October 9, 2017 15:47

“ኦሮሞነት – እስቲ እንወያይ” እና “አማራነት – እስቲ እንወያይ” በሚሉ ርእሶች አንዳንድ ጥያቄዎች አቅርቤ ነበር። በርካታ አስተያየቶች ደርስዉኛል። በተለይም የዘር ነገር በከረረበት አገር በጣም ቀላል የሆነች ጉዳይ የሰዎችን ነርቭ ልትነካ እንደምትችል ይገባኛል። አይምሯችን በዘር አጥር ውስጥ ከታጠረ ከሌሎች ማእዘናት የማየት አቅም ብዙ ጊዜ ያንሰናል።

አቅርቢያቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል የአማራ ክልልን በተመለከተ “አማራ ሳይንት (ቤተ አማራ) ከሚባለው ወደ ምእራብ ሰሜን ወሎ አካባቢ ካለው ትንሽ ግዛት ውጭ አማራ የሚባል አካባቢ በታሪክ ነበር ወይ ? ( በጣሊያን ጊዜ ፋሺስት አሁን ደግሞ በሕወሃት አገዛዝ አማራ ካለው ውጭ) በታሪክ “አማራ” ይባል ከነበረው አካባቢ ጎን ለጎ፣ ላስታ፣ ጎጃም፣ በጌምድር፣ ሸዋ …ተብለው የሚጠሩ አካባቢዎች አልነበሩም ወይ ? ከነበሩ ታዲያ በታሪክ በጌምድር ፣ ጎጃም ፣ ሸዋ “አማራ” ነበር ማለት እንችላለን ወይ ? ሸዋ መሰረታችው ከአስኩም ከሆኑት ከአጼ የኩኖ አምላክ ዘመን በፊት በአብዛኛው ሙስሊም የነበረና የይፋት መንግስት (ሱልጣኔት) ስር አልነበረም ወይ ?” ፣ ኦሮሚያን በተመለከተ ደግሞ “ ባሌ፣ ጂማ፣ ሸዋ ….. የሚል እንጂ ኦሮሚያ የሚባል ቦታም ይሁን አካባቢ ሕወሃት ስልጣን ከመጨበጡ በፊት፣ በጣሊያን ጊዜ ሳይቀር ኖሮ ያወቃል ወይ ? ሸዋ ፣ ሃረርጌ…ኦሮሞዎች ብዙዎችን ቦታ ከመያዛቸው በፊት በአብዛኛው ሙስሊም የነበሩና የይፋት ፣ከዚያም አዳል በመሳሰሉ መንግስት (ሱልጣኔትቶች) ስር አልነበረም ወይ ?አሁን አርሲ ባሌ የሚባለውን ቦታ ጨምሮ ትልቅ ግዛት የነበረ፣ የሃዲያ መንግስት ወይንም ሱልጣኔት አልነበረም ወይ” የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ።

ከአክሱም መውደቅ በኋላ፣ ሰሜን ኢትዮጵያ (ትግሬ፣ በጌምድር፣ ደምቢያ፣ ቋራ፣ ላስታ፣ አማራ/ሳይንት ወይም ቤተ አማራ ፣ግማሹ ጎጃም፣ ወሎ) መቀመጫቸው በላስታ(ላሊበላ) ባደረጉ በዛግዌይ (አገው) ነገስታት ስር ነበሩ። በሸዋ፣ መቀመጫቸዉን ተጉለት ያደረጉ የሸዋ ሱልጣኖች ከ895 ዓ.ም ጀመሮ ይገዙ ነበር። የሸዋን ሱልጣን በማሸነፍ በሸዋ ስር የነበሩ የይፋት አዉራጃ ገዢ፣ እንደ ዋላላ፣ ተጉለት ያሉ ቦታዎችን ተቆጣጠርሩ። የይፋት ሱልጣኔት/መንግስት ተጀመረ። ከዚያ በሁዋላ መቀመጫቸውን ዘይላ (የሶማሌ ላንድ ታሪካዊ የወድብ ከተማ) በማድረግ የይፋት ሱልጣኖች አሁን ሶማሌላንድ የምትባለውንን፣ ጅቡቲን፣ አብዛኛውን ሃረርጌን እና ሸዋን ጨመረው መግዛት ጀመሩ።

የአክሱም ነገስታት ዘር ነኝ ይሉ የነበሩት አጼ የኩኖ አምላክ የላስታን ነገስታት በመፍራት ወደ ደቡብ፣ ወደ ሸዋ ዘልቀው በተጉለት ይኖሩ ነበር። በ1287 አካባቢ ጦራቸውን አስተባብረው የላስታን መንግስት አስወገዱ። የላስታን ግዛት የነበረዉን ብቻ ሳይሆን ከይፋት መንግስት የወሰዱትን አብዛኛዉን ሸዋ በግዛታቸው ስር አካተቱ። አጼ የኩኖ አምላክ የአክሱም መንግስት እንዳስቀጠሉ ቢገለጸም፣ መቀመጫቸውን ግን አክሡም አላደረጉም ነበር። የሸዋ ሱልጣኔት መቀመጫ የነበረችዉን ተጉለትን ነበር ዋና ከተማቸው ያደረጉት።

ከአጼ ተኩኖ አምላክ ቀጥሎ የነገሱ የተለያዩ እንደ አጼ አምደጽዮን፣ አጼ ዳዊት ያሉ የሽዋ ነገስታት አብዛኛው የኢትዮጵይ ግዛት አስገብረው እንደነበረ ታሪክ ይነግረናል። የተወሰነ የባሌ ግዛትን ያካትት የነበረው የሃዲያ ፣ የይፋትና የባሌ ሱልጣኖችም ለሸዋ ይገብሩ የነበረ ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ አንገብርም በሚል ጦርነቶች ተደርገዋል። ጦርነት እና ሰላም ሲፈራረቁ ቆይተው በ14ኛው ክፍል ዘመን የይፋት መንግስት ፍጻሜ ሆነ። በምትኩ ዋና ከተማዉን ዳካር (አሁን ጭናክሰን የሚባለው ቦታ) ያደረገ የአዳል መንግስት ተተካ። በአዳልና በሸዋ መንግስት መካከል ጦርነቱ ቀጠለ።
ከዚህ እንግዲህ የምንማረው ቢያንስ ከአስራ ሁለተኛው እስከ አስከ አስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ፣ በሸዋ፣ በሃረርጌ፣ በሶማሌላንድ በፑትላንድ፣ በጅቡቲ፣ በአፋር፣ በአርሲና በባሌ ይገዙ የነበሩት በዋናነት የይፋት/አዳል ሱልጣኔቶችና የሸዋ ነገስታት ነበሩ።

በጎንደር፣ በትግራይ በኤርትራ እንደ በጌምድር፣ ቋራ፣ ደምቢያ፣ ጎጃም፣ ላስታ ፣ አማራ(ሳይንት) ..የተባሉ የተለያዩ አውራጃዎች ቢኖሩም ከአሥራ ስድስተኛው ከፍለ ዘመን በፊት፣ ከላስታና ከሸዋ ነገስታት ዉጭ የነበረ አካባቢ ስለመኖሩ ብዙ የተጻፈ ነገር የለም።

በዚህ ወቅት ከባሌ በስተደቡብ በገዳ ስርአት የሚተዳደሩ የኦሮሞ ፊዴረሽን የሚባል ነበር። በአሥራ ስድተኛው ክፍለ ዘመን ኦሮሞዎች ወደ ሰሜንና ምስራቅ በመዝለቅ መስፋፋት ጀመሩ። በምስራቅ ሙስሊም በሰሜን ደግሞ ክርስቲያን እየሆኑ ከሶማሌው፣ ከአማራው፣ ከሃዲያው፣ ከሲዳማው … ጋር ተደባለቁ። በሸዋ የሰፈሩት የሸዋ መንግስት አካል ሆነው ቀጠሉ። ወደ ሃረር ደግሞ ተመሳሳይ ሁኔታም ነበር። ለምሳሌ በጨለንቆ ጦርነት የአጼ ሚኒሊክ ጦርና የሃረሩ ኤሚር አብዱላሂ በሚዋጉበት ጊዜ ፣ ኦሮሞዎች በሁለትም ወገን ነበሩ። የሸዋ ኦሮሞዎች በአጼ ሚኒሊክ ወገን፣ የሃረር ኦሮሞዎች ደግሞ በኤሚር አብዱላሂ ወገን ሆነው ነበር የተዋጉት።

ለዚህ ነው አማራ ወይንም ኦሮሞ የሚባል፣ ከተወሰኑ አዉራጃዎች ውጭ በስፋት እንደ አገር ወይንም የአሱ መንግስት ኖሮ አያውቅም የምንለው።

አማርኛ ተናጋሪዎችና አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች በተለያዩ ጊዜያትና ወቅት በጦርነት በመስፋፋታቸው በብዙ ቦታዎች አማርኛና አፋን ኦሮሞ ይነገራል። ያ ማለት ግን ከደቡብ ባሌ የመጡና ከአማራ ሳይንት የመጡ ነበሩ ማለት አይደለም። ሶማሌው ከኦሮሞው፣ ኦሮሞው ከአማራው በጣም የተደባለቀ ነው። ኦሮሞ ሆነው አማርኛ የሚናገሩ ( እንደ አብቹ ኦሮሞዎች)፣ አማራ ሆነው አፋን ኦሮሞ የሚናገሩ ብዙ ናቸው።፡የኦሮሞ መሬት፣ የሶማሌ መሬት የአማራ መሬት ብሎ አገሪቱዋን መሸንሸን ለዚህ ነው አስቸጋሪ የሆነውን ለደም መፋሰስ ምክንያት የሆነው። በታሪክ ያልነበረ፣ የሕዝቡን ትስስርና አብሮነት ከግምት ባላስገባ መልኩ፣ በስልጣን ለመቆየት ሲባል ብቻ ነው የዘር ሽንሸናው በሕወሃትና በኦነግ የተዘረጋው።

የሚያሳዝነው ይሄ የዘር ሽንሸናና የዘር ፖለቲካ ላለፉት 26 አመታት በሕወሃትና በኦነግ ከመጠን በላይ ስለተራገበ አሁን ደግሞ እንደ ጃዋር ያሉ አዛማቾች ስላሉ፣ አንድ ትዉልድን በአስተሳሰብ ተመርዟል። ለብዙዎች መፈናቀል፣ ለብዙዎ መገደልም ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር ለወደፊቱን ትልቅ አደጋ በአገሪቷ እንዲጋረጥ አድርጓል።
(በሃረርጌ፣ ሸዋ፣ አርሲ፣ ባሌ ….ያሉትን እንደ ምሳሌ አቀረብኩ እንጅ በጂማ፣ በወለጋ፣ በኢሊባቡርም ኦሮምዎች ተስፋፍተው አካባቢዉን ከመዉረራቸው በፊት ሌሎች መንግስታት ነበሩ። የከፋ፣ የአናሪያ፣ የዳሞት ….መንግስታት የሚባሉ)

በመጨረሻ አንድ ነጥብ ላስቀምጥ። “በታሪክ የኦሮሚያና የአማራ ክልል ባይኖርም ፣ ሕወሃትና ኦነግ በሕዝቡ ላይ በሃይል ቢጭኑትም ችግር የለውም። ከዚህ በፊት የነበሩ የአስተዳደር ግዛቶች በሃይል አይደለም ወይ የተዘረጉት ? “ ብለው የሚከራከሩ አሉ። ትክክል ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ በሕዝብ ፍቃድ የተመሰረተ አወቃቀር ኖሮ አያውቅም። ግን አሁን ባለው አወቃቀር ያልተደሰተ ነገ እርሱ ደግሞ ሃይለኛ ሲሆን በጉልበት እንዲቀይረው ነው የሚፈለገው ?

በ21ኛ ክፍለ ዘመን በጉልበት ሳይሆን በሕዝብ ፍላጎት ዘለቄታ ባለው መልኩ ችግሮችን መፍታት ያስፈለጋል በሚል ነው በተለይም የአማራውና የኦሮሚያ ክልሎች ፈርሰው ህዝብ በፈለገው መልኩ ግዛቶች እንዲዋቀሩ የምንጠይቀው። በተለይም አማራና ኦሮሞ ከማንም በላይ የተደባለቀ ነው። በመሆኑም የአማራና የኦሮሞ ክልል ብሎ መክፋፈል ጠቃሚ አይደለም። ኦሮሞዉም፣ አማራውም ሌላው እኩል የሆኑባቸው፣ ለአስተዳደር አመች የሆኑ አስተዳደሮች ነው የሚያስፈልጉት። “አይ አማራ ጠላታችን ነው። ኢትዮጵያን አንፈልግም። የአረንግጓዴ ቢጫ ቀ ሰንደቅ ስናይ ደም ብዛታችን ይነሳል” የሚሉ የከረረ አቋም ያላቸው አሉ። እነዚህን መቼም አስገድደን ኢትዮጵያዊነትን ተቀበሉ ልንላቸው አንችልም። የፈለጉትን ነን ማለት ይችላሉ። እኛ ምን አገባን።፡ ግን አብዛኛው አማራው ሆነ ኦሮሞ በአማራነት ሆነ በኦሮሞነት ጠቦ መቀጠሉን የሚፈልግ አይመስለኝም።