August 16, 2017 18:53

በአዲስ አበባ በአፋን ኦሮሞ(ላቲን) የሚያስተምሩ አራት ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል።

በጄ/ል ታደሰ ብሩ ት/ቤት – 4,198 ፣

በጄ/ል ዋቆ ጉቱ ት/ቤት – 1,517 ፣

በቡርቃ ወዮ ት/ቤት – 1,176

እና በጋረ ጉሪ ት/ቤት – 428 ፣ በድምሩ – 7,319 ተማሪዎች እንደተመዘገቡ መረጃዎች ደርሰዉኛል።

ከ15 አመታት በፊትም በአዲስ አበባ የኦሮሞ ት/ቤቶች ተከፍተው የነበረ ሲሆን በወቅቱ በድምሩ የተመዘገቡት ወደ አምስት መቶ ብቻ ነበሩ። በርካታ የኦህዴድ ባለስልጣናት ሳይቀሩ ልጆቻቸዉን ወደ አፋን ኦሮሞ ት/ቤት የላኩበት ሁኔታ አልነበረም። ወደ አምስት መቶ ተመዝግበው ለመማር የመጡት ደግሞ ወደ 90 ብቻ ነበሩ።ከዚህም የተነሳ ብዙ ሳይቆዩ ት/ቤቶች የመዘጋት እድል ነበር ያጋጣማቸው።

እንዴ አዉሮፓዊያን አቆጣጠር፣ በ2007 በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ዉጤት መሰረት፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ወደ 2.9 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን አንደኛ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ የሆኑት ደግሞ ወደ ሁለት መቶ ዘጠና ሺህ የሚጠጉ ነበሩ። (የአዲስ አበባ ህዝብ 10%) ። ከዚህ ሁሉ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ወደ ዘጠና ተማሪዎች ብቻ በአፋን ኦሮሞ ለመማር መቅረባቸው፣ በአዲስ አበባ ያለው የኦሮሞ ማህበረሰብ ልጆቹን በአማርኛ ወይንም የግል ት/ቤቶች እንዲማሩ ፍላጎት እንደነበረው ነው የሚያሳየው።

አሁን የአዲስ አበባ ህዝብ ከሰባት ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ነው የሚገመተው፡፡ እንበል አሁን አሥር በመቶውን አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ነው ብንል ወደ ሰባት መቶ ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ነው ልንል እንችላለን። ከሰባት መቶ ሺህ ህዝብ ሰባት ሺህ ብቻ (1 %) በአፋን ኦሮሞ ለመማር መመዝገቡ በድጋሚ የሚያሳየው አብዛኞቹ የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት ልጆቻቸው በአማርኛ እንዲማሩላቸው መፈለጋቸውን ነው።

እዚህ ጋር ሶስት ነጥቦች አንርሳ፡

1) ጉዳዩ በኦሮሞ ብሄረተኞችና በኦህዴድ ባለስልጣናት ብዙ ቅስቀሳ የተደረገበት መሆኑን፣

2) የተጠቀሱት አሃዞች የተመዘገቡትን እንጂ በት/ቤት ገበታ የተገኙትን እንደማይገልጹና ለመማር የሚመጡት የበለጠ ቁጥራቸው በጣም ያነሰ እንደሚሆን፣

3) የኦሮሞው ማህበረሰብ ልጆቹ አማርኛ እንዲማሩለት መፈለጉ፣ አፋን ኦሮሞን አለመፈለጉን ወይንም የኦሮሞነት ስሜቱ መቀነሱን የሚያመለክት ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ በኢኮኖሚው፣ በሥራ ..ዘርፍ ለመሻሻል አማርኛ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ፣

(ማንም ቤተሰብ ለልጆቹ የተሻለውን ነገር ነው የሚፈልገው። ልጆቹ ተምረው፣ ተሻሽለው፣ ጥሩ ደረጃ እንዲወድቁለት ይፈልጋል።በመሆኑም ኢትዮጵያ ዉስጥ እስከተኖረ ድረስ፣ አማርኛ ማወቅ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ወላጆች ያውቃሉ። አማርኛ አለማወቅ እንደ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ አዋሳ፣ ድሬዳው፣ ደቡብ ክልል፣ አማራ ክልል፣ ቤኔሻንጉልና ጋምቤላ ክልል በመሳሰሉት አብዛኛው የአገሪቷ ክፍሎችና እና በፌዴርል መንግስቱ የመስራት እድል የሚያቀጭጭ በመሆኑም አማርኛን ያስቀድማሉ)

በአጭሩ አነጋገር በአፋን ኦሮሞ ት/ቤቶች መክፈቱ ችግር ባይኖረዉም፣ ሙሉ መብት ቢሆንም፣ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ በማዳበር፣ በማሳደግ አንጻር ግን ሊኖረው የሚልቸው ሚና እጅግ በጣም ቁንጽልና ዉስን ነው። ይልቅስ የተሻለ የሚሆነው አፋን ኦሮሞ በሌላው ማህበረሰብ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ሁሉም ዜጎች በፍቃደኝነት እንዲማሩት የሚደረግበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።

አፋን ኦሮሞ ኦሮሞ ነኝ የሚለው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ቢማሩት ይጠቀማሉ እንጅ አይጎዱም። ይሄም ይሆን ዘንድ፡

1) ላቲኑን ሳይሆን የግእዝ ፊደልን መጠቀሙ በጣም ይረዳል።

2) በሁሉም የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች እንደ ሰብጀክት አፋን ኦሮሞ ቢሰጥ በጣም ይረዳል። ሁሉም ተማሪዎች ከእንግሊዘኛና ከአማርኛ በተጨማሪ ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ እንዲማር አስገዳጅ የትምህርት ፖሊሲ ቢወጣ፣ አፋን ኦሮሞ እንደ ሶስተኛ ቋን ተማሪዎች በምርጫ ሊማሩት ይችላሉ። ሌሎች ቋንቋዎች ሊመርጡ የሚችሉ ሊኖሩ ቢችሉም በአብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ ግን አፋን ኦሮሞን ይመርጣል የሚል እምነት ነው ያለኝ።

ያው እንደተለመደው በግእዝ ፊደል ላይ፣ በአማርኛ ላይ ጥላቻ ያላቸው ሰዎች፣ ላቲኑ ይቅር በማለታችን አንዳንድ ኦሮሞን የማይወክሉ ጥቂት የኦሮሞ አክራሪዎች፣ “ጸረ-ኦሮሞ” ሊሉን ይችላሉ። ሆኖም ግን የማን ሐሳብ በርግጥ ለአፋን ኦሮሞ እድገት እንደሚጠቅም፣ ማን ጸረ-ኦሮሞ እንደሆነ ግን ራሱ የኦሮሞ ማህበረሰብ ጠንቅቆ ያውቀዋል።