በሃገራችን ኢትዮጵያ የወያኔ መንግሥት የመግዛት አቅም መቀነስና ህዝቡም እንደቀድሞው መገዛት አለመፈለግና ለውጥ ፈላጊነት እያደገ መምጣት /Decremental Deprivation/ እንዲሁም ለዚህ የሕዝቡ ፍላጎት ምላሽ መስጠት ስለተሣነው ወይም ባለመፈለጉ ሃገራዊ ፖለቲካዊ ቀውሱ ተከስቷል:: ተባብሷል:: ወያኔም ይህን የለውጥ ማዕበል እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ ሃይሉ እጅጉን ተዳክሟ ል(Loses Momentum)::

በሃገራችን ኢትዮጵያ በህወሃት አማካኝነት የተተገበረውና ቋንቋን የታከከ ፖለቲካዊ አደረጃጀት ከአንድነት ይልቅ ልዩነት:ከድርድር ይልቅ ፍጥጫን:ከመተማመን በላይ የእርስ በርስ ተጠራጣሪነትን መርዝ በህዝብ ውስጥ ረጭቷል::በሃገሪቱ ያሉ ከ80 በላይ ጎሣዎች በተቆለፈ ክፍሎች ውስጥ ታሽገው የእርስ በርስ መስተጋብር እንዳያደርጉና በጎሪጥ እንዲተያዩ ተደርጏል::ብሄራዊ እሴቶቻቸውን እንዳይመለከቱ በአፓርታይዳዊ ዘይቤ ዓይናቸው ተጋርዷል::ጎሣ ተኮር የጎሣ ፖለቲከኞች እንዲፈለፈሉ ጥርጊያ አመቻችቷል::የጎሣ አባላቱም የተቆለፈባቸውን በር በመስበር ለመውጣት ይዳክራሉ::ኢትዯጵያዊ ማንነታቸው በጎሣ ፖለቲካ አዙሪት ቀጭጯል::የመበታተን አደጋም ተጋርጧል:;ይህ በዚህ ከቀጠለ ወደማያባራ የእርስ በርስ ግጭት ሁኔታው እንደሚያመራ ፍንጮች/Omens/ ታይተዋል::

የፖለቲካ ሃይሎቹ አሰፋፈር

1. የወያኔ መንግሥት
<< የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት>>አምጣለሁ ብሎ ስልጣንን ከ26 ዓመት በፊት በጠመንጃ የያዘው ይህ የአንድ አናሳ ጎሣ መንግሥት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምህዳርን ጠርቅሞ በመያዝ የራሱን የጎሣ ድንበር ያሠፋል:ጦሩን ያደራጃል ሃብቱን ይዘርፋል::ህዝብ እርስ በርሱ በጥርጣሬ ዓይን እንዲተያይ በማድረግ ህብረታቸውን ለመግታት ሲል ኢትዮጵያዊነትን አደብዝዟል::26 ዓመት የእኩልነት ትርክቱ ተኗል::ህዝባዊ እምቢተኛነትና አልገዛም ባይነቱ ድንበሩን ጥሶ በመላ ሃገሪቱ ዛሬ ያስተጋባል::የወያኔም ምሱ ጥላቻ ብቻ ሆኗል::ህዝቡ እንደቀድሞው ለመገዛት አለመፍቀድና የዚህ ያለመገዛት ህዝባዊ ፍላጎት በህዝባዊ እምቢተኛነት ታጅቦ በወያኔና በህዝቡ መሃል ሚዛኑ/equilibrium/ ተመጣጥኗል::ወያኔም ሁኔታውን ለመጨፍለቅ እንዲችል ፋሽስታዊ እርምጃ ለመውሰድ ይዘጋጃል::ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ጥገናዊ የመንግስት ግልበጣ ለማድረግ እያሟሟቀ ይገኛል::
2. የጎሣ ፖለቲከኞች

እነዚህ ሃይሎች በተለይም የኦሮሞ የጎሣ ፖለቲከኞች በህዝብ ውስጥ የተቀሰቀሠውን ዐመጽ የመምራት ብቃታቸው በውስጣቸው በሚንከባለለው የመገንጠል ፖለቲካዊ ህልም እየተደናቀፈባቸው የነርሱን የግል ፍላጎት በህዝቡ ትከሻ ላይ በመጫን ኢትዮጵያን በማፍረሱ ተግባር ከተሠማሩ አረፋፍደዋል::በአንድ ጎኑ የምንታገለው የወያኔን መንግሥት ለምጣል እየታገልን ነው እያሉ በሌላ ጎኑ ይህን መንግስት ለመጣል ከሚታገሉ ህብረ ብሄራዊ ሃይሎች ጋር ለመጣመር <<ኢትዯጵያዊ ማንነት የለም>>የሚለው የትግል ግባቸው እየተጋጨባቸው ሲቸገሩና የወያኔን ዕድሜ ሲያራዝሙ ይስተዋላል::ህብረ ብሄራዊ ሃይል በዲሞክራሲያዊ መርሆ ላይ እንዳይተገበር ከጎሣ መንግስታዊ ቅዠታቸው ጋር ይጋጭብናል እያሉ በህዝቡ መስዋዕትነት ላይ ያላግጣሉ::ከ100 ሚሊየን የማያንስ ህዝብ አላት ተብሎ በሚታመነው ሃገራችን ውስጥ ሊከሠት የሚችለውን የተገመተና ያልተገመተ መዘዝ/intended & unintended consequences/ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ሃገሪቱን እነ ሩዋንዳ የተጏዙበትን የዕልቂት መንገድ ሲቀይሱ ይስተዋላሉ::
3. የአንድነት ሃይሎች
ኢትዮጵያን ለማስቀጠልና በህግ የበላይነት የምትደዳደር ሃገር ለማድረግ ያላቸውን ራዕይና ንድፍ ቢያቀርቡም <<የድሮ ስርዐት ናፋቂዎች>> <<የድሮ ትዝታ ምርኮኞች>> በሚሉ ጥራዝ ነጠቅ የጎሣ ፖለቲከኞቹ ያዋክቧቸዋል::እነዚህ ሃይሎች አማራጭ ሃሳብ እንዳያቀርቡም ወይም እንዲደበዝዝ ይረባረቡባቸዋል::እምቅ ሃሣባቸውን የሚያነሳን ጊዜና ብርቱ ጥረት ቀጥለዋል::

4. ሃያላን ሃገሮች

እነዚህ ሃይሎች ከምንግዜውም በላይ የጎሣ ፖለቲካን ጠንቅና መዘዝን የተረዱ ይመስላል::ትምህርት ቀመስ የሆነው አካል በመነመነባቸው እንደ አፍሪቃ ባሉ አህጉራት ውስጥ ውጤቱ የሚጎመዝዝ መሆኑን ከሩዋንዳው የዘር እልቂት ይረዳሉ::በእርግጥ ችግርን መረዳትና ለችግሩ መፍትሄ መፈለግ የተለያዩ ነገሮች ቢሆኑም::አፍሪቃ 55 ነፃ የሆኑና እውቅና ያላገኙ 10 ሃገሮችን ይዛለች::ሁሉም ሃገሮች በተለያዩ ጎሣዎችም የተመሰረቱም ናቸው::ለምሣሌ ያህል ናይጄሪያን ብንወስድ ከ140 በላይ የሚሆኑ ጎሣዎችን አቅፋለች::ይህ ከ80 በላይ የሚሆኑ ጎሣዎችን በያዘችው ኢትዮጵያ የተዘራውና የሶሻሊዝም ቅሪተ አካል ወያኔያዊ የጎሣ ፖለቲካ መርዝ በሁለቱ ሃገሮች ብቻ ከ 220 ያላነሱ መንግስታትን ከእርስ በርስ ግጭትና እልቂት በሁዋላ እንደሚፈጥር መላው አፍሪቃን ችግሩ እንደሚያምስ ይረዳሉ::ይህ መርዛማ ወያኔያዊ ቀመር ስር ከሰደደ መላው አህጉሩ በጎሣ ፖለቲካና ግጭት ተናውጦ በሺዎች ለሚፈጠሩ መንግስታት ምክንያት እንደሚሆን የበለፀጉት ሃገሮች ይረዱታል::በተለይ ከአፍሪቃ ጋር ባላቸው የጥሬ ሃብት ቅርምት ውጥናቸው ጋር ከመጋጨቱም በላይ ለተቀናቃኛቸውም ቻይና በር እንደሚከፍት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ጥንታዊቷን ሃገር ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ ይፈቅዳሉ ብሎ ማሰቡ ይከብዳል::ስለዚህም

ሀ) በጎሣ ላይ የተዋቀሩ ጎሣዊ የፖለቲካ ሃይሎችን ህልም ገቢር እንዳይሆን ካለው ወያኔያዊ አፖርታይድ ስርዐት ጋር በጊዜያዊነት መስራት
ለ) የህዝቡ እምቢተኝነት እያየለ ከመጣና ሁኔታው ከቁጥጥር እንደሚወጣ ከተገነዘቡ የጎሣ ሃይሎቹን ለማዳከም ጥገናዊ ለውጥ በመንግስት ግልበጣ ሽፋን/ግብፅ ውስጥ በሙርሲ ላይ እንዳደረጉት/መሞከር
ሐ) መዘዙን ያመጣውን የጎሣ ፖለቲካ በማዳከም ህብረ ብሄራዊ መንግስት የሚመጣበትን መላ ማፈላለግን ይጨምራል::

ማጠቃለያ:-
ከገባንበት የወያኔ ማጥ ለመውጣትና ካንጃበበብን የእርስ በርስ እልቂት አደጋ ለመዳን የሁሉንም ሃይሎች ማስተዋልና በእኩልነትና በሕግ የበላይነት ላይ የሚመሠረት ህብረ ብሄራዊ መንግስትን ማቋቋሙ ለሁሉም ይበጃል::አለበልዚያ ሁሉም መንገዶች ወደ ገደል እያመሩ ነውና ሃገራችንንና ህዝባችንን እንታደግ::