August 4, 2017 16:09

የደርግ መንግሥት የተዋቀረው ከአገሪቷ የተለያዩ መከላከያ፣ ፖሊስና ብሔራዊ ጦር አባላት በተወጣጡ ነበር፡፡ እነኝህ የደርግ አባላት የተመረጡት እጅ በማውጣት ስለነበረ አሰራራቸውም ይህንኑ አካሂድ የሚከተል ነበር፡፡ የህዝብ ሕይወትን የሚያክል ሰዎችን ለመግደልም ሆነ ለማስተዳደር የሚጠቀሙበት መንገድ ሕግና ሥርአትን የተከተለ አልነበረም፡፡ የደርግ መዛግብት እንደሚያመለክቱት ደርግ ብዙ አይነቶች የውሳኔ አሰጣጥ ነበረው፡፡

1. በኮሚቴ ስም በመሰባሰብ ወይም ስብሰባ በመጥራት እጅ በማውጣት ቅፅበታዊ ውሳኔ መስጠት፤ የዚህ አይነት አሰራር በቀይ ሽብር ጊዜ የቀይ ሽብር ኮሚቴ ወይም የአብዮትና ዘመቻ አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም ይሰራበት እንደነበረ ይታወቃል፡፡ አሰራሩ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ደርግ ጽ/ ቤት ድረስ የተለመደ ነበር፡፡ ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የደርግ አባላትን ሰብስቦ 59 የቀድሞ የኃይለሥላሴ መንግሥት ባለስልጣኖችን፣ ሚንስትሮችን፣ ጄኔራሎችንና ሌሎችን የፖለቲካ ውሳኔ በሚል እጅ በማውጣት በድምፅ ብልጫ እንዲረሽኑ አደረገ ፡፡

በዚህ እጅ እየቀሰሩ ድምፅ በተሰጠበት ጊዜ ከድምፅ ሰጭዎቹ ከ50 % በታች አነስተኛ ድምፅ ያገኘ እንዳይገደል የቅድሚያ ስምምነት ሳይደረግ አይቀርም፡፡ ሆኖም የደርግ አባሎች ለሰው ህይወት ደንታ እንደሌላቸው የሚያመለክተው ይህ ተጥሶ አነስተኛ ድምፅ ያገኙት ሌቴናት ጄኔራል በለጠ አበበ ከሌሎች ጋር ተደባልቀው ተገድለዋል፡፡ በጊዜው በስብሰባው የተሳተፉት የደርግ አባላት ጠቅላላ ቁጥር ባይታወቅም የድምፅ አሰጣጡ ላይ ከፍተኛው የእጅ ድምፅ ቁጥር 93 ሲሆን ለሌቴናት ጄኔራል በለጠ አበበ የተሰጠው ድምፅ 45 ነበር፡፡ ለአንባቢዎች ለግንዛቤ እንዲያመች ለአንዳንዶች የተሰጠው ድምፅ እንደ መረጃ ቀጥሎ ቀርቧል፡፡ ለፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሐብተወልድ-93 ድምፅ፣ ለሌቴናት ጄኔራል ከበደ ገብሬ-93 ድምፅ፣ ለሌቴናት ጄኔራል በለጠ አበበ-45፣ ለልጅ እንዳልካቸው መኮንን-77፣ ለኮለኔል ይገዙ ይመኔ-51፣ ለጁ/ኤ ዮሐንስ ፍቱይ-72፣ ለም/አ/አ ተክሌ ኃይሌ-73፣ ወዘተ (ደም ያዘለ ዶሴ)፡፡

ደርግ በስልጣን ሊቆናጠጥ አካባቢ የኃይለሥላሴ መንግሥት እንደወደቀ ከፍ ብሎ የተጠቀሱት ባለሥልጣኖች ታስረው እያሉ የሰሩትን ወንጀል ለማጣራት አንድ ከህብረተሰቡ የተወጣጣ የመርማሪ ኮሚሽን ተቋቋሞ ነበር፡፡ የዚህ ኮሚሽን ሊቀመንበር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረጠው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ነበር፡፡ ይህ ኮሚሽን የምርመራ ሥራውን እያከናወነ እያለ ሳይጨርስ 59 ሰዎች በደርግ ባለሥልጣኖች እጅ በማውጣት መገደላቸው ከፍ ብሎ ቀርቧል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ፕሮፌሰር መስፍን በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ተጠይቆ ምርመራውን አጠናቀው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ሳይደርሱ ብዙዎቹ በጅምላ በመገደላቸው በጣም መበሳጨቱንና በጊዜውም ከሊቀመንበርነቱ እንደለቀቀ ገልጿል፡፡ ምርመራ በሚያካሂዱበት ጊዜ የህግ መስመሩ ከሚፈቅደው ውጭ እንዳይሆንና ተመርማሪዎቹ ያለአግባብ እንዳይጎዱ የምርመራ ኮሚሽን አባል ከነበሩት መካከል ጄኔራል ዓለማየሁ ስዩምና (በዚያን ጊዜ ሻለቃ የነበረ ከክቡር ዘበኛ ሠራዊት የተመረጠ) ሌሎችም ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ እንደነበር መስክሯል፡፡ በተለይ ጄኔራል ዓለማየሁ ስዩም በጣም ጥንቃቄ የተሞላበት አሰራር ይወድ ነበር፡፡

እኔ የዚህ መጣጥፍ ፀሐፊ ጄኔራል ዓለማየሁ ስዩምን በቤተሰብ ግንኙነት በቅርብ አውቀዋለሁ፡፡ በዚህ የተነሳ የፕሮፌሰር መስፍን አባባል አላሰደነቀኝም፡፡ ከጄኔራል ዓለማየሁ ጋር በዚህና በሌሎች ጉዳዮች በተለያየ ጊዜያት ስለተነጋገረበት የፕሮፌሰር መስፍንን ሃሳብ እጋራለሁ፡፡ ምንም እንኳን ከጄኔራል ዓለማየሁ ስዩም ጋር በሕይወት እያለ በፖለቲካ አቋምና በባህርይ ጉዳይ ባንጣጣምም የነበረው ስብእናና ለህግ ተቆርቋሪነት የሚደነቅ እንደነበረ ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡ በደርግ የተረሸኑት ባለሥልጣኖች አግባብነት የሌለውና ሰብአዊ ርህራሄ የጎደለው ስለሆነ አጥብቆ ይቃወም እንደነበር አውቃለሁ፡፡ በምርመራ ኮሚሽን ባገኙት መረጃ መሰረት፣ ደርግ በጅምላ ከገደላቸው መካከል እንዳንዶቹ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ በፈፀሙት የአሰራር ጉድለት ፍርድ ቤት ቀርበው እስር ሊፈረድባቸው ይችል እንደሆነ እንጅ ለሞት የሚዳርግ ወንጀል አልፈፀሙም የሚል ነበር የጄኔራል ዓለማየሁ ስዩም አቋም፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ጄኔራል ዓለማየሁ ስዩም በህግ ባለሙያነቱ ደርግን ለመገልበጥ ኩደታ ለማካሄድ ሞክረው ሲከሽፍባቸው ጦር ፍርድ ቤት ጄኔራሎች ሲቀርቡ ከተሰየሙት ሦስት ዳኞች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም የፍርድ ሂደቱ ሳያለቅ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ውሳኔ አብዛኞቹ ጄኔራሎች ከጄኔራል አብዱላሂ በስተቀር በሞት እንዲቀጡ ሲወሰን የጄኔራል ዓለማየሁን ስሜት የተፈታተነ ነበር፡፡ እነኝህ የተገደሉ ጄኔራሎች በእስራት ሊታለፉ ይገባ ነበር ባይ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ባጋጠመው ሁኔታ በጣም በመበሳጨት ህግ በማይከበርበት አገር የሕግ ባለሙያ በመሆኑ እስከለተ ሞቱ ይፀፅተውና ይናደድ ነበር፡፡

እንግዲህ ወደ ዝምባቤ ከፈረጠጠ በኋላ “እኔ እንኳን ሰው ትንኝም አልገደልኩም” እያለ የሚንቀባረረው ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በዚህ መልክ ነበር የሰው ህይወትን የሚቀጥፈው፡፡ ሌላው ቀርቶ የቀድሞ ባለሥልጣኖች ከየእስር ቤቱ ተሰብስበው ወህኒ ቤት ሲረሸኑ መንግሥቱ ኃይለማርያም በቦታው ተገኝቶ መገደላቸውን አልተመለከተም ወይም አላስፈፀመም ማለት አይቻልም፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም በግድያ በጣም እንደሚያምን የሚያመለክተው እርምጃውን የሚያካሂዱት ገዳዮች እንዲነቃቁና ለመግደል እንዲተጉ ለመገፋፋት ሶደሬና ላንጋኖ ሄደው እንዲዝናኑ ያደርግ ነበር፡፡ የተገደሉት አፈር ሳይለብሱ አንቆ ገዳዮቹ ግዳይ እየጣሉ ይዝናኑ እንደነበር አንድ በጊዜው በግድያ ላይ ይሳተፍ የነበረ ግለሰብ ምስክርነት እንደሰጠ በደም ያዘለ ዶሴ ውስጥ ሰፍሯል፡፡ በደርግ የተወረሰው የልዑል አሥራተ ካሣ መኖሪያ ቤት የግድያ ቦታ፣ የደርግ ባለሥልጣኖች መዝናኛ ቦታ፣ የተገደሉ ሰዎች የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን የሚታይበት ቦታ ነበር፡፡

ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ እነ ጄኔራል አይኔን ሲገድል “ማዕረጋቸውን ከትከሻቸው ላይ እየገነጠልንና ቂጣቸውን በሳንጃ እየወጋን አስወገድናቸው” እንዳላለ ዝምባቤ ሲደርስ “እንኳን ሰው ዝንብም” አልገደልኩም አለ መባሉ ያስደንቃል፡፡ ምን ያድርግ የፈጀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሱ ከዝንብም አይቆጠርም፡፡

2. የሰነድ ላይ ውሳኔ፣ ይኸ ደግሞ በደርግ ጽ/ቤት፣ በማዕከላዊና በሌሎች የምርመራ ቦታዎች እስረኞችን በድብደባና በተለያዩ መንገዶች እያሰቃዩ ቃላቸውን ተቀብለው መግለጫ አውጥተው ለበላይ በለሥልጣን አስፈላጊው ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚቀርብ ሰነድ ነበር፡፡ ወሳኞቹ አገሌ የሰጠው ቃል የሚለውን ከማየት በስተቀር በስም የተጠቀሰው ሰው ማን እንደሆነ አያውቁም፤ ቃሉን የሰጠው ተገዶ ይሁን ወዶ አይመለከታቸውም፤ መርማሪው ካሰፈረው በስተቀር የሰውዬው እድሜ ሕፃን ይሁን አዋቂ አያውቁም፡፡ በስም የቀረበላቸው ሰነድ ላይ የደርጉ ዋና ፀሐፊና ረዳት ፀሐፊ ሻምበል ፍቅረሥላሳ ወግደረስና ኮለኔል ፍሥሐ ደስታ የሚሰጡት ውሳኔ የሰው ሕይወትን መግደልና የወደዱትንም ማዳን ነበር፡፡ የዚህ የወረቀት ወይም የሰነድ ላይ ውሳኔ ከበላያቸው ከኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ከበታቾቻቸውና በጎንዮሽ ካሉት የቀይሽብር አረማጆች እነ ሻምበል ለገሰ አስፋው፣ ኮ/ካሣሁን ታፈሰ፣ ኮ/ተካ ቱሉ፣ወዘተ ጋር በመመካከር የሚቀባበሉት ውሳኔ ነበር፡፡ በወረቀት ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች በጣም በርከት ያሉ ናቸው፡፡

ይህንን ውሳኔ ሰጭዎች በዋነኛነት ሻምበል ፍቅረሥላሴና ኮለኔል ፍሽሐ ደስታ ነበሩ ብለናል፡፡ ከብዙዎቹ ውሳኔዎች መካከል ጥቂቶቹ ለመረጃነት እዚህ ላይ ተጠቅሰዋል፡፡ ሀ) ሻምበል ፍቅረሥላሴ እንዲገደሉ ከወሰነባቸው መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

1. አቡነ ቴዎፍሎስ ወልደማርም
2. ቄስ ጉዲና ቱምሳ
3.አቶ ስይፈ ማህተመሥላሴ
4.ደጃዝማች ካሣ ወልደ ማርያም
5.ደጃዝማች ሐረጎት አባይ
6.አቶ አስፋ ድፋዬ
7.አቶ አበበ ከበደ
8.ፊተውራሪ ክፍሌ እንቁሥላሴ
9.ጄኔራል ሳሙኤል በየነ
10.ዶ/ር ሃይሌ ፊዳ
11.ዶ/ር ንግሥት አዳነ
12.አቶ ደስታ ታደሰ
13.ወ/ት ቆንጅት ከበደ
14.አቶ ኃይሉ ገርባባ

ለ) ኮለኔል ፍሥሐ “ለመቀጣጪያ” በሚል እንዲገደሉ የወሰነባቸው የኢሕአፓ ሊግ አመራሮችና ሌሌችም የዚሁ የወረቀት ላይ ውሳኔዎች ሰለባዎቸች ናቸው፡፡ በጣም የሚገርመው ኮለኔል ፍሥሐ የአስራ አንድ ሰዎች ስም ሲቀርብለት አንድ ከመታሰሩ በፊት አንጃ የነበረን በማስቀረት የሚከተሉት አስር ወጣቶች እንዲገደሉ ይወስናል፡፡

1.ቲቶ ህሩይ
2.ዓለማየሁ እግዜሩ
3.ባዩ ስዩም
4.ሃብተሥላሴ ይባስ
5.መዝገቡ ከበደ
6.ሜሮን አሰፋ
7.ሲራክ ተፈራ
8.መኮንን ባይሳ
9.ገበየሁ ዳኘው
10.ሙኸዲን ኡመር

ሐ)አንድ ኡመር መሐመድ የሚባል በኢሕአፓ አባልነት የተጠረጠረ ከሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ ከአላባ ወረዳ ደርግ ጽ/ቤት ድረስ ለግድያ ውሳኔ መዝገቡ ተልኮ ኮለኔል ፍሥሐ ደስታ የሰጠው ውሳኔ ልክ እንደ መዝገቡ አመጣጥ የአስተዳደር እርከኑን ተከትሎ ተመልሶ የግድያ እርምጃ ተወስዶበታል፡፡ በጣም የሚገርመው አንድ ወጣት ለመግደል የዚህ መሰል ከታች ወደላይ ከላይ ወደታች የሰነድ ልውውጥ መደረጉ ነው፡፡

3. አልፎ ሂያጅ ወይም ተዘዋዋሪ ውሳኔ ሰጭዎች፣ እነኝህ ደግሞ ከማዕከላዊ መንግሥት ወደየአካባቢው ተልከው የአካባቢው ፖሊስና የቀይ ሽብር አራማጆች ያጣሩትን የመጨረሻ የግድያ ውሳኔ የሚሠጡ በድርጊቱ የተራቀቁ ታማኞች ነበሩ፡፡ ከእነኝህ መካከል የሰላሌን ወጣት የፈጀው አ/አለቃ መሰለ ገብሬ በግንበር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ የጎንደሩ ሻለቃ መላኩ ተፈራና የደቡቡ ሻለቃ አሊ ሙሳም በራሳቸው ስልጣን ባለፉበት ቦታ ሁሉ የትም (on the spot) ሰዎች እንዲገደሉ ውሳኔ ይሰጡ ነበር፡፡ ደብረማርቆስና ጎጃም የነበረው ጨፍጫፊ መ/አለቃ እሸቱ ዓለሙና በአዋሳ ሕዝብን የጨረሰው መ/አለቃ ጴጥሮስ ገብሬም እንደዚሁ በተዘዋወሩበት ቦታዎች ሁሉ ውሳኔ በመሰጠት ይታወቃሉ፡፡

4. የሚስጥር ውሳኔና ግድያ፣ አፄ ኃይለሥላሴ ከሥልጣን እንደተወገዱ ውጭ አገር ገንዘብ ደብቀዋል በሚል ከደርግ ጋር አታካሪ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ በተለይ እስር ላይ አያሉ ገንዘቡን ለማስመለስ ከደርግ እንዲተባበሩ ተጠይቀው ገንዘብ ባለመገኘቱ በመንግሥቱ ኃለማርያም ትዕዛዝ በኮለኔል ዳንኤል አስፋው ፈፃሚነት በሚስጥር ታንቀው እንዲገደሉና ታላቁ ቤተ መንግሥት ኮለኔል መንግሥቱ ቢሮ ስር በሚስጥር እንዲቀበሩ ተደርጓል፡፡

5. በመደበኛና በጦር ፍርድ ቤት የሚሰጡ ውሳኔዎች፣ ምንም እንኳን በፍርድ አሳጣጡ ደርግ ባይደሰትም የእጅ ከፍንጅ መረጃ የያዘባቸውን የፖለቲካ እስረኞች በፍርድ ቤት ውሳኔ ያስቀጣበትም ጊዜ ነበር፡፡ ከሻሸመኔ ንግድ ባንክ ገንዘብ ከወሰዱት የኢሕአፓ አባላት መካከል ጀማል፣ መስፍንና ሌሎች አባሪዎቻቸው ፍርድ ቤት ቀርበው ከአነስተኛ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ተወስኖባቸው በይግባኝ ተቀንሶላቸዋል፡፡

ከመደበኛው ፍርድ ቤት ሌላ የካንጋሮ የውሸት ፍርድ ቤትም ያካሄድ ነበር፡፡ በውሸት ጦር ፍርድ ቤት እንደቀረበ አስመስሎ መግደልም ነበር ማለት ነው፡፡ ብርሃነ መስቀል ረዳ አንድም ጊዜ ጦር ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በጦር ፍርድ ቤት እንደተወሰነበት በማስመሰል የህዝብ ጠላት በሚል በርዕሰ ብሔር፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም ፀደቀ በሚል በኮለኔል ፍሥሐ ደስታ ውሳኔ ተገድሏል፡፡ የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሜቴ አባል የነበረው ፍቅሬ ዘርጋውም የተገደለው በዚሁ ጊዜ በኮለኔል ፍሥሐ ደስታ ውሳኔ ፊርማ ነበር፡፡ ከወታደራዊው ክፍል የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ያደረጉት ጄኔራሎች ጦር ፍርድ ቤት ለስም ያክል ቀርበው የፍርድ ሂደቱ ሳይጠናቀቅ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ትዕዛዝ እንደተገደሉ ከፍ ብሎ ተጠቅሷል፡፡

6. ለምሳ ሲያስቡን ቁርስ አደረግናቸው፣ ይህ ደግሞ መንግሥቱ ኃይለማርያም አብረውት ሲሰሩ የነበሩትን የደርግ አባላት የፖለቲካ ልዩነትና የስልጣን ሽኩቻ ሲያጋጥመው ፈጣን በሆነ ዘዴ ቀድሞ የሚገድሉበት መንገድ ነበር፡፡ በተለመደው የደርግ አሰራርና ስብሰባ ስበብ መሳሪያና ትጥቅ በማስፈታት አንድ ላይ ሰብስቦ የሚፈፀም ግድያ ነበር፡፡ በዚህ የሥልጣን ሽኩቻ ከተገደሉት መካከል፣

ሀ) ጄኔራል ተፈሪ በንቲ

ለ) ጄኔራል አማን አንዶም በተኩስ ልውውጥ እራሱን የገደለ

ሐ) ሻ/ ሞገስ ወልደሚካኤል

መ) ሻ/ ዓለማየሁ ኃይሌ

ሠ) ሌ/ኮ/ አስራት ደስታ

ረ) ሌ/ኮ/ ሕሩይ ወልደ ሥላሴ

ሰ) ሻ/ ተፈራ ደነቀ

ሸ) አ/አለቃ ኃይሉ በላይ

እዚህ ዝርዝር ውስጥ መፈንቅለ ደርግ ሊያካሂዱ ነበር በሚል በ1968 መጨረሻ የተገደሉትን እነ ሻለቃ ሲሳይ ሃብቴና 20 አባሪዎቻቸውን ማካተት ይገባል፡፡ ከዚያም ጥቅምት 17 ቀን፣ 1969 ዓ.ም. የመኢሶን አባል የነበረውን ዶ/ር ፍቅሬ መረእድን ሞት ተከተሎ 34 የኢህአፓ ደጋፊዎች ከማዕከላዊ ተወስደው ተገደሉ፣ በነሱም ቀይ ሽብር ተጀመረ፡፡

ደርግ በማዕክል ሲፈፅም የነበረውን አይነት በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ቦታዎች የሚያስፈፅሙ የሱ ፎቶ ኮፒ የሆኑ ሌሎች መንግሥቱ ኃይለማርያሞች በብዛት ነበሩ፡፡

7. በመገኛኛ ብዙሐን እየፈከሩ መግደል፡ በቆየው የአገራችን ልምድ መሰረት ገዳይ የሚያቅራራውና ግዳይ የሚጥለው ፊት ለፊት ገጥሞ ጦርነት ካካሄደ ወይም በአደን ጊዜ አንበሳና ዝሆን ከገደለ በኋላ ነው፡፡ ደርግ ግን በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ሰዎች ለመግደል አካኪ ዘራፍ እያለ በታወቁ የአገራችን ዘፋኖችና ሸለላዎች እየታጀበ ያቅራራ ነበር፡፡ በተለይም “የፍየል ወጠጤ… የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች” የሚለው ዜማ ለሱ መደንፊያው ሲሆን ለሕዝቡ ደግሞ መርዶ መንገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ይህ የሚያመለክተው ደርግ ምን ያክል ፈሪና ወኔ ቢስ ደንፊ እንደነበረ ነው፡፡ የደርግ ግንባር ቀደም መሪ የነበረው ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም “አንድ አራሴ እስክቀር እዋጋለሁ” እያለ ሲደነፋ እንዳልነበረ ቀውጢ ቀን ሲመጣ እራሱን ለማዳን ወደ ዝንባቤ መፈርጠጡ ወኔ የከዳው መሆኑን ያመለክታል፡፡ በጠቕላላው የደርግ መንግሥት አመራሮች ከወታደሩ ክፍል ሳይሆን ከየት እንደመጡ አይታወቅም፡፡ እነሱ ደንፊና ፈሪ ሆነው የኢትዮጵያን ጀግኖች ወታደሮች ሽሽት አስተማሯቸው፡፡ ይህንን ሲሰሩ የኖሩት የደርግ ባለሥላጣኖች አሁን ደግሞ የብዕር አርበኞች ሆነው የተለያዩ የውሸት መፅሐፍት እየፃፉ ይደነፉብናል፡፡

“ግንቦቴዎች” ምንድን ናቸው?

ማንም የኢሕአፓን ታሪክ የሚመረምር ግለሰብ በድርጅቱ ውስጥ የተከሰተውን መከፋፈልና አንጃ መፈጠር ይገነዘባል፡፡ ነገር ግን “ግንቦቴዎች” እነማን እንደሆኑ፣ እንዴት እንደተነሱና ከአንጃው ጋር ያላቸው ትስስር ምን እንደነበረ ላይረዳ ይችላል፡፡ ባጭሩ ለመግለጥ “ግንቦቴዎች” የአዲስ አበባ ወህኒ ቤት አተራማሾች ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ ወህኔ ቤት የነበሩትን የኢሕአፓ እስረኞች እንዲሰልሉና እንዲያጋልጡ በ1970 ዓ.ም. በሚያዝያና ግንቦት ወራት ሻለቃ ብርሃኑ ከበደ ከመገደሉ ቀደም ብሎ የመለመላቸው የቀድሞ ኢሕአፓዎች ወይም አንጃዎች ናቸው፡፡

የታሰሩ የኢሕአፓ አባላትን “አጋልጥ፣ ተጋለጥ” እያሉ እስረኛውን የሚያተራምሱ አንደነበሩ በጊዜው አዲስ አበባ ወህኒ ቤት የነበሩ እስረኞች ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ደርግ በከተማና በገጠር የነበረውን የኢሕአፓ መዋቅር ካፈራረሰ በኋላ ወህኒ ቤት እራሳቸውን ደብቀው ያልተጋለጡትን ለመለየት የተጠቀመበት ዘዴ እንደነበረ” የግንቦቴዎች” ድርጊት ያመለክታል፡፡ በዚህ የተነሳ እነኝህ ከደርግ ጋር በመወገን በእስር ቤት ሲያተራምሱ የነበሩት ኢሕአፓዎች ወህኒ ቤት በነበሩት ሌሎች እስረኞች ወቅቱንና ድርጊቱን በማስታወስ “ግንቦቴዎች” የሚል ስም አወጡላቸው፡፡ “ግንቦቴዎች” በፊት የኢሕአፓ አባል ስለነበሩና ውስጥ አዋቂም ስለሆኑ በወህኒ ቤቱ እስረኞች በጣም የሚፈሩና የሚጠሉ ነበሩ፡፡ ከመካከላቸው የአንጃውን አቋም የሚያራምዱ ወይም በእስር ጊዜ ከተጋለጡ በኋላ ጭልጥ ብለው በደርግ ወገን የቆሙ ነበሩባቸው፡፡

የወዝ ሊግ ከደርግ ጋር በፈጠረው ልዩነት ሻለቃ ብርሃኑ ከተገደለ በኋላ ደርግ “ግንቦቴዎችን” ይጠቀምባቸው አይጠቀምባቸው ግልፅ አይደለም፡፡ “ግንቦቴዎችን” በመፍራት ሲበረግጉ የነበሩት ሌሎች እስረኞች በተለይ የእስሩን ሰቆቃና ግርፋት ተቋቁመው የድርጅታቸውን ሚስጥር በመጠበቅ ቀደም ብለው ቀይ ሽብር በይፋ ከመጀመሩ በፊትና በኋላም በቀይ ሽብር ጊዜ የታሰሩት ነበሩ፡፡ “ግንቦቴዎችም” ትኩረታቸው አክራሪ የኢሕአፓ ደጋፊዎች በሚሏቸው ላይ ነበር፡፡

“ግንቦቴዎች” የራሳቸውን ግንኙነትና መዋቅር ፈጥረው ሌሎችን ሰው በሰውና በጓደኝነት አንዳንድ ጊዜም በማስፈራራት በመቅረብ “ኢሕአፓ ስለተደመሰሰ እራሳችሁን በማጋለጥ አብዮቱን ተቀላቀሉ” በሚል የሚሰብኩ ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ የሚኖሩት በቀጠሮ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ ቤቶች ነበር፡፡ ጎላ ብለው ከሚታወቁት መካከል አንድ ከመታሰሩ በፊት የሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ የነበረ ሲሆን ሌላው ደግሞ በፓርቲው ውስጥ የነበረ ሲሆን በታሰረበት ጊዜ በአዲስ አበባ በዞን ሁለት የማይታወቁና የማይጠረጠሩ የፓርቲ አባላትን ሳይቀር ያጋለጠ ግለሰብ ነው (የክፍሉ ታደሰ፣ ያ ትውልድ የሚለው መፅሐፍ)፡፡ የሊግ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረው ከመታሰሩ በፊት ከጌታቸው ማሩ ጋር የተሳሰረ አንጃ ስለነበር ከኮሜቴ አሰራር ተገልሎ በነጠላ ግንኙነት እንዲቆይ ተደርጎ ነበር (የኢሕአፓ የወጣት ሊግ አባላት ለማዕከላዊ ምርመራ የሰጡት ቃል)፡፡

በአንጃነቱ የተነሳ ኮለኔል ፍሥሐ ደስታ አስር የኢሕአፓ የሊግ አመራር ወጣቶችና ሌሎች በሌላ የአመራር እርከን የነበሩ ወጣቶችን “ለመቀጣጪያ” በሚል እንዲገደሉ ሲወስን እሱን ግን የደርግ ተባባሪ ነው በሚል ሕይወቱ ሊድን ችሏል፡፡ ወህኒ ቤት ከደረሰ በኋላ ግንባር ቀደም “ግንቦቴና” አተራማሽ ሆነ፡፡ ሌላው የፓርቲ አባል የተባለው ታዋቂ ምሁር ሲሆን “ከግንቦቴነት” በተጨማሪ በቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ የኢሕአፓ የጥቃት መከላከያ እስኳዶች በድርጅቱ በገንዘብ ተገዝተው የሚገሉ ናቸው በሚል የሀሰት መግለጫ የሰጠ ነበር (የዚህ መጣጥፍ ፀሐፊ ከመታሰሩ በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተመለከተው መረጃ)፡፡ ከእነኝህ ከሁለቱ የማይተናነሱ ሌሎች አንጃ የነበሩ “ግንቦቴዎችም” በእስር ቤቱ በርከት ያሉ ይገኙ ነበር፡፡

“ግንቦቴዎች” ሌሎች እስረኞችን እየቀረቡ፣ “ኢሕአፓ ፈረሷል”፣ “ቀይ ሽብርም ቆሟል” “የሰጠኸው ቃል የሚያጠራጥር መሆኑን ደርሰንበታል”፣ “ለምን ራስክን በትክክል አጋልጠህ ህይወትክን አታድንም “፣ “ለምን የምትታወቅበት ከፍተኛ ሄደህ ራስክን አጋልጠህ አትፈታም”፣ ወዘተ በማለት ያደናግሩ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ከኢሕአፓ ጋር ንክኪ ያለው ማንኛውም እስረኛ ማንነቱን እንዳይታወቅበት ለመደበቅ ይጠነቀቅ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ስሙ እንኳን እንዳይታወቅ ይጣጣር ነበር፡፡ አንድ በዚያን ጊዜ ወህኒ ቤት የነበረ እስረኛ “ከግንቦቴዎች” መካከል አንዱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያውቀው “የፖለቲካ እስረኛ ነህ ብሎ ሲጠይቀው” “የለም እኔ የታሰርኩት በገንዘብ ማጉደል ነው” ብሎ እንደሸወደው አጫውቶኛል፡፡

በርከት ያሉ አስረኞች ከእነኝህ “ግንቦቴዎች” ግፊት ለማምለጥ ቢጥሩም አንዳንዶች በመታለል ወደየከፍተኞቻቸው በመሄድ የቀናቸው ሲፈቱ የተወሰኑት ደግሞ የቀይ ሽብር ሰለባ ሆነዋል፡፡ በተለያዩ ከፍተኞች የሚገኙት የቀይ ሽብር አራማጆችና የከፍተኛ ሊቀመናብርትም በከርቸሌ የነበሩትን 4300 የፖለቲካ እስረኞች እንደገና ወደየከፍተኞቻቸው ተልከው ጉዳያቸው በድጋሚ በደንብ እንዲጣራ በስብሰባ ወስነው ለመቀራመት አቆብቁበው ነበር (ደም ያዘለ ዶሴ)፡፡ ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት የከፍተኛና የቀበሌ የአብዮት ጥበቃ ሊቀመናብርት በብሔራ ሸንጎ በ13/8/70 ባደረጉት ስብሰባ ላይ ነበር፡፡ ጥያቄው እንዲቀርብ ያነሳሱትና ግፊት ያደረጉት የቀይ ሽብር አምላኪዎች የሆኑት ዶ/ር አለሙ አበበና ኮለኔል ተካ ቱሉ ነበሩ፡፡ እንዲያውም ኮለኔል ተካ ቱሉ ማንኛውም የሚገደል የኢሕአፓ አባል በደንብ ተመዝግቦ እንዲቀመጥና አንደም እንዳያመልጥ አስገንዝቧል፡፡ ለወደፊቱ ኢሕአፓ እንዳያንሰራራ ከሚታወቁት አባላቱ መካከል እንማን እንደሞቱ መታወቅ አለበት የሚል መመሪያ ሰጥቷል፡፡

የአቶ ክፍሉ ታደሰን መፃሕፍት ከሌሎች መረጃዎች ጋር ስናነፃፅር የሚነሱ ጥያቄዎች

የኢሕአፓ አመራር የነበረው አቶ ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ”በሚል በፃፈው ተከታታይ መፃሕፍት ውስጥ በርከት ያሉ በየጊዜው የምናነሳቸው በእንጥልጥል የቆሙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አጋጥመውናል፡፡ ያንን እያሰላሰልን እያለን ሌላ ተጨማሪ መፅሐፍ እንዳቀረበ ተረዳን፡፡ አዲሱን መፅሐፍ በመጠኑ ተመልክቸዋለሁ፤ በደንብ ግን አልመረመርኩትም፡፡ ከአንዳንድ ተጨማሪ ማብራሪያና ሌሎች በኢሕአፓ ላይ በተዛባ ያቀረቡትን ከማስተባበል በስተቀር ካለፈው ብዙም እንደማይለይ ተረድቻለሁ፡፡ በአንዳንድ ጋዜጦችም ላይ የተሰጠውን አጫጭር ግምገማዎች ተከታትያለሁ፡፡ በበኩሌ ከበፊት ጀምሮ እየተንከባለሉ በመጡት እንዳንድ ቅሬታዎችና ግድፈቶች ላይ በመንተራስ ያለኝን ሃሳብ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

የወጣት ሊግ አመራሮች አሰራር ለምን ወደ ገጠር እንዲዛወር አልተደረገም?

አቶ ክፍሉ ወደ ጎንደር ሲጓዙ ለምን የወጣት ሊግ አመራሮች ወደ ገጥር እንዲዛወር ተደርጎ እራሱን እንዲያድን አልተደረገም? እነኛ ሳተና የነበሩ የሊግ አመራር ወጣቶች ደርግ እጅ ከወደቁ በኋላ የሰጡትን ቃል ከአቶ ክፍሉ መፅሐፍ ጋር ስናነፃፅር የነሱን ህይወትና የድርጅቱን መፈራረስ አቶ ክፍሉ ለማዳን ሳይሞክር በ1970 ዓ.ም. ወደ ጎንደር ተጉዟል፡፡ በተለይ የቲቶ ቃል እንደሚመሰክረው የፓርቲ አመራር ሰጪው አቶ ክፍሉና ቲቶ ከመስከረም 1970 ዓ.ም. በኋላ አልተገናኙም፡፡ ሙኸዲን ኡመር (በፊት የሊግ አመራር የነበረ በኋላ የአዲስ አበባ በይነ ቀጠና አመራር የሆነ)፣ አባተ በሚል የኮድ ስም ሲገናኝ የነበረው፣ (ምናልባት ዜና እንደሚለው ሌላው የኮድ ስም የአቶ ክፍሉ ታደሰ ሌላው የኮድ ስም እንደሆነ እጠረጥራለሁ) እራሱ ክፍሉ ታደሰ በፃፈው መሰረት ሲያዝ ከላይ የአዲስ አበባ ፓርቲ ኮሜቴን የሚመራ አልነበረም ማለቱ ምናልባት እንደ ሊጉ የአዲስ አበባ በይነቀጠናም ከግንኙነት ውጭ ሳይሆን አይቀርም ያሰኛል፡፡

ነገር ግን ሊጉና የአዲስ አበባበይነ ቀጠና ለዚህ ባይታደሉም የፓርቲውን Secretariat (የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት) ወደ ጎንደር ለማዛወር ስለተወሰነ አቶ ክፍሉ Sub-Secretariat ለነበሩት እነ መኮንን ባይሳ፣ ከድር መሐመድ፣ ወዘተ አዲስ የስራ ኃላፊነት በመስጠት ወደ ተለያዩ ክፍለ አገራት ሄደው እንዲያደራጁ መመሪያ እንደሰጠ የመኮንን ባይሳ ቃል ያረጋግጣል፡፡ምንም እንኳን ታአማኒነት ቢጎድለውም ህይወት ተፈራ “Tower in the  sky”  በሚል እንደፃፈችው ወደ ደቡብ የሄደችው በመኮንን ባይሳ Sub- Secretariat ስር በመሆን ነበር፡፡ የህይወት ተፈራን መፅሐፍ የምጠራጠረው አንድ ሰው በአንድ ጊዜ እንዴት ለሁለት ሰዎች፣ ለኢሕአፓ ድርጅትና ለፍቅረኛዋ፣ እኩል ታማኝ ትሆናለች በሚል መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡

በጊዜው በአዲስ አበባ አመራር የሚሰጡት አቶ ክፍሉ ታደሰና ሌሎች በሌላ ቦታዎች የነበሩት የፕርቲው አመራሮች ያልተገነዘቡት የወጣቱ ሊግ፣ የአዲስ አበባ በይነ ቀጠናና ሌሎች የፓርቲው ብዙሐን ድርጅቶች ውሃ ላይ እየሰመጡ ያሉ ከአንድ የበረዶ ክምር የተገመሱ በበረዶ ኳስ የሚሰየሙ ነበሩ፡፡ የበረዶው ኳስ ውሃ ውስጥ እየሟሟ ሲያልቅ የበረዶው ክምር ይድናል ማለት ዘበት ነው፡፡ ያጋጠመውም ይኸው ነበር፡፡ ሌላው ከአንጃው ጋር የነበረው ትግል በአንድ ሰውነት ላይ እንዳጋጠመ የቁስል “ጋንግሪን” የሚታይ ነው፡፡ “ጋንግሪኑ” በአግባብ ካልተወገደ ወይም ካልተቆረጠ ዋናውን ሰውነት አሰልስሎ ይጨርሰዋል፡፡ ለዚህም ነው በጥቂት ሰዎች የተፈጠረው ልዩነት ፓርቲው እበቀለበት ቦታ ሁሉ እንደ “ጋንግሪን” በልቶ የጨረሰው፡፡

ለማንኛውም ለአንባቢ ግልፅ ለማድረግ አቶ ክፍሉ ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር ተጓዝኩ የሚለው ጥቅምት መጨረሻ ወይም ህዳር 1970 ዓ.ም. ሲሆን የኢሕአፓ ወጣት ሊግ አመራሮችና ሌሎች በሌላ የአመራር እርከን ላይ የነበሩ ወጣቶች የተያዙበትና የተገደሉበት ቀን ለማመሳከር እንዲያመች እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

ተራ ቁጥር                ስም                            የተያዘበት ቀን                 የተገደለበት ዓ.ም.
1                 ቲቶ ህሩይ (የሊግ አመራር)         19/3/70                         1971
2                 ዓለማየሁ እግዜሩ                    18/3/70                          1971
3                 ባዩ ስዩም                               17/3/70                          1971
4                  ሃብተሥላሴ ይባስ                    20/3/70                         1971
5                   መዝገቡ ከበደ                        16/3/70                          1971

6                  ሜሮን አሰፋ                             2/3/70                          1971
7                 ሲራክ ተፈራ                               6/6/70                         1971
8              መኮንን ባይሳ (ሳብ ሴክረተሪየት)       8/6/70                          1971
9                  ገበየሁ ዳኘው                              3/5/70                        1971
10          ሙኸዲን ኡመር (አአ ኢንተር ዞን)          1/5/70                        1971
11                           ?                          7/8/69 ወይም 7/8.70         አልተገደለም

ምንጭ፣ 1. ከማእከላዊ ምርመራ የተገኘ ሰነድ፡፡

2. ደም ያዘለ ዶሴ፣ ገፅ 281:: የእነኝህ 11 ወጣቶች ስም ዝርዝር ለውሳኔ ኮለኔል ፍሥሐ ደስታ (የዚያን ጊዜ ሻለቃ) ሲቀርብለት “ለመቀጣጪያ” በሚል ከ1-10 ያሉት እንዲገደሉ ይወስናል፡፡ ምንም የታወቀ ቢሆንም በ11ኛ የተጠቀሰውን ስሙን ያላስገባሁት ውሳኔው ለየት ስለሚል ነው፡፡ 11ኛው ተከሳሽ ከመታሰሩ በፊት አንጃ በመሆኑ የደርግ ደጋፊ በሚል ህይወቱ ተርፎ ብዙ ጊዜ ታስሮ ተፈቷል፡፡ አንጃም እንደነበረ የመሰከሩለትና ሕይወቱን ያዳኑትና ከጌታቸው ማሩ ጋር የሚገኛኝ እንጃ እንደነበረ ያረጋገጡት እነ ቲቶ ነበሩ፡፡ በዚህ መልክ ህይወቱ የዳነው ከርቸሌ ታስሮ የታወቀ የደርግ ደጋፊና ሌሎችን የሚያስገድል ዋናው “ግንቦቴ” ሆኖ አረፈው፡፡

3. ዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ፣ 1987 ዓ.ም.

ከፍ ብሎ የቀረበው የወጣት ሊግ አመራሮች በምን ጊዜ በደርግ እንደተያዙና እንደተገደሉ ለማስታወስ ነው እንጅ በተመሳሳይ ጊዜ ሌሎች በ1971 ዓ.ም. የተገደሉ በርከት ያሉ ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የተገደሉት አብዛኞቹ የጥቃት መከላከያ እስኳዶች ናቸው፡፡ ደርግ ከዋናው ምንም ምርጫ ካልነበረው የ1970 ዓ.ም. የቀይ ሽብር ጭፍጨፋ በኋላ፣ ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ ሲገድል የነበረው የአመራርና የትጥቅ ትግል ተሳትፎአቸውን እያመዛዘነ ነበር፡፡

በጊዜው አዲስ አበባ ያለቀውን የወጣትና የፓርቲ አባላት ህይወቱን ለማዳን ምንም ሙከራ አለመደረጉ ፓርቲውንና በተለይ አዲስ አበባ አመራር ሲሰጥ የነበረውን አቶ ክፍሉ ታደሰን ያስጠይቃቸዋል፡፡ የሊግ አመራር ወጣቶችን ቃል ስንመረምር በዚያን ጊዜ ፓርቲው ግፋ በለው ከሚል የሚከተሉትን ሦስት የነፍስ አድን እርምጃዎች ከመስከረም 1970ዓ.ም. በኋላ ወስዶ ቢሆን የብዙ አባላትን ህይወት ማዳን ይቻል ነበር በሚል ስንገምት ከተሳሳትን እንታረማለን፡፡ በጊዜው ሌላ የተሞከረም እርምጃም ካለ አቶ ክፍሉ ሳይደብቅ ይግለፅልን፡፡ በጠቅላላው የሚከተሉት ሦስት እርምጃዎች አስፈላጊ ነበሩ እንላለን፡፡

  1. እንደ የፓርቲው አመራር ሁሉ የወጣት ሊግ አመራሩን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ወደሌላ ቦታ ለማዛወር መመከር፡፡

      2. ደርግን መቋቋም ስላልተቻለ ራስን ለመከላከል በሚል ሲካሄድ የነበረውን የትጥቅ ትግል ከ1970 ዓ.ም.

መጀመሪያ በኋላ ማቋረጥና (Call off urban armed struggle and cease hostilities) ለምን እንደተቋረጠ ሰፊ የቅስቀሳ ስራ ማካሄድ፡፡ በዚህ አቋም ከደርግ የሚሰነዘረውን እርምጃ መግታት ባይቻል እንኳን ጨፍጫፊ መሆኑን የበለጠ ማጋለጥ ይቻል ነበር፡፡ ከአንጃውም ጋር የነበረውን ግብግብ ለማቆም ይረዳ ነበር፡፡ በተለይ የመርሃቤቴው ማፈግፈጊያ በብርሃነ መስቀል ረዳ ከተቀማና የሲዳሞውም ሳያሳካ ከቀረ በኋላ ያለው አማራጭ ይኸው ብቻ ነበር.፡፡

      3. አቶ ክፍሉ ታደሰ በመፅሐፉ እንደሚለው ሊጉና የፓርቲው መዋቅሮች እስከ ታህሳስ 1970 ዓ.ም. (end of 1977)ከነበሩ ከአንጃውና ከደርግ የሚሰነዘረውን ትንኮሳ ለመቋቋም በአጣዳፊ የፓርቲውን፣ የሊጉንና ሌሎች አጋር ዴሞክራቲክ ድርጅቶች መዋቅሮች መቀያዬርና መፐወዝ (Restructuring) ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ
እርምጃ በተራ ቁጥር 2. የተወሰደው እርምጃ የታሰበለትን ግብ ባይመታ እንኳን ለተጨማሪ መከላካያነት ይረዳል፡፡
እነንህን ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን ድርጅቱ ከአንጃው ጋር በነበረው መቆራቆስና መጠላለፍ፣ አንዳንድ አባላቱ በደርግ ደህንነት ሲጋለጡና በአሰሳም ጊዜ ህይወት ለማዳን ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ነገር ግን ከቀይ ሽብር አባላቱን ለመታደግ ይሞከሩ አይሞከሩ ግልፅ አይደለም፡፡ በአቶ ክፍሉ መፅሐፍ ውስጥ አንጃው ባነሳው ጥያቄ የተነሳ በአባላት መካከል እርስ በእርስ መጠራጠርና አለመተማመን እንደተፈጠረ ተጠቅሷል፡፡ እኔም በእስር ላይ አብረውኝ ተሰቃተው ስለሞቱት ጓደኞቸ በመቆርቆር እንጅ ይህንን ሃሳብ የማነሳው የአንጃውን መስመር የማንፀባርቅ ሆኘ አይደለም፡፡

ተሻለ ፍርዴ፣ አዲስ አበባ፣ 2009 ዓ.ም.