ethiopia devalues birr by 15%

የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የገንዘቧን የመግዛት አቅም ዝቅ እንድታደርግ ግፊት ሲያደርግ ቢቆይም የብርን የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ማድረግ ከሚያስገኘው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል በማለት መንግሥት ሳይቀበለው ለረጅም ጊዜ ቆይቷል።

አሁን ግን የተቀዛቀዘው የወጪ ንግድን እንዲያንሰራራ ለማድረግ የብር የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በ15 በመቶ እንዲቀንስ ተደርጓል።

ይህ እርምጃ በህብረተሰቡና በገንዘብና በምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ዘንድ ትልቅ ስጋትን ፈጥሯል።

በተለይ ይህ ከፍተኛ የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል ወትሮም በፍጆታ እቃዎች እጥረት እየተቸገረ ለሚገኘው ሸማቹ ህብረተሰብ አስደንጋጭ ክስተት ነው።

በየወሩ የሚደረገውን የነዳጅ ዋጋ ክለሳን ተከትሎ በፍጆታ ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ያስመረራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ደቻሳ ”በዚህ እርምጃ ምክንያት እየተጋፈጥነው ያለው ችግር ከቁጥጥር ውጪ ይሆናል” ብለው እንደሚሰጉ ይናገራሉ።

የመዋዕለ ነዋይ ባለሙያው አብዱልመናን መሃመድም ይህንን ስጋት ይጋሩታል። ”ከውጪ በሚመጡ የፍጆታ ምርቶች፣ የጥሬ ዕቃና የማምረቻ መሳሪያዎች ግዢ ምክንያት የንግድ ጉድለት እየሰፋ በሚመጣበት ሃገር ውስጥ፤ በዚህ መጠን የብርን የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዋጋ መጋሸብን ያስከትላል” በማለት ሊያስከትል የሚችለውን ጫና አስቀምጠዋል።

የብር የመግዛት አቅም እንደሚቀንስ ከተነገረ በኋላ በምርቶችና በአገልግሎት ዋጋ ላይ ከፍ ያለ ለውጥ እንደሚኖር በእርግጠኝነት የሚናገሩት አቶ ደቻሳ ”በዕለታዊ ሥራና እንደኔ ተቀጥሮ ለሚተዳደረው ብዙ ህዝብ ይህ ለውጥ ከባድ ችግርን የሚያስከትል ይመስለኛል” ይላሉ።

አክለውም “የታሰበው ለውጥ መምጣቱን እርግጠኛ ለመሆን በማይቻልበት የውጪ ንግድ ሲባል ድሃው መስዋዕት መሆን አለበት ወይ?” በማለት ይጠይቃሉ።

ግብይት

የኢንቨስትመንት አማካሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ተክለማርያም እንደሚሉት ”የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው መሠረቱን ከውጭ በሚመጡ ምርቶች ላይ ያደረገ በመሆኑ፤ በመጋዘን ምርት ያለው ነጋዴ እንኳን ወደፊት የሚጠብቀውን የኢትዮጵያ ብር መጠንን በወጪነት እያሰላ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ አይቀርም” ይላሉ።

ይህም ምግብ፣ አልባሳትና መድኃኒትን ጨምሮ ለየዕለት ፍጆታም ሆነ ለዘላቂ ኑሮ የምንጠቀምባቸውን አብዛኞቹ ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸው ምርቶች ላይ የምንዛሪ ለውጡን መሠረት ያደረገ ጭማሪ መከሰቱ አይቀሬ መሆኑን አቶ ጌታቸው ያክላሉ።

መርካቶና ካዛንችዝ አካባቢ በፍጆታና ቋሚ ምርቶች ንግድ ላይ የሚገኙ ነጋዴዎችን ጠይቀን እንደተረዳነው፤ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ በመደረጉ ምክንያት በአቅርቦታቸው ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደሚኖር እርግጠኛ ቢሆኑም በምን ያህል መጠን የሚለው ላይ ለመወሰን የገበያው ሁኔታና የነጋዴውን ስምምነት እየጠበቁ መሆናቸውን ገልፀውልናል።

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት ”የብር የመግዛት አቅም አንሷል የምንለው በጥቁር ገበያ እና በባንኮች የብር ምንዛሬ መካከል የሰፋ ልዩነት ሲታይ ነው። ይህ የሚያሳየው በገበያ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት ከፍተኛ አለመመጣጠን ስለሚታይበት ነው” በማለት ያስረዳሉ።

ከዚህ አንፃር ”አሁን የተወሰደው የብርን የመግዛት አቅም የመቀነስ እርምጃ ይህንን ክፍተት ከማጥበብ አንጻር አወንታዊ ሚና ሊኖረው ይችላል” ተብሎ እነደሚታሰብ አቶ ጌታቸው ይናገራሉ።

ethiopia devalues birr by 15%

ስጋት

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ደሴ ከተማ ውስጥ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ እነደነገሩን “ለገበያ የሚቀርቡ ሸቀጦች በዶላር እጥረት ምክንያት ከገበያ እየጠፉ ባሉበት ሁኔታ የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ በህብረተሰቡም ሆነ በነጋዴው ላይ ከባድ ጫናን መፍጠሩ አይቀርም” ይላሉ።

ይህ የመንግሥት እርምጃ ወትሮውንም የተቀዛቀዘውን የንግድ ሥራቸውን የበለጠ ሊጎዳው እንደሚችልም ይሰጋሉ።

ሁለቱም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይህን ያህል የብር የመግዛት አቅም ቅነሳ መንግሥት ያሰበውን ያህል ወጤት ቢያመጣለት እንኳን ዘለቄታው ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

አቶ አብዱልመናን እንደሚሉት ”ከሰባት ዓመት በፊት የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ሲደረግ በወጪ ንግድ ላይ የታየውን አይነት ውስን ለውጥ ያመጣል። ነገር ግን ለውጪ ንግድ ምርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ዋጋ ስለሚጨምር ይህ አውንታዊ ለውጥ ዘላቂነት አይኖረውም” ሲሉ፤ አቶ ጌታቸውም ”በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚታዩ ብዙ ችግሮች አሉ፤ ስለዚህ ይህ እርምጃ የሚታየውን የማክሮ ኢኮኖሚ ያለመመጣጠን ችግርን ይቀርፈዋል ማለት አይደለም” ይላሉ።

በመንግሥት በኩል ለዚህ እርምጃ የሚቀርበው ምክንያት የውጪ ንግድን ለማበረታታት እንደሆነ ቢነገርም አቶ ደቻሳም ሆኑ የደሴዋ ነጋዴ ህዝቡ ላይ የሚፈጠረውን ጫናና የኑሮ ውድነትን በምን እንዲቋቋመው ታስቦ እነደሆነ ይጠይቃሉ።

”የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ሲደረግ የውጭ ምንዛሪ መጠን አብሮ ይለወጣል። ይህ ደግሞ በምርቶች አቅርቦት ላይ ስለሚንፀባረቅ ችግሮች ይከሰታሉ። የሚያጋጥመው የዋጋ ጭማሪም ከተቀነሰው የብር የመግዛት አቅም በላይ ሊሆን ይችላል” የሚሉት አቶ አብዱልመናን የህብረተሰቡ ስጋት ተገቢ መሆኑን ያሰምሩበታል።

ሌላ ዕዳ

”የብርን የመግዛት አቅም በመቀነስ የወጪ ንግድን ማበረታት ይቻላል የሚለው የፖሊሲ አውጪዎች ዕይታ የራሱ የሆኑ ፈተናዎች አሉት” የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ ”እንዴት የብርን የመግዛት አቅም በመቀነስ ብቻ ነው የወጪ ንግድን ማበረታታ ይቻላል? ላኪዎች በዓለምአቀፍ ገበያ ውስጥ ያላቸው ተወዳዳሪነትስ የተገደበው በብር የመግዛት አቅም ምክንያት ነው?” በማለት ይጠይቃሉ።

ይህ እርምጃ በሃገሪቱ ላይም ከበድ ያለ ጫናን እነደሚፈጥር የሚያምኑት አቶ አብዱልመናን ”የብር የመግዛት አቅም መቀንስ በመንግሥት የልማት ድርጅቶችና በመንግሥት የውጪ ብድር ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ ይኖረዋል። እስከ ሰኔ 2009 ድረስ ሃገሪቱ ከ23.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ብድር ዕዳ አለባት። የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ ሲደረግ የሃገሪቱ ዕዳ በአስር ቢሊዮን ብሮች ያሻቅባል ማለት ነው” በማለት ይገልፃሉ።

ይህም ሃገሪቱ ያለባትን የብድር ጫና ከማክበዱ በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችን ያስከትላል። ከሁሉ አሳሳቢው ደግሞ የዋጋ ግሽበት እንዲጨምርና ሌሎች ምጣኔ ሃብታዊ ቀውሶች እንዲከሰቱ ሊያደርግ ይችላል።

የብርን የመግዛት አቅም ዝቅ በማድረግ ሊከሰቱ የሚችሉ አሳሳቢ ሁኔታዎች አቶ አብዱልማናንና አቶ ጌታቸው እንዲህ ያስቀምጧቸዋል።

ከውሳኔው በፊት የነበረው የቅርብ ጊዜ የዋጋ ግሽበት 10.8 በመቶ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው ”ገና ከጅምሩ ይህ ግሽበት በጣም ከፍ ሊል ይችላል” ሲሉ፤ አቶ አብዱልመናን ድግሞ ”ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከውጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ ቀድሞ በነበረበት ይቀጥላል። ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እርምጃ ወደማያቋርጥ የብር የመግዛት አቅም ቅነሳና የዋጋ ግሽበት አዙሪት ውስጥ ያስገባናል” በማለት ያጠቃልላሉ።

Source     –     BBC/Amharic