አዲስ አበባንና በዙሪያዋ ያሉ የሸዋ ዞኖችን ያካተተ አዲስ ክልል የመኖሩን አስፈላጊነት በተመለከተ ከዚህ በፊት አንዳንድ ጽሁፎችን  ለንባብ ማብቃቴ ይታወቃል።ለደረሱኝ በርካታ የድጋፍና የማበረታቻ መልእክቶች ያለኝም ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ። በርካታ ጸሃፊያንም የሸዋን ክልል አስፈላጊነት መጻፍና ግፊት ማድረግ መጀመራቸውም አስደሳች ነው።

ሆኖም ግን ሸዋ ራሷን የቻለች ክልል እንዳትሆን የሚፈልጉ ቡድኖች እንዳሉ መረሳት የለበትም። ለዚህም ነው በዚህ ዙሪያ በተደራጀ መልኩ ትግልና ግፊት መደረግ ያለበት። በተለይም የሸዋ ህዝብ።

አንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶች የሸዋ ክልል መኖሩን አምረው ይቃወማሉ። ያም ለኦሮሞው ጥቅም ከማሰብና ከመቆርቆር ሳይሆን ኦሮሚያ የምትባለው ክልል ልትጠፋ ነው ከሚል ነው። ከዚህም የተነሳ “ኦሮሚያን” ከኦሮሞ ጋር በማገናኘት ይሄንን ሐሳብ በማቅረባችን “ጸረ-ኦሮሞ” ሊሉንም ይዳዳቸዋል። አንድ የዘነጉት ነገር ቢኖር ግን ኦሮሚያ የሚባል ነገር ከ26 አመታት በፊት ኖሮ የማያውቅ መሆኑን ነው። በአንጻሩ ግን ሸዋ ከአንድ ሺህ አመት በፊት የነበረ ነው።

ወደ ሕወሃቶች ስንመጣ፣ ኦሮሞውም አማራዉ፣ ጉራጌውም ድብልቁም ሁሉም እኩል የሆኑባት አዲስ አበባን የምትመስል፣ ሰፋ ያለች ክልል ተፈጠረች ማለት፣ የዘር ፖለቲካቸው ስርዓታቸው ተናጋ ማለት ነው። ህዝብ በዘር ላይ ሳይመሰረት መተያየት ከጀመረ፣ መደጋገፍ፣ መቀባበል፣ መያይዝ ይጀምራል። ያ ደግሞ ለነርሱ ስልጣን ያሰጋቸዋል። በስልጣን ለመቆየትም ሲሉ ኦሮሞ ፣ አማራ፣ ጉራጌ እያሉ የግድ መከፋፈል አለባቸው።

በሸዋ ያለው የኦሮሞ ማህበረሰብ በሸዋ ካለው ከተሜው ጋር እድል ፈንታው የተያያዘ ነው። የሸዋ ኦሮሞ አክቲቪስቶች፣በኦሮሞ ስም፣ በኦነጋዊያን ፣ ለተረጨው የዘረኝነትና የጥላቻ ወሬ ጇራቸዉን ዘግተው፣  በአብዛኛው በገጠር የሚኖረውን የሸዋ ኦሮሞ ህዝብን መሰረታዊ ጥያቄና ጥቅም የሚያስጠብቅ ሥራ ነው መስራት ያለባቸው። ከነጃዋር፣ ከነጸጋዬ አራርሳ፣ ከነ አሰፋ ጀላታና ከመሳሰሉት ጋር አብሮ መንጎድና የኦሮሞዉ ማህበረሰብ ከሌላው ጋር ማጋጨት በተለይም የሸዋን ኦሮሞ የሚጎዳ ነው። ጎድቶታልም። የሸዋ ኦሮሞ ጥያቄና ጥቅም የሚከበረው በዋናነት የሸገር አዲስ አበባን፣ የአዳማን፣ የቢሾፍቱን፣ የዝዋይን …በአጠቃላይ የከተሜዉን ህዝብ antagonize በማድረግ ሳይሆነ ከከተሜው ጋር በመተሳሰር ነው።

አሁን ያለችዋ የኦሮሚያ ክልል በሸዋ ያሉ ከተሞች የሚኖረዉን አፋን ኦሮሞ የማይናገር ማህበረሰብ የምትወክል ክልል አይደለችም። የኦሮሞዎች ብቻ የሆነች ክልል ናት። ያ ደግሞ ተቀባይነት አይኖረውም። የዘር ግጭቶችን ጥላቻን ነው የፈጠረው።

እኛ ግን በጥላቻ ምትክ ፍቅር፣ በልዩነት ምትክ አንድነት፣ “ኦሮሞ፣ አማራ ..” በመባባል ምትክ በዜግነት መከባበርን፣ እንደ ድሮው ስርዓት አማርኛ ብቻ ይሁን ወይንም አሁን በኦሮሚያ እንዳለው አፋን ኦሮሞ ብቻ ይሁን በሚለው ምትክ አፋን ኦሮሞም አማርኛም የሥራ ቋንቋዎች ይሁኑ የሚል ፣ አስማሚ ሐሳብን ነው እያቀረብን ያለነው። የሸዋ ክልል መኖሩ በሸዋ ያሉ ሌሎች ማህበረሰቦችም መብታቸው እንዲጠበቅ ከማድረግ ባሻገር፣ በሸዋ ያለዉን የኦሮሞ ማህበረሰብ የኢኮኖሚንም ጥቅም የሚያስጠበቅ ነው። የሸዋን ጉዳይ ብበዋናነት የሚመለከተው የሸዋ ነዋሪው ነው። እንጂ ከነጆና ከበደኖ የመጡ በሸዋ ጉዳይ ሊወስኑለት አይችሉም።

ህወሃት በስልጣን እስካለ ድረስ የሸዋ ክልል  እንዲኖር ሰለማይፈቅድ የአዲስ አበባን ህዝብ ጨመሮ የሸዋ ህዝብ በወልቃይት ኮሚቴ አቋቁመው ሲንቀሳቀሱ እንደነበሩት ፣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጀመር አለበት። በሕገ መንግስቱ መሰረት ህዝቦች የራሳቸውን ክልል የመመስረት መብት አላቸውና የሸዋ ህዝብም ከኦሮሚያ መዉጣት ከፈለገ ፣ ያ ሙሉ መብቱ መሆኑ መታወቅ አለበት።፡

(ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሮ የተያያዘ አንድ ካርታ አለ። ከአራት መቶ አመታት በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያ የሚያሳዩ ነው። በካርታው እንደምናየው ሸዋ የሚባል አካባቢ መሐል ላይ እናያለን። በምእራብ ወሎም “አምሃራ” የሚባል ቦታም ነበር። ግን በጣም ትንሽ ቦታ ነበር፤ አሁን  አማራ የሚባለው አልነበረም።  ኦሮሚያ የሚባለው አንድ ቦታ አይታይም)