ባለፈው በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በሚገኘው ¨The Brookings Institution” በዴሞክራሲ ዙሪያ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ተሳትፌ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ከተጋበዙት እንግዶች ውስጥ የቀድሞ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር “Madeleine Albright” ይገኙበታል። በንግግራቸው ወቅት ሽብርተኝነት ለዴሞክራሲ አደጋ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። በውይይት ወቅት ለቀድሞዋ የአሜሪካ የውጪ ሚኒስትር ጉዳይ አንድ ጥያቄ አንስቼላቸው ነበር። እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራት ዜጎች እየተሸበሩ ያሉት በአሸባሪዎች ሳይሆን በፀረሽብር ሕጉ እንደሆነ በመግለፅ በአሸባሪዎች (terrorists) እና በጨቋኞች (Tyrants) መካከል ያለውን ልዩነት እንዲነግሩኝ ጠይቄያቸው ነበር።

በአሜሪካ መንግስት ፊት አውራሪነት የተጀመረው አለምአቀፉ የፀረሽብርተኝነት ትግል እንደ አልቃይዳ ባሉ የሽብር ድርጅቶች በምዕራባዊያን ሰላምና ዴሞክራሲ ላይ የጋረጡትን አደጋ ለማስወገድ ዓላማ ያደረገ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ የአሜሪካኖች የፀረሽብር ዘመቻ በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኢሲያ ላይ አሰቃቂ ጦርነት እና ዕልቂት አስከትሏል። እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራት ደግሞ የፀረሽብር ዘመቻው በቀጥታ ፀረዴሞክራሲ ሆኗል። በፀረሽብር ትግሉ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የፀረሽብርተኝነት አዋጁ ነው።  

ኢህአዴግ መንግስት የፀረሽብርተኝነት አዋጁን በማውጣት በፀረሽብር ስም ሕዝቡ በማሸበር ላይ ይገኛል። የፀረሸብርነት አወጁ ከአሸባሪዎች ጋር ፍፁም ተመሳሳይ የሆነ ዓላማና ግብ አለው። ከአሸባሪዎች የበለጠ ዜጎችን በፍርሃትና ስጋት የሚያርድ ነው። ይህ ሕግ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከመሸራረፍና ከሕገመንግስቱ መርሆች ጋር ተፃራሪ ከመሆኑም በተጨማሪ መሰረታዊ ዓላማው ህዝቡን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል ሳይሆን ንቁ የሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ተሳትፎ እንዳይኖር ማድረግ ነው። የፀረሽብርተኝነት አዋጁ ከወጣ በኋላ ባሉት ጥቂት አመታት የፖለቲካ ነፃነት የሚባል ነገር ተሟጥጦ ጠፍቷል። 

በኢትዮጲያ የፀረሽብር ሕግ መሰረት ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ “በአሸባሪነት” ሊያስከስስ ይችላል። ለምሳሌ፤ “‘የፀረሽብር ሕጉ ይሻሻል!’ የሚል መፈክር ይዛችሁ ውጡ” ማለት – “አመፅና ሁከትን በማነሳሳት – ‘inciting violence and protest’” በሚል ያስከስሳል፤ በሰላማዊ ሰልፍ መንገድ ከተዘጋ – “የሕዝብ አገልግሎትን በማቋረጥ – “disruption of public services’” በሚል አንቀፅ፤ ሰልፈኞቹን “አይዟችሁ በርቱ” ብሎ የተናገረ – “ለአሸባሪዎች የሞራል ድጋፍ በመስጠት – ‘providing moral support or …advice’”፤ “አግ7 ወይም ኦነግ በሰላማዊ መንገድ’ ለመታገል ቆርጧል” ማለት – “አሸባሪነትን በማበረታታት – ‘encouragement of terrorism’” በሚለው አንቀፅ ያስከስሳል። 

በዚህ መሰረት የሀገራችን የፀረሽብርተኝነት አዋጅ የዜጎችን ነፃነት የሚገድብና የፍርሃትና  ስጋት ምንጭ እንደመሆኑ ከሽብርተኝነት ተለይቶ አይታይም። እንደ የቀድሞዋ የእንግሊዝ የሀገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊ “Eliza Manningham Buller” አገላለፅ “…What terrorism does is frighten us through its random effect and deter us from behaving normally. But we compound the problem of terrorism if we use it as a reason to erode the freedom of us all.” 

ሽብርን በሌላ የሽብር ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በራሱ አሸባሪነት ነው። የሽብር ወንጀልን ለመከላከል በሚል የወጣው የኢትዮጲያ የፀረሽብርተኝነት አዋጅ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት በመገደቡ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ሳይሆን፣ የአሸባሪዎች ዓላማና ግብ ማስፈፀሚያ ሆኗል። በመሆኑም፣ የጨቋኞች ፀረሽብርተኝነት በተግባር አሸባሪነት ነው። 

የኢትዮጲያ የፀረሸብርተኝነት አወጅ፤ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚሸራርፍና የሕገመንግስቱ መርሆች የሚፃረር፤ በዚህም ከአሸባሪዎች ጥቃት የበለጠ ኢትዮጲያኖችን እያሸበረ ነው። በተለይ ለአዲሱ ትውልድ ትልቅ የፍርሃትና ስጋት ምንጭ ሆኗል። አብዛኞቹ በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙ መከራና ግፍ እየተፈፀመባቸው ያሉት እስረኞች የዚህ “አሸባሪ ሕግ” ሰለባ ናቸው። 

ለዚህ ደግሞ ethiotrailtracker.org የተሰኘው ድህረገፅ ያዘጋጀውን ዝርዝር እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ድረገፁ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ክሳቸውን በእስር ሆነው የሚከታተሉ እና ጉዳያቸው የተዘጋ በድምሩ የ1405 ዜጎችን ስም ዝርዝር እንደሚከተለው አጠናቅሮታል። 

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ክሳቸውን በእስር ሆነው የሚከታተሉ እስረኞች ዝርዝር  (ብዛት 879) ይህን ማያያዥ (Link) በመጫን በፒዲኤፍ ማግኘት ይችላሉ። 

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የተፈረደባቸው [አሁንም በእስር የሚገኙ ወይም ፍርዳቸውን ጨርሰው የተፈቱ] ፣ ክሳቸው የተቋረጠ እና በነፃ የተለቀቁ እስረኞች ዝርዝር (ብዛት 526) ይህን ማያያዥ (Link) በመጫን በፒዲኤፍ ማግኘት ይችላሉ። 

https://ethiothinkthank.com/