August 16, 2017

በዶክተር ዳንኤል ተፈራ፤ የኤኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ኤመረተስ።

የጎንደር ወጣት ሰማእታት የአንደኛ አመት መታሰቢያ ቀን ንግግር፤

ሴንትፖል፤ ምንያፖልስ፤ አሜሪካ፤ ኦገስት 12፣ 2017 ዓ. ም. ።

ክቡራትና ክቡራን እንደምን አላቻሁ? አካም ጅርቱ? ኬሬዎ? ወቾንጌ? ከመይለሁም? ነበድ? አይመላ ዴኤስ? ፈያነ? እላለሁ ከብዙ በጥቂቱ።
ይህን የጎንደር ወጣት ሰማእታት የመጀመሪያ ዓመት መታሰቢያ ቀን ከእናንተ ጋር ለማስታወስ እድል በማግኘቴ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው።

በመጀመረያ፤ አቶ መኮንን ዶያሞን ከልብ አመሰግናለሁ። አቶ መኮንንን ያወቅኋቸው የሲዳሞ ክፍለሀገር ክሚቴ ለማቋቋም በሚያደርጉት ሥራቸው ነው። አቶ መኮንን፤ ኢትዮጵያ በክፍለሀገራዊ ነፃነት መሠረት እንድትደራጅ ጥረት ከሚያደርጉት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።  በዚህ ጠቃሚ ጉዳይ ላይ አስተያዬቴን ለማበርከት  በርሳቸው አማካኝነት ይኸው በእናንተ መሀል እገኛለሁ።

ስሜ ዳንኤል ተፈራ ይባላል። ተወልጄ ያደግሁት ኢትዮጵያ፤ በሲዳሞ ክፍለሀገር፤ በሲዳማ አውራጃ፤ በይርጋአለም ከተማ ነው፡፡ ሙያዬ አስተማሪነት ሲሆን የምርምር ሥራዬም የሚያተኩረው በኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ልማት ላይ ነው።

ዛሬ የምናገረው ኢትዮጵያን በክፍለሀገራዊ ነፃነት ስለማደራጀት ጉዳይ ሲሆን፤ ይህን ሃሳብ የተመለከቱ ወረቀቶች ከዚህ በፊት በኢንተርኔት ማሰራጫዎች ማቅረቤን ላስታውስ እወዳለሁ። በተለይ የዛሬ አመት በጻፍኩት ወረቀት፤ የጎንደር ህዝብ ያነሳውን የነፃነት ጥያቄ ሌሎችም በምሳሌነቱ ሊከተሉት እንደሚገባ ጠቅሻለሁ።
የጎንደር ህዝብ እንቅስቃሴ የተነሳው የጎንደር ኮሚቴ ያቀረበውን ጥያቄ አስመልክቶ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ታሪክ እንዲህ አይነቱ ህብረትና ህዝባዊ እንቅስቃሴ ሲታይ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። በ1981 በምስራቅ አውሮፓ የተካሄደውን ከፍ ያለ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ያስታውሰናል።
የጎንደር ኮሚቴ፤ የተለያዩ የጎንደር ህዝብ ክፍሎች የተወከሉበት ሲሆን፤ የኮሚቴው መሪ፤ ዛሬ በህወሀት አገዛዝ  ታስረው የሚገኙት፤ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ናቸው።
የጎንደር ጥያቄ ትክክለኛ የነፃነት ጥያቄ ነው። እንዲህ ይላል ባጭሩ፤ “ወልቃይታ ጎንደር ነው፤ ጎንደር ኢትዮጵያ ነው፤ አንለያይም፤ ህወሃት አይገዛንም፤ ራሳቻንን እናስተዳድራለን።”
የጎንደር ጥያቄ፤ ለኢትዮጵያ ከፍ ያል ጠቃሚነት አለው። የተቀሩት ክፍለሃገሮች ራሳቸውን የማስተዳደር ነፃነት ለማግኝት እንዲጥሩ ያበረታታል። በነፃነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊ አንድነትን እንዲመሰረት ይረዳል።

ይህ ከግብ ሊድር የሚችለው ግን፤ በመጀመሪያ የጎንደር  ህዝብ ጥያቄ ተጠናክሮ ሲቀጠለ፤ ሁለተኛ በጎንድር ዙሪያ ያሉት ክፍለሀገሮች፤ ማለትም ጎጃም፤ ወሎና፤ ሸዋ ከጎንደር ጋር ሲተባበሩ ነው።

ላለፉት 26  ዓመታት የህወሀት ገዝዎችና ደጋፊዎቻቸው የኢትዮጵያ ማዕከል የነበረችውን የሸዋን ክፍለሀገር በኢኮኖሚና በፖለቲካ አዳክመዋታል። ስለዚህ፤ የሰሜን ክፍለሀገራት ትብብርና ጥንካሬ የትግሬን የበላይነት ለመቋቋም የሚያስችል ሀይል ሊሆን  ይችላል።

እዚህ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ስለሚገኙ የሲዳማ/ኦሮሞ/ሌሎችም ክፍለሃገሮች አስተያየት ለማቅረብ እወዳለሁ። በመጀመሪያ ግልፅ መሆን ያለበት አንድ ጉዳይ አለ።

“ያላዩት አገር አይናፍቅም” ነውና፤ ኢትዮጵያ ብትበታተን የደቡብ ክፍለሀገራት የተሻለ አገር ያገኛሉ ማለት አይደለም። የተሻለ የሚሆነው፤ ለነርሱም ሆነ ለተቀሩት፤  ኢትዮጵያ በክፍለሀገራዊ ነፃነት መሠረት ስትደራጅ ብቻ ነው።

ታሪክ ያወቃቸው የደቡብ ክፍለሀገሮች አርሲ፤ ባሌ፤ ወለጋ፤ ኢሉባቦር፤ ከፋ፤ ገሙጎፋ፤ ሲዳሞና ሀረርጌ ናቸው። እነዚህ በህወሀት ገዝዎች ተሰርዘው፤ በዘር ክፍፍል  መተካታቸው ህዝቡን ጎዳ እንጂ አልጠቀመም።  በተለያዩ ጊዜያት ይህን ችግር ልገነዘብ ችያለሁ።

ለምሳሌ፤ የአገሪቱ ለም መሬት የሚገኘው በደቡብ በኩል ሲሆን፤ መሬቱ ሊታረስና ሊለማ አልቻለም። ካፒታልና የሰው ሀይል በዚህ አካባቢ እንዳይኖር በገዝዎቹና በደጋፊዎቻቸው ሆን ተብሎ የተፈጠሩ እንቅፋቶች አሉ።

ለምሳሌ፤ የህወሀት ገዝዎች ሲናገሩ፤ አገሪቱን በቋንቋ እንጂ በዘር አልከፋፈልንም ይላሉ። ታድያ ከአንድ አካባቢ ወደሌላ አካባቢ ሄደው ለብዙ ጊዜ የኖሩና በዚያም ስፍራ የተወለዱ፤ በልዩልዩ ሞያ ተሠማርተው የሠሩ፤ የአካባቢውንም ቋንቋና ባሕል ጠንቅቀው የሚያውቁ ለምን ከስፍራው እንዲባረሩ ተደረጉ? በግፍ ተገድለዋልም፤ ሕፃናት እንኳን ሳይቀሩ።

የደቡቡ ክፍል፤ የአስተዳደር በደል አልተፈጸመበትም ለማለት ባይቻልም፤ መፍትሄው ግን እንደዚህ መሆን አልነበረበትም።  እርግጥ ነው፤ የደቡቡ ክፍል፤ ከሰሜኑ ጋር ሲነጻጸር፤ ለረጅም ጊዜ አስከፊ በሆነ የመሬት ስሪት እንዲኖር ሆኗል። የፖለቲካ ሥልጣንም ተነፍጓል።

መታየት ያለበት ዋና ጉዳያ ይህ ሆኖ ሳለ፤ መፍትሄ ግን አልተደረገለታም። ለምሳሌ፤ እስከአሁን ድረስ ገበሬው የመሬት ባለቤት አይደለም። መሬት ከመንግሥት እየተከራየ ነው የሚያርሰው። በተጨማሪ፤ በነፃነትና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዲሞክራሲ አልተዘረጋም። እነዚህ ሁሉ መደረግ ሲገባቸው፤ ጸያፍና የሰውን ልጅ አዋራጅ በሆነ በዘር መከፋፈል እንደመፍትሄ ተቆጠረ። እንዲህ ዓይነት አላዋቂነት ራስን ብቻ ከመውደድ ይመነጫል።

የሰው ልጅ በነፃነት ሠርቶ የመኖር መብቱን ኣስካልተነፈገ ድረስ፤ የሀገር ሀብት ይስፋፋል፤ የሁሉም ድርሻና የኑሮ ደረጃ ይሻሻላል። ይህ መብት የተፈጥሮ መብት ሲሆን፤ የሰው ልጅ መንግስት የፈጠረውም፤ ይህን የተፈጥሮ መብቱን ሊያስከብርበት እንጂ፤ የመንግስት አገልጋይና መጠቀሚያ ለመሆን አይደለም።

ኢትዮጵያ፤ የደቡብንም ሆነ የተቀረውን ህዝብ ችግር ልትፈታ የምትችለው፤ በዲሞክራሲ ብቻ ነው። ዲሞክራሲ ማለትም ለራስ የሚፈልጉትን መብት ሌላውን መከልከል ማለት አይደለም። የዘር  ፖለቲካ የተዘረጋው ግን ራስን ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት ስለሆነ ዲሞክራሲን ይጻረራል። የሰውን ልጅ የተፈጥሮ መብት ይነፍጋል።
እንዲህ ዓይነቱ የዘር አስተዳደር ቀንበር በኢትዮጵያ ላይ ሲጫን (ከኢጣሊያን ፋሽስታዊ አገዛዝ በስተቀር) ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። ይህንን መቅፀፍት የጎንደር ህዝብ ከራሱ ላይ አውርዶ ለመጣል እየታገለ ይገኛል።

የለውጥን አቅጣጫ ማወቅ ባይቻልም፤ ለውጥ ገን መኖሩ የማያቀር ነው። ስለዚህ፤ የዛሬ አመት የተነሳው የጎንደር ህዝብ የነፃነት እንቅስቃሴ፤ አዲስ የለውጥ ዕድል ለኢትዮጵያ ህዝብ ፈጥሯል ማለት ይቻላል።

እዚህ ላይ አንድ ነገር መገንዘብ ይገባናል። ዛሬ ከትግሬ ክፍለሀገር በስተቀር፤ የተቀሩት ክፍለሀገራት በዘር ተለያይተው በህወሀት የወታደር ሀይል ታስረዋል። ስለሆነም፤ ትግሬ ራሱን ሲያለማ ሌሎቹ ግን ራሳቸውን እንዳያለሙ ነፃነት ተነፍገዋል።

ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት በንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት ስትገዛ ኖራለች። ይህ ስርዓት፤ ባለንጉሥና ራሳቸውን ያስተዳድሩ የነበሩ አገሮችን፤ በወታደር ኃይል በአንድ ላይ ጠቅልሎ በመያዝ አገሪቷን ሲገዛ ኖሯል። ላለፉት አርባ ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ የንጉሠ ነገሥት መንግሥት ባይኖራትም፤ የፓለቲካው ባህል አልተቀየረም። ኢትዮጵያ አሁንም በወታደር ኃይል ነው የምትገዛው።

አንዱ ሌላውን በመሣሪያ ኃይል የሚገዛበት ኋላቀር ስርዓት ከኢትዮጵያ ጨርሶ ሊጠፋ የሚችለው በህዝባዊ የነፃነት እንቅስቃሴ ብቻ ነው። ስለዚህ፤ የጎንደርን ምሳሌነት በመከተል፤ የተቀሩት ክፍለሀገራት በኮሚቴ ተደራጅተው ለነፃነት በመታገል፤ ኢትዮጵያን በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ነፃ አገር ማድረግ አለባቸው።