August 9, 2017 

አግባው ሰጠኝ እና አንጋው ተገኝ፤ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን የመኢአድ ፓርቲ ዋና ጸሀፊ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን በመቶ አለቃ ጌታቸው ስም የተከፈተው የክስ መዝገብ ውስጥ ከተካተቱ 16 ተከሳሾች ውስጥ ይገኙበታል። በ2001 .ም የወጣውን የጸረሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 7(1) [ራሱን ግንቦት ሰባት እያለ በሚጠራውና ከዚሁ የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ከተቀላቀለው ራሱን አርበኞች ግንባር እያለ በሚጠራው የሽብር ድርጅት ውስጥ አባል በመሆን በማናቸውም መልኩ ለመሳተፍ በማሰብ] እና በ1996 .ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1) () በመተላለፍ እንደተከሰሱ በ13/07/2007ዓም የቀረበባቸው ክስ ያመለክታል፡፡

አንጋው ተገኝ በሰሜን ጎንደር የምእራብ አርማጭሆ ወረዳ የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ የነበረ ሲሆን አግባው ሰጠኝ ደግሞ የሰሜን ጎንደር ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ እና የብሄራዊ ምክር ቤት አባል ነበር። ሁለቱም ከጥቅምት ወር መጨረሻ 2007 ዓም ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ። ክሱ በ13/07/2007ዓም ከመመስረቱ በፊት ከ5 ወር በላይ ማእከላዊ ቆይተዋል። አንጋው ማእከላዊ በቆየበት ወቅት ጨለማ ቤት ብቻ እንዲቀመጥ በመደረጉ አይኑን ታሟል፤ በደረሰበት ድብደባ ብዛት የተነሳም ጆሮው መስማት እንደተሳነው እና ህክምና ማግኘት እንዳልቻለ ለፍርድ ቤት ቢያመለክትም መፍትሄ አላገኘም። ክሳቸውን በሚከታተሉበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አብዛኛውን ጊዜ በሰበብ አስባቡ ጨለማ ቤት እንዲቀመጡ በማድረግ ከሌሎች እስረኞች ተገለው እና ከቤተሰብ ሳይገናኙ ነው የኖሩት።

2008 ነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ ከተከሰተው የቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘም ተጠርጥራችኋል ተብለው ሸዋሮቢት ተወስደው ከፍተኛ ድብደባ እና ስቃይ ደርሶባቸዋል። ከሸዋሮቢት መልስም ለደረሰው ቃጠሎ ተጠያቂ ናችሁ ተብለው የሽብር ክስ ከተመሰረተባቸው 38 እስረኞች መሃል አግባው እና አንጋው ይገኙበታል። (ፕሮጄክታችን ኢሰመፕ አግባው ሰጠ የደረሰበትን የመብት ጥሰት ባለፉት ሳምንታት ሲቀርብ የነበረው የእስረኞች የመብት ጥሰት ታሪክ ውስጥ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡)

በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለተከሰተው ቃጠሎ፣ የሰው ህይወት መጥፋት እና የንብረት ጉዳት ተጠያቂ ናችሁ ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው (እንዲሁም በተለያያ ምክንያት ክስ ከተመሰረተባቸው ውስጥ ያልተካተቱ) ምላሽ ባያገኝም ሸዋሮቢት እያሉ እና ከዛ መልስ ደረሰብን የሚሉትን የመብት ጥሰት ለፍርድ ቤት ባገኙት አጋጣሚ ይናገራሉ። ደረሰብን ብለው ከዘረዘሯቸው ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል።

የመብት ጥሰት በሸዋሮቢት ፣ ከነሃሴ 28/2008 እስከ ህዳር 10/2009- እስረኞች ያቀረቧቸው አቤቱታዎች)

እጃችንን እና እግራችንን በብረት ካቴና በብረት አልጋ ላይ ታስረን እንውል እና እናድር ነበር።

 ካቴናው ከአልጋው የሚፈታልን ለሽንት ቤት እና ለምግብ ለ10 ደቂቃ ነበር።

 ኢትዮጵያ ውስጥ አይደገምም ተብሎ ሃውልት የተሰራለት የቶርቸር ግርፋት ተፈፅሞብናል።

 በካቴና ሁለት እጃችንን ታስረን የግድግዳ ማገር ላይ ተንጠልጥለን/ተሰቅለን የውስጥ እግራችንን ተገርፈናል።

 ብልታችን ላይ ባለ ሁለት ሊትር ሃይላንድ ውሃ ተንጠልጥሎብናል።

 በኤሌክትሪክ ሾክ ተደርገናል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቻችን ለተለያዩ የጀርባ እና የስፓይናል ኮርድ በሽታ ተዳርገናል።

 በምርመራ ወቅት የተደበደብነው ፊታችንና የሰውነታችን ጠባሳ እንዳይታይ ከቤተሰባችን ሲያገናኙን የበዋሮቢት ማ/ቤት ት/ቤት ውስጥ በማስገባት በመስኮት በኩል ፊታችን ብቻ ሚታይበት መስኮት ውስጥ ፊታችንን አዙረው ነበር የሚያገናኙን።

 በአልጋ ላይ ታስረን ከምንውልበትና ከምናድርበት ቤት ጎን ሆን ብለው የተመርማሪዎችን ጩኸት እና ስቃይ እንድንሰማና እንድንረበሽ በስነ ልቦና እንድንጎዳ አድርገውናል።

 እንደዚህ አይነት ስቃይ እየደረሰብን ያላደረግነውን አድርገናል ብለን በወንጀል ስነስርቸት አንቀጽ 27(2)ን መሰረት በማድግ ቃል እየሰጠን ቪዲዬ ተቀርፀናል።

አንድ ሰው ከ1–9 የሚሆኑ ሰዎችን ገድያለሁ ብሎ አምኗል። አንድን ሟች ደግሞ የተለያዩ ሶስት ሰዎች ገለነዋል ብለው አምነው ፈርመዋል።

የመብት ጥሰት በቅሊንጦ ከሸዋሮቢት መልስ (እስረኞች ያቀረቧቸው አቤቱታዎች)

 ፍርድ ቤት የቀረብነው ምርመራ ከተካሄደብን ከ2ወር በኋላ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ በምርመራ ወቅት የደረሰብን ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ምክንያት አካላችን ላይ በሚታየው የመቁሰል አደጋ እስኪያገግም ድረስ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው።

 ቂሊንጦ ስንመለስ ከሌሎች እስረኞች ተለይተን እንድንታሰር ተደርጓል።

 23/03/2009 እና በ4/4/2009 በዋለው ችሎት ሸዋሮቢት የተደረግነውን በመናገራችን 4 6 በሆነ ጨለማ ቤት ውስጥ 16 ፍራሽ ላይ 37 ሰዎች ታጭቀን እንድንቀመጥ ተደርገናል።

 ሁለት እጃችን በካቴና ታስረን ነው የምንውለው። ሸንት ቤት ስንሄድም ካቴናው አይፈታልንም።

 በቃጠሎው ወቅት የነበረን ንብረት ማለትም ብር፣ ልብስ ጫማና የተለያዩ ንብረቶቻችንን ተዘርፈናል።

በማንነታችን፣ በሃይማኖታችን እና በፓለቲካ አመለካከታችን፤ ዛቻ ማስፈራሪያ እና ድብደባ ይፈፀምብናል።

አግባው እና አንጋውም በተለይም ከቂሊንጦ ቃጠሎ በኋላ ለቃጠሎው መንስኤ ናችሁ ተብለው ለምርመራ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት የደረሰባቸውን አሰቃቂ ድብደባ፤ ከተመለሱ በኋላም በቂሊንጦ የሚደርስባቸውን በደል ጥር ወር 2009 ዓም ጉዳያቸውን ያይ ለነበረው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት አቅርበው ነበር። ፍርድ ቤቱም የቂሊንጦ ማ/ቤት ሃላፊዎች ቀርበው ምላሽ እንዲሰጡ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ሃላፊዎቹ አግባው እና አንጋው ያቀረቡት አቤቱታ ከእውነታ የራቀ መሆኑን ለችሎቱ በማስረዳታቸው ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ገለልተኛ ወገን እንዲያጣራ በማለት ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን ትእዛዝ ሰጥቶ ኮሚሽኑ በመጋቢት ወር 2009 ዓም ምላሹን ለፍርድ ቤት አስገብቷል። ከኮሚሽኑ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀም አለመፈፀሙን ለማረጋገጥ ወደ ቂሊንጦ ማ/ቤት የሄደው ቡድን የታሰረ ታራሚ አለማየቱን እና ሌሎች በአቤቱታው የተካተቱ የመብት ጥሰቶችን ተፈፅሟል ለማለት በቂ ማስረጃ [በምስክር እጦት] ሊገኝ አለመቻሉ በሪፓርቱ ተካቷል። የኮሚሽኑ ሪፓርት አግባው እና አንጋው ባሉበት መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓም በችሎት ከተነበበ በኋላ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።

አቤቱታችን ተቀንሶብናል። እኛ የቂሊንጦን ብቻ ሳይሆን በሸዋሮቢት የደረሰብንም የመብት ጥሰት እንዲጣራልን ጠይቀን ነበር። ሸዋሮቢት ዘግናኝ ቶርቸር ተፈፅሞብናል። ከነሃሴ 28/2008 ጀምሮ እጃችንን ታስረን ነው የምንፀዳዳ የነበረው። በኛ ላይ ግፍ ተፈፅሞብናል። የጣት ቀለበት፣ ያንገት ሃብል እና ፓንት ሳይቀር ተዘርፈናል። የይስሙላ ሪፓርት ነው። ከኮሚሽኑ የመጡ ሰዎች ቤቱን ሲለኩት አይተናል። 4 6 ነው። በሪፓርት ሲያቀርቡት ግን ዋሽተዋል። ምስክርም አስመዝግበን ነበር። ሪፓርቱ ላይ ግን ምስክር አላገኘንም ብለዋል። የደረሰብንን ለማወቅ ልብሳችን አውልቀን ሰውነታችንን ለማሳየትም ፈቃደኛ ነበርን።”

በመጨመርም ሁለቱም በህክምና እጦት እየተሰቃዩ እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፤ አንጋው የማ/ቤት ሃላፊዎቹ “ዳኛው ጋር ትመረመራለህ” እንዳሉት ገልፆ ማ/ቤቱ የፍ/ቤትን ትእዛዝ እንደማያከብር ተናግሯል።

የደረሰባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰትም ሆነ የጤናቸው ጉዳይ መፍትሄ ሳያገኝ ቀድሞ በቀረበባቸው ክስ ሰኔ 9/2009 ዓም በተሰጠ ፍርድ ፍርድ አግባው ሰጠኝ ክሱን በሚገባ ተከላክሏል ተብሎ “ነፃ” ሲባል አንጋው ደግሞ የቀረበበትን ክስ በአግባቡ መከላከል ሳይችል ቀርቷል በሚል ሰኔ 16/2009 ዓም በተሰጠው የቅጣት ብይን 4 ዓመት ከ6ወር ተፈርዶበታል። [አግባው ዋስትና ተከልክሎ ከ2 አመት ከ6ወር በላይ ያለምክንያት በእስር ከቆየበት ክስ “ነፃ” ቢባልም፤ ለቂሊንጦ ቃጠሎ ተጠያቂ ነህ ተብሎ የቀረበበትን ክስ ስላለ ከእስር አልወጣም።]

አግባው ዛሬ ነሃሴ 1,2009 ቀን ከቂሉንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ለቀረበበት ክስ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ሊሰሙ በተያዘው ቀጠሮ ደግሞ ተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደደረሰበት ተናግሯል። ከሰኔ 11/2009 ጀምሮ ከቂሉንጦ ዝዋይ ተወስዶ ለ6 ቀናት ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰበት በችሎት የተናገረ ሲሆን የደረሰበትን ጉዳት በችሎት ለማሳየት ጠይቆ ተከልክሏል። በዚህ ሁሉ የመብት ጥሰት አቤቱታን የማጣራት ሃላፊነተ የተሰጠው መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበው ሪፓርት ከዚህ በታች ባለ ሊንክ ይገኛል።

http://ethioforum.org/amharic