Wednesday, 09 August 2017

አዲስ ጽላት ለማስገባት በሚል ነባር ታቦትና ቅርሶች ይሰረቃሉ፣ ይለወጣሉ፤ ተብሏል

ዝርፊያው፥ የጦር መሣርያ በታጠቁ ግለሰቦች እንደሚፈጸም ተጠቁሟል

ዞኑ፥ ከደብረ ሲና እስከ አንኮበር ተራራ የቱሪስቶች የኬብል ማጓጓዣ ያሠራል

በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናትና በርካታ የታሪክ ቅርሶች በሚገኙበት ሰሜን ሸዋ ዞን የሚፈጸመው የነባር ጽላትና ቅርሶች ዘረፋና ቅሠጣ፣ ከሀገረ ስብከቱ አቅም በላይ እንደሆነ መረጋገጡ ተገለጸ፡፡

ከመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ከቅርስ ዘረፋና ለውጥ ጋራ ተያይዞ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በቀረቡ የምእመናንና የሠራተኞች አቤቱታዎች መነሻ በተካሔደው ማጣራት፣ የሀገሪቱ የታሪክ አሻራ ያሉባቸው በርካታ ቅርሶች፣ የመንግሥት ለውጥ ከኾነበት ከ1983 .. ጀምሮ ለተጽዕኖ እየተጋለጡና እየተዘረፉ እንዳሉ ለመረዳት መቻሉን፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ አጣሪ ልኡክ ሰሞኑን ለአስተዳደር ጉባኤው ባቀረበው ሪፖርት ገልጿል፡፡

የጻድቃኔ ማርያም፣ የሸንኮራ ዮሐንስ፣ የሳማ ሰንበት፣ የሚጣቅ ዐማኑኤል፣ የዘብር ገብርኤል እና መልከ ጸዴቅ ገዳማትንና አድባራትን ጨምሮ ከሁለት ሺሕ በላይ አብያተ ክርስቲያናትን አቅፎ የያዘው የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ ቅርሶቹን ለማስጠበቅ የአቅም ውሱንነት እንዳለበት፣ በመስክና በመድረክ በተደረጉት የልኡኩ የማጣራት ሒደቶች ሁሉ ማሳያዎች እንደቀረቡ ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

በሚጣቅ ዐማኑኤል ቤተ ክርስቲያን የነበረ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የብራና ዳዊትና ከዐጤ ምኒልክ የተሰጠ መስቀል ተዘርፎ የደረሰበት እንዳልታወቀና ሀገረ ስብከቱም እንዳልተከታተለው፤ የመንዝ የቀያ ቅዱስ ገብርኤል ጽላት ተሰርቆ ሲፈለግ ቆይቶ ጽላቱን የያዘው ሰው በቁጥጥር ሥር ውሎ በፖሊስ ከተጣራ በኋላ ሲመለስ ነባሩ ቀርቶ አዲስ ጽላት ተለውጦ መመለሱን፤ ከተዘረፉት ቅርሶች ጅቡቲ ድረስ የተወሰዱ መኖራቸውንና አንድ ጽሌ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቅርስ ጥበቃ መመሪያ ጋራ በመተባበር እንዲመለስ መደረጉን፤ በሚዳ ኦሮሞ ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፥ የሀገረ ስብከቱን ይሁንታ ሳያገኝና ማዕከሉን ሳይጠብቅ አዲስ ጽላት ለማስገባት በሚል አግባብነት የሌለው ሒደት መፈጸሙንና ታቦታቱ እስከ አሁን በኤግዚቢት ተይዘው እንደሚገኙ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት ነን ያሉና የወታደር ልብስ የለበሱ የተደራጁ ግለሰቦች፣ ቄሰ ገበዙንና የጥበቃ ሠራተኞችን በደጀ ሰላሙ አግተው የነጭ ገደል በኣታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን ንብረቶች ዘርፈው መውሰዳቸውን፤ በሌላም ጊዜ ተደራጅተው ሊዘርፉ የመጡ ግለሰቦች ተይዘው በእስር ላይ እንደሚገኙና የጥበቃው አቅም አነስተኛ መሆኑን፤ ደንባ ከተማ ላይ መሸኛ የሌለው ታቦት ተይዞ በሀገረ ስብከቱ አመራር ሰጭነት መቀመጡን፤ ሁለት የቅዱስ ገብርኤል እና ሁለት የቅዱስ ሚካኤል ጽላት መሐል ሜዳ ተገኝተው ቢመለሱም እስከ የስርቆት ሙከራው መቀጠሉን፤ በአፈር ባይኔ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጽላቱ ባይለወጥም የቅርስ ዘረፋው እንዳልቆመ፤ በቁንዲ ቅዱስ ጊዮርጊስ 14 የብራና መጻሕፍት፣ የብር ከበሮ፣ መስቀል፣ ኹለት ኩንታል የተቋጠሩ ንብረቶች ተዘርፈው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ አዋሬ ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው ቢመለሱም ዘራፊዎቹ ለ8 ዓመት በሕግ ተፈርዶባቸው ሳለ 5 ዓመት ተቀንሶላቸው በ3 ዓመት እስራት መፈታታቸውን፤ በጃን አሞራ ተክለ ሃይማኖት የብራና መጻሕፍት መጥፋታቸውን፤ የአንኮበር ቅዱስ ሚካኤል ደወል ተሰርቆ በክትትል ላይ እንደኾነ… ወዘተ በማጣራቱ ሒደት ከቀረቡት ማሳያዎች ውስጥ እንደሚገኙበት በሪፖርቱ ተዘርዝሯል፡፡

በቅርስ ዘረፋውና ቅሠጣው ተይዘው የታሰሩ ቀሳውስትና ዲያቆናትም መኖራቸውን በማረሚያ ቤቶችም ማየትም እንደሚቻል በአቤቱታ አቅራቢዎች የተነገረውን ያሰፈረው ሪፖርቱ፤ ዘረፋው የሚፈጸመው፥ የወታደር ልብስ የለበሱና የተደራጁ ግለሰቦች፣ የጥበቃ ሠራተኞችን በማገትና በማታለል እንደሚፈጸም ለሀገረ ስብከቱ የሚደርሱ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ለልኡኩ ማስረዳታቸውን ጠቅሷል፤ የሀገረ ስብከቱ ቅርስ ክፍል ሓላፊም፣ “በርካታ ቅርሶች በኃይልና በአፈና ተዘርፈውብናል፤ ከተዘርፉት ቅርሶች መካከል አብዛኞቹ ጅቡቲ ሲደርሱ ተይዘው የተመለሱ አሉ፤” ብለዋል፡፡

በማጣራቱ ሒደት የተሳተፉት የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ምንውየለት ጭንቅሎ፣ የቀያ ቅዱስ ገብርኤል ነባር ጽላት በአዲስ መለወጡን አረጋግጠው፣ ይሁንና ነባሩ ጽላት በአዲስ ጽላት እንዲለወጥ ስምምነት የተደረገው፣ በወቅቱ ጉዳዩን በተከታተለው ፖሊስና በሌሎች ካህናት እንደነበርና ፖሊሱ በወንጀል ተከሦ እስር ቤት ከመግባቱም በላይ ከሥራ እንዲሰናበት መደረጉን፣ ካህናቱም በእስር ላይ እንደነበሩ አውስተዋል፡፡

ለዘረፋው መንገድ የሚከፍተው ተጠቃሹ መንሥኤ፣ አዲስ አበባ የሚኖሩ ካህናትም ሆኑ ምእመናን፣ “ተወላጆች ነን” በሚል ከአንዳንድ ግለሰቦች ጋራ እየተመሳጠሩ፣ “ታቦት በበጎ አድራጊነት በድርብ እናስገባለን፤” በሚል የሚፈጥሩት ችግር እንደሆነ ሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ታቦት የሚያስፈልጋቸው አብያተ ክርስቲያናት ጥያቄን በማዕከል እንዲያስተናግድ አሳስቦ፣ “ከአዲስ አበባ በመንደር ካሉ ነጋዴዎች የሚመጡ ጽላት፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ያልጠበቁ፣ የመለወጡ ሒደትም ሕገ ወጥ ተግባር መሆኑን” አስገንዝቧል፡፡ ይህን በሚፈጽሙ አካላት ላይ ሀገረ ስብከቱ ተከታትሎ አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወስድ፣ የመንግሥት አካላትም ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አስታውቋል፡፡

ሪፖርቱ አክሎም፣ የዞኑ መስተዳድር ቅርስን ለማስመለስና ዘራፊዎችን ለመያዝ የሚያደርገው ጥረት እንደሚያስመሰግነው ገልጾ፤ በማጣራቱ ሒደት፣ በቅርስ ዘረፋ ወንጀል ተከሠው በሕግ የተፈረደባቸው አንዳንድ ዘራፊዎች፣ የቅጣት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ከእስር እየተለቀቁ በሚል የተሰጠው አስተያየት፣ “አጽንዖት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል፤” ብሏል፡፡

ባለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ በተካሔደውና የዞኑና የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች በተሳተፉበት የጋራ መድረክ ላይ የተገኙት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ፣ ከሙሰኝነትና የቤተሰባዊ አስተዳደር ጋራ ተያይዘው የተነሡ ውዝግቦች ለመንግሥትም አሳሳቢ እንደሆኑን ሀገረ ስብከቱ ራሱን መፈተሸ እንደሚገባው አሳበዋል፡፡ ዞኑን ለቱሪዝም እንቅስቃሴ አመቺ ለማድረግ አስተዳደሩ ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገ እንዳለም አስረድተዋል፡፡ ዞኑ ባሉትና ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚስችሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት የጋራ ተጠቃሚዎች ለመሆን ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ ከደብረ ሲና ተራራ እስከ እመ ምሕረት አንኮበር ተራራ ድረስ የአየር ላይ የኬብል ማጓጓዣ ለማሠራት ውጭ ሀገር ድረስ እየተጻጻፍን እንገኛለን፤” ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ስንደቅ