JULY 23, 2017

ሆን ብለውና ለሌለ ሰው ተገቢ ያልሆነ መብት ወይም ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ፣ ሐሰተኛ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማዘጋጀት ግለሰቦችን በማሰር የተጠረጠሩ ሁለት ከፍተኛ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መኮንኖችና ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሾቹ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሐጎስ መራ፣ የጣቢያው ኃላፊ ኮማንደር ግርማ ሰንበቶ፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ማኅደር ከዋኝ አማኑኤል ነዋይ፣ ችሎት ሥነ ሥርዓት ሽመልስ ታፈሰ፣ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መካከል ዘርፍ የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግቢ ጥበቃ ሳጅን መሐመድ  ናስርና የአንበሳ ባንክ ፒያሳ ቅርንጫፍ የጥበቃ ሠራተኛ አብርሃም አበበ መሆናቸውን፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሾቹ ከየካቲት 15 ቀን 2008 .. እስከ የካቲት 28 ቀን 2008 .ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ አብርሃም አበበ የተባለው ተከሳሽ አማኑኤል ነዋይ ከሚባለው ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር፣ ቢኒያም ታደሰና ዮሴፍ ብርሃኑ የተባሉ ግለሰቦች ተይዘው እንዲቀርቡ ሐሰተኛ የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ ማዘጋጀታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በሀሰት የተዘጋጀው የመያዢያ ትዕዛዙን ሳጅን መሐመድ የተባለው ተከሳሽ ሽመልስ ለሚባለው ተከሳሽ በማቅረብ ማኅተም እንዳስመታበትም በክሱ ተካቷል፡፡

ሳጅን መሐመድ የተባለው ተከሳሽ ከኮማንደር ግርማ ጋር በመመሳጠር ‹‹ገንዘብ ተወሰደብን›› ባዮችን እንዳስተዋወቃቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ ኮማንደሩ ዮሴፍ ብርሃኑ የተባለ የግል ተበዳይ እንዲያዝ ትዕዛዝ በመስጠት በክትትል ፖሊስ እንዲያዝ ካደረጉ በኋላ፣ ገንዘብ ተወሰደብን ባዮች የጠየቁትን 487,000 ብር እንዲከፍል መጠየቁን ክሱ ያብራራል፡፡ ነገር ግን የአዲስ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ የዕለት ሁኔታ ጸሐፊ በተያዘው ግለሰብ ላይ የቀረበና በጣቢያው የተመዘገበ አቤቱታ የሌለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ግለሰቡን አንቀበልም›› ማለታቸውን ዓቀቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ኮማንደሩ ለክፍለ ከተማው ፖሊስ መምርያ ግለሰቡን እንዲያስረክቡ ለክትትል ፖሊስ ትዕዛዝ በመስጠታቸው፣ ክትትሉ ለመምርያ ኃላፊው ረዳት ኮሚሽነር ሐጎስ እንዳቀረቡት በክሱ ተጠቅሷል፡፡

ረዳት ኮሚሽነር የቀረበላቸው የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ በአሠራሩ መሠረት ገቢ ሳይሆንና የመምርያው አሠራር ከሚፈቅደው ውጪ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም፣ ‹‹የግል ተበዳይ ዕቁብ እየሰበሰበና ገንዘብ እየወሰደ የማይመልስ በመሆኑ በጥብቅ ይጣራበት፤›› ብለው ለክፍለ ከተማው ወንጀል ምርመራ ኃላፊ መምራታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

የክፍለ ከተማው ወንጀል ምርመራ ኃላፊ የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዙን በመጠራጠር ሲያጣሩ፣ ሐሰተኛ መሆኑን እንዳረጋገጡ በክሱ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጀ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(2)ን ተላልፈው በመገኘታቸው፣ ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

ክስ ከተመሠረተባቸው ውስጥ ረዳት ኮሚሽነር ሐጎስ መራና አብርሃም አበበ ሐምሌ 12 ቀን 2009 .. ፍርድ ቤት ቀርበው ማንነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ክሱ ተሰጥቷቸው ተነቦላቸዋል፡፡ በጠበቃ እንደሚከራከሩ ተናግረውም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸውም  ጠይቀዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ግን በተከሳሾቹ ላይ የተጠቀሰው አንቀጽ ከአሥር ዓመታት በላይ እንደሚያስቀጣ ገልጾ ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡ ሳጅን መሐመድ መጥሪያ ደርሷቸው በመቅረታቸው ተይዘው እንዲቀርቡ፣ ሌሎቹ ደግሞ መጥሪያ እንዲላክላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቀረቡት ተከሳሾች የተጠቀሰባቸው አንቀጽ ዋስትና እንደሚከለክል ገልጾ፣ የዋስትና ጥያቄያቸውን እንዳልተቀበላቸው ነግሯቸዋል፡፡ መጥሪያ ደርሷቸው ያልቀረቡትን ተከሳሽ ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርብ፣ መጥሪያ ያልደረሳቸው እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ በመስጠት ለሐምሌ 21 ቀን 2009 .. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

reporter Amharic