October 9, 2017

የመጀምሪያዎቹ የክርስቶስ ተከታዮች የክርስትና ዕምነትን ለማስፋፋት በየአገሩ ተሰማሩ:: ጊዜውም የከፋ ስለ ነበር የሮማ ገዢዋች አሰደዱአቸው ሐዋሪያትም እንደምንም እየተሽሎክለኩ ደቀመዛሙርትን አፈሩ:: በየአገሩ ዞረው ዞረው ደቀመዛሙርትን ካፈሩ ቦሃላ እነዚያ መጀመሪያ ላይ ያፈሩቸው ደቀመዛምርትን እምን ደረጃ ላይ እንደደረሱ ላማየት ሲመለሱ ነገር ዓለሙ ተዘበራርቆባቸው ጠበቃቸው:: ዋነውን አሳዳጅ የሮማውን መንግስት ጨርሶ ረሱት ሊከተሉት የተጠመቁለትንም ክርስቶስን ረሱት::

ዓላማቸውን ስተው ተከፋፍለው ጠበቁአቸው: ያስተማሩአቸውን ሐዋሪያትን ብቻ ስም እየጠሩ እኔ የጳውሎስ ነኝ::” “እኔ የኬፋ ነኝ::” “እኔ የአጵሎስ ነኝ::” ” እኔ የክርስቶስ ነኝ::” እያሉ የእኔ መምህር ከአንተ መምህር ይልቃልበማለት ከዘጠኝ በላይ ተከፋፍለው ተጣልተውና ተኮራርፈው ጠበቁአቸው:: ይህንን ጉድ ያልጠበቀው ሐዋሪያው ጳውሎስ በጣም አዝኖ ተበሳጭቶና ተቆጥቶ ለቆሮንጦስ ሰዋች በመጀመሪያው መልዕክቱ ክርስቶስ ተከፋፍላልንአላቸው::

በተመሳሰይ ሁኔታ አገራችንን ኢትዮጵያን የኢሕአዴግ እኩይ ሃይል ጥፍንጎ ይዞአት ሊያጠፋት ለሀያ አምስት ዓመታት ተግተው ሲሰሩ:: ይህንን የኢሕአዴግ እኩይ ተግባር ከአገርና ከህዝብ ጫቅና ለማላቀቅ ከአገር ርቀው የሚገኙ በውጪ አገር ያሉ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች እኔ የእገሌ ነኝ እኔ የእገሌ ነኝበመባባል ተከፋፍለው ይገኛሉ እውነት አገራችን ኢትዮጵያ ተከፋፍላለችን? ስንትስ ኢትዮጵያ ነው ያለችው? እባካችሁ እነንት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራሮች እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች መልሰልኝ::

ሐምሌ ነሐሴ አልፎ መስከረም ሲጠባ እንኮን ሰው ወዳጁን ይጠይቃል ባዳ” የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል በየትኛውም አገር እንደ አገሩ ወግና ልማድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው:: ተወልደን ባደግንባት በአገራችን በኢትዮጵያም ዘንድ ደግሞ ልማዳችንና ወጋችን እጅግ ከመጠንከሩ የተነሳ ጶጎሜ ከገበ ጀምሮ ሁሉም በየቤቱ እንደ አቅሙ ሸብ ረብ ነው:: እኛም በውጪ አገርም የምንኖር ኢትዮጵያውያን ለአዲስ ዓመት ወይም ለዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ዝግጅታችንም ሆነ አከባበራችን በጣም ጠንካራና ደስ የሚል ነው::

አዲስ ዓመት የሁሉ ነገር መጀመሪያ ነው ስለሆነም ነው እያንዳንዱ አገር ባለው የቀን መቁጠሪያ ተመርኩዞ የተለያዩ እቅዶችን በአዲሱ ዓመት መግቢያ ወር ላይ የሚጀምራው:: ያቀደው ነገር በዓመቱ መጨረሻ ሊሳካም ወይም ላይሳካም ይችል ይሆናል ዋናው ቁምነገር ግን በዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ለማሳካት የታሰበ እቅድ መኖሩላይ ነው:: ለእቅዱ አለመሳካት የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ እነዚህን ምክንያቶች ለይቶ ማወቅ በራሱ የእቅዱ አንድ አካል በማድረግ እንደገና ለመጪው አዲስ ዓመት ለተሻለ እቅድ ግባት ይሆናሉ::

የዘንድሮ የኢትዮጵያውያን አዲስ አመት ከግለሰባዊ አሊያም ከድርጅት ፋይዳ በላይ አገራዊና ህዝባዊ የለውጥ ፋይዳ የበዛ እንደሚሆኑ ምልክቶች አብዝተው ይታያሉ እነዚህ ምልክቶች ከባለፈው ዓመት የተሸጋገሩ የለውጥ ምልክቶች ናቸው በመሆኑም ለለውጥ የተነሳሳው ለውጥ ፈላጊ ለውጡ የሚከሽፍበት አንዳችም ስለመኖሩ እጠራጠራለው ክሽፈት ቢያገጥመው እንኮን ወድቆ ለመነሳት ቡዙ ግዜ የሚወስድበት አይመስለኛም::

ካለፈው ዓመት ወደ አዲሱ አመት የተሸጋገሩት የለውጥ ምልክቶች ከሞላ ጎደል የምከተሉት ይገኛሉ

() የኦሮሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በተለያዩ ቦታዎች ያደረጉት ያልገዛም ባይነት ሰላማዊ ተቆውሞ እስከ ህይወት መሰዋትናት::

() የጎንደር ህዝብ ወልቃይት የአማራ ክልል እንጂ የትግራይ አይደለም በማለት ነፍጥ አንስቶ በቃኝ ኢሕአዴግ ብሎ የተታካሰበትና የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም የኔም ደም ነው ብሎ ከኦሮሞ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር አብሮ የቆመበት::

() የጎጃም ህዝብ እምቤ ለሀገሬ እምቤ ለወገኔ ብሎ ከወንዶምቹ ከኦሮሞ ተወላጆችና ከአማራ ተወላጆች ጋር በጋራ ቆሞ ገዢውን ምንግስትና ተከታዮቻቸውን ያርበደበት አመት ነበር::

() በዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ እምነቶች መካከል ክርስትና እና እስልምና ዋንኞቹ ናቸው:: እነዚህን እምነቶች በመቀበል እኛ ኢትዮጵያውያን ከቀዳሚዋቹ መካከል እንገኛለን ክርስትናንና እስልምናን እምነት ከመቀበላችን ባሻገር የተቀበልነውን እምነት በህግና በስራአት አክብሮ በመያዝና ተከባብሮ በመኖር ወደር አይገኝልንም:: ገዢው መንግስት በልማት ስም የአምልኮ ቦታዎችን በመድፈርና ቤተ ክርስቲያንን በማርከስና የሁለቱን የሃይማኖት አባቶችን በማሰርና በመግደል መላውን ኢትዮጵያዊ አስቆጥቶል::

() በተለያዩ ቦታዎች የድንበር ግጭቶች መከሰት በምስራቅና በደቡብ; እንዲሁም የተለያዩ የጎሳ ጥያቄዎች ማለትም ወልቃይትና ቅማንት መጥቀስ ይቻላል; ሌላው ደሞ የአመቱ መጨረሻ አካባቢ በነጋዴው ህብረተሰብ ላይ የተጫነው ከአቅም በላይ የግብር ክምርናሌሎች በርከት ያሉ ያልጠቀስኮቸው ሁሉ ከአምናው ወደ ዘንድሮ የተሻጋጋሩ ሲሆኑ እነዚህ ሁሉ መልስ የሚሹትና መንግስትን ወዶ ሳይሆን ተገዶ ወደ ክብ ጠረንጴዛ እንዲመጣና አገራዊ ውይይትና አገራዊ እርቅ ማድረግ እንዳለበት የማስገደጃው ግዜው አሁን መሆኑን በውጪም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያኖች እንስማማለን የሚል እመነት አለኝ::

ይህንን አገራዊ ውይይትና አገራዊ እርቅ አሻፈረኝ የሚል ከሆነ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሲንከባለሉ በመጡት ህዝባዊ አመጾችና በህዝባዊ ትግል 2010 /ም የመጨረሻው መሆን አለባት በማለት ሁላችንም ቃል ኪዳን መግባት አለብን እላለው:: “ጠፍረን ጠፍንገን እንሰረው ሁለት ሺ አስርን በአንድነት ገመድ ወደ ሁለት ሺ አስራ አንድ የኢሕአዴግ መንግስት እንዳይረማመድ

መውደቅ መነሳት ከሚንቀሳቀስ ነገር የሚጠበቅ ክስተት ነው መንቀሳቀስ ሲባል ደሞ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ በሚገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ፖለቲክኞች; በሃይማኖት ተቆማት: በሲቭክ ማህበራት እና በመሳሰሉት ሁሉ እንቅስቃሴው በትጋትና በመተባበር መሰልቸትና ድካም በማይታይበት ሁኔታ የሚደረግ ጠንካራ እንቅስቃሴ ነው::

ይህ እውን ሆኖ እንዲወጣ የአገራችን የኢትዮጵያና የህዝቦቾ ጉዳይ ይመለከተናል የምንል በዊጪ አገር የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይመለከተናል በተለይ በተለይ ደሞ መሰረታቸውን በዊጪ አገር አድርገው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ባለፈው አንድ ዓመትና ሁለት አመት በየጎራቸው ድርጅቶችን አሰባስበው የሚገኙት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ; የአርበኞች ግንቦት ሰባትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት በጋራ ሆነው የሚያግባባቸው መርሆዎች አውጥተውና መክረው በዊጪ አገር ያለውን ኢትዮጵያዊ ሃይል ሁሉ ሊጠቀሙበት የሚችሉበት ሰዓቱ አሁን ይመስለኛል::

እኛም በመላው አለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እነዝሂን ድርጅቶች ገንዘብ ያለው በገንዘቡ; እውቀት ያለው በእውቀቱ ጉልበት ያለው በጉልበቱ ለመርዳትና ለማጠናከር በአዲሱ ዓመት ለአገራችን ለኢትዮጵያና በኢሕአዴግ ግፈኛ አገዛዝ ሲር ላለው ህዝባችን ቃልኪዳን መግቢያችን ሰዓት አሁን ነው ብለን ማመን አለብን::

እነንተም ስማችሁን ከላይ የጠቀስኩት የፖለቲካ ድርጅቶች የአገራችንንና የህዝባችንን ሰቆቃ ከመቼውም በላይ ተግንዝባችሁ የድርጅታችሁ ህልውና እንደተጠበቀ ሆኖ በሚያግቦቦችሁ አገራዊ ጉዳይ ላይ የሚያሰራ እቅድ አውጥታችሁ በዊጪ ያለውን እትዮጵያዊ ሀይል ከመቼውም በበለጠ በአሁኑ ሰአት መጠቀም ይጠበቅባችዎል::

ይህ ሳይሆን ቀርቶ በትንሹም በትልቁም መግባባት ሳትችሉና ከአገራችን ከኢትዮጵያና ከህዝቦቾ ይልቅ ቅድሚያ የምንሰጠው ለድርጅታችን ነው የምትሉ ከሆነ እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ በዊጭም ሆነ በመከራ ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድርጅታችሁን ከአገርና ከህዝብ በላይ የምታስቀድሙ ከሆነ እናንተም የተደበቀ አጀንዳ ያላችሁ በመሆናችሁ አንፈልጋችሁም አናውቃችሁም እኛ በአገራችን ላይ በመሞትና በመኖር ምሃል እያለን እነንተ በኛ ሰቆቃና በኛ ደም የምንታገለው ለአገርና ለህዝብ ነው እያላችሁ ድርጅታችሁን ከሆነ የምታስተዋውቁት በአገራችን ስምና በምናፈሰው የነጻነት ደም ላይ እንደ መቀለድ ስለሆነ ድርጅታችሁ ይዛችሁ አርፋችሁ ተቀመጡ እንደሚላችሁ ከወዲሁ ብትገነዘቡ ጥሩ ይሆናል::

ምክንያቱም ኢትዮጲያዊ እናቶችና አባቶች ምን ያህል ልጆቻቸውን ለገዢው መንግስት ጥይት መገበር አለባቸው? በዊጪ አገር ያሉና በኢትዮጵያውያን ስም የሚታገሉ ድርጅቶች በሚያስማማቸው የአገር ጉዳይ አብሮ ለመስራት ምን ያህል ኢትዮጵያዊ ወጣቶች መሰዋት አለባቸው? እውነት እንነጋገር ካልን አብዛኛውን ግዜ በተፈጥሮ ህግ ልጆች ነበሩ እናቴ እናቴ አሊያም አባቴ አባቴ ብለው አልቅሰው መቅበር የነበረባቸው እየታየ ያለው ግን የኢትዮጵያዊያን አናቶችና አባቶች ላለፉት አርባ አመታቶች በተለይ ደሞ በኢሕአዴግ ዘመን ልጅን ለጥይት ገብሮ ልጄ ልጄ ማለትና መቅበር እንደ ስራ ተቆጥሮ በየቀኑ ሆኖል:: እሥቲ ዞር ብለን እናስታውስ በቅርቡ በ2009 /ም እንዲት የኦሮም እናት በርበሬ ንግዶ የሚያኖራት ልጆን የመንግስት ሃይሎች በጥይት መግደላቸው አንሶ አምጣ የወለደቸው ልጆ አስክሬን ላይ ተቀመጪ ብለው ሲያሰቃዮት በመላው አለም ያለን ኢትዮጵያውያን የሰማነው እውነታ ነው ታዲያ ይህን የሰማ የድርርጅት መሪና የድርርጅት ተመሪ አብሮ ላለመስራት የናቴ ቀሚስ አደናቀፈጅ ቢል በአገራችን ውስጥ በጥይት በሚያልቁት ወጣቶች ደም መቀለድ አይሆንም? እኛም በውጪ አገር የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እነዚህ ድርጅቶች አንድ አርገውን እንዲመሩን በድጋሚ በሰቆቃ ላይ ባለችው አገራችንና በግፍ ቀምበር ውስጥ ባለው ህዝባችን በአዲሱ አመት ቃል እንግባ::

በሌላ በኩል ደሞ ለነዚህ ድርጅቶቹም የማያዳግም ምለእክት እናስተላልፍ እሱም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ወቅት ላይ የአገር ውስጥ ተፎካካሪ ድርጅቶችን ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ እንዳሉት ሁሉ እኛም በውጪ አገር ያለን ኢትዮጵያውያን እነዚህን በውጪ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሳንፈራ ተባበሩ ወይም ተሰባበሩብለን አስረግጠን መንገር ያስፈልጋል:: በግልጽ እንነጋገር ከተባለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ካሎቸው አስሩ አገራዊ መርሆዎች ውስጥ በዘጠኙ ይስማሙና በልተሰማሙበት በአንዱ ችግር ሲበታተኑ ይታያሉ አሁን ግን ያን ያልተስማሙበትን ችግር ለነገ ትተው በተስማሙባቸው ለይ መስራት ያለባቸው ሰዓት ላይ ስለሚገኙ ይህንን አምነው መቀበል አለባቸው::

በራስ መኩራትና ራስን ማድነቅ በማንኛቅም መለኪያ ቢመዘን ስህተት አይደለም አሊያም በምንም መንገድ አሉታዊ የለውም:: በእርግጥ ዛሬ የታሪክ ቦታ ይዞ መገኘትና አገራችንን ኢትዮጵያንና ህዝቦቾን ከለው መንግስት መታደግ ደግሞ ከእኛ ከአሁኖቹ የሚጠበቅ እንጂ በይደር ለነገዎቹ የምናሳድረው እዳ መሆን የለበትም:: እርግጥ ነው በተሳካ ሁኔታ የገዢው መዳፍ ውስጥ መግባት ለድርጅቶች ሆነ ለእኛ ለኢትዮጵያውያኖች ብርቃችን አይደለም ይህንንም ለማስታወል የፖለቲካ ሊቅ አለያም ተንታኝ መሆን የሚያስፈልገው አይደለም ለአንዳፍታ ቆም ብለን ላለፉት ሃያ አምስት አመታቶች የሄድንባቸውን መንገዶች ማስተወል ብቻ በቂ ነው:: የሄድንባቸውን የአንድ ትውልድ እድሜ ብነጤነው የሚነግረን ነገር ቢኖር እኛ ኢትዮጵያውያን የጎደለን የተፈጥሮ የህይወት ቅማም እንዳለ ነው ከዚህ ውስጥም አንዱ ቅራኔ ሲፈጠሩ ቅራኔውን የመፍታት ችሎታ ማነስ ነው::

ባብዛኛው ኢትዮጵያዊ እምነት አሁን በአገራችን ያለውን ችግር ለመፍታት በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በግዴታ ወደ ውይይትና ክብ ጤረንጴዛ እንዲመጣ በሁሉም አቅጣጫ ጫና መፍጠር ያለንበት ሰዓት ላይ ደርሰናል ብለን እናምናለን ይህንን የማይቀበል ከሆነ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለበት ብለንም እናምናለን:: ስለሆነም ሁላችንም በአንድ ልብ መካሪ በአንድ አንደበት ተናጋሪ ሆነን መነሳት አለብን:: የሃገራችንን ሁኔታ ልብ ብለን ስንመለከተው ይህ ዘመን ከመቼውም ጊዜ የከፋና ይበልጥ የሚያስፈራ ሆኖ ይገኛል በተለይ ከ2009 መጀመሪያ አንስቶ ያለውን በጽሞና ስናጤነው በጣም ይሰቀጥጣል አሁን በሁሉም መንገድ እንደሚታየው ገዢው መንግስት በማንኛውም ግዜ ተገልብጦ ወደ መጨረሻ ውድቀት እንደሚያመራ በሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያኖች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በራሱም በገዢው መንግስት ውስጥ ባሉት ከፍተኛ ባለሰልጣኖች ጭምር የታመነ ነው:: ለዚህ መሰረቱ የወገንተኛው አምባገነን ሕግገወጡ መንግስት የፓለቲካ ፍልስፍናውና የአስተዳደር መርሆው የወራሪነት ዓይነት ስለሆነ ነው:: ስለዚህ በአዲሱ የኢትዮጵያ አመት ይህንን የገዢውን መንግስት ማስወገድ የሚያስችል የትግል መንገድ ንድፈው እንዲያሳዩን ከኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ከፍተኛ አመራሮችና ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት አመራሮች በከፍተኛ ደረጃ ይጠበቃል:: በተጨማሪ ውጪ አገር ካለው ኢትዮጵያዊ አገራዊ አደራ ተቀብለው ትግሉን አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንዲወስዱት በሚደግፋቸው ህዝብ ፊት ከወረቀት የዘለለ አዲስ ቃል ኪዳን እንዲገቡ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እጠይቃለው::

ለነዚህ ድርጅቶች ይህንን የመሰለ የቀውጢ ቀን የአገር ማዳን ሃላፊነት የሚሰጣቸው ምክንያት የትግሉ ምንነት ነው:: ይህ ሲባል ደሞ ሶስቱም ድርጅቶች በአገራችን ያለው ገዢ መንግስት የወራሪ አይነት አስተዳደር የዘረጋ መሆኑን መቶ በመቶ በመቀበላቸው ከ2012/ም ጀምሮ በፊት ተበታትነው ይታገሉ የነበሩትን የተለያዩ ድርጅቶችን በየጎራቸው አሰባስበው ስለሚገኙ ነው:: ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለያየ የሚዲያ አውታር እንደሚከተተላው በነዚህ ሶስት ድርጅቶች ውስጥ ከሀያ የሚበልጡ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቨክ ማህበራቶች አቅፈው እንደሚገኙ በየግዜው የምንሰማው ዜና ነው ይህንንም በመስራታቸው ሊመሰገኑና ለቀጣዩ ትግል እጅና ጎንት ሆነው እንዲሰሩ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ድጋፍና ማበራተቻ ሊቸራቸው ይግባል:: በሌላ በኩል ባሳለፍናቸው ሃያ አምስት የኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ውስጥ ቡዙ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ተመስርተው ነበር:: ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የእነዚህ ድርጅቶች አባላቶች በውስጣቸው የሚፈጠረውን ቅራኔ መፍታት ባለመቻላቸው ጨርሰው ጠፍተዋል::

እነዚህ ቅራኔዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንፀባረቁትን ያህል በዊጪ ባሉ ድርጅቶችም ውስጥ ይንጸባረቃል እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ በጣም አስገራሚ ክስተት ነው ለምን ቢባል በዊጪ አገር ባሉ ድርጅቶች ውስጥ ዽህነት ሳይኖር; የፖለቲካ አፈናና የትምህርት እጥረት ሳይኖር በቅራኔ አፈታት ተክኖት በተላላቅ ተቆማት ውስጥ ገብተው የሰለጠኑ ኢትዮጵያዊ ሙህራኖች ባሉበት አገር ቅራኔዎች ጥርስ አግጠው ሲወጡና ቅራኒዎችን መፍታት አቅቶን ስንበታተን መመልከት እኛ ኢትዮጵያኖች ያላወቅነውና የተሰወረብን ችግር አለብን ማለት ነው ይህም ችግራችን በዓለም ላይ መሳቂያ ያደረገን ጉዳይ ነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም:: ይህንን እያወቅን የተሰወረብንን ቅራኔ ላይ ነው ኢትዮጵያዊ የቅራኔ አፈታት ሙህራን ሌት ተቀን መስራት ያለባቸው ምክንያቱም ያገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬይባል የለ::

በቡዙዎቻችን እይታ ውጪ አገር ያሉት ተቃዋሚ ሀይሎች ያለባቸው ችግር በጢቅቱ የሚከተሉት መሆነቸውን ሁላችንም የምንስማማ ይመስላኛል::

. ግልጽ አለመሆን

ግልጽነት ጤናማን ግንኙነት እንዲኖር ይረዳል ድርጅቶች የደርጅታቸውን አስተሳሰብ ግልጽ ካለማድራጋቸው በተጨማሪ የሌላውም ድርጅት አስተሳሰብ ግልጽ ይሆናል ብለው አይጠብቁም ስለሆናም ሊፈታ የሚችለው ቅራኔያቸው ተካሮ አጥናፍ ለአጥናፍ ቆመው የተበታተነ ትግል ሲያደርጉ ይታያሉ::

. ጥርጣሬ በመጀመሪያ ድርጅቶች የሚተያዩት በጥርጣሬ አይን ነው በዚህም ምክንያት ጉዳት የሌላቸው ሃሳቦች ከጀርባቸው ሌላ ነገር አላቸው ብሎ በመጠርጠር ይፍራራሉ::

. ጉራና ኩራት እኛ ኢትዮጵያውያን ኩሩዎች ነን ብለን እናምናለን ስለሆነም ክርኩራት ጋር የተያያዘ ታሪክ አለን ማለት ነው ይህንን ታሪክ አንዳንድ ድርጅት ውስጥ ያሉ ከፈተኛ አመራሮች በዚህ ጉራና ኩራት የተነሳ አልፎ አልፎ በድርጅታቸው ውስጥና በሌላው ድርጅት ውስጥ የሚታየው መናናቅና መጠላላት ችግራቸውን ከመፈታት ይልቅ ሲያራርቃቸው ይታያል በሌላ በኩል ደሞ አገራችን ኢትዮጵያ ህዝቦቾ በርሃብ; ወጣቶችዎ በመንግስት ደህንነቶች ጥይት እየረገፉ ባለበት ወቅት ድርጅቶች ጉራ ወይም ክብርን መታገያ ማድረግ የሚያሳዝንና አንዱ ትልቅ ችግር ነው::

. ይሉኝታ ይህ ሌላው ድርጅትንም ሆነ ግለሰብን ላለማስቀየም የሚወሰድ ባህላዊ እርምጃ ነው የድርጅቶችን ወይም የግለሰቦች ህልውና ላለመንካት ሲባል ከእውነት የራቀ ሃሳብ ወይንም ድርጊትን ሳናስተካክል ወይንም ሳናርም ስለምናልፍ ሁሉም እርስ በርሱ ሳይተማመን ጉዞ ይጀምራል ውጤቱም ውሀ ቢወቅጡት እንቦጭእንደምባለው ሆኖ ትግሉ የተፈለገውን ያህል ውጤት አያመጣም ሠ. ቂም መያዝና መቀያያም ድርጅቶች ቅራኔዎችን መፍታት ሲገባቸው በእውቀት ማነስ አሊያም በአወኩሽ ናኩሽ ቂም ይያያዙና ያንን ቂም አለመርሳትና ድርጅቴ በደረሰበት አትድረሱ መባባል ይጀመራል ይቀር መባባልን እንደድክመት ይቆጠርና ስም መተፋፋትና አሉባልታ ይከተላል:: ከፍ ሲልም እናንተ በምትፈልጉበት ሂዱ እኛ በፈለግንበት እንሂድ የሚሉት ፈሊጥ ይጀምራሉ:: . አስመሳይነት ድርጅቶች እራሳቸውን አለመሆንና እንደ እስስት የተለያዩ ገፅታዎችን ማንጸባረቅ ይህን ዓይነት የድርጅት አወቃቀርና የማያውቁትን አውቆ መገኘትና ያልሰሩትን እንደሰሩ ማቅረብ ሲያበዙ ለቅራኔ በር ይከፍታል::

እነዚህነ ሌሎች ያልተጠቀሱት ችግሮች ስላሉን ይህንን ችግሮች የሚፈቱ የቅራኔ አፈታት ክኖት ያላቸው ሙህራኖችን ህዝባችንና አገራችን እንዲሁም ድርጅቶች ከመቼውም ግዜ ይበልጥ አሁን ስለምትፈልጋቸው በያሉበት ያሉ ሙህራኖች እለን ብለው ግዜቸውንና እውቀታቸውን አስተባብረው በድርጅቶ ወስጥ ያለውን ቅራኔ ለመፍታት ፍቃደኛ እንዲሆኑ በዚህ አጋጣሚ እጠይቃለው:: እነዚህን የቅራኔ አፈታት ክህኖት ያላቸውን አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰብና በድርጅቶች ወስጥ ያሉትን ቅራኔዎች እንዲፈቱ የኢትዮጵያ የውይትና መፍትሄ መድረክና ቪዥን ኢትዮጵያ ተባብረው እነዚህን የችግር አፈታት ተክኖት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ማሰባሰብ ይጠበቅባቸዋል:: እነዚህን ሁለት ስብስቦች የጠቆምኩበት ምክንያት እኔ ለግዜው የማውቃቸው እነርሱ ስለሆኑ ነው ሌሎች በተለያየ ክፍለ ዓለም ካሉ ሊጨመሩ አሊያም ራሳቸውን ሊያጩ ይችላሉ::

ለኢትዮጵያ የውይትና መፍትሄ መድረክና ለቪዥን ኢትዮጵያ እንደማሳሲቢያ የምጨምረው ነገር ቢኖር እነዚህ የቅራኔ አፈታት ችሎታ ያላቸው ወንድሞቻችንም ሆኑ እህቶቻችን በአሁን ሰዓት ከምንም አይነት የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑ መሆን አለባቸው ምክንያቱም አድሎ እንዳይታይባቸው:: የኢትዮጵያ የውይትና መፍትሄ መድረክና የቪዥን ኢትዮጵያ እነዚህም ባለሞያዎች ለዚህ የተቀደሰ ስራ ሲያጮቸው የታጩትም ሰዎች በታጩበት ግዜ የማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑ መሆናቸውን በሒሊነቸው የሚያምኑ መሆን አለባቸው:: ሌሎች ይህንን የሚያግዙ በውጪ አገር ያሉ የኢትዮጵያውያን ሚዲያዎች ሲሆኑ እነዚህ ሚድያዎች ስራው መጀመሩ የኢትዮጵያ የውይትና መፍትሄ መድረክና የቪዥን ኢትዮጵያ አስተዳዳሪዎችን ቀርቦ ጉዳዩ የት እንደደረሰ መጠየቅ ስራው ተጀምሮ ከሆነ የት ላይ እንደደረሰ መከታተልና ለህዝብ ማሳወቅ; ቅራኔን ለመፍታት የታጩትን ግለሰቦች ለህዝብ ይፋ በማድረግ ስራ መጀመራቸውን መግለጽ:: ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው የፖለቲካ ድርጅቶች ለውይይት ፍቃደኞች መሆነቸውን ካበሰሩ እሰየው: የሚዲያ አውታሮች በቅርብ ሆነው እያበረታቱ መዘገብ; ምናልባት ይህን ዓይነት አካሄድ አያወጣኝም የሚል ድርጅት ካለ ሚዲያዎች ሳይፈሩ ሳይችሩ ለህዝብ ማሳወቅ:: ህዝቡም እንዴት ነው የህዝብን ሀሳብ ስታስቀደም ለህዝብ ነው የቆምኩት የምትለው ብሎ ያንን የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ የሚለውን የፖለቲካ ድርጅት አጥብቆ ይጠይቃል ማለት ነው በእምብተኝነቱ ከገፋ ከህዝቡም ሆነ ክድርጅት ደጋፊዎች የሚያገኘውን ድጋፍ እንደማይኖረው በውጪ ያለንና ከድርጅት በላይ ህዝብና አገር የምንል ኢትዮጵያኖች ያለምንም ፍራቻና ይሉኝታ አበክረን መናገር አለብን ማለት ነው::

በታሪክ እንደተማርነው ዳዊት ጎልያድን ያንጋለለው እንድ ጠጠር ድንጋይ በወንጪፍ አወናጭፎ ወይም ወርውሮ ግንባሩን ላይ መቶት ነው:: በሌላ በኩልም ምን የሚያክልን ትልቅ ተራራን እንዲት ትንሽ ወንዝ ሸርሽራ ታፈርሰዋለች ይባላል::

የአንድ ሰው ጠጠር አልበግር ባዩን ጎልያድን ካንጋለለ ትንሽ ወንዝም ማን ይነካኛል ብሎ ተኮፍሶ የተቀመጥን ተራራ ሸርሽሮ ታፈረሰ በዊጪ አገር ያሉት ተቃዋሞ ድርጅቶች ተባብረው በውጪ ያለነውን ኢትዮጵያውያን ካስተባበሩ ብል የበላው ዋርካ ይመስል የተቦረቦረውን የኢህድግን መንግስት ወደ ውይይት ጠሬንጴዛ እንዲመጣ ይህንን ምርጫ በራሱ ውድቅ ካደረገ ደሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ከስሩ መንግሎ ለመጣል ከበቂ በላይ ሀይል እንዳለ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚስማማ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል:: ይህን ከ2009 ከህዝባችን ሲንከባለል የመጣውን የለውጥና የነጻነት አውሎ ንፋስ ምንም ሃይል የማይመልሰውና ውጤቱም ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ነጻነት እንደሚሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ እምነት ነው::

ይህ ሊሆን የሚቻለው ግን በውጪ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች ስማቸውን ከላይ የጠቀስኮቸውም ሆኑ ስማቸውን ያልጠቀስኮቸው ተባብረው ሲያስተባብሩ ብቻ ነው:: በሌላ በኩል ደሞ እያንዳንዱ በዊጪ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ እያንዳንዱ ባላሞያ ይህ የራሴ ጉዳይ ነው; ይህ የአገሬ ጉዳይ ነው ብሎ በቅንንቅትና በንጹህ ልቦና ትብብር ፈጥረው ከሚያስተባብሩ ድርጅቶች ጋር እጅና ጎንት ሆኖ ሲሰራና ትግሉን አገር ቤት ካለው ትግል ጋር ሲይስተባብር ብቻ ነው:: ይህ ሳይሆን ቀርቶ ድርጅቶች ተበታትነውና ለብቻችን ነጻነት እናመጣለን ብለው የሚቅበዘበዙ ከሆነ ህዝቡም በተቀኛጀ የሚመራው መሪ እጥቶ በራሱ ነጻ የሚወጣበትን መንገድ ከመረጠ በአገራችንና በህዝባችን ላይ የሚደርሰው ከፍተኛ አደጋ የአገራችን አልቃሽ ሞሾ ስታወርድ ጋዳዩ ነው ባልሽ ሞቹ ወንድምሽ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣእንዳይሆንብን መልሰን ከልሰን የምናስብበት ሰዓት ላይ እንዳለን መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል::

ሁለት ሺ አስር የነጻነት ዓመት ይሆን ዘንድ ፈጣሪ ከጎናችን ይሁን እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ሕዝቦን ይባርክ!

ግልባጭ: ለአሜሪካው የአማርኛው ፕሮግራም (VOA) ለጀርመን የአማርኛው ፕሮግራ (D W) ለኢትዮጵያ የውይትና መፍትሄ መድረክ ለቪዥን ኢትዮጵያ Addis Dimts Radio/TV
EAST Radio/TV Zehabesha TV BBN Radio Hiber Radio

SBS Radio

ፎረም 65