welkait.com welkait.com

እንደሚታወቀው ወያኔ በ1983 ዓ/ም አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኃላ የወልቃይትንና የጠለምትን ሙሉ መሬትና ጠገዴን ደጋማውን ማለትም ሰሊጥና ጥጥ የማያመርተውን ክፍል በመተው አብዛኛውን የእርሻ ኢንቨስትመንት ቦታዎችን ወደ ትግራይ አካልሏል፡፡

በግዜው የአማራው ጠገዴና የትግራዩ ጸገዴ ብለው የከፈሉትን አንዱን የአማራ መሬት የሆነውን ጠገዴ ድንበር ሶሮቃ ወንዝ ተደረገ፡፡

ከዛም በበድኑ ብአዴን አማካኝነት እስከ በ1990 ዓ/ም አከባቢ በአማራ ክልል ስር ሲተዳደሩ የቆዩቱን ሙሉ በሙሉ የወልቃይት ጠገዴ አማሮች የሚኖሩባቸውን ጎቤና ግጨው የተባሉትን ሁለት ቀበሌዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለትግራይ ክልል አስረከቧል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስም አሁን ጎቤ የተባለችው ቀበሌ እስከ 1998 ዓ/ም ታችኛው ሶሮቃ (ላይኛው ሶሮቃ ደግሞ አሁን ሶሮቃ የምትባለው ቀበሌ ናት) ተብላ ነበር የምትጠራው፡፡ ሁለቱም ታችኛውና ላይኛው ሶሮቃ የተባሉበት ምክንያት ሶሮቃ ወንዝ ከላይና ከታች ዳር ሆነው ስለተቆረቆሩ ነው፡፡ ከዛም ታችኛው ሶሮቃ ወደ ትግራይ ከተካለለች በኃላ ግን ወያኔ ቀስበቀስ ስሙን ወደ ጎቤ ቀየረው፡፡ አሁንም ሌላ አዲስ ድንበር ተደረገ፡፡

ይሄ የወንበዴ ስብስብ ቀጥሎ ደግሞ ይሄንን ድንበር ተሻግሮ ግጨውንና ጎቤን አልፎ በአማራ ክልል ስር የሚስተዳደሩትን እነ ስላንዲ፣ማይምቧና አየር ማረፊያ የሚባሉትን የጠገዴ የእርሻ ኢንቨስትመንት ቦታዎች የኛ ቦታዎች ናቸው በማለት ገበሬውን ከርስቱ ሊያፈናቅሉት ተነሱ፡፡ ከገበሬው ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው ነፍሱን ይማረውና በአባታችን ጎቤ መልኬ መሪነት በ2006 ዓ/ም ስላንዲ ጦርነት ተካሂዶ ብዙ የትግራይ ልዩ ሃይል ፖሊስ አፈር ደሜ በልቷል፡፡

ከዛ በኃላ ግን እነ ደጀኔ ማሩ የሚመሩት ህጋዊ ኮሚቴ ተቋቋሙ “አንድ ጠገዴ እንጂ ሁለት ጠገዴ የለም” የሚል ጥያቄ ይዘው ለዓመታት ያክል ከቀበሌ እስከ ፌደሬሽን ምክር ቤት ቢመላለሱም ምንም መልስ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡

ከዛም የጨነቀው የትግራይ ክልል መንግሥት በሽምግልና እንደራደር ብሎ ከአማራው ክልል ጠገዴ እነ ደጀኔ ማሩ 15 ሰዎች ሁኖው ወደ ትግራይ ከተካለለው ጠገዴው ደግሞ በተወሰኑ የአከባቢው ሆድ አድር ካድሬዎችና ከትግራይ የመጡ የትግራይ ተወላጅ ሽማግሌዎች አንዴ ሶሮቃ፣አንዴ ዳንሻ እየተመላለሱ ሽምግልናው እየተካሄደ ያለ ምንም መፍትሄ ለብዙ ግዜ ቆይቷል፡፡ በዚህ መሃልም የወልቃይት የአማራ ብሄርተኝነት የማንነት ጥያቄ ተነሳ፡፡ ከዛም ፌደሬሽን ም/ቤት የጠገዴን ኮሚቴ ጠርቶ የናንተን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ እንመልስላችኃለን ነገር ግን ወልቃይትን ላትጠይቁን ፈርሙልን ብለዋቸው ነበር፡፡ ኮሚቴውም እኛ የጠየቅናችሁ ሌላ ነው የወልቃይት ኮሚቴ ደግሞ ሌላ ጥያቄ ነው ብለዋቸዋል፡፡

ሳጠቃልለው:- ወያኔ አሁን እነ ደጀኔን፣ነፍሱን ይማረውና ጎቤንና እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን በየእስር ቤቱ ከወረወረ በኃላ መለስኩ ያለው ጥያቄ የእቃ እቃ ጨዋታ ነው፡፡ ሲጀመር ጎቤና ግጨው አሁን ሳይሆን ለትግራይ የተሰጡ በ1990 ዓ/ም ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን ብአዴን ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎችን አስመለስኩ ብሎ ሲያደነቁረን የነበረውም እዛው በአማራ ክልል ስር የሚስተዳደሩ ነገር ግን ትግራይ ክልል የይገባኛል ጥያቄ ያነሳባቸው የእነ ስላንዲ፣አየር ማረፊያና ማይምቧ የሚባሉት የእርሻ ኢንቨስትመንት ቦታዎች በጎቤ መሪነትና በአከባቢው ገበሬዎች ተቃውሞ ወደ ትግራይ ሳይከለሉ የቀሩትን ቦታዎችን ነው፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ውሳኔ በአማራ ክልል ስር ከሚተዳደረው ደጋማው የጠገዴ ክፍል መሰረተ ልማት ተሟላላቸው የሚባሉት ቀበሌዎች ወደ ትግራይ ክልል እስከ መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ/ም ትካለላላችሁ እንደተባሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ሲገልጹ ነበር፡፡

ወልቃይት ጠገዴ አማራ ነው!!