August 11, 2017 07:38

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ስብሰባ እንደሚያደርጉ አገር ቤት የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል። በስብሰባው፣ እንደ ሪፖርተር ገለጻ፣ በገንዘብ ተቋማት ወቅታዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉ የተባሉ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳብ እንዲሁም በሰፋፊ እርሻዎች አጋጠሙ የተባሉ ችግሮችን ያካተቱ ሁለት ጥናቶች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በፊት ብዙ የምክክር መድረኮች እንደተደረገና በአገዛዙ መሻሻሎች እንደሚኖሩ ቃል ተገብቶ እንደነበረ የዘገበው ሪፖርተር፣ በዚሁ ስብሰባ ቃል የተገበላቸው ጉዳዮች እንደገና ሊታዩ እንደሚችልም አስፍሯል።
አንድ ኢሕአዴግ የተከናበት ነገር ቢኖር፣ ዜጎችን ከማሰር፣ ከማሰቃየት፣ ከመሰለልና ከማፈን በተጨማሪ ስብሰባዎችን ማድረግ ነው። “ግምገማ፣ ይሄ ሪፖርት፣ ያ ጥናት፣ እናሽሽላለን፣ እንታደሳለን …” እያሉ ስንት ስብሰባ እንደጠሩና ስብሰባዎችንም ለማካሄድ የወጣዉን የሕዝብ ሃብት ብናሰላው ቁጥሩ ጣራዉን አልፎ ነው የሚሄድ ነው።
አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ አቶ መለስ ዜናዊን ተክተው ጠቅላይ ሚኒስተር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች እየተገኙ በተለያዩ የመንግስት ክፍሎች፣ መንግስታቸው የመልካም አስተዳደርና የብቃት ችግር እንዳለው አምነው፣ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ ሲናገሩ ብዙ ጊዜ ሰምተናል።
አንድ ምሳሌ እንድጠቅስ ይፈቀድልኝ። ኢህአዴግ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ካለበት የ2007 ምርጫ በኋላ፣ ከታች እስከ ላይ ያሉትን የመንግስት መዋቅሮች የሚገመግም ኮሚቴ አቶ ሃይለማሪያም አዋቅረዉ፣ ኮሚቴዉም መጠነ ሰፊ ጥናት አድርጎ፣ ለመንግስት ባለስልጣናት ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል። በሪፖርቱም የፍትህ ስርዓቱን በተመለከተ ዳኞች በመመሪያ የሚወስኑበት ሁኔታ እንዳለና አቃቢ ሕጎችም የዉሸት ምስክሮችን እንደሚያስጠኑ፣ በኢኮኖሚውም ዘርፍ የስልጣን መባለግና ሙስና የበዛ እንደሆነ ተገልጿል። በወቅቱ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ያኔ ቃል ይገባሉ። ያኔ ከተናገሩት ዉስጥ የሚከተሉት ይገኝበታል፡
“እስከ መቼ የመልካም አስተዳደርን ችግር እንፈታለን እያልን እናወራለን ? ..ኮሪያ ፣ ቻያና ፣ ብራዚል እያልን ህዝቡን አሰልችተነዋል። ኮርያ ያልሄደ የለም። አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም። ብዙ ጊዜ። ብዙ ወረቀት፣ ብዙ ሐሳብ አምጥተናል። ብዙ ጥናት አድርገናል። State of the art ጥናቶች አሉን። ጥናቱ/ሪፎርሙ ግን ተግባራዊ መሆን አለበት። ሪፎርም መሳሪያ ነው። ተግባር ላይ ካልዋለ ዋጋ የለዉም። ከሥራ አስፈጻሚ ጀምሮ ተማምነን ሪፎርሙን ተግባራዊ ለማድረግ፣ በዘመቻ በንቅናቄ መነሳት አለብን። …በዚህ አመት አጋማሽ ላይ ሪፎርሞቹን ተግባራዊ የሚያደርግ manual አዘጋጅቶ በተግባር በማሳየት ለሕዝቡ ተስፋ መስጠት አለብን..”
አቶ ሃይለማሪያም መሰረታዊ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ችግሮችን በዘመቻና በንቅናቄ መልክ ለመፍታትና የሕዝብን ጥያቄ ግልጽነት ባለው መልኩ ለማስተናገድ፣ በመስከረም 2008 ዓ.ም ቃል ቢገቡም፣ ነገሮች ከመሻሻል ይልቅ የበለጠ እየባሱ መጡ። ከአራት ወራት በኋላ በታህሳስ 2008 ዓ.ም በዋናነት በኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃዉሞ ተቀሰቀሰ። ከሰባት ወራት በኋላ ደግሞ በሐምሌ 2008 ዓ.ም፣ በአማራው ክልልና እንደ ኮንሶ ባሉ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ሕዝብ ምሬቱን ገለጸ። እንኳን ለሕዝብ ተስፋ ሊሰጥና የሕዝብን ጥያቄ ሊመልስ ቀርቶ ፣ አቶ ኃይለማሪያም የሚመሩት አገዛዝ እንደዉም የሕዝብን ጥያቄን መጨፍለቁን መረጠ። ያሰማራቸው ታጣቂዎች በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በግፍና በጫካኔ ገደሉ። በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩትን አሰሩ፣ አፈናቀሉ። አገራችን ኢትዮጵያ ለልጆችዋ ሲኦል እንድትሆን አደረጉ። ይኸው ከ23 ወራት (ሁለት አመት) በኋላም፣ በሕሊና እስረኞች ፣ በአፋኝ የግብር አሰራር ፣ በግፍ በተገደሉ ወገኖች ዙሪያ….በአብዛኛው የአገሪቷ ክፍሎች በአሁኑ ሰዓት ተቃዉሞ እየተሰማ ነው።
አቶ ሃይለማሪያም ከሁለት አመት በፊት እንደገለጹት፣ አንድ ሺህ ጥናት ማቅረብ ዋጋ የለውም። ችግሩ የሀሳብ ወይም የጥናት ማነስ ሳይሆን ተግባር ላይ ነው። በመሆኑም ከነጋዴዎች ጋር አቶ ሃይለማሪያም ሊያደርጉ ያሰቡትም ስብሰባ፣ ጉንጭን ከማልፋት በስተቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም።
አቶ ሃይለማሪያም በስብሰባ መድረኮች ወንበሮችን ከማሞቅና ከወሬ ቆጠብ ብለው፣ ተግባር ላይ ቢያተኩር ጥሩ ነው። በአደባባይ የሚናገርትን ተግባራዊ ማድረግና በስራቸው ያሉትን ሚኒስትሮች ማዘዝ ካልቻሉ፣ ከሃላፊነታቸው መልቀቅ ነው ያለባቸው። በርሳቸው ዘንድ ቁርጠኝነት ከሌለ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መቀመጣቸው የበለጠ አገርን የሚጎዳ ነው የሚሆነው። ወደዱም ጠሉም በማንኛውም የመንግስት አካላት ለሚፈጸሙ በደሎችም በቀጥታ ተጠያቂ ነው የሚሆኑት።
ምን አልባት ረስተዉት ከሆነ፣ ከሁለት አመት በፊት ከተናገሩት የተወሰነውን ከዚህ በታች ያለውን የድርጅታቸው ኦፌሴል ድህረ ገጽ ላይ የተለጠፈዉን ማዳመጥ ይችላሉ።
እርግጥ ነው ሰሞኑን በሙስና የተጨማለቁ በሚል አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን እያየን ነው። እርግጥ ነው ከፖለቲክ ፓርቲዎች ጋር ዉይይቶች እየተደረገ ነው። ሆኖም ግን እንደ አባይ ጸሃዬና ወ/ሮ አዜብ መስፍን ያሉ ቀንደኛ የሕዝብ ገንዘብ መዝባሪዎች እየታለፉ ከታች ያሉትን ማሰር ፌዝ ነው። ተቃባይነት ያላቸው እንደ መድረክና ሰማያዊ ያሉ ፓርቲዎች ራሳቸው ያገለሉበትና ባልተሳተፉትበት፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በታሰሩበት፣ መሰረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች አጀንዳ ሆነው ባልቀረበቡት ሁኔታ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደረገው ድርድር/ስብሰባ ጠብ የሚል አስተዋጾ አይኖረውም። ይኸው ለወራት ውይይት እየተደረገ ነው። ኤሊ በፍጥነት እየቀደመቻቸው ነው። ምን ውጤት ተገኘ ቢባል መልሱ ዜሮ ነው።
የአገር ችግር በጣም ውስብስብ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ያለችን አገር መምራት በጣም ከባድ ነው። አንዳንድ ስር የሰደዱ ችግሮች በአንድ ሌሊት ሊፈቱ አይችሉም። ሆኖም ግን አቶ ሃይለማሪያም ቢያንስ ትንሽም ቢሆን ለሕዝብ ተስፋ የሚሰጡ በቀላሉ ሊተገበሩ የሚችሉ ምልክቶችን ከወሬ ባለፈ ማድረግ አለባቸው ባይ ነኝ። ለምሳሌ ከዚህ በታች ያሉትን ተግባራዊ ማድረግ በምንም መስፈርት ሊከብዱ የሚችሉ እርምጃዎች አይደሉም፡
1) የጸረ-ሽብርተኘነትን ህግ በማሻሻል ወይም በመሻር በሽብርተኝነት ሕግ የተከሰሱ ወይም የታሰሩ በሙሉ እንዲፈቱ ማድረግ ብዙ አያስቸግርም። ከጸረ-ሽብር ሕግ ዉጭ የታሰሩ የሕሊና እስረኞችን በተመለከተ ደግሞ፣ የፍርድ ዉሳኔ የተሰጠባቸውን በምህረት፣ በክስ ሂደቱ ላይ ያሉትን ደግሞ አቃቢ ሕግ ክሳቸውን እንዲያነሳ በማድረግ ሁሉንም መፍትታ ይቻላል። ይሄን ማድረግ ያለውን የአገሪቷ ሕግ በምንም መልኩ አይጻረርም።
2) ከፖለቲክ ፓርቲዎች ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር/ዉይይት መሰረታዊ በሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ማተኮር አለበት። በተራ ቁጥር አንድ እንደተጠቀሠው፣ የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከተፈቱም፣ ድርጅቶቻቸውን ወክለው በድርዱሩ መሳተፋቸው ሂደቱ ተአማኒነት እንዲኖረው ያደርጋል።

https://youtu.be/Q2gurI2R9jA