራስ መኮንን ኃይለመስቀል ጉዲና ልጅ እንደሆኑ ምሁሮቹ አደሉም ተራውም ሰው ያውቀዋል፡፡ እንግዲህ እሳቸው አማራ እንደሆኑ ባይናገሩም አማራ ናቸው ተብሎ በግድ ዛሬ የሚወራላቸው ሚኒሊክ ዛሬ ኦሮሞ ከሚባለው ዘር እንዳላቸው አይነገረን እንጂ በሥልጣናቸው ዘመን ከየትኛውም ማህበረሰብ በላይ የኦሮሞ ሕዝብ ልጆች ዋና ተዋናይ እንደነበሩም አይካድም፡፡ ለነገሩ ሸዋ በዘር እከሌ አይባልም፡፡ ልብ በሉ ራስ መኮንን የሚኒሊክ አጎትም እንደሆኑ አስተውሉ፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ዛሬ በተቃራኒው እንደሚወራው ሳይሆን ሚኒሊክ ሥልጣንን ሆን ብለው ለኦሮሞ ልጆች ለመሥጠት ብዙ ሞክረዋል፡፡ መጀመሪያ ለወዳጃቸው ለጎበና የልጅ ልጅ ከዛም ለኢያሱ በማስረከብ ነው ያለፉት፡፡ ዛሬ ያለው የመከነው የቁቤ ትውልድ ይህ እውነት ያስደነብረዋል፡፡ ኦሮሞን ያወረደው ይሄ የመከነ ትውልድ እንደእነዚህ ያሉ እውነታዎችን እንዳይቀበል አዚም ተደርጎበት ይሄው ዛሬ ምልክት የሌለው ሆኖ ማንም እንደፈለገ ሲዘውረው እናያለን፡፡ ደርግ ከሆነም እነተፈሪ በንቲን ጨምሮ ራሳቸው ከርኔል መንግስቱ ማን ነበሩ; እንግዲህ ዛሬ 50ዓመት ጀምረው ኦሮሞን ነጻ እናወጣለን ሲያሻቸውም ከቀኝ ግዛት ሌላ ጊዜ ከጨቋኝ ስርዓት የሚሉት ኦሮሞን ዛሬ የት እንዳደረሱት ታዘቡ፡፡ መካን በዘመኑ ሁሉ የማይሳካለት ሕዝብ ብለህ ጻፍ እንደላው አይነት ነው የሆነው፡፡ ኦሮሞ ገዥ እንጂ ተገዥ የሆነበት ዘመን አልነበረም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በቋንቋና ባህል ከኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ በተወሰነ ተጽኖ ነበረበት፡፡ ይህ ግን እውነት ለመናገር በልዩ ሴራ አራማጆች ሆን ተብሎ የተጋነነና አልነበረም፡፡ ልብ በሉ አዲስ አበባ ዙሪያ ያለው የሸዋ ኦሮሞ እስከዛሬም አማርኛ ተናጋሪ አደለም፡፡ ሩቅ ያሉት ወለጋዎች ግን አማርኛን አቀላጥፈው የሚናገሩ ግን አማርኛ በግድ እንድናውቅ ተደረግን ብለው የሚያማርሩ ናቸው፡፡ እውነታውን አንካካድ፡፡ ችግሩ ከውጭ በመጡ ሰዎችና ተማርን በአሉ ግለሰቦች የተፈጠረ ነው፡፡ የኦሮሞን ሥርዓትና ባህልም ስናይ ኢሬቻንም በሉት ሌሎች ሥርዓቶችን የሚያኪያሂደው ይሄው ነገስታቶቹ ዙሪያ ያለውና በብዛት በመሪነት የነበሩ የኦሮሞ ልጆች የወጡበት የሸዋው ሕዝብ ነው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ገዳም በሉት ኢሬቻ ወላጋ ሆነ አርሲ አያውቁትም፡፡ ገዳ በቦረናና ጉጂ እስከ ኃይለሥላሴ ድረስ ሳይበረዝ እንደነበር የገዳው አጥኚ ፐሮፌሰር አስመሮም የሚናገሩት እውነት ነው፡፡ ይሄም የሆነው የዛሬዎቹ ምሁር ነን የሚሉት ኦሮሞዎች እንደሚሉት ኦሮሞ በሚኒሊክ ቅኝ ግዛት በመያዙ ሳይሆን ቦረናና ጉጂ ከኢንግሊዝ ቅኝ ግዛትነት በሚኒሊክ በመዳኑ ነው፡፡ ይህን የፈጠጠ እውነት ነው የሚክዱት፡፡ በኢነግሊዝ ሥር ቦረና ወድቆ ቢሆን የመጀመሪያ እንዲወድም የሚደረገው የገዳ ሥርዓት ነበር፡፡ ይህ ሥርዓጥ ለቅኝ ገዥዎች አደገኛ ነበርና፡፡ ምሁር ነኝ የሚለው የዛሬዎ በኦሮሞ ሕዝብ ልጅ የሚነግደው ኦሮሞ ነኝ ባይ ነው ኦሮሞን ዛሬ እየገደለ ያለው፡፡ ይህ እውነት እስከሚገባው ኦሮሞ መውረዱ ይቀጥላል፡፡

ልብ በሉ አሁን ያለውን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚቆመረውን ቁማር፡፡ በቃ ሕዝቡ ባዶ እንዳደረጉት ስለአመኑ እንደፈለጉ ይዘውሩታል፡፡ የአዲስ አበባና ምናምን ጥቅማጥቅም ሰጠንህ ብለው አወጁለት፡፡ ጮቤ ሊያስረግጡት አሰቡ፡፡ ሆኖም ነገሩ እንኳን ጮቤ የሚያስረግጥ ጭራሽ በኦሮሞ ላይ የታወጀ አዋጅ እንደሆነ ታዘብን፡፡ የኦሮሚያ ቲቪ ሰበር ዜና ብሎ አቀረበው፡፡ ኦሮሞን የናቁት እንዲህ ነው፡፡ ምክነያቱ ግልጽ ነው፡፡ ኦሮሞን ገለልተኛ ስላደረጉት አሁን ሁሉንም ለኦሮሞ በሚል ሥም መለጠፍና ኦሮሞን በወሬ ማታለል እንደሚቻል ስለአመኑ ነው፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ ተሳክቶላቸዋልና፡፡ ኦሮሞ ቁቤው ትውልድ ጥላቻው ከሌሎች ጋር ነው፡፡ ራሱን ከሚገድሉት ጋር አዚም ስላደረጉበት ብዙም አይታዩትም፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ በጀነራል ታደሰ ብሩና ዋቆ ጉቱ ሥም ት/ቤት ልንሰራልህ ነው ብለው ያውጁለታል፡፡ ሲጀምር ምን ማለት እንደሆነ ራሱ እኔን አይገባኝም፡፡ ልብ በሉ ለመሆኑ ይሄ ቁም ነገር ሆኖ የሚወራስ ነበር; የኦሮምኛ ትምህርት ቤት መሠራት ራሱ ትልቅ ጉዳይ ነው ወይስ; ደግሞ እኮ ትምህርት ቤቱ ተሰርቶ ሲመረቅ ነበር አብሮ ስሙንም ለመናገር የሚመቸው፡፡ ለምን ይህን እንደትልቅ ነገር ማውራት ተፈለገ; ግልጽ ነው በወሬ እንደፈለጋቸው እንደሚዘውሩት ስለአመኑ ነው፡፡ ሌላው የመከነው የቁቤ ትውልድ ስንት ከታወቁ የኦሮሞ ጀግኖች ታደሰ ብሩንና ዋቆ ጉቱን ብቻ ስለሚያውቅ ነው፡፡ የእነዚህንም ቢሆን ራሱ በፈጠረላቸው ታሪክ ይፈነጥዛል እንጂ በትክክል የጀነራሎቹን እውነተኛ ታሪክ አያውቀውም፡፡

የአሁኑ የኦሮሚያ መሪ የሆኑተ ለማ መጀመሪያ ተስፋ ብናደርግም እየቆየን ስናያቸው ለካ አሁን ለአለው የኦሮሞ ትውልድ ጥሩ መድሀኒቱ ስለነበሩ ነው አሰኘን፡፡ ይሄው እየዞሩ በየቦታው ያስጨበጭቡታል፡፡ አሁን እንኳን በእስር እየማቀቁ ያሉ ከሞት የተረፉ ወገኖቹ እንዲፈቱ በጥያቄ ደረጃ እንኳን በማንሳት ለማን የፈተነ የለም፡፡ ብቻ ለማ በወሬ አፍዘው ያስጨበጭቡታል፡፡

ዓላማውም ይሄ ነው፡፡ ሕዝብን በግብር አሳቦ ለመዝረፍ ግን ያው እንደምናየው ኦሮሞ የመጀመሪያው ኢላማ ነው፡፡ አዲስ አበባን ፊንፊኔ አልንልህ፣ በጀነራል ዋቆና ታደሰ ሥም ትምህርት ቤት ሰራንልህ ከዚህ በላይ ምን ትፈልጋለህ; ነው የሚሉን፡፡ ያሳዝናል፡፡ እንዲህ ነው እያዋረዱን ያሉት፡፡ የቱንም ያህል አመጽ ቢነሳ ኦሮሞን ለማስተንፈስ ዛሬ ቀላል ሆኗል፡፡ ኦሮሞ የመከነበት ስልት አሁን ወደ አማራው ዞሯል፡፡ እስከዛሬ አማራ የተባለውን ሕዝብ ማስጨብጨብ ይቅርና እንደመሪ እንኳን በፊቱ መናገር አልተቻለም፡፡ የሚያነሳው ጥያቄ ከባድ ነው፡፡ አማራን ግን እነ ሞረሽንና ቤተ አማራን አሰማርተውበታል፡፡ ምን አልባትም ተሳክቶላቸው እንደኦሮሞ አንድ ቀን ሊያስጨበጭቡት ይችላሉ፡፡ ሰው ከገዥነት መንፈስ ወጥቶ ተገዥ ነኝ ሲል ያኔ መውደቁ እውነት ነው፡፡ የገዥነት መንፈሱ ከተለየው ማሸነፍ የለም፡፡

ሌላው አሁን ሰሞኑን የኦሮሞን ሕዝብ በተረት ተረት መካን በማድረግ አንዱ ተዋናይ የሆነው ኤርትራዊው ተስፋዬ ገብረአብ አሁንም ኑራ ነቢ የሚል ተረት አዘጋጅቼልሀለሁና ገዝተህ አንብብና ይበልጥ ባዶ ሁን እያለ ነው፡፡ ሲጀምር ኑራ ነቢ የሚል ከኦሮሞ ጋር መሠረት ያለው ታሪክ ሊኖር አይችልም፡፡ በተስፋዬ አስተሳሰብ ኦሮሞ እስላም ስለሆነ እንዲህ ያለ ነገር ቢጻፍለት ተረቱን በደንብ ተቀብሎ ያነበዋል ነው፡፡ ኦሮሞ በእምነት እንደሌሎቹ ሁሉ የእስልምናም የክርስትናም ተከታይ ቢሆንም ይበልጥ ግን ኑራ ነቢ ከሚባል ታሪካዊ መሠረት ጋር እንደማይገናኝ እኔ ላረጋግጥለት እወዳለሁ፡፡ የኦሮሞ የእስልምና ታሪክ አለ ከተባለ እኮ ከ16ኛው መ.ክ.ዘ በኋላ ነው፡፡ ዛሬ እንደመሠረት በዋቢነት የምናያቸው ቦረናዎች ሳይቀሩ አብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ አደለም፡፡ አሰቂኙ እውነታ ተሰፋይ በአለፉት 2 ዓመት በኤርትራ በአሳለፈበት ወቅት የሰማውን የአንድ የኤርትራ እስልምና ተከታይ ሕዝብ ታሪክ ነው ለኦሮሞ ቢጻፍ ፅሩ ገበያ ያመጣል በሚል የሚቀልድብን፡፡

በአጠቃላይ ዛሬ ያለው የቁቤ ኦሮሞ በወሬ እንደልብ የሚፈዝ መሆኑ በይፋ እየታየ ስለሆነ ሴረኞቹ ይሄንኑ ስልት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ ብዙ ቀላል የማይባ ቁጥር ያለው ኦሮሞ ሁኔታዎች እየገቡት ቢሆንም አሁንም ገና ብዙ ይቀራል፡፡ ኦሮሞ የአባቶቹን ታሪክ እንደገና ከአላሰበ፣ ለዘሙ ጠላቶቹ ተረትና ወሬዎች ማጨብጨቡን ከአላቆመ፡፡ ዛሬ ለሚያታልሉት ነጋዴዎች ፍጹም እምቢ ከአላለ፡፡ የሚያስፈልገውን ሁሉ በራሱ ማድረግ ሲችል የገዳዮቹን ይሁንታና የማታለያ ወሬ እየተቀበለ መጨፈሩን ከአላቆመ፣ እሱም ነጻ አይወጣ ለኢትዮጵያውያን ሁሉም ነጻ መውጣት ዋና እንቅፋት መሆኑና ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ጠላቶች ዋና መጠቀሚያ መሆኑ ይቀጥላል፡፡
አመሰግናለሁ!

እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን

ልዑል አምላክ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ!

አሜን!

ሰርጸ ደስታ