August 12, 2017

(ከሃራ ተወሃዶ ድረገጽ የተወሰደ)

የፈረሰው ቤተ ክርስቲያንና የፓርቲዎቹ ስጋት – ጽላቱ፥ ፖሊስ ጣቢያ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ፥ በኦሕዴድ ጽ/ቤት መጋዘን!
“ሕዝቡን ሳያማክሩና ዘላቂ መፍትሔ ሳያስቀምጡ በጸጥታ ኃይል ማፍረስ የእምነት ነጻነትን የሚጋፋ፣ ችግር ፈጣሪ ርምጃ ነው፤” (መኢአድ እና ሰማያዊ)

“በቤተ ክርስቲያን ስም የመሬት ወረራ ተፈጽሟል፤…ያስቆምነው የግለሰቦችን እንቅስቃሴ እንጂ የቤተ አምልኮን ግንባታ አይደለም፤” (ከንቲባ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ)

“ይዞታው በስጦታ የተገኘ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኑም ለ8 ወራት ያገለገለ ነው፤ የቤተ ክርስቲያኑ መፍረስና የጽላቱ ፖሊስ ጣቢያ መቀመጥ አማንያንን ያሳዘነና ያስቆጨ ጉዳይ ነው፡፡ የሚመለከተው አካል ሊያስብበትና መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል፤” (የደብሩ አለቃ)(የሐበሻ ወግ፤ ቅጽ 1 ቁጥር 40፤ ነሐሴ 2009 ዓ.ም.)

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣ ለእምነት ነጻነት ከፍ ያለ ቦታ ይሰጣል፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንደማይገባ በጉልሕ አስቀምጧል፡፡ ይኹንና ባለፉት ታሪኮቹ፣ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ላይ እጁን ያስገባል፤ ተብሎ የተወቀሰባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ፥ “መንግሥት የማንፈልገውን አስተምህሮ ሊጭንብን ይፈልጋል፤” ሲሉ ዘለግ ላለ ጊዜ ተቃውመዋል፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ቢኾን፣ መንግሥት ሰዋራ እንቅስቃሴዎች ያደረገባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡

መንግሥት፣ ጥንቃቄ በሚሻው የእምነት ጉዳይ ላይ እየዘለቀ የፖሊቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት መዘዙ ቀላል አይደለም፤ ያስብበት እየተባለም በብዙ ተመክሯል፡፡ ይኹንና ለእነዚህ ጉዳዮች፥ ጆሮው ላይ እጁን ጭኖ ወደ እምነት ተቋማት ከማማተር ወደ ኋላ አላለም፤ በሚል ይተቻል፡፡ ለዚኽ እንደ አንድ ማሳያ የተወሰደው ደግሞ፣ በዐዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኘው ለገጣፎ በሚባለው ቦታ ላይ፣ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ የመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን እንዲፈርስ የመደረጉ ጉዳይ ነው፡፡

በሕገ ወጥ ግንባታ ስም እንዲፈርስ የተደረገው የቤተ ክርስቲያኑ ጉዳይ፣ አኹን ላይ ብዙዎችን እያሳሰበና እያነጋገረ ነው፡፡ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲዎችም በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንዲያወጡ አድርጓል፡፡ ኹለቱ ፓርቲዎች በለገጣፎ ገዋሳ በሚባለው አካባቢ የተገነባውን የመጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን፣ ሕገ ወጥ ግንባታ በሚል ሽፋን ሕዝቡን ሳያማክሩና ዘላቂ መፍትሔ ሳያስቀምጡ በጸጥታ ኃይል እንዲፈርስ መደረጉና ጽሌው ፖሊስ ጣቢያ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ በኦሕዴድ ጽ/ቤት መጋዘን ውስጥ መቀመጡን” ኮንነዋል፤ ድርጊቱንም፣ “የእምነት ነጻነትን የሚጋፋ፣ ችግር ፈጣሪ ርምጃ ነው፤” ሲሉ ገልጸውታል፡፡

መንግሥትን የሚወክለው የአካባቢው አስተዳደር፣ “በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የሃይማኖት ነጻነት መከበር በመጋፋትና ጣልቃ በመግባት የተፈጸመውን አፍራሽ ተግባር፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች፣ በሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ አማካይነት ለኦሮሚያ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ሓላፊዎች አቤቱታ ቢቀርብም፣ ፓርቲዎቹ መግለጫ እስካወጡበት ቀን ድረስ ምላሽ እንዳልሰጠ” ጠቁመዋል፡፡

“በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር የተወሰደው ግብታዊ ርምጃ፣ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልገዋል፤” ብለዋል ኹለቱ ፓርቲዎች በመግለጫቸው፡፡

የሐበሻ ወግ መጽሔት፣ በዚኹ ጉዳይ ላይ የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒን ያነጋገረች ሲኾን፣ እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፡- “በአካባቢው በቤተ ክርስቲያን ስም ግለሰቦች የመሬት ወረራ ለመፈጸም የተንቀሳቀሱበት ኹኔታ ነበር፡፡ ቦታው ገደላማ ከመኾኑ አንጻር ለእምነት ቦታነት እንኳን የሚመጥን አይደለም፡፡ ጥቂት ግለሰቦች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ፣ በፌስቡክ ቤተ ክርስቲያን ፈረሰ እያሉ ሕዝቡን የሚያደናግሩበት ድርጊት ነው፤” ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

ወ/ሮ ጫልቱ፣ “እነዚኽ ሰዎች ማምለኪያ ቦታ አጥተው አይደለም፡፡ እየፈጸሙት ያሉት ሕገ ወጥ ድርጊት ስለኾነ፣ የተወሰደው ርምጃም የሕግን የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ ነው፡፡ የግለሰቦችን ሕገ ወጥ የጥቅም ፍላጎት የመቆጣጠር ጉዳይ ከእምነት ነጻነትም ኾነ እምነትን ከማራመድ መብት ጋራ ሊቆራኝ አይገባም፡፡ ያስቆምነው የግለሰቦችን እንቅስቃሴ እንጂ የቤተ አምልኮን ግንባታ አይደለም፤” ብለዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ አባ ጴጥሮስ ተክለ ሃይማኖት በበኩላቸው፣ ቤተ ክርስቲያኑ ለስምንት ወራት አገልግሎት የሰጠ መኾኑን በመጠቆም፣ “የተወሰደውን ርምጃ በተመለከተ ባቀረብነው አቤቱታ መሠረት፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ እና የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሥራ ሓላፊዎች ደብዳቤ ጽፈው ምላሹን እየተጠባበቅን ነው፤” ይላሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ የተገነባበት ቦታ ከምእመናን በስጦታ እንደተገኘ የጠቀሱት አባ ጴጥሮስ አያይዘውም፣ “ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የተገነቡበትን ቦታ መንግሥት አልሰጠም፡፡ ታላላቆቹ አብያተ ክርስቲያናት እንኳን በቅርቡ ነው ካርታ የተሰጣቸው፡፡ እኛም ምእመናን በሰጡን ቦታ ላይ የቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ገንብተን አገልግሎት እየሰጠን ነበር፡፡ በለገጣፎ ለገዳዲ 13 አብያተ ክርስቲያን በተመሳሳይ በስጦታ እንጅ፣ በመንግሥት በተሰጠ ቦታ ላይ አይደለም የተሠሩት፤” ብለዋል – ለሐበሻ ወግ፡፡

“ቦታው ገደላማ ከመኾኑ አንጻር ለቤተ እምነት አይመጥንም፤” ለሚለው የከንቲባዋ አስተያየት አስተዳዳሪው ሲናገሩ፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን በብዛት የሚገነቡት ተራራማና ገደላማ ቦታዎች ላይ ነው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ገደላማ ቦታ ላይ እንዲገነባ የተደረገው ለዚኽ ነው፤” በማለት ገልጸዋል፡፡ አባ ጴጥሮስ፣ “የቤተ ክርስቲያኑ መፍረስና የጽሌው ፖሊስ ጣቢያ መቀመጥ አማንያንን ያሳዘነና ያስቆጨ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ሊያስብበትና መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል፤” በማለት አክለዋል፡፡

የቀድሞው የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋራ በቅርቡ አደረጉት በተባለው ውይይት ላይ፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፦ “ቤተ ክርስቲያንን የሚያኽል ነገር ሲፈርስብኝ ለመንግሥት አመልክቼ እስከ አኹን ምላሽ የማይሰጥበት ነው፡፡ የእኛን መጥቶ ያፈረሰብን የመንግሥት አካል ነው፡፡ እኔ አመልክቻለኹ፤ ቅዱስ ፓትርያርኩም ጽፈዋል፡፡ ምንድን ነው የእናንተ ሐሳብ?” ሲሉ እንደጠየቁ መዘገቡ ይታወሳል፡፡