15 October 2017

ሻሂዳ ሁሴን

በጋ ከክረምት ለመቶ ዓመታት ያህል ምንም ነገር በቅሎበት አያውቅም፡፡ ሌሎች በዙሪያው የሚገኙ ማሳዎች ልምላሜ ለብሰው ይኼኛው ቦታ ግን በተለየ ምድረ በዳ ሆኖ መታየቱ ለብዙዎች ያልተለመደና እንግዳ ነገር ነው፡፡ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩና አሁን የሚገኙ አርሶ አደሮች ሰይጣናዊ መንፈስ ተጠናውቶታል በሚል ማረስ ከተው ዓመታት ተቆጥረዋል ይባል፡፡

በርበሬ የሚመስለው ቀዩ አፈር ለምነቱ ጠፍቶ ቦረቦር ሆኗል፡፡ አፈር ሳይሆን የተከመረ አሸዋ ይመስላል፡፡ እንደ አሸዋ ክምር በነፈሰ ቁጥር የሚንሸራተተው አፈሩ እንኳንስ ሊያርሱት ለመርገጥም ያስቸግራል፡፡ መሬቱ ከመረገጡ ደርሶ ይናዳል፡፡ በተደጋጋሚ የመሬት መንሸራተትና ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር የጎዳው ስለመሆኑ ዓይቶ መገመት አይከብድም፡፡ መሀል ለመሀልም ትልቅ ሸለቆ ሠርቷል፡፡ የምድረ በዳነትና የለምለምነት ንፅፅር ማሳያ የሚመስለው ይህ ስድስት ሔክታር መሬት በጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳ ቡልቡል ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡

‹‹ቦታው ሳርም ሆነ ሌሎች ቅጠላቅጠሎች አያበቅልም፡፡ በአፈር ውስጥ የሚገኙ እንደ ናይትሮጂንና ፎስፈረስ ያሉ ንጥረ ነገሮች ከውስጡ ተሟጠው ጠፍተዋል፡፡ ምንም ዋጋ የሌለው ዴድ ላንድ ነው፤›› የሚሉት የተራቆቱ ቦታዎችን መልሶ ማልማት ላይ ምርምር የሠሩት አያሌው ታለማ (/) ናቸው፡፡ /ር አያሌው፣ በቡልቡል ቀበሌ ከሚገኘው ከዚህ ቦታ በተጨማሪ በግልገል ጊቤ ግድብ ዙሪያ የሚገኙ ሌሎች አምስት ወረዳዎችንም በጥናታቸው አካተው ነበር፡፡

ጥናቱ 96 በመቶ ለሚሆነው ለግልገል ጊቤ ግድብ ምንጭ የሆኑት በደደዎ፣ በሰቃ ጨቆርሳ፣ በቀርሳ፣ በኦሞ ናዳ፣ በጢሮ አፈታና ሰኮሩ በተባሉ ስድስት ወረዳዎች የሚገኙ 650 ቦታዎችን ያካተተ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ወረዳ እንደ ቡልቡል ያሉ  የተራቆቱ አካባቢዎች አሉ፡፡ ዶ/ር አያሌው በምርምራቸው በአሁኑ ወቅት ቡልቡል መልሶ እንዲያንሰራራ፣ ሌላው ቢቀር ሳር ማብቀል እንዲችል አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና 85 በመቶ ጠቅላላ የሥራ ድርሻ፣ እንዲሁም 38.7 በመቶ ለሚሆነው ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ምንጭ ነው፡፡ ይህም የአገሪቱ ኢኮኖሚ በግብርና ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያሳያል፡፡ 85 በመቶ ለሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ህልውና መሠረት የሆነው ዘርፉ ግን እንደ ስለት ልጅ ስንክ ሳር የበዛበት ነው፡፡ ለዚህም በምርምር የበቁ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና የምርምር ውጤቶችን በበቂ ጥቅም ላይ አለመዋላቸው በምርታማነት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ሲያልፍም በአብዛኛው በዝናብ ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ግብርና ዝናብ ሲያጥር በድርቅ፣ ሲበዛ ደግሞ በጎርፍ ይፈተናል፡፡

ኦሮሚያ ተከስቶ በነበረው ድርቅ የተጎዳ ማሳ

ሌላው የዘርፉ ፈተና የመሬት መራቆት ነው፡፡ በደረቅነታቸው ከሚታወቁ ቦታዎች በተጨማሪ ለምለም የነበሩ ማሳዎችም የንጥረ ነገር ይዘታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ ሄዶ ምንም ማብቀል የማይችሉ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ያለማዳበሪያ ምርት ማግኘት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ የደረሱም አሉ፡፡ ተስማሚው የማዳበሪያ ዓይነት ካልተገኘም የምርት መጠን በዚያኑ መጠን አነስተኛ ሊሆን አሊያም ሌላ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡፡

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ 85 በመቶ የሚሆው የኢትዮጵያ መሬት በተለያየ መጠን የተራቆተ ነው፡፡ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የእርሻና የግጦሽ መሬት መስፋፋት ለመሬት መራቆት መንስኤ ከሆኑት ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ ይህም በአረንጓዴ የተሸፈኑ ቦታዎች በከፍተኛ መጠን እንዲመነጠሩ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሌሎቹን ዕፀዋት ሳይጨምር በየዓመቱ 19,000 ሔክታር ደን ይመነጠራል፡፡ ይህም ለአፈር መራቆት ያለውን ተጋላጭነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረው ይገኛል፡፡ ሁኔታው ተዳፋት የሆነ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ላላቸው ትግራይና አማራ ክልሎች ከፍተኛ የመሬት መራቆት እንዲመዘገብባቸው ምክንያት ነው፡፡ በተወሰኑ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎችም ተመሳሳይ ችግር እያስከተለ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ማኅበረሰቡ በአፈር አጠባበቅ ላይ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ተጋላጭነቱ ይበልጥ የከፋ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በአገሪቱ በዕርከን የማረስ ባህልም በተገቢው መጠን አላደገም፡፡ ስለዚህም ከፍተኛ ዝናብ በጣለ ቁጥር ለምርት ወሳኝ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ወይም ለም አፈር በጎርፍ ይወሰዳል፡፡ ይህም በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ከፍተኛ የመሬት መራቆት ከሚያጋጥማቸው የአገሪቱ ክፍሎች መካከልም ሰሜን ሸዋ ዞን አንዱ ነው፡፡ በዞኑ 210,570 ሔክታር የተራቆተና ከተራራማ መልክዓ ምድር የሚካተት ቦታ አለ፡፡ 245,062 ሔክታር መሬት በቁጥቋጦና በአስተኛ ዕፀዋት የተሸፈነ ነገር ግን በከፍተኛ መጠን የተጎዳ መሬት አለ፡፡ ‹‹በአጠቃላይ በእያንዳንዱ የእርሻ መሬት ላይ ያለውን ሳያጠቃልል 28 በመቶ የሚሆነው የዞኑ ክፍል የተራቆተ ነው፡፡ የእርሻ መሬቶችም ትልቅ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤›› የሚሉት በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም የሥራ ሒደት መሪው አቶ ጌታነህ ተክለማሪያም ናቸው፡፡

 መንዝ ጌራ፣ መንዝ ማማ፣ መንዝ ቀያ፣ መንዝ ላሎ፣ ሞጃ ወደራ፣ ጣርማ በር፣ ባሶና ወረና፣ ቀወት፣ ሀገረማሪያም፣ መራቤቴ በዞኑ ከሚገኙ በከፍተኛ ደረጃ ከተራቆቱ አካባቢዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የተቀሩትም ቢሆኑ በንፅፅር የተሻሉ ሊባሉ ይችላሉ እንጂ፣ ከጉዳት ነፃ የሆኑ አይደሉም፡፡ በዞኑ የሚገኙ አርሶ አደሮች ምርታማነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከማሳቸው የሚያገኙት ምርት ከ20 ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በሁለት እጥፍና ከዚያ በላይ መቀነሱን አንዳንድ አርሶ አደሮች ይናገራሉ፡፡ ማዳበሪያ መጠቀም መቻላቸው ምርታማነቱን በተወሰነ መጠን እንዲጨምር ቢያደርገውም፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲተያይ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ያብራራሉ፡፡

‹‹በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለማዳበሪያ ማምረት የማይታሰብ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ በዞኑ ከ50 ዓመታት በፊት የነበረው ምርታማነት አሁን ካለው ጋር ሲተያይ ትልቅ ልዩነት እንዳለው ያሳያል፤›› በማለት አቶ ጌታነህ የአርሶ አደሮቹን አስተያየት እንደሚጋሩ ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ባለው የአየር ፀባይ ለውጥ ምክንያት በልግ አብቃይ የሆኑ ቦታዎች በበልግ ማብቀል ካቃታቸው ቆይተዋል፡፡ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ባለባቸው ቦታዎች የሚለሙ ሰብሎች ብዙውን ጊዜ በውርጭ ይጠቃሉ፡፡ ይህም በዞኑ ካለው ከፍተኛ የመሬት መራቆት ጋር ተዳምሮ በምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የአፈር ልማት ጥበቃ ባለሙያና የማኅበረሰብ ሥራዎች ማስተባበሪያ ዩኒት አስተባባሪው አቶ አብነት መንግስቱ እንደሚሉት፣ የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ ተፋሰስን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ የዕርከን ሥራዎችና ከእነዚህ ጋር ተቀናጅተው የሚሠሩ የውኃ ማፋሰሻ ሥርዓቶችን የማበጀት፣ እንዲሁም የተጎዱ አካባቢዎች በአጭር ጊዜ እንዲያገግሙ ለማድረግ የመከለል ሥራ ይሠራል፡፡

ከፍተኛው የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በትግራይና በአማራ ክልል፣ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ በኦሮሚያ አካባቢ፣ በምዕራብ ሐረርጌ፣ በደቡብ ክልል በተወሰነ መጠን ተጋላጭነቱ አለ፡፡ ከሌሎቹ በተለየ ከፍተኛ ተጋላጭነት የነበረው በትግራይ ክልል ነበር፡፡ በክልሉ ከ1984 .. ጀምሮ በተሠሩ ሥራዎች 1.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም የከርሰ ምድር ውኃ መጠን እንዲጨምር፣ የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስና የክልሉ ነዋሪዎች በመሬቱ ላይ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን እንዲያለሙ አስችሏል፡፡ ለዚህ ተምሳሌታዊ ተግባርም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማበረታቻ ሽልማት ተችሯል፡፡

በአማራ ክልልም እንደዚሁ ተመሳሳይ ሥራ ለመሥራት ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን ክልሉ ካለው የመልክዓ ምድር አቀማመጥና ከሚኖረው ከፍተኛ የዝናብ መጠን አንፃር ለአፈር መሸርሸር ያለው ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው፡፡ በኦሮሚያም ከፍተኛ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች እንደዚሁ ተመሳሳይ የተጋላጭነት ችግር ይታያል፡፡

ሁኔታው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በከፍተኛ ደረጃ በድርቅ ለሚፈተኑና የምግብ ዋስትና ችግር ላለባቸው አገሮች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደገፍ ያህል በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ብቻ 4.3 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ ማጣቷም አስደንጋጭ ነው፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም መንግሥት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዋነኛ አካል አድርጎት እየሠራበት ይገኛል፡፡ በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በጀት መጨረሻ 10,860.6 ሔክታር የሚሸፍኑ አካባቢዎች ተከልለው እንዲያገግሙ ማድረግ ተችሏል፡፡ 15,399.17 ሔክታር ቦታም ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ባላቸው የዛፍ ችግኞች መሸፈንም ተችሏል፡፡ በ24,509.1 ተፋሰሶች የተለያየ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በጀት ዓመት መጀመርያ ላይ ማለትም በ2008 .1812000 ሔክታር መሬት ከንክኪ ነፃ እንዲደረግና ተከልሎ እንዲያገግም ለማድረግ ታቅዶ 1707468 ሔክታር ከንክኪ ነፃ ተደርጎና ተከልሎ እንዲቆይ ማድረግ መቻሉን የተፈጥሮ ሀብት ልማት የበጀት ዓመቱ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በ2655132 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ የሥነ አካላዊና የአፈር ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ለችግሩ ከፍተኛ ተጋላጭነት ባላቸው በአራቱ ክልሎችም የ15922.2 ሔክታር መሬት ዕርከን መሥራት ተችሏል፡፡

2009 .ም በጀት ዓመት ደግሞ 1463000 ሔክታር መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተከልለው እንዲያገግሙና መልሰው አገልግሎት መስጠት ወደሚችሉበት ሁኔታ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ በ2267000 ሔክታር መሬት ላይም የሥነ አካላዊ፣ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ የተራቆተን መሬት መልሶ እንዲያገግም የሚያስችሉ 5.37 ቢሊዮን የዕፀዋት ችግኝ በክልሎቹ ማሠራጨት ተችሏል፡፡ እነዚህ የችግኝ ዝርያዎች ሰስባኒያ፣ ሉሲኒያ፣ አልቢዳግራር፣ አኬሻ አልቢዳ፣ ግራቪሊያ፣ ሽፈራው፣ ፒጀንፒ፣ ዲከረንስ፣ የመሳሰሉትና የተለያዩ የሳር፣ እንዲሁም የመኖ ዘሮች ናቸው፡፡

 2010 .2192000 ሔክታር ቦረቦሮችና አካባቢዎች ከንክኪ ነፃ ሆነው ተከልለው እንዲያገግሙ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ 1155000 ሔክታር የተራቆተ መሬት በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ እንዲሸፈኑ፣ በክልሎች በተፈጥሮ ሀብት ሥራዎች የሠለጠኑ ባለሙያዎችን 19000፣ አርሶ አደሮችን 601000 ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ በበጀት ዓመቱ የፊዝካል ሥራዎች ዕቅድ ዝግጅት ያመለክታል፡፡

የሚሠሩት ሥራዎች አገሪቱ በመሬት መራቆት ምክንያት የሚገጥሟትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመቅረፍ ዓይነተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሁንና ዘለቄታዊ ጥቅሙን ባለመረዳት ‹‹ከብቶቻችን የት ይግጣሉ›› በማለት ቦታዎች እንዳይከለሉ የሚከላከሉ አርብቶ አደሮች እንደሚያጋጥሙ አቶ አብነት ይናገራሉ፡፡

የመሬት መራቆት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ነው፡፡ ‹‹በ1999 .ም ከቀያቸው ሊፈናቀሉ ጥቂት የቀራቸው አባወራዎች በተሠሩ ሥራዎች መሬቱ መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ስለተቻለ በቀያቸው ሊቆዩ ችለዋል፤›› ያሉት አቶ ጌታነህ፣ የመሬት መራቆት ለብዙዎች መፈናቀል ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በየዓመቱ 12 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ይራቆታል፡፡ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ተሸርሽሮ የሚነሳው የለም አፈር መጠን 24 ቢሊዮን ቶን ይደርሳል፡፡ የመሬት መራቆት ለበረሃማነት መስፋፋት ዋነኛው ምክንያት ሲሆን፣ 3.6 ቢሊዮን ሔክታር ወይም 25 በመቶ የሚሆነው የመሬት ክፍል የተራቆተና በመራቆት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው የመሬት ክፍል ወደ በረሃነት ተሸጋግሯል፡፡ በረሃማነትና ድርቅ በመቶ አገሮች ለሚኖሩ 1 ቢሊዮን የዓለም ሕዝቦች ፈተና ናቸው፡፡