August 15, 2017

አቶ አግባው ሰጠኝ በእስር ቤት በሚደርስበት ተደጋጋሚ ጥቃት ምክንያት
ለህይወቴ ዋስትና የለኝም” አለ !


የሰሜን ጎንደር ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ እና የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆነው አግባው ሰጠኝ ! በህዳር ወር 2007 .ም ጀምሮ እስካሁን በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን “የሽብር” ክስ እስኪ መሰረትበት ድረስ ለ5 ወር ያህል በማዕከላዊ እስር ቤት በምርመራ ወቅት ከፍተኛ ድብደባ የተፈጸመበት ሲሆን፣ለረጅም ቀናት በጨለማ ቤት ታስሮ በቤተሰብ እና በጠበቃ እንዳይጠየቅ ክልከላ ተደርጎበት ነበር።አቶ አግባው ሰጠኝ ክስ ተመስርቶበት ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት ከተዘዋወረ በኋላ በእስር ቤት ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ጥሰት ይፈጸምበት እንደነበር በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት ይገልጽ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፣ “እኔ ዘረኛ አይደለሁም፣ፍጹም ዘራኛ በሆኑ የማረሚያ ቤት አስተዳደሮች እና ጥበቃዎች “ዐማራ” ነህ እያሉ ስቃይና እንግልት እያደረሰብኝ ነወ፡፡” በማለት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 16 ቀን 2008 .ም አቤቱታ አቅርቦ እንደነበረ ይታወቃል። አቶ አግባው ለሚያቀርበው ተደጋጋሚ አቤቱታ ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘቱ በግንቦት ወር 2008 .ም በቂሊንጦ ጨለማ ቤት ውስጥ ታስሮ ለአንድ ሳምንት የዘለቀ የረሃብ አድማ አድርጎ እንደነበር ይታወቃል።

በማንነቱ የተነሳ ስቃይ እንግልት እየደረሰበት ያለው አግባው ሰጠኝ ! በተከሰሰበት የ”ሽብር” ወንጀል ለሁለት አመት ያህል አስከፌ የሆነውን የእስር ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ከተከሰሰበት ክስ በነፃ የተሰናበተ ቢሆንም ፤በ2008 ነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ ከተከሰተው የቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረሃል ተብሎ ሸዋሮቢት ተወስደው ከፍተኛ ድብደባ እና ስቃይ ተፈጽሞበታል:: ከሸዋሮቢት መልስም ለደረሰው ቃጠሎ ተጠያቂ ናቸው ከተባሉት 38 እስረኞች መሃል አግባው ሰጠኝ ይገኝበታል። ነሃሴ 1ቀን 2009 .ም ከቂሉንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ለቀረበበት ክስ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ሊሰሙ በተያዘው ቀጠሮ አቶ አግባው ተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደደረሰበት የተናገረ ሲሆ ” ከቂሉንጦ ዝዋይ ተወስዶ ለ6 ቀናት ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰበት፤ ማታ ማታ መሬት ላይ እያንከባለሉ፣ አንገቴን ረግጠው ደብድበውኛል። ጭካኔ ፈፅመውብኛል። ራሴን ያወኩት ፖንቴን ልበስ ሲሉኝ ነው። አሁን ራሴን ያዞረኛል። ይህ የተፈፀመብኝ በበቀል ነው። ዐማራ በመሆኔ ነው። ይህን ያደረገው የማረሚያ ቤቱ ሀላፊ ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳነ ነው። ዝዋይ ለሚያውቃቸው ሰዎች ” ቂጡንገልባችሁ ግረፉት” ብሎ አዝዞ ነው ያስደበደበኝ!” በማለት ልደታ ምድብ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታው አቅርቦ ነበር።


ሆኖም ግን የአሰረው አካል በዛሬው እለት ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ በሰጠው ምላሽ አቶ አግባው ሰጠኝ ካቀረበው እና ከደረሰበት የሰብዓዊ ጥሰት ፍጽም ተቃራኒ የሆነ ምላሽ ሰጥቷል ።አቶ አግባው የደረሰበትን ድብደባ ልብሱን አውልቆ ለማሳያተ ያደረገው ጥረት በፍርድ ቤት ፍቃድ ሣያገኝ መቅረቱ የሚታወቅ ነው። የማረሚያ ቤቱ ምላሽ ተከትሎ አቶ አግባው ሰጠኝ “ለህይወቴ ዋስትና የለኝም”በማለት ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል ። አቶ አግባው ሰጠኝ ከ15 ዓመት በላይ የፖለቲካ ተሳትፎ ያለው ሲሆን፣በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ በሚሰሩ ፓርቲዎች ውስጥ በመሳተፍ በተለያየ የኃላፊነት ቦታ ያገለገለ ሲሆን፣ ለ5 ዓመት የህዝብ እንደራሴ በመሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበር ሲሆን፤ በማህበራዊ ሕይወቱ እጅግ በጣም ተግባቢ እና በጠባዩ ተወዳጅ እንደነበር እሱን በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ የሚመሰክሩለት ሃቅ ነው።


(
ይድነቃቸው ከበደ)