በብር ምንዛሬ ለውጥ ምክንያት እያንዳንዳችን በአገዛዙ እንደተዘረፍን እናውቅ ይሆን? – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

image_pdf

ከነገ ጥቅምት 1 ቀን 2010 .. ጀምሮ የብር ምንዛሬ ለ1 የአሜሪካ ዶለር 22.97 (23 ብር) ከነበረው 27 ብር እንዲሆን ብሔራዊ ባንክ (ቤተንዋይ) ገልጿል፡፡ ይሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ልብ ብላቹህታል ወገኖቸ? ይሄ ማለት ከነገ ጀምሮ መቶ ብር ያለው ሰው ከመቶው ብሩ 17 ብሩን አገዛዙ ወስዶበት 83 ብር ተደርጎበታል ማለት ነው፡፡ 1 ሽህ ብር ያለው መቶ ሰባ ብር ተወስዶበት 830 ብር ተደርጎበታል ማለት ነው፡፡ 10 ሽህ ብር ያለው 1,700 ብር ተወስዶበት 8,300 ተደርጎበታል ማለት ነው፡፡ 100 ሽህ ብር ያለው 17 ሽህ ብር ተወስዶበት 83 ሽህ ብር ተደርጎበታል ማለት ነው፡፡ 1 ሚሊዮን (አእላፋት) ብር ያለው መቶ ሰባ ሽህ ብሩ ተወስዶበት 8 መቶ ሽህ 3 መቶ ብር ተደርጎበታል ማለት ነው፡፡ እንዲህ እያላቹህ እንግዲህ ባላቹህ ገንዘብ መጠን ምን ምን ያህል ገንዘብ እንደተዘረፋቹህ ማስላት ነው፡፡

በሌላ አማርኛ የብር የመግዛት አቅም በ17 በመቶ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ይሄም ማለት ቀደም ሲል በመቶ ብር ስንገዛው የነበረው ዕቃ አሁን 117 ብር እንገዛለን ማለት ነው፡፡ በዚህ የምንዛሬ ለውጥ ምክንያት ገበያው ላይ የሚከሰተው የዋጋ ግሽበት ግን በ100 ብር ዕቃ በ17 ብር ጭማሪ ሒሳብ ይወሰናል ብየ አልጠብቅም፡፡ እንደምታውቁት ትንሽ ምክንያት ብቻ የሚፈልገው ገበያችን ይሄንን የምንዛሬ ለውጥ ምክንያት አድርጎ ገበያው እሳት እንደሚሆን ከፍተኛ ሥጋት አለኝ፡፡

ምናልባትም መቶ ብር እንገዛው የነበረውን ዕቃ 150 እና ከዛ በላይ ሊሆን እንደሚችል እሠጋለው፡፡ በ150 ብንይዘው እንኳ ነጋዴው ተጨማሪ 33 ብር በመቶ ብር ይወስድብናል ማለት ነው፡፡ ይሄም ማለት መቶ ብር ያለው ሰው ከነገ ጀምሮ ሐምሳ ብር ይሆንበታል ማለት ነው፡፡ ስሌቱን ከላይ ባስቀመጥኩላቹህ ስሌት መሠረት አስሉት፡፡ በአጭር ቋንቋ የአምስት ሽህ ብር ደሞዝተኛ ከነገ ጀምሮ ኑሮን የሚኖረው የ2,500 ብር ደሞዝተኛን ሰው ኑሮ ነው፡፡ አንድ የአምስት ሽህ ብር ደሞዝተኛ እስከ አሁን የነበረውን የማያዘባንን ኑሮ ከዚህም ሳይከፋ ከነገ በኋላ መኖር ካለበት ከነገ ጀምሮ ደሞዙ 7,500 መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ ይሄ የሚሆንበት ዕድል ደግሞ የለም፡፡

እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! በአዲሱ የተመሰቃቀለና የችጋር ኑሮ ለመጠበስና ለመሰቃየት ዝግጁ ነህ ወይስ በቃኝ ብለህ የችጋርህን፣ የግጭትህን፣ የመለያየትህን፣ የውድቀትህን፣ የአሣርህን፣ የመከራህን የሁሉንም ክፉ ነገሮችህን ምንጭ ወያኔን ትገላገላለህ???

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com

No widget added yet.

← የሰሜን ጎንደር ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ይፋ ሆነ። Roundup: Experts question Ethiopian National Bank's currency devaluation →

Leave A Reply

Comments are closed

Visit Us On TwitterVisit Us On FacebookVisit Us On YoutubeVisit Us On Linkedin