(ቢቢኤን ዜና) በአዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ በተለምዶ አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ መግባትና መዉጣት እየተከለከለ መሆኑ ታወቀ። በልማት ስም ነዋሪዎች ተፈናቅለው በርካታ ቤቶች የፈረሱበት አሜሪካን ግቢ የብዙ ደሃ ነዋሪዎች ህይወት የተመሰቃቀለበት እንደሆነ ይታወቃል።ተለዋጭ ቤት ያላገኙ ተፈናቃይ የአሜሪካን ግቢ ነዋሪዎች ላስቲክና ሸራ ዘርግተው በዳስ ዉስጥ የሚኖሩ መኖራቸው ቢታወቅም ወደ ዉስጥ እንዳይገቡ ፖሊስ እየከለከላቸዉ መሆኑን ለቢቢኤን ገልጸዋል።

ወይም ተለዋጩ ቦታው አይመጥነንም ያሉ ቤተሰቦች መድረሻና ማረፊያ የሌላቸው በመሆኑ ቦታዉ ላይ ዳስ ሰርተው እንደሚኖሩ ይገልጻሉ።

እነዚሁ ነዋሪዎች «እቃችንን ከሰራነው ዳስ ገብተን እንዳናወጣ መንግስት መግቢያና መዉጫዉን በፖሊስ አጥሮ እያሰቃየን በመሆኑ እሮሮአችንን ህዝብይስማልን» ሲሉ ይጣራሉ።ቤታቸው የፈረሰባቸው የአሜሪካን ግቢ የቀድሞ ነዋሪዎች መካከል ተለዋጭ ቦታን ያገኙ መኖራቸው ይታወቃል።ባንጻሩ ተለዋጭ ቦታን ያላገኙ አሜሪካን ግቢ በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሰፈሩበት ቦታ ሲሆን ጠንከር ያለ የንግድ እንቅስቃሴ የሚታይበት ቦታ እንደነበር ይታወቃል። በህወሃት የሚመራዉ መንግስት ቦታዉን በልማት ስም ካፈራረሰዉ በሗላ በስፋራው ለአያሌ አመታት ሰፍረው የነበሩ ነዋሪዎች ህይወት መናጋቱ ቢታወቅም የሚመለከተው አካል አመርቂ መፍትሄን ማምጣት ባለመቻሉ ዜጎች አደጋ ላይ መዉደቃቸው አነጋጋሪ እየሆነ ነው።

ሰዎች የተፈናቀሉበት ልማትና እድገት በተቀላጠፈ መልኩ ባልተከናወነበት መልኩ የብርድ፣የዝናብና የበሽታ ሰለባ በመሆን ዳስ በመስራት በጊዜያዊ መጠለያ ዉስጥ የሰፈሩ ሰዎች ያስቀመጧቸዉን እቃዎች እንዳያነሱ ወይም በእቃዎቹ እንዳይገለገሉ በመደረጋቸው በጣሙን ይማረራሉ «አገር አልባ የሆንን መስሎንእንድንሸማቀቅ ሆነንናል! » ሲሉም ይገልጻሉ።

ማደሪያ ቦታ ተከራይተን ለመኖር አቅም የለንም።ቤት ለመከራየት በቂ ገንዘብ የለንም። ወደ ዳሳችን እንዳንገባ መደረጋችን ደግሞ ድርብ ጭቆና ነዉ የሚሉት ነዋሪዎች ለቢቢኤን በላኩት በድምጽና በፎቶ የተደገፈ ማስረጃ ክልከላዉን የሚያስፈጽሙት የፖሊስ አካላት ወደ አሚኤሪካን ግቢ ማስገባትና ማስወጣቱ ላይ ምንም አቅም እንደሌላቸዉና ከበላይ አድርጉ የተባሉትን የሚያስፈጽሙ መሆናቸዉን በአዘኔታ ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ቢቢኤን ሁናቴዉን ለማጣራት ወኪሉን ወደ ቦታዉ ልኳል። ፖሊሶቹ መታወቂያን በማየት የተወሰኑ ሰዎችን ፈትሸው የሚያስገቡ ሲሆን ክልከላዉን ግን በተግባር ሲያስፈጽሙ የሚያመላክት የድምጽ መረጃን ለመያዝ ችሏል።