የአባዱላን የአፈጉባኤነት ሥልጣን መልቀቅ እንድምታ በፖለቲካችን (በእምነተ አሥተዳደራችን) ላይ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁ ግለሰቦችን የመተንተን አቅም በጣሙን ተፈታትኗል፡፡ ይሄም ብቻ ሳይሆን ለኔ ለሀገራችን ፖለቲካ ቅርብ ነን ብለው የሚያስቡ ፖለቲከኞችን (እምነተ አሥተዳደራውያንን) የቅርብ ሩቅ መሆናቸውን ሳያይቶኛል፡፡ ይመስለኛል!” እያሉ የሚያቀርቧቸው መላምቶች ገለጥ ተደርጎ ከሚታየው መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ሊጣጣምልኝ አልቻለም፡፡ እንደነሱ እምነት አባዱላ ከአፈ ጉባኤነቱ እራሱን ያገለለው በትክክልም በሱማሌና በኦሮሚያ የድንበር ግጭት ጦር ሠራዊቱ ባደረገው ሱማሌን የደገፈ ጣልቃ ገብነት ቅር ስለተሰኘና ጠንካራ የኦሮሞ ሕዝብ ድጋፍ ስላለው በዚህ እርምጃው ከአገዛዙ የከፋ ምላሽ እንደማይገጥመው እርግጠኛ ስለሆነ ነው!” ብለው ያምናሉ፡፡ እነኝህን ተንታኞች ለዚህ የተሳሳተ ምልከታቸው የዳረጋቸው ወይም የሸወዳቸው ዋና ጉዳይ 1993.. አቶ መለስ አባዱላን ከጦር ሠራዊቱ አንሥቶ የኦሮሚያ ክልል ለሚሉት የወያኔ ክልላዊ አሥተዳደር ፕሬዘደንት (ሊቀ ሥልጣናት) አድርጎ ከሾመው በኋላ ወደ አፈጉባኤነት እስከመጣበት ጊዜ ድረስ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ታች ድረስ ወርዶ የሠራውን የማደራጀትንና የማነቃቃትን ሥራ በመመልከት ነው፡፡

በእነኝህ ተንታኞች ግምት አባዱላ ይሄንን የማደራጀትና የማነቃቃት ሥራ የሠራው ከወያኔ በመሸፈጥ የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን ጥቅም የማስከበር አቅም እንዲፈጥር አስቦ ነው ታች ድረስ የማደራጀትና የማንቃት ሥራውን ሲሠራ የነበረው ብለው ያስባሉ፡፡ ይሄንን ብለው ማመናቸው ነው አሁን ላይ አባዱላን በተመለከተ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸው፡፡ እውነታው ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ወይም የራቀ ነው፡፡ አዎ እርግጥ ነው አባዱላ የኦሮሞን ሕዝብ ታች ድረስ ወርዶ የማደራጀትና የማንቃት፣ የማነቃቃትን ሥራ በሚገባ ሠርቷል፡፡ ይሄንን ያደረገው ግን በወያኔ ትዕዛዝ እንጅ አባዱላ ከወያኔ ሸፍጦ ለኦሮሞ ሕዝብ በማሰብ በግል ተነሣሽነት አይደለም ያደረገው፡፡

ነገር ግን እንዴት? ለምን?” የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ ይኖርብናል፡፡ ቁልፉ ነገርም ያለው እዚህ ላይ ነውና፡፡ እንዴት? ለምን? የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ ይሄንን የተወሳሰበ ጉዳይ አጥርቶ ለመረዳት ያስችላሉ፡፡ ወያኔ አባዱላን እንዲህ እንዲያደርግ ያደረገበት ምክንያት ወያኔ እና ኦነግ የሸፍጥ ጋብቻቸውን በፍች ከፈጸሙ ጊዜ ጀምሮ የኦሮሞን ሕዝብ ድጋፍ፣ ተቀባይነትና ታማኝነት ለማግኘት ከፍተኛ ሽሚያና ጥረት ውስጥ ነው የነበሩት ያሉትም፡፡ በሽሚያው የኦነግ ተቀባይነት በሕዝቡ ዘንድ ፍጹም የበላይነቱን መቆጣጠሩ ወያኔን እጅግ ያስጨንቀው ነበር፡፡ ወያኔ ኦነግ በምን ምክንያት በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እሱን በልጦ ተቀባይነት እንዳገኘ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ብየ ስል አጠቃላይ የኦሮሞ ሕዝብ ማለቴ ሳይሆን ኦነግን በተቀበሉት ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህም ወያኔ አቀራረቡን ኦነግ በቀረበበት መንገድ የኦሮሞን ሕዝብ ካልቀረበ በስተቀር የኦሮሞን ሕዝብ ድጋፍና ተቀባይነት ሊያገኝ እንደማይችል ተረዳ፡፡ ይሄንን ለማድረግም ወያኔ ተፈጥሯዊ ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ አማራ አቋሙ እረድቶት ያለ አንዳች መወላከፍ ሊፈጽመው ቻለ፡፡

ይሄንን ተልእኮ ወያኔ ሲፈጽም በቀጥታ እራሱ ወደ ኦሮሞ ሕዝብ ቀርቦ አይደለም፡፡ ኦሕዴድን በመጠቀም እንጅ፡፡ የዚህ ተልእኮ ዋና አስፈጻሚና ተዋናይ አባዱላ ነው የነበረው፡፡ አቶ መለስ አባዱላን 1993.. የክልሉ ፕሬዘደንት (ሊቀ ሥልጣናት) ካደረገ በኋላ በኦነግ ተሰብከው ወደ ኦነግነት የተለወጡትን 50 ሽህበላይ የኦሕዴድ ካድሬዎችን (ወስዋሾችን) አባዱላ ከኦሕዴድ አስወግዷል፣ የእስር ቤቶች ቋንቋ ኦሮምኛ እስኪመስል ድረስ እስር ቤቶችን በኦሮሞዎች እንዲሞሉ አድርጓል፡፡ ይሄን ብቻ አድርጎ አልቀረም አባዱላ፡፡ የተልእው ዋና ዓላማ የኦሮሞን ሕዝብ ከኦነግ እጅ መንጠቅ ስለሆነ ወያኔ አባዱላን ኦነግ የኦሮሞን ሕዝብ በቀረበበት ጽንፈኛ አቀራረብ ቀርቦ ሕዝቡን የኦሕዴድ ታማኝ ደጋፊ ማድረግ በመሆኑ ይሄንን እንዲያደርግ ወያኔ አባዱላን በጣም እንዲፈጋ አደረገው፡፡ አባዱላና በሱ እየተደራጁ የሚንቀሳቀሱ የኦሕዴድ ካድሬዎችን (ወስዋሾችን) ይዞ ጽንፈኛ የሆኑ ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ አማራ ስብከቶችን በማጧጧፍ የኦነግን ቦታ መንጠቅ ቻሉ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ አባዱላ ወደ አፈጉባኤነት ከመጣም በኋላ ኦሕዴድ ቀጥሎበት በአሩሲ ሔጦሳና በሐረር ጨለንቆ ላይ ፍጹም ሐሰተኛ ታሪክ በመፍጠር የተቆረጠ ጡትና እጅን የሚያሳይ የሕዝብን ልብ የሚመርዝና ለበቀል የሚያነሣሣ ሐውልት እስከመገንባት ደርሰዋል፡፡

ደንቆሮው ወያኔ ያልተረዳው ነገር እንዲህ ዓይነቱ ጽንፈኛ መንገድ መጨረሻ ላይ የሚያደርስበት ጽንፈኛ ግብ ያለው መሆኑን ነው፡፡ ኦነግ ይሄንን ጽንፈኛ መንገድ የተጓዘበት ምክንያት ከመንገዱ ጫፍ ላይ ካለው ጽንፈኛ ግብ (መገንጠል) እንዲያደርሰው በማሰብ ነው፡፡ ወያኔ ግን ይሄንን የኦነግ ጽንፈኛ መንገድ የተጓዘበት የኦሮሞን ሕዝብ ከኦነግ እጅ ለመንጠቅ ነው፡፡ ወያኔ እነ አባዱላ ከኦነግ እጅ ነጥቀው እንዲያቀጣጥሉት ያደረገው የጽንፈኝነት ስሜት እየተቀጣጠለ ሔዶ ግለቱ ከማይፈለግ ደረጃ ሲደርስበት የዚህን እንቅስቃሴ መሪ ያደረገውን አባዱላን ከክልሉ ፕሬዘደንትነት (ሊቀ ሥልጣናትነት) አንሥቶ ወደ አፈጉባኤነት በማምጣት እንዲበርድ ለማድረግ ሞከረ፡፡ እርምጃው ግን በኦሕዴድ በኩል ቅሬታን ፈጠረና አቶ አባዱላን የተካውን አቶ ዓለማየሁ ኩምሳን በማያውቀው ነገር የመሥዋዕት በግ አድርጎ ለሕልፈት ዳረገ፡፡ የጽንፈኝነት ግለቱም ሳይበርድ ቀረና የጽንፈኝነት ስሜት ምስ የሆነውን ጽንፈኛ ውጤት ፈልጎ ተንተከተከ፡፡ ሕዝቡና የኦሕዴድ አባላት ይሄንን ምስ ኦሕዴድ ሊሰጣቸው እንደማይችል ሲገባቸው እንደገና ወደ ኦነግ እጅ ገቡ፡፡ ወያኔ ሊመልሳቸው የማይችላቸውን ጽንፈኛ ጥያቄዎችንም በየአቅጣጫው ማስተጋባት ያዙ፡፡ ሕዝባዊ ዐመፅን ጨምሮ በርካታ ችግሮች ተፈጠሩ፡፡

በዘንድሮው የደብረዘይቱ የእሬቻ በዓል እንዳያቹህት የኦነግና የኦሕዴድ መለያዎች ከፍ ብለው ተውለብልበዋል፡፡ ወያኔ ይሄ ጉዳይ አስጨንቆታል፡፡ ያበላሸው ነገር ወደነበረበት ቦታው እንዲመለስም ይፈልጋል፡፡ ወደቦታው ለመመለስም ቀደም ሲል ሕዝቡን ከኦነግ እጅ ለመንጠቅ ኦነግ በሔደበት መንገድ ሔደው ጽንፈኝነትን ሲሰብኩ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን፣ ታማኝነትን፣ ተወዳጅነትን ያገኘውን አባዱላን አሁንም መጠቀም ፈልጓል፡፡ እንደምገምተው ወያኔ አባዱላን ወደ ኦሮሚያ የወያኔ ክልላዊ አሥተዳደር ፕሬዘዳንትነት (ሊቀ ሥልጣናትነት) ሳይመልሰው አይቀርም፡፡ ይሄ ግን ረጅም ጊዜ የሚጠይቅና ምናልባትም ላይሳካ የሚችል አኪያሔድ ነው፡፡ የሚያስፈልገን መፍትሔ አፋጣኝ መፍትሔ በመሆኑ ሌላ አማራጭ መፈለግ ይኖርበታል፡፡

እንግዲህ ወያኔ አባዱላን የኦሮሚያ ክልል የራስ ገዝ አሥተዳደር!” ብሎ ወደሚጠራው ከመመለሱ በፊት አባዱላ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት፣ ታማኝነት፣ ተወዳጅነት መጨመር፣ ማጥበቅ፣ ማጽናት እና የመመለሻ መንገድ ለመፍጠር ስለፈለገ ነው አባዱላን ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ሲል ራሱን ለአደጋ አጋልጦ ከባድ እርምጃ የወሰደና በውጤቱም ለእንግልትና ለችግር እንደተዳረገ አስመስሎ አሁን እያደረጉት ያለውን ነገር ሁሉ እያደረጉ ያሉት፡፡ እናም ጉዳዩ ይሄው ነው እንጅ በፍጹም በፍጹም አባዱላ ለዓመታት ሲያደርገው የቆየውን የማደራጀቱንና ሌላው ሌላውን ነገር ሁሉ ከወያኔ ዕይታ ውጭ ሆኖ ማድረግ ችሎ፣ ከወያኔ ጥቅም በተፃራሪ የኦሮሞን ሕዝብ ለመጥቀም አስቦ በራሱ ተነሣሽነት ያደረገው ሆኖ አይደለም፡፡ ይህ ሊሆን የማይችልባቸውን ምክንያቶች ከሦስት ቀናት በፊት በጻፍኩት ጽሑፍ ላይ ጠቋቁሜያለሁና ወደሱ አልመለስም፡፡ አቶ ገዱንም በዚህ መልኩ ነበር ሲጠቀሙበት የቆዩት፡፡ ሕውሐትን የሚቃረንና ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ መስሎ እንዲተውን በማድረግ፡፡ አስቸጋሪ ምዕራፍ አጋጥሟቸው በቅርቡ ሊጋለጥባቸው ቻለ እንጅ፡፡

በሌላም በኩል ወያኔ እንደ ዘኢኮኖሚስት ባሉ ዓለም አቀፍ ተነባቢ መጽሔቶች በተከታታይ ኅትመት ለ26 ዓመታት የነበረችበት የዘውግ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) ሥርዓት ሀገሪቱን ሊያፈርሳት እንደሆና አጥፊ የአሥተዳደር ሥርዓት መሆኑን እንዲጻፍ አድርጓል፡፡ ወያኔ ይሄንን እያደረገ ያለው ኃላፊነትና ተጠያቂነት ስለተሰማው እንዳልሆነ ከማንም ሰው የሚሠወር አይመስለኝም፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ወደከፋና ማባሪያ ወደሌለው የቀውስ አዙሪት ውስጥ ሊሰምጥ መሆኑ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እጅግ አሳስቦታል፡፡ በወያኔም ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ላለፉት 10 ዓመታት በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የመንገድ ግንባታና የመብራት ኃይል አገልግሎት ሽፋን እጅግ በተዛባና ኢፍትሐዊ በሆነ መልኩ ለትግራይ ማድላቱን ማጋለጡ ለዚህ ጠቋሚ ነው፡፡ ለአሜሪካ መንግሥት የቀረበው የወያኔን አገዛዝ የተመለከተው የውሳኔ ሐሳብም የዚህ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና የማሳደሪያ እርምጃዎች አንዱ አካል ነው፡፡ የወያኔ አመራሮች የትም ሔደው ሊያመልጡ እንደማይችሉና ተለቃቅመው ለፍርድ እንደሚቀርቡ በመንገር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩበት ይገኛሉ፡፡ የፍትሕ የበላይነትን ባረጋገጠ መልኩ ሰላማዊ ሽግግር ሊመጣ ይችላል ወይ?” የሚለው ጉዳይ በወያኔ ላይ በሚደረገው ጫና መጠን የሚወሰን ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጫና ምክንያት ወያኔ ምን እናድርግ?” የሚለውን ለመወሰን በዝግ ስብሰባ ላይ ከሳምንት ላለፈ ጊዜ እንደተቀመጠ ነው፡፡ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና በተጨማሪ የእኛ ጸሎትና በየአቅጣጫው ሊደረግ የሚገባው የየግልና የቡድን ጥረቶች ከታከለበት ውጤቱ ሊያምር ይችላል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ወያኔ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመረውን እርምጃ ትቶ ወደኋላ በመመለስ አይ አይሆንም! አጥፍቸ እጠፋለሁ እንጅ!” ካለም መቀመቅ መውረዳችን ነው፡፡ እስኪ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ቸሩን ያሰማን! የሚበጀንን ነገር ያድርግልን! አሜን!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com