23 Sep, 2017

በ ጋዜጣዉ ሪፓርተር

መንግሥት በፌዴራል ሥርዓቱ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ፖለቲካዊ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ፣ በጊዜያዊ መፍትሔ ላይ ያተኮረ ዕርምጃ መውሰድ ላይ በማተኮሩ ውጥረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተን ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የቋንቋ ፌዴራሊዝም ሥርዓቱን መንግሥት እንዲፈትሽ ጠየቀ፡፡

ኢዴፓ ዓርብ መስከረም 12 ቀን 2010 .. ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ሰሞኑ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች ተነስቶ የነበረው ግጭት አድማሱን እያሰፋ እንዳይሄድ ከፍተኛ ሥጋት እንዳለው ገልጿል፡፡

ኢዴፓ በመግለጫው፣ ‹‹አስቀድሞ የፌዴራል መንግሥቱና የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናት ግጭቱን ለመከላከልና ጉዳቱን ለማስቀረት ያደረጉት ጥረትም ሆነ፣ ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ የተሰጠው ምላሽ አዝጋሚ መሆን ጉዳዩን ከፍተኛ እንዳደረገው ፓርቲያችን ተገንዝቧል፤›› ብሏል፡፡

መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የፌዴራል ሥርዓቱን አወቃቀር ከቋንቋና ከብሔረሰባዊ ማንነት በተጨማሪ ሌሎች ለመከባበርና ለመቻቻል፣ እንዲሁም ለጠንካራ አገራዊ አንድነት መሠረት የሚጥሉ መሥፈርቶችን ያካተተ በማድረግ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባም ገልጿል፡፡

ግጭቱን በተመለከተ ሁለቱ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ችግሩን ለመፍታት በማለት እየወሰዱ ያሉትን የጅምላ እስርና የኃይል ዕርምጃ በአስቸኳይ በማቆም፣ ከግጭቱ በስተጀርባ ያለውን ማንኛውንም የጥፋት እጅ አድነው እንዲይዙም ጠይቋል፡፡

ኢዴፓ በግጭቱ ምክንያት በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም ጠይቋል፡፡

ኢዴፓ በ2008 .. እና በ2009 .. መጀመርያ ላይ በአገሪቱ የነበረው አደጋና ግጭት በተደጋጋሚ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች ዋነኛው ምንጭ፣ የኢሕአዴግ ቋንቋንና ብሔረሳባዊ ማንነትን ያማከለ የፌዴራል ሥርዓት ነው የሚል ዕምነት አለው፡፡ ‹‹ሥርዓቱ ከአንድነት፣ ከመቻቻልና ከመከባበር ይልቅ የጎሪጥ ለመተያየትና ለእኔ ብቻ የሚል የጠባብነት ስሜትን የሚፈጥር ለልዩነት በር የሚከፍት ነው፤›› ያለው ኢዴፓ፣ መንግሥት ይኼንን ሥርዓት እንዲፈትሸው ጠይቋል፡፡

Author

anon