የቅማንት ሕዝብ የራሱ አስተዳደር ይኖረዋል ተብሏል

ባለፉት ሁለት ዓመታት አመፅና ተቃውሞ ተከሰቶባቸው ከነበሩ የአገሪቱ ክፍሎች መካከል አንዱ የሆነው ሰሜን ጎንደር፣ ወደ ሦስት ዞኖች ሊከፈል መሆኑ ታወቀ፡፡

ሰሞኑን የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ውስጥ ካሉት ዞኖች መካከል አንዱ የሆነው ሰሜን ጎንደር ወደ ሦስት ዞኖች ይከፈላል፡፡

እስካሁን ድረስ ሰሜን ጎንደር ዞን 16 ወረዳዎች ያሉት ሲሆን ሰሜን ጎንደር፣ መሀል ጎንደርና ምዕራብ ጎንደር ተብሎ እንደሚከፈል ታውቋል፡፡

የፋሲለደስ ግንብ የሚገኝበት የአሁኑ ሰሜን ጎንደር መሀል ጎንደር ዞን እንደሚባልና ይህም ዞን በዙሪያው ያሉ ወረዳዎችን እንደሚያካትት ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ሰሜን ጎንደር ዞን ተብሎ የሚጠራው ሌላው ዞን ደግሞ በሰሜን ተራሮች አካባቢ ያሉ ወረዳዎችን እንደሚያካትና ደባርቅን የዞኑ ዋና ከተማ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡ ምዕራብ ጎንደር ዞን ተብሎ የሚጠራው ዞን ሦስተኛው አዲሱ ዞን ሲሆን፣ በአሁኑ የሰሜን ጎንደር ዞን በምዕራብ አቅጣጫ ያሉ ወረዳዎችን የሚያካትት እንደሆነ ታውቋል፡፡ የዚህ ዞን ዋና ከተማ ማን ሊሆን እንደሚችል እንዳልተወሰነ ተጠቁሟል፡፡

ሰሜን ጎንደር ዞን ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ በልማትና በመልካም አስተዳደር ተደራሽነት ላይ አስቸጋሪ ሆኖ እንደቆየ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዞኑ የሚገኘው ማኅበረሰብ በአብዛኛው አርሶ አደር በመሆኑ በቅርበት አግኝቶ ፍላጎቱን ለማርካትና የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት እንደታቀደ አክለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ለረጅም ጊዜ ሲታሰብበት የቆየ ቢሆንም ወደ ውሳኔ ሳይመጣ የዘገየ ጉዳይ እንደሆነ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት ኅብረተሰቡን ደረጃ በደረጃ እያወያየና የጋራ መግባባት እየፈጠረ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የአዳዲሶቹ ዞኖች አስተዳደራዊ ወሰንም በአብዛኛው እየተጠናቀቀና ተገቢው ግብዓቶች እየተሞሉ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ እንደ ቢሮና መሰል ሌሎች አገልግሎቶች በመዘጋጀት ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በቅርብ ጊዜ ወደ ተግባር ሊገባ እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

በዚሁ አዲስ መዋቅር የቅማንት ሕዝብ የራሱ አስተዳደር እንደሚኖረው ታውቋል፡፡ የቅማንት ሕዝብ ማንነቱ እንዲከበር ለብዙ ዓመታት ጥያቄ ሲያነሳ እንደነበር የገለጹት ኃላፊው፣ ‹‹ቢዘገይም በቅርብ ጊዜ ምላሽ ያገኛል፤›› ብለዋል፡፡ የቅማንት ሕዝብ በጎንደር በተለያዩ ቦታዎች የሚኖር ከመሆኑ አኳያ አከላለሉ ይኼን ከግምት ውስጥ ያስገባ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የቅማንት ሕዝብ አስተዳደር በዞን ወይም በወረዳ ደረጃ  ይሁን እስካሁን ባይታወቅም፣ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንደሚያስተዳድር ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ሰሜን ጎንደር ወደ ሦስት ዞኖች ተከፍሎ በሌላ በኩል የቅማንት ሕዝብ የራሱ አስተዳደር ይኖረዋል ሲባል፣ ዞኑ ወደ አራት ዞን የመከፈል ዕድል ሊኖረው ይችላል? የሚል ጥያቄ ኃላፊው ቀርቦላቸው፣ ‹‹ይህ ገና ውይይት እየተደረገበት ነው፤›› ብለዋል፡፡
እነዚህ ውሳኔዎች ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት አኳያ የተሰጡ ምላሾች እንደሆኑ ምንጮች ቢገልጹም፣ በዚህ ውሳኔ በተለይም ሰሜን ጎንደር ወደ ሦስት ዞኖች መከፈሉን እንደሚቃወሙ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ሰሜን ጎንደር ወደ ሦስት ዞኖች በሚከፋፈልበት ወቅት ጎንደር ጎንደርነቱን ያጣል፤›› ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ በሰሜን ጎንደር ዞን ውስጥ ካሉት ወረዳዎች አንዱ የመጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልም፣ ‹‹ሕዝቡ በዚህ ጉዳይ የሚስማማ አይመስለኝም፡፡ እኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው የጠየቅነው እንጂ፣ የመከፋፈል አይደለም እያለ ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሰሜን ጎንደርን ወደ ሦስት ዞን የመከፋፈልና የቅማንት ሕዝብ የራሱ አስተዳደር መካለልን በተመለከተ የክልሉ ከፍተኛ ካቢኔ ውይይት አድርጎበት ስምምነት ላይ የደረሰ መሆኑን፣ በቅርቡ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ እንዲመፀድቅም ይጠበቃል ተብሏል፡፡

ዘመኑ ተናኘ

Source    –    Ethiopian Reporter