August 15, 2017 08:0

ወሀት ከምስረታው ማግስት ጀምሮ የአጎራባች ህዝቦች መሬቶችን ቀምቼ የታላቋን ትግራይ ሉአላዊ መንግስት እመሰርታለሁ የሚል እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ጫካ የገባ ድርጅት እንደሆነ ይታወቃል። ጉልበቱን በመጠቀምም ያለቅድመ ሁኔታ መገንጠል የሚያስችል ያልተለመደ አንቀጽ  በህገ መንግስቱ  እንዲካተት አድርጎአል። የእቅዱ ቀሪ ክፍል የሆነውን መሬትና ሀብት  የማሰባሰብ  ስራን  ያለከልካይ ከተያያዘው እነሆ  26 አመታት ተቆጥረዋል። ለአለም አቀፍ ንግድ የሚያግዙ መግቢያና መውጫ አማራጮቹን የማስፋት እንዲሁም ለምግብ ምርት ማምረቻ የሚሆኑ የእርሻ መሬቶች ወደ ክልሉ የማጠቃለል ስራዎች በዚህ የእቅዱ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ። ትመጣለች ተብላ ለምትጠበቀው  ሉአላዊ ትግራይ የኢንዱስትሪ ልማት መሰረት ለመጣል ሲል  ገና በልቶ ካልጠገበው የኢትዮጵያ  ህዝብ ጉሮሮ ላይ ካፒታልና ጥሬ እቃ ይዘርፋል፤ ይነጥቃልም።። ይህ እኔና አንተ/ቺ በእለት እለት ህይወታችን የምናየውና የሚሰማን ጸሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። ማሳዎች ይቅረቡ ለሚል አካል እስኪ ምልከታችንን መረጃ አዘል እናድርገው፡፡

ህወሀት አባሎቹን እያበረታታ ሀብት እንዲያከማቹ ከሚያደርግበት መንገድ መካከል አንዱ ለሌሎች ኢትዮጳውያን የጤፍ ወንፊት የሆነ የመንግስት ባንኮች የብድር አሰጣጥ ስርኣትን ለአባላቶቹ የአሸዋ ወንፊት እንዲሆን መስራቱ አንዱ ነው። ከስምንት ወር በፊት በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ችግሮች መወሳሰብ ተከትሎ  መደበቅ የማይቻልበት ደረጃ በመድረሱ  በአባላቱ የደረሰ ብክነትና ዘረፋን  አምኖ ለመቀበል ተገዶ  ነበር። በጉዳዩ ዙሪያ የቀረበው ሪፖርት እንዳመለከተው የህወሀት ካድሬዎችና ጭፍራዎች የክልሉን ለም መሬት የቀኝ ገዥ ወረራ  በመሰለ መልኩ ዘምተው ተቀራምተውታል። መሬቱን ለማልማት በሚል ስምም መጠኑ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ገንዘብ በኢትዮጵያ ልማት ባንኩ ፕሬዝደንት በህውሃቱ ኢሳያስ ባህረ አመቻችነት በብድር ስም አውጥተው ተከፋፍለውታል። ከዚህ እንደምንረዳው ትንንሽ ሌቦች ላይ ከበሮ የሚያስደልቀው  ህወሀት/ኢህአዴግ  በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በግብርና ልማት ስም ያለ ማስያዣ  ወስደው በየከተማው ህንጻ   የሚያቆሙ አሊያም የገንዘቡን አድራሻ የሚያጠፉ አባሎቹ እንዲበረታቱ በዝምታ  ሲንከባከብ መቆየቱን ይሆናል። በአንድ መሬት ላይ እስከ ሶስት ሰዎች ብድር እንዲወስዱ መደረጉም ማስረጃነቱን ያጠናክረዋል። በቤኒሻንጉል ግሙዝ፣ አፋር እና ደቡብ ኦሞ ያለው የግብርና ኢንቨስትመንት ታሪክ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።  እንደ አንዳንድ ምንጮች ዘገባም ባለሃብት ተብዬ የትግራይ ተዋላጆች በቤኒሻንጉል ግሙዝ፣ አፋር እና ደቡብ ኦሞ  ካለው መሬት ወሳጅ ባለሀብት አንጻር ሲታይ በትንሹ 75% በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ 90%  ይደርሳሉ። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ቤኒሻንጉል ግሙዝ ክልል ሰራተኛ በነበረበት ወቅት የተመለከተውም ሀቅም ነው። ይህም በሀገሩቱ ውስጥ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል የለም የሚለውን ጩሀታችንን ያረጋግጥልናል።

ሌላው ህወሀት ለታላቂቱ የትግራይ መንግስት ምስረታ እየሰራባቸው ከሚገኝበት ዘርፎች መካከል ከአጎራባች ዞኖች መሬት እየነጠቀ አዲስ ካርታ ማተሙ ይሆናል። ከተነጣቂዎቹ ውስጥ ሰሜንና ምህራብ ጎንደር እንዲሁም የሰሜን ወሎ አካባቢዎችን መጥቀስ ይቻላል።  ከድርጅቱ ሰዎች አንደበት አዳልጦአቸው ከሚሰሙ መረጃዎች በመነሳት መሬት የማሰባሰቡ ስራ  ገና እንዳልተጠናቀቀና ሌሎች ይገባናል  የሚሏቸው ቦታዎች እንዳሉም አይተናል። የቅርቡን ብናይ የፍትህ ተሟጋች ነኝ እያሉ ከበሮ ከሚደልቁ ነገር ግን የህወሀት ፈላጭ ቆራጭነት ማብቃት  ላይ ሲደርሱ ወገቤን ከሚሉት ጸሃፊያን መካከል አቶ ዳንኤል ብርሀነ  በፌስ ቡክ ገጻቸው ያሰፈሩትን መልእክት መመልከት ይቻላል። ጎንደሬ ትግራይነቱን  የሚቀበልበት ሁኔታ ይኖር ይሆንን ሲሉ በፈረንጆቹ ኦገስት 11̦ ቀን 2017 በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ጥያቄ አስፍረዋል። ይሄም እስካሁን ከተነጠቁት የአማራና አፋር  መሬቶች ውጪ ሌላም ያልረካ ፍላጎት እንዳላቸው ያመለክታል።

መንግስት ይሁን ነጋዴ ባልለየለት መልኩ ከሀገሪቱ ሀብት በመቀማት የንግድ ድርጅቶችን ማስፋት ሌላው የህወሀት ኢህአዴግ ባህርይ ነው። ሲጀመር በዘረፋ ሲቀጥልም  በብድር ስም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ እየዘረፈ የገነባቸው እነዚህ ግዙፍ የንግድና ኢንደስትሪ ተቋማት ፍትሀዊ ባልሆነ የንግድ ውድድር ተሰማርተው ስለሚገኙ በጥቂት አመታት ውስጥ ከሚሊየርነት ወደ ቢሊየነት ተሸጋግረዋል። በሌላ በኩል የተራ  አባላቱን የስነልቦናና የኢኮኖሚ አቅም  በማሳደግ ላይ የሰራው ስራም ቀላል የሚባል አይደለም። በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች የስነልቦናና የኢኮኖሚ ውድቀትና ዋጋ መክፈል ማለታችን ነው። በአንድ በኩል  በኩል  ለአባላቱ የአዲስ አበባን መሬት እና አነስተኛ ኪራይ የሚከፈልባቸው የመንግስት ቤቶች በማደል መጠመዱን ማንሳት ያስፈልጋል። ለነገዋ ትግራይ የእውቀትና አሰራር ሽግግር እንዲሁም ከጠቅላይነት በሽታው መነሻነት  አባላቱ የስራ አመራር እውቀትና ክህሎታቸውን ኣያወደሙ አንዲያሳድጉ በፌደራልና አዲስ አበባ መስተዳድር ተቋማት ውስጥ ሰግስጎአል።

እስቲ በአካባቢዎቻችሁ ያሉ ወይም የነበሩ ልዩ ልዩ የተሻለ ጥቅማ ጥቅም ይገኝባቸዋል ተብሎ የሚታመኑ ተቋማትና አደረጃጀቶችን አስቡ። ማነው እየመራቸውና እየተጠቀመ  ያለው?  ከእድር ሊቀመንበር ጀምሩ፣  የቤተክርስትያን  አስተዳዳሪዎች፡ የሙያ ማህበራት የሴቶችና እና ወጣቶች ማህበራት አመራሮች፣ የአረጋውያን፡ የልማትና ግብረሰናይ ድርጅቶች መሪዎች፣ ወጣት አስመጪና ላኪዎች እና ሌሎች ዘርፎችም በደጋፊዎቹ እንዲዋጡ ቀጥተኛ ባልሆኑ ስልቶች እየሰራ ይገኛል። ነባር አመራሮቹ እንዲለቁ በመግፋት የራሱን አባላት ወደ ቦታው እንዲደርሱ በተቀናጀ መልኩ በመርዳት። በ push and pull እስትራቴጂ ማለት ነው።   አየር መንገድ፡ ብሄራዊ ደህንነት፣ መከላከያ ሙሉ በሙሉ፣ የመከላከያ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን፣ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ተቋማት፣ የብሮድካስትና መረጃ ደህንነት መስሪያ ቤቶች፣ የግብር እና ግሙሩክ፣ የወሳኝ ተቋማት የቦርድ ሰብሳቢዎች እነማን ናቸው? ይህ በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ዋጋ መክፈል የሚያካሂደውን የቀኝ ገዥነት ተግባር ሳያንሰው  ነጻ ወጥታችሁአል፣ በዲሞክራሲ መንገድ ላይ ናችሁ ማለቱ ምን ይሉታል? መልሱ አንድ ነው። የንቀት ጥግ።

By ሳተናው