August 10, 2017 –

 ቆንጅት ስጦታው

የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር የሆኑት መምህር በቀለ ገርባ የዋስትና መብታቸውን ተከለከሉ !



የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር መምህር በቀለ ገርባ “በሽብርተኝነት” ተከሰው ላለፉት አንድ አመት ከሰባት ወር የእስር ጊዜ ካሳለፉ በኋላ ቀርቦባቸው የነበረው የሽብር ወንጀል ወደ መደበኛ የወንጀል ህግ አንቀፅ 257()ን እንዲከላከል ተብሎ ውሳኔ ተላልፉ እንደነበረ የሚታወስ ነው። የፍርድ ቤቱ ውሳኔው ተከትሎ ጠበቃቸው አቶ አመሃ መኮንን “መምህር በቀለ እንዲከላከሉ ብይን በተሰጠበት ጉዳይ በቀጥታ የፈፀሙት ወንጀል የሌለ በመሆኑ በዋስትና ቢወጡ ከሃገር ወጥተው ይቀራሉ ተብሎ የማይገመት ከመሆኑ በተጨማሪ ግዴታቸውን አክብረው በቀጠሮ ቀን ሊቀርብ እንደሚችሉ እና ቋሚ አድራሻ እና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን በመጥቀስ” የመምህር በቀለ ገርባ የዋስትና ጥያቄ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረቡ ሲሆን ።ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ “ተከሳሽ ተከላከል በተባለበት የህግ ድንጋጌ ዋስትና መጠየቅ እንደሚችል የሚደነግግ የሕግ መሰረት የሌለ መሆኑን፣ተከሳሹ በዋስትና ቢወጡ ከሃገር ሊወጡ ወይም ተመሳሳይ ወንጀል ሊሰሩ ስለሚችሉ “የቀረበው ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም በማለት ተቃውሞ ያቀረበ ሲሆን። ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄዎን በተመለከተ የከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ተቃውሞ እና አስተያየት መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ የተሰጠ ቢሆንም ለ1ወር ያህል ጊዜ ዳኞች በተለያየ ወቅት በመታመማቸው ፣እንዲሁም ውሳኔው ተሰርቶ አላለቀም እና መሰል ምክንያቶች በመስጠት የዋስትና ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ለ5 ጊዜ ተደጋጋሚ ቀጠሮ ከተሰጠ በኋላ በዛሬው እለተ ውሳኔ ተሰጥቷል ።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ያደረገ ሲሆን ።ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ያልተቀበለበት ምክንያት ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ተቃውሞ ታሳቢ በማድረግ ምምህር በቀለ ዋስትና ቢፈቀድላቸው” የተከሰሱበት ክስ ወይም ተከላከል የተባሉበትን ወንጀል በድጋሚ ከእስር ቤቱ ወጥተው ሊፈጽሙ ይችላሉ የሚል ግምት ፍርድ ቤቱ እንዳለው” በመግለጽ ዋስትናው ውድቅ መደረጉን ገልጿል ። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ተከትሎ ምምህር በቀለ ገርባ “እንዲህ አይነቱ ውሳኔ በእኔ አልተጀመረም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዲሁ ተወስኗል ። ምን አልባት ለህሊናቸው ያደሩ ዳኞች ካላ የተለየ ነገር ይኖራል ብዬ ገምቼ ነበር፤ግምቴ ግን ትክክል አልነበረም “በማለት ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል ። መምህር በቀለ ገርባ 26 ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነልሳን መምህር በመሆን ከማገልገላቸውም በተጨማሪ አንቱታን ያተረፉ ስመጥር ፖለቲከኛ ናቸዉ ።መምህር በቀለ በነሐሴ ወር 2003 ለእስር ተዳርገው “በሽብርተኝነት” ክስ ጥፋተኛ ተብለው 4 ዓመታት ያህል እስር ቤት ቆይተው ከተፈቱ ከተወሰኑ ወራቶች በኋላ በታህሳስ ወር 2008 .ም በድጋሚ ለእስር መዳረጋቸው የሚታወቅ ነው።

(ይድነቃቸው ከበደ)