እንደ ቅርስ ያልተያዙት የጎንደር ድልድዮች

 

እንደ ቅርስ ያልተያዙት የጎንደር ድልድዮች

8 October 2017

ምሕረተሥላሴ መኰንን

ኤፍሬም ምትኩ በጎንደር ከተማ የባጃጅ ሹፌር ነው፡፡ ተወልዶ ካደገበት አንገርብ ወንዝ አካባቢ ደፈጫ የሚባል ድልድይ ይገኛል፡፡ ልጅ ሳለ ድልድዩን አፄ ፋሲል (1624-1659 ዓ.ም.) እንዳሠሩትና በድልድዩ የሚተላለፉ ሰዎች ‹‹የፋሲልን ነፍስ ይማር›› እያሉ ያልፉ እንደነበር የተነገረውን ያስታውሳል፡፡ ኤፍሬምና ጓደኞቹ በልጅነት ታላላቆቻቸው ከሚነግሯቸው የድልድዩ ታሪክ በበለጠ፣ በድልድዩ ሥር የሚያልፈው ወንዝ ትኩረታቸውን ይስበው ነበር፡፡ ወንዙ በሚሞላበት የክረምት ወራት ለዋና ይጠራራሉ፡፡ ምሽት እስከሚለያያቸው ያለ ድካም ሲዋኙም ይውላሉ፡፡

ከልጅነት ትውስታቸው ጋር የጠበቀ ትስስር ያለው ወንዝ ላይ የሚገኘው ድልድይ፣ ከመተላለፊያነት ባለፈ ታሪካዊ ዋጋው ከፍ ያለ መሆኑን የተገነዘበው ካደገ በኋላ ነበር፡፡ ስለ ድልድዩ ታሪክ የጽሑፍ መረጃ ባያገኝም፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከሚያወራው በመነሳት ስለ ድልድዩ አሠራር ግንዛቤ አገኘ፡፡ ታሪካዊ መሠረቱን በውል ባያውቅም በአፈ ታሪክ የሰማው ድልድዩን አፄ ፋሲል እንዳሠሩት ነው፡፡

እንደ ቅርስ ያልተያዙት የጎንደር ድልድዮች

ሰባራ ድልድይ

አፄ ፋሲል ከሮም የመጡ ሁለት እህትማማቾች (ዘሊሀና መሊና የተባሉ) ጋር ግንኙነት መጀመራቸው ይነገራል፡፡ የንጉሡ ድርጊት ‹‹የኦርቶዶክስ ክርስትና ሕግጋትን የጣሰ ነው›› በሚል የሃይማኖት መሪዎች ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ፡፡ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙም ከአፄ ፋሲል ወታደሮች ጋር ይጋጫሉ፡፡ በዚህ ወቅት ብዙዎቹ መነኰሳት (ወደ 9,999 እንደሚደርሱ ይነገራል) ይገደላሉ፡፡ የንፁሀኑ ማለፍ በእጅጉ ያሳዘናቸው ንጉሡ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ነፍሳቸው ይማር ዘንድ ድልድዮች እንዲያሠሩ ሲነገራቸው ተቀበሉ፡፡ በድልድዩ የሚሸጋገሩ ሰዎች ‹‹የአፄ ፋሲልን ነፍስ ይማር›› እንዲሉ አዋጅ ወጣ፡፡

በዚህ መሠረት ንጉሡ በተለያዩ አካባቢዎች 12 ድልድዮች እንዳሠሩ ይነገራል፡፡ ከድልድዮቹ አንዱ አንገርብ ወንዝ ላይ የተሠራው ደፈጫ ድልድይ ነው፡፡ ወደ 36 ሜትር ርዝመትና አራት ሜትር ስፋት አለው፡፡ ኤፍሬም እንደሚለው፣ ድልድዩን ከሚያውቅበት ካለፉት አርባ ዓመታት ወዲህ የድልድዩ ይዘት ተለውጧል፡፡ የተሠራበት ድንጋይ ፈራርሷል፡፡ በየጊዜው ስለሚሸራረፍ እንዳልነበረ ሊሆን ጥቂት ጊዜ ብቻ ቀርቶታልም ሲልም ይሰጋል፡፡
‹‹ድልድዩ ምንም ዓይነት ጥበቃና እንክብካቤ አልተደረገለትም፡፡ ከዓመታት በኋላ ሳየው ከፊሉ የድልድዩ አካል ፈራርሷል፡፡ ቀድሞ የነበረው ይዘት በመጥፋቱ አዝኛለሁ፤›› ይላል፡፡ ድልድዩ ቀስተ ደመና የመሠሉ (ግማሸ ክብ ቅርፅ) አርኰች (ቅስት) አሉት፡፡ እነዚህ የተሠሩባቸው ድንጋዮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈራረሱ መጥተዋል፡፡

እንደ ኤፍሬም ያሉ የአካባቢው ተወላጆች ብቻ ሳይሆን የድልድዩን ታሪካዊ ዋጋ የሚያውቁ ሁሉ አሁን በሚገኝበት ሁኔታ ያዝናሉ፡፡ ደፈጫ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ድልድዮቹ ጥበቃ እየተደረገላቸው ስላልሆነ፣ ባለፉት ዓመታት የደረሰባቸውን ጉዳት በመመልከት ለወደፊት ምን ይሆናሉ? የሚለው አሳሳቢ ነው፡፡

በአፄ ፋሲል ዘመን እንደተሠሩ ከሚነገርላቸው ድልድዮች መካከል ደፈጫ ድልድይን የጎበኘነው ከኤፍሬምና አስጎብኚ አሰግድ ጋር ሆነን ነበር፡፡ አሰግድ ጎንደር የምትታወቅባቸውን ዕድሜ ጠገብ ቅርሶች ለዓመታት ካስጎበኙ ሙያተኞች አንዱ ሲሆን፣ ድልድዮቹ የሌሎች ቅርሶችን ያህል ቦታ እንዳልተሰጣቸው ይናገራል፡፡

እንደ ቅርስ ያልተያዙት የጎንደር ድልድዮች

ገንፎ ቁጭ ድልድይ

ድልድዮቹ የተሠሩበትን ትክክለኛ ወቅት በተመለከተ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ ኪነ ሕንፃቸው በአፄ ፋሲል ዘመን ከተገነቡ ሕንፃዎች ጋር መመሳሰሉ በዛው ወቅት መሠራታቸውን ያመላክታል ይላል፡፡ ደፈጫ ድልድይ ላይ ቀድሞ በጎንደር በኩል ወደ አድዋ የሚሄዱ ነጋዴዎች ቀረጥ የሚከፍሉበት ክፍል አለ፡፡ ይኼም ድልድዮቹ የንግድ መስመርን ተከትለው እንደተገነቡ ያሳያል ሲል አስጎብኚው ይገልጻል፡፡ ድልድዮቹ በአሠራራቸውና ታሪካዊ ዳራቸውም ጭምር ከሌሎች በጎንደር ከሚገኙ ግዙፍነት ያላቸው ቅርሶች እንደማይተናነሱ ያስረዳል፡፡ ሆኖም ቸል መባላቸው አንዱን ቅርስ ከሌላው የበለጠ የሚያደርገው መስፈርት ይኖር ይሆን? ያስብላል፡፡

‹‹ጎንደር ቅርስ በዝቶባት ነው መሰለኝ የቱ እንደሚጠበቅና የቱ እንደሚጠገን አይታወቅም፤›› ይላል አስጎብኚው በሐዘኔታ፡፡ ድልድዩን በጎበኘንበት ወቅት የአካባቢው ሕፃናት ከበታቹ ባለው ወንዝ እየዋኙ ነበር፡፡ በድልድዩ ይተላለፉ የነበሩ ሰዎች ዕቃ የጫኑ አህዮች እየነዱም ነበር፡፡ ድልድዩ ስለፈራረሰ እንዲጠገንላቸው ከሚጠይቁ የማኅበረሰቡ አካላት አብዛኞቹ እንደ ቅርስ ሳይሆን እንደ ማንኛውም መተላለፊያ መንገድ ይመለከቱታል፡፡
እንደ ኤፍሬምና አሰግድ ያሉ የአገሪቱ ሀብት የሚያሳስባቸው ሰዎች በበኩላቸው፣ ማኅበረሰቡ ስለ ድልዩዮቹ ታሪክ እንዲያውቅ መደረግ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ ግንዛቤ ከማሳደግ ባሻገር ለቅርሶቹ አስፈላጊው ጥበቃና ጥገና መደረግ አለበትም ይላሉ፡፡ በእርግጥ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ እውቅና ካላቸው ቅርሶች መካከልም ተገቢውን ጥበቃ ያላገኙ ብዙ ናቸው፡፡ እንደ ደፈጫ ድልድይ ቅርስነታቸው በበርካቶች ዘንድ ያልታወቀ ሀብቶች ምን ያህል ሊዘነጉ እንደሚችሉ መገመትም አያዳግትም፡፡

ድልድዩን ስንጎበኝ ካስተዋልናቸው ነገሮች አንዱ ጥንት የተሠራ ድልድይ ለዘመናት አገልግሎት መስጠቱ ነው፡፡ ቀደምቶች ያኖሩት ሀብት ከምንም ሳይቆጠር በዚህ ትውልድ እጅ መበላሸቱም ያሳዝናል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ወንዝ ለመሻገር እንዲሁም በአስቸጋሪው መልክዓ ምድር ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ለመጓጓዝ ከድልድዮቹ ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ደግሞ ተጓጓዡ ሕዝብም በዝቷል፡፡ ከድልድዮቹ ሌላ ተለዋጭ መንገድ በሌለበት ሁኔታ በብቸኛነት ያገለገሉት ድልድዮች፣ ከድልድይም በላይ የአገር ቅርስ መሆናቸው ተዘንግቷል፡፡

እንደ ቅርስ ያልተያዙት የጎንደር ድልድዮች

ባምብሎ ጭልቃሳ ድልድይ

‹‹ለምሳሌ መገጭ ድልድይ ከአናቱ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ በገመድ ተንጠልጥሎ ከማለፍ ውጪ አማራጭ አልነበረም፤›› ይላል አሰግድ፡፡ ድልድዮቹ እየሰጡ ያሉት ጥቅም ቀላል ባይሆንም እንደ መጓጓዣ እንኳን ትኩረት ተነፍጓቸዋል፡፡ በቅርስ ደረጃ መንከባከብ ዳግም ከነጭራሹ የታሰበበትም አይመስልም፡፡

ኤፍሬም ደፈጫ ድልድይን ሲመለከት ወንዙ ውስጥ የሚዋኙ ታዳጊዎችን ዓይቶ በትውስታ ወደ ልጅነቱ መመለሱ አልቀረም፡፡ ሆኖም ከወንዙ ውጪ ድልድዩን እንደ ቀድሞው አላገኘውም፡፡ በሱ ዕድሜ እንኳን በአሳዛኝ ሁኔታ የፈራረሰው ድልድይ ለቀጣዩ ትውልድ ስለመተላለፉም ይጠራጠራል፡፡

‹‹ዘ ጎንደርያን ፔሬድ ብሪጅስ›› በሚል ጥናት የሠሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራን እንግዱ ገብረወልድ፣ ሒሩት ስንታየሁና ሰሎሞን ልንገርህ የድልድዮቹ ጉዳይ ከሚያሳስባቸው መካከል ናቸው፡፡ የቱሪዝም ትምህርት ክፍል መምህሩ እንግዱ እንደሚናገረው፣ ድልድዮቹ በአፋጣኝ ጥገና ካልተደረገላቸው መጥፋታቸው አይቀሬ ነው፡፡ በጥናታቸው መሠረት፣ ደፈጫን ጨምሮ 12ቱ ድልድዮች በአፄ ፋሲል ሳይሆን በፖርቹጋላውያን እንደተሠሩ የሚገልጹ የውጭ አገር ተመራማሪዎች አሉ፡፡ ከድልድዮቹ ጥቂቱ የተሠሩት በአፄ ሱስንዮስ ዘመን (1598-1624 ዓ.ም.) ነው የሚል መላ ምትም አለ፡፡ ነገር ግን በአፈ ታሪክና እንደ ሪቻርድ ፓንክረሰት (ፕሮፌሰር) ባሉ የታሪክ ምሁራን መሠረት ድልድዮቹ የተገነቡት በአፄ ፋሲል ዘመን ነው፡፡

መምህሩ እንደሚናገረው፣ በአቡነ ሐራ ድንግል ገድልም ድልድዮቹ በአፄ ፋሲል መሠራታቸውን የሚጠቁም መረጃ ተገኝቷል፡፡ አፄ ፋሲል በወቅቱ የውጭ ዜጎችን ያለማስገባት ዝግ ፖሊሲ እየተከተሉ እንዴት ፖርቹጋሎች መጥተው ሊገነቡ ቻሉ? የሚለውም ጥያቄ ይሆናል፡፡ ከድልድዩ አንዱ የሆነው ደብረ ሊባኖስ አካባቢ የሚገኘው ድልድዩ ‹‹የፖርቹጋል ድልድይ›› እየተባለ መጠራቱ ደግሞ የታሪክ ሌላው ገጽታ ነው፡፡ ሆኖም ድልድዮቹ በኢትዮጵያ ታሪክ በተለይም በኪነ ሕንፃና የመሠረተ ልማት ዘርፍ ተጠቃሽ መሆናቸው ቅርስነታቸውን ያጎላዋል፡፡

እንደ ቅርስ ያልተያዙት የጎንደር ድልድዮች

መገጭ ድልድይ

ለምሳሌ ጉዛራ የተባለው ድልድይ የአገሪቱ ግንባር ቀደም ድልድይ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ድልድዮቹ ባጠቃላይ የተሠሩት ያለ ብረት ነው፡፡ ዘለግ ያለ የንግድ ጉዞን ተመርኩዘው የተገነቡት እነዚህ ድልድዮች፣ ከባዛልት ድንጋይ የተሠሩ ናቸው፡፡ ከድልድዮቹ ብዙዎቹ በጎንደር ከተማ የሚገኙ ሲሆን፣ በጎንደር ዙሪያ፣ በጎጃምና ሸዋ የሚገኙም አሉ፡፡

ከድልድዮቹ መካከል ገንፎ ቁጭ (ጐባጤ በመባል የሚጠራው)፣ ግልገል መገጭ፣ ርብና አለታ ይጠቀሳሉ፡፡ አለታ ድልድይ 64 ሜትር ርዝመትና ሁለት ሜትር ስፋት አለው፡፡ ጉዛራ ድልድይ ከእንፍራንዝ ወደ ባህር ዳር በሚወስደው መንገድ የሚገኝ ሲሆን፣ እንደ ሌሎቹ ድልድዮች ኖራ በመጠቀም የተገነባ ነው፡፡ ሰባራ ድልድይ በዓባይ ወንዝ አቅራቢያ የተሠራ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን አርበኞች የጣልያን ወታደሮችን እንቅስቃሴ ለመግታት እንደሠበሩ ይነገራል፡፡ አያያዥ ድልድይ ሳይሠራለት በፊት ሰዎች በድልድዩ ጫፍና ጫፍ በገመድ እየተንጠላጠሉ ይተላለፉ ነበር፡፡

በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 የሚገኘው ገንፎ ቁጭ ድልድይ፣ 36 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ የድልድዩ አንድ አርክ ከተቀሩት አራቱ መስፋቱ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ባምብሎ ጭልቃሳ ድልድይ ወገራና አርማጨሆ ወረዳን የሚያገናኝ ሲሆን፣ በጣልያን ወረራ ወቅት ተጎድቶ ለሁለት ተከፍሏል፡፡

ርብ ድልድይ በርብ ወንዝ እየተገነባ ያለው ዘመናዊ ድልድይ አቅራቢያ የሚገኝ ነው፡፡ በአፄ ሱስንዮስ ዘመን በፖርቱጋሎች ተገንብተዋል ከሚባሉ ድልድዮች መካከልም ይጠቀሳል፡፡ ሌላው ድልድይ መገጭ በአቅራቢያው የመስኖ ግድብ እየተሠራ ሲሆን፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ መገጭን ውኃ ይውጠዋል የሚል ሥጋት እንዳለ እንግዱ ያስረዳል፡፡

መምህሩ እንደሚገልጸው፣ ድልድዮቹ ከተገነቡበት ጊዜ አንስቶ ያለ ጥገና አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ ከድልድዮቹ አንዱ በአፄ ምንሊክ ዘመን ጥገና ተደርጎለታል የሚል መረጃ ቢኖርም፣ የተቀሩት ዛሬም ያለምንም ጥበቃ ብቸኛ መተላለፊያ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ ‹‹በዞንና በክልል ደረጃ ስለ ድልድዮቹ ስንጠይቅ በዕቅድ ተይዘዋል ከሚል ምላሽ ያለፈ ምንም ሲደረግ አልታየም፤›› ይላል፡፡

ድልድዮቹ ከፍተኛ ጉዳት ውስጥ ከወደቁባቸው ምክንያቶች የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የከተማ መስፋፋት ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ ቀበሌ 18 ባሉ የጎንደር ከተማ አዳዲስ የሰፈራ ቦታዎች የነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር፣ ወደ ገበያ ለመሄድ ያለው አማራጭ ገንፎ ቁጭ ድልድይ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ነዋሪዎች ቅርስ ስለሆነ አንጠቀምበት ቢሉ እንኳን አማራጭ የላቸውም፤›› የሚለው መምህሩ፣ አማራጭ መሠረተ ልማት አለመዘርጋቱ የችግሩ አካል መሆኑን ያስረዳል፡፡

ድልድዮቹ ከመተላለፊያነት ባለፈ ባልተገባ ሁኔታ ለእርሻ የዋሉባቸው እንደ ባምብሎ ጭልቃሳ ያሉ ድልድዮች አሉ፡፡ ስለ ድልድዮቹ አሠራርና ታሪክ ተጨባጭ መረጃ ያለው አካል ባለመኖሩ እነዚህ ድልድዮች መዘንጋታቸውን ይናገራል፡፡ ሩጫው በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶችን ለመጠበቅ ብቻ ቢሆንም የቅርስ ትንሽ የለውም ይላል፡፡

ከቅርስ ጥበቃ በፊት ቅርሶች ያሉበትን ቦታና ሁኔታ የመመዝገብ ሥራ  መቅደም እንዳለበት ይናገራል፡፡ ቅርሶቹ ምዝገባ ስላልተደረገላቸው ለመንከባከብ፣ ለመጠገንና በተገቢው መንገድ ለቱሪዝም ለማዋል አልተቻለም፡፡ አልፎ አልፎ ጎብኚዎች ከሚጽፉት በዘለለ የተዋቀረ መረጃ በሚመለከታቸው የባህልና ቱሪዝም ተቋሞች እጅ መገኘት እንዳለበት ያስረዳል፡፡ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ጥበቃና ጥገና ሊደረግ የሚችለው መረጃ ሲኖር እንደሆነም ያስረዳል፡፡

ሌላው ችግር ቅርሶቹ ባለቤት አልባ መሆናቸው ነው፡፡ ‹‹ቅርሶቹ በቤተ ክርስቲያን፣ በክልል አልያም በፌዴራል ሥር መሆናቸው መለየት አለበት፡፡ ከሌሎቹ የጎንደር ቅርሶች ጋር አስተሳስሮ ለቱሪዝም ማዋልም አልተቻለም፤››  ይላል፡፡ አለታ ድልድይ ወደ ጢስ ዓባይ በሚሄዱ ጎብኚዎች ቢታይም ራሱን እንደቻለ ቅርስ ተወስዶ አይጎበኝም፡፡ ስለ ድልድዮቹ ለጎብኚዎች መረጃ ተሰጥቶ፣ ወደ ድልድዮቹ የሚሄዱበት መንገድ መመቻቸትና በስፋት መተዋወቅ አለባቸው ይላል፡፡ ከሁሉም አስቀድሞ ግን ቅርሶቹ ሳይጠፉ ሊደረስላቸው ይገባል፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ድልድዮቹ ያሉበትን ሁኔታ የሚያሳይ ጥናት ማዘጋጀቱን ይናገራል፡፡ በማኅበረሰባዊ አገልግሎት ሥራቸው በጎንደር ከተማና በዙሪያዋ ላሉ ድልድዮች ጥገና የሚደረግበት ዕቅድ እንዳወጡም ይገልጻል፡፡ የጎንደር ከተማ ቅርሶች የሚገኙባቸው ቦታዎችን ለጎብኚዎች የሚያመላክት አፕልኬሽን የተዘጋጀ ሲሆን፣ ድልድዮቹን በአፕልኬሽኑ የማካተት ዕቅድም አለ፡፡

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ልዑል ዮሐንስ እንደሚናገሩት፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሠራው ቅርሶቹ የሚጠበቁበት የድርጊት መርሐ ግብር የሚተገበር ይሆናል፡፡ ድልድዮቹ የሚጠገኑት በኖራ በመሆኑ፣ ኖራው የሚመረትበት ፋብሪካ ግንባታ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አሁን የኖራ ማቃጠያ ማሽን መገዛቱንና ቅርሱ የሚጠገንበት ኖራ ዱቄት አለመገኘቱ ተግዳሮት እንደነበረና ከፋብሪካው መጠናቀቅ በኋላ መፍትሔ እንደሚኖር አመልክተዋል፡፡ ኖራው ወደ ጎንደር የሚወስደው ከበለሳ ከተማ ይሆናልም ብለዋል፡፡

ድልድዩቹ እንደ ጎንደር ቤተ መንግሥትና ሌሎችም ቅርሶች ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ይስማሙበታል፡፡ ‹‹የሚጠበቅብንን ያህል እየጠበቅናቸው አይደለም፤›› ይላሉ ኃላፊው፡፡ ከመሸጋገሪያ ድልድይነት ባለፈ እንደ ቅርስ እንዳልታዩም ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ጥገናቸው ብዙ ሚሊዮን ብር ወጪ ያስፈልገዋል›› የሚሉት አቶ ልዑል፣ ቅድመ ሁኔታዎች በዚህ ዓመት ተጠናቀው በመጪው ዓመት ወደ ጥገና እንደሚገቡ አሳውቀዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የቅርሶቹ የባለቤትነት ስሜት የሚሰማው አካል ባይኖርም አሁን የጎንደር ከተማ መስተዳድር ኃላፊነቱን ወስዶ ሥለ ድልድዮቹ ሪፖርት እንዲያቀረብ ተደርጓል፡፡ ከከተማው የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባለፈ የመንገድ ግንባታ የሚመለከታቸው ተቋሞች ጉዳይ መሆናቸውንም ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ከቱሪዝም አገልግሎታቸው ይልቅ እንደ መሠረተ ልማት ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው ያመዝናል፡፡ ስለዚህ የመንገድ ባለሥልጣንም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል፤›› ይላሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ሰዎችና እንስሳት ለመጓጓዣ የሚጠቀሙባቸው ድልድዮች መካከል ድንጋያቸው የተሰባበረና፣ የሳሱም ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ መካከል ተጠግነው ዳግም አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ቅርስ ሆነው ሲጠገኑ፣ የማይችሉት በተለዋጭ ድልድይ እንዲተኩ እንደሚደረግ ይናገራሉ፡፡ ከመስኖ ግድብ ግንባታው በኋላ የመገጭ ድልድይ ይዋጣል የሚለውን ሥጋት በተመለከተ ‹‹ግድቡና ድልድዩ ያለበት ከፍታ የተለያየ ስለሆነ እንደማይዋጥ አረጋግጠናል፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

በክልሉ ከፍተኛ አደጋ ካንዣበበባቸው ቅርሶች በግንባር  ቀደምት የሚጠቀሱት ድልድዮቹ እንደሆኑ ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡ ድልድዮቹ በሚቀጥለው ዓመት ጥገና ከተደረገላቸው በኋላ መሸጋገሪያ ብቻ ሳይሆን የቱሪስት መዳረሻ እንደሚሆኑም ያክላሉ፡፡ ‹‹አሁን ድልድዮቹ እንደ ቅርስ አልተዋወቁም፡፡ ሆኖም ውድ ሀብቶች ናቸው፡፡ ጥገናቸው ከተጠናቀቀቀ በኋላ በቱሪስት መዳረሻ ዝርዝር ከፋሲል ቤተ መንግሥት፣ ከመዋኛ ገንዳውና ሌሎችም ቅርሶች ጋር ይካተታሉ፤›› ይላሉ፡፡

ድልድዮቹ እንደ ቅርስ ተጠብቀው፣ አስፈላጊው ጥገና እስከሚደረግላቸው ባለው ጊዜ የሚደርስባቸው ተጨማሪ ጉዳት ግን አሁንም አሳሳቢ ነው፡፡

Source    –       መነሻ ገጽ