October 12, 2017 06:26

ጌታቸው ሺፈራው

አቶ እንግዳው ዋኘው

( አቶ እንግዳው ዋኘው የቀድሞው አንድነት ፓርቲ የአርማጭሆ አመራር ነበር። አቶ እንግዳው የ”ሽብር” ክስ ቀርቦበት የአራት አመት ፍርድ ጊዜ ከታሰረ በሁዋላ በፍርድ ቤት ነፃ ተብሏል። ከመታሰሩ በፊትና በታሰረበት ወቅት የደረሰበትን በደል አጫውቶኛል። እኔም ለንባብ በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ! ____ጌታቸው ሺፈራው)
እኔ በመጀመሪያ ወያኔን ለመታገል ቆርጬ የተነሳሁት በሀገራችን ላይ የሚያደርሰውን በደል በመመልከት ነው። በምሰራበት መስርያቤት በኩል ገበሬው ላይ የሚደርሰውን በደል ስላየሁ ከወገኔ ከገበሬው ጎን መቆም ስለነበረብኝ ነው። በህገ ወጥ መንገድ መሬት ለሱዳን ሲሰጥ ዝም ማለት ስላልነበረብኝና ስላልቻልኩም ነው።
ወያኔ እራሱ ባወጣው ህገ መንግስት መሰረት ከ1996 ዓም ጀምሬ ስታገል ቆይቻለሁ። በዚህ ወቅትም በ1997፣በ2005፣ ከ2007 እስከ 2009 ዓም (በመጨረሻው እስር ሁለት አመት ከስምንት ወር ያህል) ለእስር ተዳርጌያለሁ። በ2007 ከመታሰሬ በፊት ስሰራበት የነበርኩት ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ መሬት አስተዳደር እና አካባቢጥበቃ መስሪያቤት ነበር። ወረዳው ኢትዮጵያ ከሱዳን የምትዋሰንበት ነው። ብዙ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የሀገራችን መሬት ለሱዳን የተሰጠው በዚህ ወረዳ ነው። በወረዳ በምሰራበት ጊዜ አብረውኝ ከተከሰሱት እና አሁን እስር ቤት ከሚገኙት ከእነ አንጋው ተገኘ ጋር በመሆን የአንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ቅርጫፍ ፅ/ቤት ከፍተን ከመንግስት ስራ ስንመለስ የፓርቲ ስራ እንሰራ ነበር።
መሬታቸውን ተነጥቀው ለሱዳን የተሰጠባቸው እና ትክ መሬት ያልተሰጣቸው ገበሬዎች በየጊዜው ለአንድነት ፅ/ቤት የደረሰባቸውን በደል ይገልፁ ነበር። እኔ በበኩሌ ለሱዳን መሬታቸው የተሰጠባቸውን እና ትክ መሬት ይሰጠን ብለው የሚጠይቁት ከ1000 በላይ ገበሬዎች እንደነበሩ አውቃለሁ። ትክ መሬት እንደማይሰጣቸው ከምሰራበት መስርያ ቤት መረጃው ስለነበረኝ፣ እነሱም መግስት ትክ መሬት እንደማይሰጣቸው ከወረዳ እስከ ክልል ጠይቀው ስለተረዱት መሬታቸው በራሳቸው እንዲይዙ እመክራቸው ነበር። ምስጢሩን ስለማውቅ በነገርኳቸው መሰረትም መሬታቸው ሱዳንን አባረው ይዘው ነበር። ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም!
ሆኖም ደህንነቶች ገበሬዎች ጋር ተመሳስለው እየገቡ ሁኔታውን ስለሚያውቁ እኔን በስልክ እየደወሉ ለገበሬው መወገኔን፣ ተቃዋሚነቴን እንድተው ካልተውኩ ከስራዬ እደሚያባርሩኝ፣ ከዚህም በተጨማሪ ሊያስሩኝና ሊገድሉኝ እንደሚችሉ ይዝቱብኝ ነበር።
ለሱዳን ከተሰጠው መሬት በተጨማሪ ከገበሬዎች እየተነጠቀ ለደህንነቶች፣ለኮለኔሎች፣ለጀኔራሎች እንዲሁም ለባለስልጣናት እና ቤተሰቦቻቸው ይሰጥ ነበር። ለምን በመሬት አዋጁ መስረት ለገበሬዎቹ አይሰጥ የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ አቅርቤያለሁ። በወረዳው ሙስና ስለተስፋፋና እኔም ሙስናን ስታገል ቆይቻለሁ። በዚህም በወረዳ ከ2004 ዓም ጀምሮ በሙስና በአመራሮች ከድሃው ገበሬ የተዘረፈ 125000 ( መቶ ሀያ አምስት ሽህ) በላይ ብር አስመልሻለሁ። በዚህ ምክንያት ግን ከሙሰኞቹ ቂም ተይዞብኛል።

ባለሙያ ተብለው የተቀጠሩት እና የወረዳ አመራሮችን 2004 ዓም በወረዳው የመሬት ሽግሽግ ስለነበር ለስራ ማስኬጃ ከተመደበው ብር መካከል 11ሚሊዮን ብር በልተዋል። ይህን የሙስና ወንጀል የፈፀሙ ባለሙዎች እና አመራሮችን በማጋለጥ እዲጠየቁና ከስራ እዲታገዱ ጥረት አድርጌያለሁ። በዚህም ምክንያት በብአዴን ትዕዛዝ ሰጭነት “የተበላ ቢበላ ምን አገባህ”! አይነት የቃልና የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ በመስርያ ቤቴ በኩል ደርሶኛል። እዲሁም “ፊልድ” ወጥቸ ስሰራ የውሎ አበል እንዳይከፈለኝ፣ እንዲሁም ሌሎች ህጋዊ ጥቅማጥቅሞችንም ተከልክያለሁ።ከተለያዩ ማህበራዊ ሁኔታዎች ተገልያለሁ። ሙሰኞችን በመታገሌ፣ ለወገኔ ለገበሬው ጥቅም በመቆሜ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ህይወቴ ብዙ በደል ደርሶብኛል።
እኔ ለሀገር ሉዓላዊነት ስለቆምኩ፣ ለገበሬው ወገኔ ስለወገንኩ ብዙ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶብኝ ወደሁዋላ አላልኩም። እኔ አልበገር ስላቸው ግን በትዳር ጓደኛዬ በኩል መጡ። ባለቤቴ ተቃዋሚነቴን እንድተው ካደረገች ቤትን ጨምሮ ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን እንደሚሰጧት ቃል ገቡላት። ከተቃዋሚነቴ ማስቆም ካልቻለች ግን እኔን እንደሚገድሉኝ ያስፈራሯት ነበር።
ከታሰርኩ በሁዋላ አንዴ መጥታ ስለጠየቀችኝ ብዙ ማስፈራሪያ ደርሶባታል። ከአሁን በሁዋላ ብትጠይቂው እናስርሻለን ብለዋታል። እኔን የሞት ፍርድ እንደሚጠብቀኝ በመንገር ተስፋ እንድትቆርጥ፣ የእኔን ጉዳይ እንዳትከታተል በማስፈራራት እኔ እስር ላይ እያለሁ ተገዳ ከትዳሬ በላይ የራሳቸውን ሰው እንድታገባ አድርገዋል። እኔ ህዝብን ሲዘርፉ፣ ገበሬውን አፈናቅለው የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን ሲሰጡ ስለታገልኳቸው በግፍ ማሰራቸው ሳይበቃ ትዳሬን አፍርሰዋል። ስልጣናቸውን ተጠቅመው የትዳር አጋሬን ነጥቀውኛል።
ትዳሬ ክብሬ ነበር። ይህን ትዳሬን ነጥቀውኛል። ግን የእኔ አላማ ከትዳሬም በላይ ነው። የእኔ አላማ ከጥቅም እና ከግሌ ክብር በላይ ለህዝቤ መቆም ነው። ከባለቤቴ ጋር ከሁለት አመት በላይ አብረን ስንኖር በጋራ ያፈራነው ንብረት ነበር። ባለቤቴን ነጥቀውኛል። አብረን ያፈራነውን ንብረትም ቀምተውኛል። ንብረቴን ይቅርና መረጃዎችን እንኳን ስጠይቅ የሰጡኝ መልስ “ደግመህ እንዳትታሰር!” የሚል ማስፈራሪያና ዛቻ ነው። በግፍ ሁለት አመት ከስምንት ወር አስረው፣ ቤቴን አፍርሰው፣ ንብረትና ማስረጃዎቼን ስጠይቅ አሁንም ዳግመኛ በሀሰት እንደሚያሳስሩኝ ከመዛት አልተመለሱም።
በታሰርኩበት ወቅት እህቴ ለበሽታ ተጋልጣና የሚያሳክማት አጥታ ታማሚ ሆናለች። ማዕከላዊ እስር ቤት እያለሁ ያልፈፀምኩትን ፈፅመሃል ተብዬ፣ የማላውቀውን ተናገር እየተባልኩ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞብኛል። ቂሊንጦ ቀኝ እጄን በፌሮ ብረት መትተው ሰብረውኛል። አሁንም እጄ አልዳነም!
በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ 13ኛ ተከሳሽ ሆኜ በሀሰት የቀረበብኝን ክስ ስከታተል ከቆየሁ በሁዋላ “የግንቦት ሰባት አባል ነህ፣ አባላትን መልምለህ ትልካለህ” በሚል የቀረበብኝ የሀሰት ክስ በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጎ የአራት አመት ፍርድ ( 2 አመት ከ8 ወር) ከታሰርኩ በሁዋላ ነፃ ተብያለው። በዚህ ወቅት ብዙ ነገር አጥቻለሁ። ተበድያለሁ። ቤቴ ፈርሷል። ንብረቴን ወርሰውኛል። አሁንም ችግር ላይ እንድወድቅ አድርገዋል።
ሰራተኛ እያለ የታሰረ ሰው ነፃ ሲባል ወደ ስራው ይመለሳል። በእስር ወቅት ያልተከፈለው ደመወዝም እንዲከፈለው ይደረጋል። እኔም ነፃ ከተባልኩ በሁዋላ ወደ ስራ እንድመለስ ስጠይቅ ” ስለፈታነህ ልታመሰግን ይገባል” ብለውኛል። ወደ ስራ እንድመለስ ወረዳ፣ ክልልና ዞን ሲቪል ሰርቪስ መስርያ ቤቶችን ጠይቄያለሁ። ያገኘሁት መልስ ግን ተመሳሳይ ነው። መፈታቴን እንደ ልግስና ቆጥረው ወደ ስራ መመለስ መብት እንደሌለኝ ነግረውኛል። ከእኛ መስርያ ቤት ሆነህ ልትታገለን አይገባም ብለውኛል። ይህን ጥያቄየንና ሲቪል ሰርቪስ የሰጠኝን መልስ ለእንባ ጠባቂ ተቋም ሳቀርብ ተቃዋሚ መሆኔን አውቀው ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ያሉ ካድሬዎች ያስተላለፉትን የጥላቻ ውሳኔ ትክክል ነው ብለው አፅድቀዋል።