Posted by | September 22, 2017

 የምትባል አነስተኛ ከተማ ታገኛላችሁ፡፡ የከተማዋና የወንዟ ስም አንድ ነው፡፡ አርኖ ላይ ወርዳችሁ ወደ ቀኝ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል በእግራችሁ ስትጓዙ ሜዳውን ትጨርሱና ገደሉን ፊት ለፊት ትጋፈጡታላችሁ፡፡ በገደሉ መካከል እንደ ሞሰበ ወርቅ በተሸለመች ተራራ አናት ላይ የሰንደባ ኢየሱስ ወተክለ ሃይማኖትን ጥንታዊ ደብር ታገኙታላችሁ፡፡

የደብሩ ካህናት የቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ ከአንድ ሺ ዓመት በላይ እንዳለፈው ይናገራሉ፡፡ በአካባቢው የምናገኛቸው የሥነ ሕንጻና አካባቢያዊ ማስረጃዎች ደግሞ ታሪኩ ቢያንስ ሰባት መቶ ዓመት ሊሆነው እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ የሰንደባ ኢየሱስ ወተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሥነ ሕንጻው ከዛግዌ ዘመን፣ አካባቢያዊ መረጃዎቹ ደግሞ ከ13ኛውና 14ኛው ዘመን ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ክብ ሆኖ ውጩ በጭቃ የተገረፈ ነው፡፡ የጭቃ ግርፉ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የደረሰውን የመፍረስ አደጋ ለመታደግ በአካባቢው ባለሞያዎች የተገነባ ነው፡፡ ወደ ውስጡ ሲዘልቁ ግን ሁለት ጥንታዊ ክፍሎችን ያገኛሉ፡፡

የደብሩ መስኮቶች እንደ ይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ወጥ እንጨት የተሠሩ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ መስኮት ያራሱ ቅርጽ ያለው ሲሆን፣ አንደኛው ከሌላኛው የተለየ ዲዛይን አለው፡፡ ብዙዎቹ መስኮቶች ለውበት የተሠሩ እንጂ የሚከፈቱ አይደሉም፡፡ የመስኮቶቹ መቃኖች ከአንድ ወጥ እንጨት ወጣ ብለው የተሠሩ፣ በአራቱም መዓዝን ወጣ ወጣ ያሉ ጌጦች ያሏቸው ናቸው፡፡ ይህ አሠራራቸው ከይምርሐነ ክርስቶስ አሠራር ጋር ያዛምዳቸዋል፡፡ ሰንደባ ኢየሱስ ወተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያንን ከይምርሐነ ክርስቶስ ጋር የሚያዛምዳቸው መስኮታቸው ብቻ አይደሉም፡፡ የመቅደሱ ግድግዳ አሠራርም ተመሳሳይ ነው፡፡ ግድግዳው በቀጫጭን ጠፍጣፋ ድንጋዮች እየተሰካካ፣ በኖራ መሰል ነገር እየተያያዘ ቀጥ ብሎ የተሠራ ነው፡፡ እጅግ የሚገርመው ግን ድንጋዮች የተያያዙበት ኖራ መሰል ነገር የተለሰነበት መንገድ ነው፡፡ የደብሩ ሊቃውንት ኖራ ከተነከረ ቆዳ ጋር እየተያያዘ እንደተሠራ ይናገራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ከውጭ ክብ ቢሆንም ሁለቱ የውስጥ ክፍሎቹ ግን አራት መዓዝን ናቸው፡፡ መዓዝኖቹ በርግጠኝነት 90 ዲግሪ ናቸው፡፡ ወደ ላይም በቱምቢ ሲለካ ቀጥ ብሎ የወጣ ወጣ ገባ የሌለው ነው፡፡

በግድግዳው አማካይ በሐረግ የተጌጠ ነው፡፡ ጌጡ ከጥግ እስከ ጥግ በሁለት ወይም በሦስት መሥመር እየተዘረጋ ተገጥግጧል፡፡ ከመስኮቶቹ በላይ ደግሞ ሌላ ጌጥ አለ፡፡ በመስኮቶቹ መቃን ርዝመት ልክ ከአንድ ወጥ እንጨት የተሠራ ሐረግ፡፡ ይህ ሐረግ በመስኮቱ ላይ በቻ ሳይሆን ከበሩ በላይም እንዲሁ በየመዓዝናቱ ተሰክቶ ይታያል፡፡
አራት መዓዝኑ የመቅደሱ ግንብ ለስድስት ሜትር ያህል ወደ ላይ ከወጣ በኋላ መቅደሱን ከጣራው ጋር በክብ ግድግዳ ያያይዘዋል፡፡ ወደ ቅድስቱ መግቢያው በር የጥንቱን ይዘት አልለቀቀም፡፡ በአራት ደረጃ የተሠራው መቃን በሥዕል የተሞላ ነው፡፡ በመጨረሻው መቃን ላይ ደግሞ የአሥራ አምስቱ ነቢያት ሥዕል በትንንሹ ተሥሎ
ይታያል፡፡

ከበሩ በላይ ሌላ ጌጠኛ መስኮት አለ፡፡ መስኮቱ ባለ ሦስት መቃን ሲሆን ሦስቱም በሥዕል ያጌጡ ናቸው፡፡ የሚገርመው ግን መስኮቱ ለውበት የተሠራ እንጂ የሚከፈት መስኮት አይደለም፡፡ ከአንድ ወጥ እንጨት የተቀረጸው
መስኮት የመስኮቱ ውስጣዊ አካል ራሱ በቀለም ያሸበረቀ ነው፡፡ የመስኮቱ ውስጣዊ አካል ደግሞ እርስ በርሳቸው በተያያዙ ክቦች ቅርጽ የተሠራ ነው፡፡ እያንዳንዱ ክበብም የየራሱ ቀለም ተቀብቷል፡፡ ዋናው በር በበሩ ላይ የቅዱሳን መላእክት ሥዕል በትልቁ ተሥሎበታል፡፡ ሥዕሉ እንዳይበላሽ በመጋረጃ የተጋረደ ሲሆን ሥዕሉን ባለ ሦስት ደረጃ መቃን አጅቦታል፡፡ ወደ በሩ የመግቢያው ደረጃ ከእንጨት የተሠራ ባለ ሰባት እርከን ነው፡፡ ሊቃውንቱ የሰባቱ መዓርጋት፣ የሰባቱ ሰማያትም ቢሉ ምሳሌ ነው ይላሉ፡፡ ከበሩ ግራና ቀኝ ቢያንስ አራት መቶ ዓመታትን የዘለቁ፣ የሥዕል አጣጣላቸው ከጎንደር ዘመን ቀደም ያሉ ዓመታትንና የጎንደርን ዘመን አሻራ ያዙ ሥዕሎች አሉ፡፡

በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ መንበር የሚመስሉና የቤተ ክርስቲያኑን ቅርጽ የያዙ ወጥ ከሆነ እንጨት የተቀረጹ ሳጥኖች አሉ፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ቅዱስ ላሊበላ ሕንጻዎቹን ከመውቀሩ በፊት ዲዛይኑን በእንጨቶቹ ላይ ማስቀመጡን ይናገራሉ፡፡ በሰንደባ ኢየሱስ ወተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያንም የመቅደሱን ቅርጽና የመቅደሱን ሐረጎችና በሮች ቅርጽ ያዘ አነስተኛ መንበር መሰል ነገር አለ፡፡ እንደ እኔ ግምት ቤተ ክርስቲያኑ ሲታነጽ የቤተ ክርስቲያኑ ቅርጽ አራት መዓዝን የነበረ ይመስላል፡፡ በኋላ ሲፈርስ ለማደስ ሳይሆን አይቀርም ውጩ ክብ የሆነው፡፡ የመቅደሱ ታችኛው ግድግዳ በዕውቅ ጠራቢ ተስተካክለውና አምረው በተጠረቡ ግዙፍና አራት መዓዝን በሆኑ ዐለቶች የተገነባ ነው፡፡ የዚህ ግድግዳ አሠራሩ በአኩስም ከተገኙ የጥንት መቃብሮች አሠራር ጋር የተዛመደ ነው፡፡ ዐለቶቹ እርስ በርስ የተገጣጠሙበት መንገድ ትኩረት ቢደረግበት ለዛሬውም የግንባታ ችግሮቻችን መፍትሔ የሚሰጡ ናቸው፡፡

የሰንደባ ኢየሱስ አስደናቂ ታሪክ የሚጀምረው አሁን ቅድስት የሆነውን ክፍል ሲገልጡት ነው፡፡ ቅድስቱ ሁለት ክፍል ያለው እጅግ ሰፊ ክፍል ነው፡፡ ምናልባትም በጥንቱ አሠራሩ ይኼ መቅደሱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በቅድስቱ ውስጥ ያለው ውስጠኛው ክፍል ባለ ሦስት በር ሲሆን የግራና ቀኙ በር ቅስት መልክ ሲኖረው፣ የመካከለኛው በር ግን የከፊል ክብ መልክ ያለው ነው፡፡ ግድግዳው ከጥርብ ድንጋይ የተሠራ፣ በዓምዱ መጨረሻ ላይ ዓምዱን ከቅስቱ የሚያያይዙ መከዳዎች የተሠሩለት ጌጠኛ ግድግዳ ነው፡፡

በውስጠኛው ክፍል ውስጥ የሚገኙት ሦስት መናብር ለየት ያሉ ናቸው፡፡ መካከለኛው መንበር እጅግ ግዙፍ ከመሆኑም በላይ አሠራሩ የላሊበላን መናብርት የመሰለ ነው፡፡ በግራና በቀኝ ያሉት መናብርት እስካሁን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ካየኋቸው መናብርት ለየት ያሉ ናቸው፡፡ ቅርጻቸውም የኦሪቱን መንበረ ታቦት የሚመስሉ ሲሆኑ ካህናቱ መሥዋዕተ ኦሪት ሲሠዋባቸው የነበሩ ናቸው በማለት ይገልጣሉ፡፡ በላያቸው ያለውን ጌጥና ቅርጽም ጊዜ ወስዶ ማጥናት ይጠይቃል፡፡
በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ጥንታዊ ሚዛን፣ ከድንጋይ የተሠራ አገልግል፣ ከአንድ ወጥ እንጨት የታነጸ የመብራት ማብሪያ፣ ከአንድ ወጥ እንጨት የተሠራች አገልግል፣ የኦሪቱን የመሰለ የዘይት ማብሪያ ይገኛል፡፡ አሁን አገልግሎት
የማይሰጥ ‹ተሰማ ጎንደር›. የሚባል ከበሮም ነበራቸው፡፡ ይህ ከበሮ በማኅሌት ጊዜ ሲመታ እስከ ጎንደር ከተማ ይሰማ ስለነበር ‹ተሰማ ጎንደር›.ተብሎ መሰየሙ ይነገራል፡፡

ሰንደባ ኢየሱስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን አካባቢውም ከመካከለኛው ዘመን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአካባቢው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ የሚነገረው ታሪክ፣ የአሥራ ሁለቱ ንቡራነ እድ ቦታዎች ናቸው ተብለው የሚነገሩት ቦታዎች፣ ደብሩ ከአቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ ጋር ተያይዞ የሚነገርለት ታሪክ፣ ጠለቅ ብለው ቢጠኑ በሀገራችን የሕዝቦች መስተጋብርና በቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን አገልግሎት ላይ ተጨማሪ ዕውቀት የሚሰጡን መረጃዎችን ልናገኝ እንደምንችል መገመት ይቻላል፡፡ የአካባቢው ሽማግሌዎችና የየደብሩ ታሪክ ሰንደባ( ታዴዎስ)፣ ጉርሐች( ኤልሳዕ)፣ቀልቀል( ገብረ ዮሐንስ)፣ ምጓዕ(በርሶማ)፣ ጥቃራ( መርሐ ክርስቶስ)፣ ደብረ ቅድስት(ጳውሎስ)፣ ዳንጉሬ(ቀሌምንጦስ)፣ ሰውበዳ(ዮሐንስ ከማ)፣ ዋሻ(እንድርያስ)፣ ገረገራ(አኖሬዎስ)፣ አግድ(እጬ ፊልጶስ)፣ ውሻ ጥርስ( እጬ ፊልሞና) ቦታቸው መሆኑን ይገልጣል፡፡ የሰንደባ ኢየሱስ መጽሐፍ ‹ቡራኬ ዘሰንደባ ታዴዎስ፣ ሲመት ዘኤልሳዕ፣ ወመጽዑ ፲ወ፪ ንቡራነ ዕድ ዘሀገረ ሴዋ ዘደብረ ሊባኖስ – ቡራኬ የሰንደባ ታዴዎስ፣ ሹመት የኤልሳዕ ነው፤ አሥራ ሁለቱ ንቡራነ ዕድ በሀገረ ሸዋ ከምትገኘው ደብረ ሊባኖስ መጡ› ይላል፡፡

እጅግ አስደናቂው ነገር አዲስ የሆነ የንቡራነ ዕድ ዝርዘር እዚህ ማግኘታችን፣ ከንቡራነ ዕዱ መካከልም ታዴዎስ፣ ኤልሳዕ፣ አኖሬዎስ፣ ፊልጶስ በሌሎች መጻሕፍት ከሚገኙት ዝርዝሮች ጋር ተመሳሳይ ሲሆኑ – ገብረ ዮሐንስ፣ መርሐ ክርስቶስ፣ ጳውሎስ፣ ቀሌምንጦስ፣ ዮሐንስ ከማ፣ እንድርያስ፣ እጬ ፊልሞና በንቡራነ ዕድ ዝርዝር የምናገኛቸው አዳዲስ ስሞች ናቸው፡፡ እነዚህን አድባራት በእነዚህ ቅዱሳን ርስትነት ቢጠሩም የየደብሩ ታቦታት ግን በሌሎች ቅዱሳን ስም የሚጠሩ ናቸው፡፡

ይህ ጉዳይ ሁለት ነገሮችን እንድንገምት ያደርጋል፡፡ በዛሬው ወሎና ኤርትራ እንደነበረው የአሥራ ሁለት አበው ሥምሪት በጎንደር አካባቢም ነበር ማለት ነው? ይህ ከሆነ ደግሞ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ሥምሪት የሚያጠናክርልን ተጨማሪ ነገር አገኘን ማለት ነው፡፡ ወይስ ደግሞ የአካባቢው ቃላዊና ጽሑፋዊ መረጃ እንደሚገልጠው ከደብረ ሊባኖስ የተነሡ አሥራ ሁለት ንቡራነ ዕድ ወደዚህ አካባቢ መጥተው ነበርን?

ያ ከሆነ ደግሞ በዚህ ዝርዝር ያገኘናቸውን አዳዲስ ንቡራነ ዕድ ታሪካቸውን መፈለግ የግድ ይለናል ማለት ነው፡፡ ሁሉም ተጨማሪ ጥናት የሚጠይቁ ፍንጮች ናቸው፡፡ ፍላጎትና ዕውቀት ያለው ሰው አጥንቶ ቢነግረን እንመርቀዋለን፡፡

 

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት