12 Aug, 2017

By ታምሩ ጽጌ

 

የ210 ግለሰቦች ንብረት በፍርድ ቤት ታግዷል

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ታሰሩ

መንግሥት በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ከሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸውና ቁጥራቸው 55 ከደረሱት የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በተገናኘ፣ በ15 ኩባንያዎች ላይ ዕግድ ተጣለባቸው፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረስ ዕግድ የተጣለባቸው ኩባንያዎች አሰር ኮንስትራክሽን፣ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን፣ ኢሊሌ ሆቴል፣ ቲና ኮንስትራክሽን፣ ዲኤምሲ ኮንስትራክሽን፣ የማነ ግርማይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ፣ ትራንስ ናሽናል ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ፣ ሀይሰም ኢንጂነሪንግ አክሲዮን ማኅበር፣ ካማኒክ ትሬዲንግ፣ የቻይናዊው ሚስተር ጂኦዬን ጆንግ ሊንግ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግና ሌሎችም መሆናቸው ታውቋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በቅንጅት እየሠሩ ካሉት የመንግሥት ኃላፊዎችን ባለሀብቶችንና ደላሎችን በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር ከማዋል በተጨማሪ፣ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል ባሏቸው ከ210 በላይ የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦችና የተለያዩ ግለሰቦች ንብረቶች ላይ ከፍርድ ቤት የዕግድ ትዕዛዝ በማውጣት አሳግደዋል፡፡ በሁለቱ የመንግሥት ተቋማት ጥምረት እየተከናወነ ያለው ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ተግባርም ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሳምሶን ወንድሙም ነሐሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡

ቀደም ብለው ሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበው 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ የተፈቀደባቸው፣ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶችና ደላሎች በድጋሚ ነሐሴ 3 እና 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለሁለተኛ ጊዜ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ የጠየቀባቸው ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር 15 ተጠርጣሪዎች፣ ከመተሐራ ስኳር ፋብራካ አራት ተጠርጣሪዎች፣ ከኦሞ ኩራዝ 5 ፕሮጀክት ሰባት ተጠርጣሪዎች፣ ከተንዳሆ ስኳር ፋብካ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች (አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል በሌላ መዝገብ የተቀጠሩ ቢሆንም በቀጣይ ቀጠሮ አንድ ላይ ይቀርባሉ)፣ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ሦስት ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡

ፍርድ ቤቱ ነሐሴ 3 እና 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀርበው በመርማሪ ቡድኑ 14 ቀናት ከተጠየቀባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል፣ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ ሲጃን አባ ጐጃም ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ለመጀመርያ ጊዜ ቀርበዋል፡፡ ተቋሙን በቴክኖሎጂ ለማዘመን የተዘጋጀ ፕሮጀክት ያለ ጨረታ አቅም ለሌለው ድርጅት እንደተሰጠ፣ በራስ አቅም መሥራት እንደሚቻል እያወቁና በአግባቡ ላልተሠራ ሥራ ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪው ወደ ተቋሙ የገቡት ፕሮጀክቱ ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ መሆኑን ገልጸው፣ ራሳቸውን በራሳቸው ስለሚያስተዳድሩ ምግብም ሆነ ልብስ የሚያቀርብላቸው እንደሌለ በመናገር ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በመቀጠል በድጋሚ ፍርድ ቤት ባቀረባቸው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች ላይ ተፈቅዶለት በነበረው 14 ቀናት የሠራውን የምርመራ ውጤት ተናግሯል፡፡ የሁሉንም ተጠርጣሪዎች ቃል መቀበል መጀመሩን፣ የ16 ምስክሮች ቃል መቀበሉን፣ ከሁሉም ተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት፣ መሥሪያ ቤትና የግል ተቋማት ያገኛቸውን ሰነዶች የመለየት ሥራ ማከናወኑን፣ በወንጀል የተገኙና የወንጀል ፍሬ ናቸው ያላቸውን ንብረቶች መለየቱንና ማሳገዱን፣ ከዋና ኦዲተር ሪፖርት መቀበሉን፣ ተጠርጣሪዎቹ በሁሉም ንግድ ባንኮች ያላቸውን ሒሳብ የማሳገድ ሥራ ማከናወኑን፣ አንድ በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩ ኃላፊ ይዞ እየመረመረ እንደሆነ በመግለጽ ያከናወናቸውን ሥራዎች አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ቀረኝ ያለውን የምርመራ ዓይነት በመጥቀስም ተጨማሪ 14 ቀናት የጠየቀው ከክልሎች ጭምር የሚሰበሰብ የሰነድ ማስረጃ እንደሚቀረው፣ የ52 ምስክሮች ቃል መቀበል እንደሚቀረው፣ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጋር የተፈራረሙባቸው ሰነዶችን ከተቋማት መውሰድና መለየት እንደሚቀረው፣ ጉዳት በደረሰባቸው ፕሮጀክቶች ላይ የባለሙያ የምስክርነት ቃል መቀበል እንደሚቀረው፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ ሰነዶችን ማስተርጎምና በብርበራ የተገኙ ኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን በፎረንሲክ አስመርምሮ ውጤት መቀበልና ሌሎችም ምርመራዎች እንደሚቀሩት በመግለጽ ነው፡፡

‹‹መርማሪ ቡድኑ ጊዜ ቀጠሮ አጠያየቁ ፎርሙላ እየሆነ ነው፤›› በማለት ከተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አንዱ ተቃውመዋል፡፡ ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ መርማሪ ቡድኑ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ የሰጠውን ትዕዛዝ አላከበረም፡፡ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ የተጠረጠረበት የወንጀል ድርሻን ለይቶ እንዲያቀርብ ቢታዘዝም፣ ተግባራዊ አለማድረጉንና የጠየቀው 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ብቻ ተመሳሳይ ጥያቄ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተጠረጠሩባቸው ጉዳዮች ፕሮጀክቶች በመሆናቸው የሰው ማስረጃ እንደማያስፈልግ የጠቆሙት ተጠርጣሪዎቹ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች በመገናኛ ብዙኃን ማስረጃዎችን አጠናቀው ከሰበሰቡ በኋላ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ከገለጹ በኋላ፣ መርማሪ ቡድኑ እነሱን አስሮ ማስረጃ የሚፈልግበት የሕግ አሠራር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ የዋና ኦዲተርን ሪፖርት እንደ አዲስ እንደተቀበለ መርማሪ ቡድኑ መግለጹ፣ ‹‹ተቋሙ መርማሪዎቹን ወይም መርማሪዎቹ ተቋሙን አያውቁትም ማለት ነው፤›› ያሉት ጠበቃው፣ ለመያዛቸው ዋና ነገር የዋና ኦዲተር ሪፖርት መሆኑ ሲገለጽ ከርሞ እንደ አዲስ እንደተገኘ መነገሩን ተቃውመዋል፡፡

ጠበቃው ሌላው ያነሱት ነጥብ፣ እነሱም (ጠበቆቹ) የወንጀሉ ተባባሪ እንደሆኑ በመግለጽ ፖሊስ እየፈረጃቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተው፣ ‹‹ወንጀል አይጣራ የሚል አንድም ጠበቃ አይገኝም፤›› ካሉ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ ሊያርመውና ሊያስተካክለው የሚገባ መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ ደንበኞቻቸውን ማግኘት እንዳልቻሉና ፍርድ ቤቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 እና 21 ላይ የተቀመጡ መብቶች እንዲከበሩ የሰጠው ትዕዛዝ ሊከበር እንዳልቻለ በመግለጽ፣ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል ራሱ ባወጣው እስረኛ የማነጋገሪያ ቀናት (ረቡዕና ዓርብ) እንኳን ሲሄዱ ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ተገልጾ እንደተመለሱ አስረድተዋል፡፡ አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ቋሚ ሕመም ያለባቸውና በቋሚነት የሚወስዱት መድኃኒት እንዳላቸው የገለጹት ጠበቆቻቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው ሳይገናኙና ምግብ በአየር ላይ እየደረሳቸው ሕመማቸውን እንዴት ሊቋቋሙ እንደሚችሉ ግራ መጋባታቸውንም አክለዋል፡፡ አንዳንድ ተጠርጣሪዎች በጡረታ የሚተዳደሩ በመሆኑ፣ በድንገት በመታሰራቸውና የጡረታ መቀበያ መታወቂያቸው በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው በችግር ላይ እንደሚገኙም ጠበቆቻቸው አስረድተዋል፡፡ ከመንግሥት ሥራ ለቀው በግል ሥራ ውስጥ እንደሚሠሩ የገለጹት አቶ በቀለ ባሻ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ደመወዝ የተቀበሉ ዕለት በመሆኑና ገንዘቡም በኤግዚቢትነት የተያዘ በመሆኑ ቤተሰቦቻቸው ችግር ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ከተቋሙ ከለቀቁ አሥር ዓመታት እንዳለፋቸውና ተጨማሪ ምርመራ ተገቢ እንዳልሆነም አቶ የኔነህ አሰፋ የተባሉ ተጠርጣሪ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ቡድን በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በእነ አቶ ፍቃዱ ኃይሌ (ኢንጂነር) ላይም ተመሳሳይ ሥራ መሥራቱን በመግለጽ፣ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በእነ አቶ ፍቃዱ ላይ ተጨማሪ ቀናት በዋናነት ያስፈለገው፣ በእነሱና በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያጣራውና ያደራጀው 26 መዝገቦችን በማግኘቱ፣ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግና የሚያጣራቸውና የሚሰበስባቸው ሰነዶች እንዳሉ በመግለጽ ነው፡፡ መርማሪ ቡድኑ 26 መዝገቦችን እንዴት እንዳገኘ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፣ የእነ ኢንጂነር ፍቃዱን ቤት ሲበረብር፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ያጣራባቸው ሰነዶች ኮፒ በማግኘቱና ተቋሙ እንዲሰጠው በደብዳቤ ጠይቆ ማግኘቱን አስረድቷል፡፡ ሌሎች በርካታ ውል ተፈጽሞባቸዋል የተባሉ የመንገድ ፕሮጀክቶችንና የግዢ ሰነዶችን መሰብሰብ እንደሚቀረውም አስረድቷል፡፡

ኢንጂነር ፍቃዱ ዕድል ተሰጥቷቸው ለፍርድ ቤቱ ሲናገሩ፣ ‹‹መርማሪ ቡድኑ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አገኘሁት ያለው 26 የምርመራ መዝገብ ለእኔም ሆነ ለጓደኞቼ ዱብ ዕዳ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የእኛም አገር ሕገ መንግሥት እንደ ሌሎቹ አገሮች ሕገ መንግሥት የሚሠራ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ሊገነዘብልኝ የምፈልገው፣ ቃሌን የሰጠሁት የሕግ አማካሪዬ በሌሉበት (እንዲገኙልኝ እየጠየቅኩ) በግዳጅ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የተጠረጠሩት ከግዢ ጋር በተገናኘ የግዢን አሠራር በመጣስ፣ በባንክ መሆን የነበረበትን ዋስትና በመቀየር በኢንሹራንስ አድርገዋል በሚል ከመሆኑ ውጪ ሌላ ነገር ባለመባላቸው ተጨማሪ 14 ቀናት መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ የዋስትና መብታቸው ተከብሮም በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና መብት ጥያቄ የተቃወመው ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ፖሊስ መተቸት ባለበት ቦታ መተቸት እንዳለበት፣ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ፎርሙላ እንዳልሆነና መባልም እንደሌለበት፣ ጠበቆች ሊታረሙ እንደሚገባ፣ የዋና ኦዲተር ሪፖርት ለፌዴራል ፖሊስ የደረሰው በቅርቡ መሆኑንና አስፈላጊ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ሊያየው እንደሚችልም ገልጿል፡፡ ፖሊስ ጠበቆችን እንደ ተጠርጣሪዎች እንደማያይና ጠበቆች የፖሊስንም ሆነ የተቋሙን ስም ለማጥፋት የሚያደርጉት በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ ቡድኑ ይዞት የቀረበው ነገር የግል ጉዳዩን ሳይሆን የሕዝብና የመንግሥት ሥራ መሆኑ እየታወቀ አላስፈላጊ አነጋገር መሰንዘርን ፍርድ ቤቱ ሊያርመው እንደሚገባ አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ በሰጠው ትዕዛዝ፣ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ የሠራውና የጥፋቱ ድርሻ ተገልጾ እንዲቀርብ መታዘዙን መርማሪ ቡድኑ አስታውሶ፣ የተወሰኑትን መለየት ቢችልም አብዛኛው ግን ተመሳሳይና ተያያዥ በመሆኑ ለመለየት አለመቻሉን አስረድቷል፡፡ ሙስና ውስብስብና ተያያዥነት ባለው መንገድ ስለሚፈጸም አንዱን ከአንዱ ለመለየት አስቸጋሪ መሆኑንም ገልጿል፡፡ አንድ የሰነድ ማስረጃ ለሁሉም ስለሚሆን እንደሚያስቸግር ገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ሥራው ገና ጅምርና በቀጣይ ብዙ የሚከናወኑ ሥራዎች እንደቀሩት በመግለጽ፣ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ የጠየቀው የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጣሪዎች ከቤተሰብ፣ ከጠበቃና ከሃይማኖት አባት ጋር መገናኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በተደጋጋሚ መናገሩንና ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሶ፣ በቀጣይ መርማሪ ቡድኑ እያንዳንዱ ተጠርጠሪ መቼና በስንት ሰዓት ከጠበቃ ጋር እንደተገናኙ በሰነድ ይዞ በመቅረብ ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ የታመሙ ተጠርጣሪዎች በክሊኒክ፣ በሪፈራል ሆስፒታልና ከዚያም ካለፈ በተቻለው ቦታ ሕክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ባለፉት 14 ቀናት የሠራቸውንና የቀሩትን ሥራዎች የምርመራ መዝገቡን በማየት ፍርድ ቤቱ ግንዛቤ መውሰዱን ጠቁሞ፣ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ በማመኑ ተጠርጣሪዎች የጠየቁትን የዋስትና መብት አለመቀበሉን አስታውቋል፡፡

በመሆኑም መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፍቀዱን ገልጿል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተጠርጣሪዎች አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል በተቀጠሩበት ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ግን ነሐሴ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

ነሐሴ 1 ቀን ተይዘው ነሐሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ የማነ ፀጋዬ ገብረ መድኅን ከወ/ሮ ፀዳለ ማሞ፣ ወ/ሮ ሳባ መኮንንና አቶ ሽመልስ ዓለማየሁ ጋር ነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

Source    –   Ethiopian Reporter