የብዙ የአለማችን ሀገራት ህዝቦች ከጭቆና የተላቀቁበትን ሂደት ስናስብ በጋራ አቋም ገዥዎችን በመታገላቸው መሆኑን እናያለን። በሀገሬ  ሁለተኛ ዜጋ አልሆንም የሚል መራር የጋራ  አቋም። የሃገራችን ህዝቦችም ከወያኔ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት  የተለያየ ስፋትና ጥልቀት ያላቸው ትግሎችን አድርገዋል ። ለአብነት የቅርቦቹን መጥቀስ  ይቻላል። በ1997 ምርጫ ዋዜማና ማግስት በመላ ሀገሪቱ እንዲሁም ላለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ፣ አማራ እና በአንዳንድ የደቡብ ክልል ቦታዎች  የሚካሄዱ ተከታታይ ተቃውሞዎች  በማስረጃነት ሊቀርቡ ይችላል። ታዲያ የሀገራችን ህዝብ ጨቋኝና ዘረኛውን የወያኔ ስርዓት እንዴት ማስወገድ አቃተው? መጠየቅ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ። በዚህ ጽሁፍ ከብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ውስጥ ከውስጣዊ ጎራ የሚመደበውና ለስርዓቱ እድሜ መርዘም ትልቅ ድርሻ ያለውን የሆዳም የህዝብ ልጆች ሚናን ለማሳየት እሞክራለሁ።

የህዝቡን ጭቆና በቃኝ ትግል ወደ ሃላ እየጎተቱና ውሀ እየቸለሱ ያዳከሙት ህብረተሰባችን “እድግ በልልኝ” እያለ ያሳደጋቸው እነዚሁ ሆዳምና ራስ ወዳድ ልጆቹ ለመሆናቸው  ብዙ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። እነዚህ ሆዳሞች ያደረሱትን የጉዳት መጠን በተሻለ ለማየት እንዲቻል በሁለት ከፍዬ አቀርባቸዋለሁ። በመጀመሪያ ረድፍ የሚገኙት በአቋራጭ ለመለወጥ ጓጉተው  ወያኔ  በኦሮሞ፥ አማራ እና ደቡብ ህዝቦች ስም ባቋቋማቸው አሻንጉሊት  ድርጅቶች ስር በተራ አባልነት የተሰለፉት ናቸው። ዲሞክራሲና የስልጣን ክፍፍል አለ ለሚለው ዲስኩሩ ስለረዱት ወያኔ ይፈልጋቸዋል። ሁለተኛው መደብ ደግሞ ከመንጋ አባላት የተመረጡና ወያኔ ህዝባቸውን እንዲገርፉ ጅራፍ ሲያቀብላቸው ስንት ግዜ ልግረፍ በማለት  ታዛዥነታቸውን ለማሳየት የሚያሽቃብጡትን ይይዛል። እነዚህ በሁለት የከፈልናቸው ሆዳም የሀገራችን ልጆች ለምን ህሊናቸውን ይሸጣሉ የሚለውን እስቲ እንመልከት።

ከመጀመሪያዎቹ እንጀምር። እነዚህ መንጋ ሲሆኑ ተሰብስበው የሚነገራቸውን ከመስማት ውጪ ሚና የላቸውም። አንዳንዴ የሰሙትን   መልሶ ለተሰብሳቢ ጓደኞቻቸው በመንገር በመስመር ውስጥ ነኝ የሚለውን መልእክት እንዲያስተላልፉ ይጠበቅባቸዋል። በአሻንጉሊቶቹ ብአዴን፣ደህዴን እና ኦህዴድ ስር ተደራጅተው ወርሃዊ መዋጮ ያዋጣሉ። ወያኔም በበኩሉ መዋጮአቸውን ለማካካስ ልዩ ልዩ ስብሰባዎችና መድረኮች እያዘጋጀ አበል ይከፍላቸዋል። ወሬ ማቀባበል ይጠበቅባቸዋል። ብዙዎቹ በአካዳሚክና ማህበራዊ ህይወታቸው ደካሞች ናቸው። ወያኔ እነዚህን የሚፈልጋቸው ለመዋጮአቸው አይደለም።  ይልቁኑ  የብዙ ብሄር ልጆች ያቀፈ ድርጅት እንደሆነ ለማስመሰያ እና ማደናገሪያነት እንጂ ።  መታዘዝን ህሊናና ክብርን በሚያቆሽሹ ልምምዶች በማለፍ እንዲካኑ ይደረጋል። አብዛኛው በመንጋነት ሲቀጥል ጥቂቶች በተከታታይ ፍተሻ ውስጥ አልፈው  የአባትና እናቶቻቸውን ኑሮ  በስቃይ ለመሙላት በተለያየ እርከን በሃላፊነት ስራ ላይ ይመደባሉ።  ወያኔ ህዝብን እንዲንቅ በማድረግ ላይ  ያላቸው ሚና ትልቅ ነው። ሆዳም እስካለ ምን እሆናለሁ በሚል።

በቀጣይ የምናያቸው  ካለማንገራገር ትእዛዝ በመቀበል፣ በመዋሸትና በክህደት ልምምድ ህሊናቸውን በመግደላቸው  በተለያዩ ደረጃ ባሉ የወያኔ ድርጅታዊ ጽ/ቤቶች እና ከቀበሌ እስከ ፌደራል ባሉ የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ ግልጽና ግልጽ ያልሆነ ሀላፊነቶች ተሰጥቶአቸው የሚሰሩ ናቸው።  ባላቸው አቅምና እውቀት ሊያሳኩት የማይችሉት ቁሳቁስ፣ ገንዘብና ስልጣን ስለተሰጣቸውም ወያኔን ለማስደሰት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።  በአቅራቢያቸው ካለ የወያኔ ድርጅታዊ ጽ/ቤት ያለምንም ጥያቄ ትእዛዝ በመቀበል በሚያስተዳድሩት ወሰን በሚገኝ ህዝብ ላይ መተግበር ዋነኛ ስራቸው ነው። ርካሽነት ህይወታቸውን  ሁሌ ስለወረሰው ደስታ አልባ፣ አስመሳይ፣ ስጉና ተናዳጅ ናቸው። በምድር ላይ ከሚንቀሳቀስ ሰብዓዊ ፍጡር ውስጥ ለህዝባችን ስቃይ ከነሱ በፊት ሌላ ተጠያቂ ሊኖር አይችልም፤ የህወሀት ምሽግ ስለሆኑ። እነሱ ከሌሉ ህልውናው ያከትማል። ዘራፊነት መለያቸው ነው። ወያኔም ይህን ዝርፊያቸውን  ይፈልገዋል፤ ያስደስተዋልም።

ለነዚህ ሆዳሞች ምክሬ አንድ ነው። እራሳችሁንና ህዝባችሁን እያስናቃችሁ  ከማገልገል ቢረፍድም እራሳችሁን ነጻ አውጡ የሚል። ያኔ ወያኔ መሽሸጊያ እይኖረውም። ትግላችንም በትንሽ መስዋዓትነት እና ግዜ ፍጻሜውን ያገኛል።