አዴኃን የአርበኞች ግንቦት 7 ክንፍ ነው ሲል አቃቤ ህግ ክስ አቀረበ

• የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባል የ”ሽብር” ክስ ቀርቦበታል

(በጌታቸው ሺፈራው)

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴኃን) የአርበኞች ግንቦት 7 ክንፍ ነው ሲል ክስ አቅርቧል። ዛሬ ጥቅምት 6/2010 ዓ•ም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል አባል በነበረ ግለሰብ ላይ በቀረበው የ”ሽብር” ክስ አዴኃን የአርበኞች ግንቦት 7 ክንፍ ነው በሚል ተጠቅሷል። አቃቤ ህግ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባል የነበረው ኮንስታብል ብርሃን በላይ ቸኮል ላይ ባቃረበው ክስ አዴኃንን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ክንፍ ከማለቱም ባሻገር የ”ሽብር ቡድን” ሲል በ”ሽብር” ፈርጆታል።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ በተነበበው ክስ ኮንስታብል ብርሃን አማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢጠና ወረዳ አውንት ጎንቻ ጫካ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ቄስ ደመቀ ዓለሜ፣ አበባው መኮንን፣ አበራ ምናሉ፣ ልቅናው ምህረት፣ ምትኩ ፀጋዬ፣ ዮናስ ጋሻው እና ደሳለኝ የተባሉ የአዴኃን ታጣቂዎች ጋር አብሮ እንዲሰራ ተልዕኮ ተሰጥቶት ተስማምቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

በተጨማሪም ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ያሉና የከዱ ጠንካራ አባላትን ለመመልመል ተስማምቷል፣ አባላትን መልምሎ ወደ ኤርትራ ልኳል፣ ባህርዳር አካባቢ ሆኖ ለአዴኃን ለመስራት ተስማምቷል፣ ስለ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና አመራሮቹ ጠቃሚ መረጃ ለአዴኃን ሰጥቷል የሚል ዝርዝር ክስ ቀርቦበታል።

አቃቤ ህግ “በኢፌዲሪ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ አባል ሆኖ ሲሰራ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ የገባውን ቃል ኪዳን በማፍረስ እራሱን የአርበኞች ግንቦት 7 በማለት በሚጠራው የሽብር ቡድን ክንፍ በሆነው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ በማለት በሚጠራው የሽብር ቡድን” አባል ነው በሚል ባቀረበው ክስ ኮንስታብል ብርሃንን የአርበኞች ግንቦት 7፣ እንዲሁም የአርበኞች ግንቦት 7 ክንፍ የሆነው አዴኃን አባል ነው የሚል ክስ አቅርቦበታል። አባላትን በመመልመል፣ በማደራጀት፣ ለአዴኃን አባላትና አመራሮች መረጃ በማቀበል ” በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ አባል መሆን በማንኛውም መልኩ በመሳተፍ ወንጀል” ክስ የቀረበበት ኮንስታብል ብርሃን የክስ መቃወሚያ ለማቅረብ ለጥቅምት 29/2010 ቀጠሮ ተሰጥቶታል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ በፀረ ሽብር አዋጁ ከተፈረጁት የፖለቲካ ቡድኖች ውስጥ እንዳልሆነ የሚታወቅ ሲሆን በፀረ ሽብር አዋጁ ባልተፈረጁት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴኃን)፣ የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ( ጋህነን)፣ የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን)፣ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን)፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) አባልነት በ”ሽብር”የተከሰሱና የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይታወቃል።

በአዋጁ በ”ሽብርተኝነት” ያልተፈረጁ ድርጅቶች ከአርበኞች ግንቦት 7 እና ኦነግ ጋር ግንባር ፈጥረዋል፣ አብረው ስራ እየሰሩ ነው እንዲሁም በ”ሽብር” የተፈረጁት ድርጅቶች ክንፍ ናቸው በሚል በድርጅቶቹ ስም ክስ የሚቀርብባቸው ተከሳሾች አቀቤ ህግ የሚያቀርብባቸውን ክስ በሀሰት እና ሆን ተብሎ ለማጥቃት የቀረበ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።