Wednesday, 09 August 2017 12:22

ኤሁድ ኦልመርት የቀድሞ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። ኦልመርት የእስራኤል አስራ ሁለተኛ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን እ... 2006 እስከ 2009 እንዲሁም ከ1993 እስከ 2003 የእየሩሳሌም ከንቲባ በመሆን አገልግለዋል። የህግ ባለሙያ እና ፖለቲከኛም ናቸው።

ኦልመርት በስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ የእስራኤል እና የፍልስጤም የሰላም ድርድርን ማዕቀፍ፤ ከጦረኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ወደ ሰላማዊ የድርድር መድረክ መቀየር መቻላቸው በስፋት ይነገርላቸዋል። ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ጉቦ በመቀበል እና የሕግ ምርመራን አስተጓጉለዋል ተብለው በቀረበባቸው ክስ መነሻ፣ ጥፋተኛ ተብለው ወደ ማረሚያ ቤት ወርደዋል። የጥፋተኝነት ውሳኔው የተደመጠው በ28 ቀን አፕሪል 2014 ነበር።  በሜይ 13 ቀን 2014፣ የስድስት ዓመት እስራት እና 290ሺ የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።

ኦልማርት በ1980ዎቹ ነበር፤ በሙስና የተጠረጠሩት። ለበርካታ ጊዜያት በሙስና ተወንጅለው በፖሊስ ምርመራ ተደርጓባቸዋል። እንደ እስራኤሉ ጋዜጠኛ ዮሲ ሜልማን አገላለፅ፤ በኦልመርት ላይ በተደረጉ ተደጋጋሚ ምርመራዎች፤ የተወሰኑ ሰዎች ሙሰኛ እንደነበሩ እንዲያምኑ አድርጓል። ነገር ግን ያለፉባቸውን ዱካዎቹን በመከለል ማስተር አድርጓል ይሏቸዋል። ሌሎቹ ደግሞ ባለስልጣናት ኦልመርትን፤ የመጎንተል ራሮት አለባቸው ብለው ያምናሉ።

2004 ኦልመርት በእየሩሳሌም በሽያጭ እና በሊዝ ፈጽመዋል በተባለ ውንጀላ  ምርመራ ተደርጎባቸዋል። ውንጀላው ከገንዘብ ጋር በተገናኘ ሲሆን፤ ኦልመርት በገንዘብ እንዲጠቀሙ ተደርጓል የሚል ነው። ለሕገወጥ የምርጫ ቅስቀሳ ወይም ጉቦ ተደርጎ የተወሰደ መሆኑን ያትታሉ። ይህም ሲባል ከገበያ ዋጋ በታች 325ሺ የአሜሪካ ዶላር እንዲከፈል አድርገዋል። የዚህ ውንጀላ ምርመራው በይፋ የተጀመረው በሴቴምበር 24 ቀን 2007 ነበር። ሆኖም በቂ መረጃ ባለመገኘቱ በኦገስት 2009 የምርመራ ፋይላቸው እንዲዘጋ ተደርጓል።

ሌላው በጃንዋሪ 16 ቀን 2007 በኦልመርት ላይ አዲስ የወንጀል ምርመራ ተደርጓል። ምርመራው የተጠናከረው ኦልመርት የፋይናንስ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ ፈጽመውታል በተባለ ሙስና ነው። የተወነጀሉት ባንክ ሌውሚ ለመሸጥ በወጣው ጨረታ፣ የጨረታ ሒደቱን በማወክ ለአውስትራሊያው የሪል እስቴት ለባሮን ፍራንክ ሎዊ ለመጥቀም በመንቀሳቀሳቸው ነበር። ፈፅመውታል በተባለው ድርጊታቸው ላይ የእስራኤል ፋይናንስ ሚኒስቴር አካውንታንት በዋና ምስክርነት፤ ቀርቧል። በሰጠው ምስክርነትም፤ ኦልመርትን ወንጅሏቸዋል። በመጨረሻ ግን የእስራኤል የምርመራ ፖሊሲ፤ የተሰበሰቡት መረጃዎች ክስ ለመመስረት በቂ አይደሉም በማለት ምርመራው እንዲቋረጥ አድርገዋል ብሏል። በኦክቶበር 2007 ኦልመርት፤ ለአምስት ሰዓታት በብሔራዊ ወንጀል ምርመራ ቡድን፣ በእየሰሩሳሌም በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የምርመራ ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል። ሆኖም በዲሴምበር 2008 የመንግሰት አቃቤ ሕግ ሞሼ ላዶር፤ በቂ መረጃ ባለመኖሩ የምርመራ መዝገቡን እንዲዘጋ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በኦፕሪል 2007 ተጨማሪ ውንጀላ በኦልመርት ላይ ቀርቧል። ይኸውም፣ የንግድ ኢንዱስትሪ እና የሠራተኛ ሚኒስትር ሆነው፤ የወንጀለኛ ባሕሪ በኢንቨስትመንት ማዕከል ውስጥ አሳይተዋል ብለዋል። አቃቤ ሕጎቹ፤ ኦልመርት በወንድማቸው እና በቀድሞ የንግድ ሸሪካቸው በተወከለ የንግድ ድርጅት ቢዝነስ ጉዳይ ውስጥ የጥቅም ግጭት ውስጥ ገብተው፣ በግል ጉዳዩን ለመመልከት ተንቀሳቅሰዋል። እንዲሁም ኦልመርት፤ በረዳት ሚኒስትሮቻቸው የተወሰኑ ውሳኔዎችን ለወንድማቸው ድርጅት በከፊል እንዲጠቅም አድርገው ውሳኔዎችን በመለወጣቸው ተወንጅላዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በጁላይ 2007 ፓርላማ ፊት ቀርበው የተነሳባቸውን ውንጀላ ሙሉ ለሙሉ ክደዋል።

በጁላይ 2008 ሃሬተዝ እንደፃፈው፣ በ1992 ኦልመርት ከአንድ አሜሪካዊ ባለሃብት ከጆይ አልማሊያሃ ብድር ወስደው ተመላሽ ክፍያ አለመፈጸማቸውን አጋልጧል። ኦልመርትም፣ በተደረገባቸው ምርመራ ብድር መውሰዳቸውን አምነዋል። በ2004 ኦልመርት 75ሺ የአሜሪካ ዶላር መውሰዳቸውን አስታውቀው፤ ልማሊያሀ የሰጣቸውን ብድር እንድከፍለው አልጠየቀኝም ብለዋል። በተጨማሪም፣ 100ሺ ዶላር ገንዘብ መቀበላቸውን እና በግል የሒሳብ ቋታቸው ውስጥ እንዳስገቡት አቃቤ ሕግ ተናግሮ፤ ኦልመርት ብድራቸውን ስለመክፈላቸው እንደማያውቅ ተናግሯል።

በሜይ 2008 ኦልመርት በአዲስ የጉቦ ቅሌት ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ በወቅቱ ለሕዝብ ይፋ ተደርጓል። ኦልመርት በበኩላቸው፣ ከጁዊሽ አሜሪካዊ ባለሃብት ሞሪስ ታላነሰኪ ለኢየሩሳሌም ከንቲባነት ለመወዳደር ለምርጫ ቅስቀሳ የሚሆን ገንዘብ መቀበላቸውን አምነዋል። ውንጀላው ግን ለአንድ ጊዜ ሳይሆን ለአስራ አምስት አመታት ከባለሃብቱ ገንዘብ ተቀብለዋል የሚል ነበር የቀረበባቸው። በዚህ ፈፅመውታል በተባለው ተግባራቸው ከሥልጣን እንዲለቁ ግፊት ቢደረግባቸውም አሻፈረኝ በማለት፣ አልመርት ጥያቄውን ውድቅ አድርገውታል። ኦልመርትም እንዲህ ብለው ነበር፤ “I never took bribes, I never took a penny for myself. I was elected by you, citizens of Israel, to be the Prime Minister and I don’t intend to shirk this responsibility. If Attorney General Meni Mazuz, decides to file an indictment, I will resign from my position, even though the law does not oblige me to do so.”

እሳቸው እንደዚህ ይበሉ እንጂ፣ ታላንስኪ ሜይ 27 ቀን በፍርድ ቤት ቀርቦ ምስክርነት ሰጥቷል። ይኸውም፣ ከአስራ አምሰት አመታት በላይ ለኦልመርት ከ150ሺ ዶላር የበለጠ ለፖለቲካ ምርጫ ዘመቻ የሚውል በፖስታ አድርጎ መስጠቱን አረጋግጧል። ይህንን ተከትሎ ሴፕቴምበር 6 ቀን 2008 የእስራኤል ፖሊስ በኦልመርት ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሰረትባቸው ምክር ሃሳብ አቀረበ። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በፖሊስ ሪፖርት መነሻ፣ በ600ሺ ዶላር ክስ መሰረተባቸው። ከ600ሺ ዶላር ውስጥ 350ሺው በቅርብ ጓደኛቸው ዩሪ ሜሰር ቋት ውስጥ እንደሚገኝ ተያይዞ ይፋ ሆነ። እንዲሁም በ2010 ብሔራዊ የሙስና ምርመራ ዩኒት፣ ኦልመርት ከሆሊላንድ ሪልእስቴት ጋር በተያያዘ ያለውን ጥርጣሬ በይፋ አሳወቀ። ይኸውም፣ ሪል ስቴቱን ፕሮሞት ለማድረግ ጉቦ መቀበላቸው ይፋ አደረገ።

አጠቃላይ ከላይ የሰፈሩት የኦልመርት ክሶች የመዝገብ ፋይል ተከፈተላቸው። እነሱም፣ “Rishon Tours”, “Talansky” (also known as the “money envelopes” affair), and the “Investment Center” በሚል የመዝገብ ስያሜ የመንግስት ዐቃቤ ሕጐች ወደ ክርክር ውስጥ ገቡ። በጊዜው አስገራሚ የነበረው ጉዳይ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ይህንን አይነት የክስ መዝገብ የተከፈተባቸው የመጀመሪያው ሰው፤ ኤሁድ ኦልመርት ናቸው። የፍርድ ሒደቱ ለአምስት አመታት ከተሰማ በኋላ፤ የእየሩስአሌም ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ጊዜ ሆሊላንድ ከሚባለው ሪል እስቴት 160ሺ የአሜሪካ ዶላር መቀበላቸው በመረጋገጡ ለስድስት አመት በእስር እንዲቆዩ ተበይኖባቸው ወደ ማረሚያ ቤት ተወስደዋል። ከስድስት የሚበልጡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጓደኞች እና ባለሃብቶች ተያይዘው ዘብጢያ ወርደዋል። እንዲሁም በ“Talansky” ጉዳይ ተጨማሪ የስምንት ወር እስር ተፈርዶባቸዋል።

በዚህ የኦልመርት የፍርድ ሒደት፣ የኦልመርት ከፍተኛ ረዳት የነበሩት ወ/ሮ ሹላ ዛከን በሰጡት ምስክርነት፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሁድ ኦልመርት በሙስና የተገኘ ገንዘብ መቀበላቸውን እና እሳቸውም ከተሞሰነው ገንዘብ የድርሻቸውን መውሰዳቸውን አምነው ለፍርድ ቤቱ አጋልጠዋል። ወ/ሮ ይህንን የጀግና ምስክርነት በማቅረባቸው የእስር ጊዜያቸው እና የገንዘብ ቅጣት ተቀንሶሏቸዋል። 

የኦልመርትን ጉዳይ የያዙት ዳኛ ዴቪድ ሮዜን የፍርድ ውሳኔውን ሲያስተላልፉ የተናገሩት፣ “የሕዝብ አገልጋይ ሆኖ፣ ጉቦ የሚቀበል ወንጀል ከፈጸሙ ከከዳተኞች ጋር ተመሳሳይ ነው” ነበር ያሉት።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሁድ ኦልመርት ከሃያ ሰባት ወራት እስር በኋላ፣ የእስራኤል የምህርት ሰጪ ቦርድ ባስተላለፈው ውሳኔ ከማረሚያ ቤት ተለቀዋል።

ከላይ ስለ ኤሁድ ኦልመርት የክስ ሂደት የሚተርከውን ጽሁፍ ያቀረብነው ያለምክንያት አይደለም። በ80ዎቹ የጀመረው ጥርጣሬ ወንጀል ክስ ፍርድ የሚሰጠን መሠረታዊ ትምህርት በመኖሩ ነው። ከላይ እንደሰፈረው በኤሁድ ኦልመርት ላይ ከ80ዎቹ ጀምሮ የሙስና ጥርጣሬ እና ውንጀላ መኖሩን ያሳያል። በወቅቱ የቀረበው ጥርጣሬ እና ውንጀላ ከረጅም አመታት መረጃ እና ማስረጃ አታካች ፍለጋና ምርመራ በኋላ ፍፃሜውን ያገኘው በ2006 መሆኑን ከግምት ከወሰድን፤ የሙስና መረቦችን ለማግኘት ጠንካራ ስራ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው።

ሌላው፣ ሙስና አንድ ሰው ለብቻው የሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት አለመሆኑን ያሳያል። ሙስና ከባለስልጣን፣ ከባለሃብት፣ ከቤተሰብ እና ከሌሎች ኃይሎች ጋር በጋራ የሚፈጸም የተቀናጀ ወንጀል መሆኑ ይጠቁማል።

ሌላው፤ ማንም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ከሕግ በላይ አለመሆኑን ጥሩ ማሳያ ነው። ይህንን ለመፈጸም ግን፤ አስፈፃሚውን ሊገዳደር የሚችል ተቋም መመስረት ፋይዳው ብዙ መሆኑን፤ ጥሩ ማሳያ ነው። እንዲሁም ዳኛ ዴቪድ እንዳሉት፣ ኦልመርት ብሩህ አዕምሮና የህዝብ ፍቅር አለው። ለሀገራችን እስራኤል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተ ነው። ሆኖም ግን የሕዝብን አገልግሎት የሚመርዝ ሙስና ፈጽሟል፤ ቅጣትም ይገባዋል፤ ብለዋል።

ሌላው፣ የሙስና ክብደትን ለመፈተሽ ጥሩ አጋጣሚ ተደርጐ የሚወሰድ ነው። ምክንያቱም ለሕዝብ ጥሩ ምሳሌ የማይሆን ማለት እና ሥርዓትን የሚያፈርስ ሙስናን ለመለየት የሚያስችል ጥሩ አብነት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የሚስችሏትን ትልልቅ የልማት ተግባራት በማከናወን ላይ ስለመሆኗ መስካሪ ማፈላለግ ውስጥ የሚገባ የለም። የኢትዮጵያ መንግስት ከዘረጋው መጠነ ሰፊ የልማት አጀንዳዎች ቢያንስ አብዛኛዎቹ ተሳክተው ማሕበራዊ ፍትህ ለማስፈን የእድገት እና የትራንስፎርሜሽ እቅዶች እየተገበረ ይገኛል።

ይህን ሁሉ ጥረት ቢደረግም አሁንም 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ምገባቸውን ከመንግስት እጅ የሚጠብቁ ናቸው። እንዲሁም 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በሴፍቲኔት ታቅፈው ወደ ድህነት ወለል ለመጠጋት እየፈለፉ ይገኛሉ። ቀሪው ሕዝብም ቢሆን፣ ከድህነት ወለል ከፍ ለማለት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝ ለማንም የሚጠፋ እውነት አይደለም። ይህ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ነው።

ይህንን ተጨባጭ የሀገሪቱን ሁኔታ ይለውጣሉ ተብለው ታምነው የሕዝብ ኃላፊነት የወሰዱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አስፈሪም አስደንጋጭ በሆነ የአብይ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ተገኝተዋል። ባክኗል ወይም ተዘርፏል ከተባለው በላይ ምላሽ የሚሻው ጥያቄ፤ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ ለመቀራመት አስተሳሰቡ ከወዴት ነው የመጣው? 20 ሚሊዮን በላይ ከድህነት ወለል በታች ዜጎች በሚገኙባት ኢትዮጵያ፤ ቢሊዮኖችን ለመዝረፍ የባለስልጣኖች እና የባለሃብቶች ሞራል በዚህ ደረጃ፤ እንዴት ሊወርድ ቻለ? የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነቱን ይዟል ሲባል ሲነገር የነበረው፤ ሀገር በቢሊዮኖች ደረጃ በምትዘረፍበት ቁመና ላይ መሆኗን ስለእውነት የሚያውቅ ዜጋ ነበርን?

እነዚህን ችግሮች ከሥራቸው ለማድረቅ ፍርደኞች ላይ ፍርድ በመስጠት ብቻ የሚታለፍ አይደለም። አጠቃላይ የሀገሪቷ ሲስተም በከፍተኛ ባለሙያዎች ማስፈተሽ እና የማሕራዊ ሳይንስ የጥናት ቡድን በሀገር አቀፍ ደረጃ አደራጅቶ እንደሕዝብ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ አራማጅ እንዴት እንደሆንን መፈተሽ ተገቢ ነው። እንዲሁም የሀገሪቷን የትምህርት ሥርዓት ከግብረገብ አንፃር መቃኘት ሌላው ተጨማሪ አማራጭ ነው። ምክንያቱም ዛሬ ዘራፊ ያልናቸው ሲዘርፉ ያገኘናቸው፤ የዚሁ ሕብረተሰብ ውጤት በመሆናቸው ነው።

ለማንኛውም፣ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በሙስና ተጠርጥረው ስማቸው የተገለጹት እና ፍርድ ቤት የቀረቡት የሚከተሉት ናቸው። የተጠርጣሪዎች ቁጥር ወደ 45 ማሻቀቡን በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

በተለያዩ 14 የክስ መዝገቦች ተከፋፍለው የቀረቡት ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፤ ከስኳር ኮርፖሬሽን እና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ 34 ግለሰቦች ናቸው።

ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ኢንጂነር ፍቃደ ኃይሌ /የቀድሞ የባለስልጣኑ ሥራ አስኪያጅ/፣ ኢንጂነር አህመዲን ቡሴር፣ ኢንጂነር ዋስይሁን ሽፈራው፣ ሚስተር ሚናሽ ሌቪ (የትድሃር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ) ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ተጠርጥረው የቀረቡት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከማዕድን ሚኒስቴር እስከ ውሃ ሀብት ድረስ ያለውን መንገድ ሲያሰሩ ያልተገባ ውል መዋዋላቸውን ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል። ተጠርጣሪዎቹ በዚህ ፕሮጀክት ከትድሃር ጋር በመሻረክ 198 ሚሊዮን 872 ሺህ 730 ብር ከ11 ሣንቲም መንግሥትን አሳጥተዋል ሲል ፖሊስ አቅርቧል።

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አቶ አብዶ መሐመድ፣ አቶ በቀለ ንጉሤ፣ አቶ ገላሶ ቡሬ፣ አቶ የኔነህ አሰፋ፣ አቶ አሰፋ ባራኪ፣ አቶ ገብረአናንያ ፃዲቅ፣ አቶ በቀለ ባልቻ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በተጠርጣሪነት የቀረቡት እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ በከፍተኛ ኃላፊነት ሲሰሩ፤ ኮምቦልቻ፣ ሐረር፣ ጅግጅጋ እና ጋምቤላ ጎሬ በተሰሩ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ አስፈላጊ የዲዛይን ጥናት ሳይደረግና ምንም ሕጋዊ ውል ሳይኖር ሆን ተብሎ ዋጋ እንዲጨመር በማድረግ፣ ከአሰራር ውጪ የኮንትራት ውል አዘግይተዋል ነው ያለው ፖሊስ።

በዚህም ፕሮጀክቶቹ በመዘግየታቸው 646 ሚሊዮን 980 ሺህ 626 ብር ከ61 ሣንቲም ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው መቅረባቸውን ፖሊስ ጠቅሷል።

ከስኳር ኮርፖሬሽን ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ አቶ አበበ ተስፋዬ /በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የአገዳ ተከላ ምክትል ዳይሬክተር/፣ አቶ ቢልልኝ ጣሰው /በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ጠቅላላ ሂሳብ ያዥ/ ሁለቱ ግለሰቦች በጋራ በመመሳጠር ፖሊስ ስሙ ለጊዜው በመዝገብ ካልተጠቀሰው ኩባንያ ጋር የአርማታ ብረት እና ሲሚንቶ በዓይነት ማስረከብ ሲገባ፤ ሳይረከብና ተቀናሽ ሳይደረግ 31 ሚሊዮን 379 ሺህ 985 ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተመልክቷል።

ከመተሃራ ስኳር ፋብሪካ አቶ እንዳልካቸው ግርማ፣ ወ/ሮ ሰናይት ወርቁ፣ አቶ አየለው ከበደ፣ አቶ በለጠ ዘለለው ሲሆኑ፤ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በተለይ አቶ እንዳልካቸው፣ ወ/ሮ ሰናይት እና አቶ አየለው በመተሃራ ስከር ፋብሪካ የግዢ ቡድን መሪ እና የውጭ ሀገር የእቃ ግዢ ኃላፊዎች ሆነው ሲሰሩ 13 ሚሊዮን 104 ሺህ 49 ብር ከ88 ሣንቲም ለአቅራቢዎች ያለአግባብ እንዲከፈል በማድረጋቸው፤ እንዲሁም አቅራቢዎቹ ባላቀረቡበት ሁኔታ ላይ 0 ነጥብ 1 በመቶ ቅጣት ማስቀመጥ ሲገባቸው በዚህም 2 ሚሊዮን 743 ሺህ 35 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል።

አቶ በለጠ ዘለለው ደግሞ በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ የፋይናንስ ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ ፋብሪካው ለመሳሪያ እድሳት ያልተሰራበትን 1 ሚሊዮን 164 ሺህ 465 ብር ክፍያ በመፈፀም ተጠርጥሯል።

ከኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 አቶ መስፍን መልካሙ /የኦሞ ስኳር ፋብሪካ ቁጥር 5 ምክትል ዋና ዳይሬክተር/ ወይዘሮ ሳሌም ከበደ፣ ሚስተር ጂ ዮኦን /የቻይናው የጄጄ አይ. . . ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ/፣ አቶ ፀጋዬ ገብረእግዚአብሔር፣ አቶ ፍሬው ብርሃኔ ሲሆኑ፤ ተጠርጣሪዎቹ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ሲሰሩ ከተዘረዘሩት ተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር በሥራ ላይ የሚገኘውን ፕሮጀክት ያለአግባብ ውል በመስጠት 184 ሚሊዮን 408 ሺህ ብር ጉዳት በማድረግ ፖሊስ መጠርጠራቸውን ጠቅሷል።

ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ አቶ አበበ ተስፋዬ፣ አቶ ዳንኤል አበበ፣ አቶ የማነ ግርማይ ሲሆኑ፣ በተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የቤቶች ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አበበ ከፋብሪካው የአገዳ ቆረጣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋዬ ጋር በመመሳጠር የተለያዩ የክፍያ ሰነዶችን በመሰረዝ እና በመደለዝ ለሦስተኛ ወገን ለአቶ የማነ ግርማይ 20 ሚሊዮን ብር ያለአግባብ ክፍያ በመፈፀም እና በዓይነት እና በገንዘብ ሳይመለስ በመቅረቱ ተመሳሳይ መጠን ያለው ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል።

በሌላ መዝገብ አቶ አበበ ተስፋዬ፣ አቶ ኤፍሬም ዓለማየሁ እና አቶ የማነ ግርማይ፣ አቶ አበበ እና አቶ ኤፍሬም ከአቶ የማነ ግርማይ ጋር በመመሳጠር ለባቱ ኮንስትራክሽን 2 ሺህ ሔክታር መሬት ምንጣሮ አንድ ሔክታሩን በ25 ሺህ ብር ተዋውሎ ሳለ ሥራውን ከባቱ ኮንስትራክሽን በመንጠቅ ለአቶ የማነ ግርማይ አንዱን ሔክታር በ72 ሺህ 150 ብር የ42 ሚሊዮን ብር ልዩነት እያለው ያለምንም ጨረታ አንዲሰጠው በማድረግ በአጠቃላይ ከ216 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል።

አቶ ፈለቀ ታደሰ፣ አቶ ኤፍሬም ደሳለኝ /የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የግዢ እና ንብረት አስተዳደር መክትል ዋና ዳይሬክተር/ አንድ ሺህ ሔክታር መሬት እንዲመነጠር ለባቱ ኮንስትራክሽን በመስጠት ተገቢው ሥራ ሳይሰራ 10 ሚሊዮን ብር ለባቱ ኮንስትራክሽን እንዲከፈል በማድረግ ተጠርጥረዋል።

ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አቶ ሙሳ መሐመድ /የሚኒስቴሩ የፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ/፣ አቶ መስፍን ወርቅነህ /የሚኒስቴሩ የፕሮጀክት ባለሙያ/፣ አቶ ዋስይሁን አባተ /የሚኒስቴሩ የሕግ ክፍል ዳይሬክተር/፣ አቶ ታምራት አማረ /የሚኒስቴሩ ባለሙያ/፣ አቶ ስህን ጎበና /የሚኒስቴሩ ባለሙያ/፣ አቶ አክሎግ ደምሴ /የሚኒስቴሩ ባለሙያ/፣ የሚኒስቴሩ ባልደረባ ያልሆኑ፣ ዶ/ር ወርቁ ዓለሙ፣ አቶ ዮናስ መርዓዊ፣ አቶ ታጠቅ ደባልቄ ሲሆኑ፤ ተጠርጣሪዎቹ በሚኒስቴሩ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ላይ ሲሰሩ መንግሥት የፋይናንስ ስርዓቱን ለማዘመን 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር በመውሰድ ለቴክኖሎጂው ማስፋፊያ ሥራ የበጀተውን ገንዘብ ያለ አግባብ በመጠቀም ቴክኖሎጂው ከሚሰሩት ዶክተር ወርቁ ዓለሙ፣ አቶ ዮናስ መርዓዊ እና አቶ ታጠቅ ደባልቄ ጋር በመመሳጠር ቴክኖሎጂው በተገቢው መንገድ አቅም ላላቸው ባለሙያዎች መስጠት ሲገባው ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ጨረታን ሳይከተሉ በማሰራት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል። ተመሳሳይ የገንዘብ መጠን ያልተሰራበትን እንደተሰራ በማድረግ ክፍያ በመፈፀም ነው የተጠረጠሩት።

በአጠቃላይም ተጠርጣሪዎች ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የፕሮጀክት ሥራ የወጣን ወጪ አጉድለዋል ሲልም ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል። ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና ጥያቄ ይፈቀድላቸው ዘንድ ችሎቱን ጠይቀዋል።

ፖሊስ በበኩሉ ያልጨረስኩት ሰነድ እና ማስረጃ ስላለ ለምርመራ ተጨማሪ 14 ቀናት ጊዜ ይሰጠኝ በማለት ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ሰነዶችን ሊያሸሹ ይችላሉ በማለትም የጠየቁት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ይሁንልኝ ብሏል።

ችሎቱም የፖሊስን ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለነሐሴ 3 ቀን 2009 .ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከዚህ ባለፈም ተጠርጣሪዎች ከጠበቃና ቤተሰብ ጋር እንዳንገናኝ ተከልክለናል በማለት ላቀረቡት አቤቱታ ችሎቱ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ከጠበቃና ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በተጨማሪም አቶ ጌታቸው አምባዬ በሰጡት መግለጫ በኦሞ ኩራዝ 5 ከቻይና ኤግዚም ባንክ 700 ሚሊዮን ዶላር ከተገኘው ብድር 30 ሚሊዮን ዶላር በኮሚሽን መልክ ሊከፈል እንደነበረ አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር የ20 ሚሊዮን ዶላር እና 19 ነጥብ 1 ማሊዮን ዶላር የማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም ለመዘርጋት የወጣውን ጨረታ በቀጥታ ለአንድ ኩባንያ ካለውድድር እንዲሰጥ መደረጉን ይፋ አድርገዋል፡፡

ስንደቅ