October 16, 2017 07:24

ሰንደቅ አላማየን እወዳለሁ፣ ልሙጡ/ንፁህ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ከላይ ወደ ታች አግድም የተቀመጡበት ሰንደቅ አላማን ከልቤ እወዳታለሁ። ይቺን ሰንደቅ አላማ የሀገሬ ምልክት አድርጌ በውስጤ ተቀብያለሁ። አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ አርማው የነጻነት ምልክት ነው፣ ለእኔ።
ይህ እኔ የተቀበልሁት ሰንደቅ አላማ ብዙዎች የሚቀበሉትና የሚወዱት እንዳሉ ሁሉ፣ የሚጠሉትና የማይቀበሉትም እንዳሉ ግልፅ ነው። አቶ ገብሩ ገ/ማርያም መድረክ የተባለው የፖለቲካ ድርጅት አመራር አባል ናቸው። አዲስ አድማስ ጋዜጣ መስከረም 27/10 ስለሰንደቅ አላማና ሀገራዊ መግባባት አነጋግሯቸው ነበር። እኒህ የፖለቲካ አመራር ስለ ሰንደቅ አላማ በገለፁበት አስተያየታቸው፣ እኔ የነጻነት ምልክቴ ነው ብየ የተቀበልሁትን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ (መሀል ላይ አርማ ያላረፈበትን) ሰንደቅ አላማን የሚጠቀሙት “ቀድሞ የነበረውን የጨቋኝ ስርዓት በድጋሜ የማምጣት ድብቅ ፍላጎት ያላቸው ናቸው” ብለው ይደመድማሉ።

አቶ ገብሩ ገ/ማርያም ሲቀጥሉ፣ “የድሮውን (አርማ የሌለውን ማለታቸው ነው) እንጠቀም የሚሉት አንዲት ኢትዮጵያ ካልሆነች ሞተን እንገኛለን የሚሉት ናቸው” ይላሉ።
እኒህ ሰው አርማ የሌለበትን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ አላማን መጠቀም ጨቋኝ ስርዓትን መመለስ እንደሆነ ያምናሉ። ይህ ማለት የአማራ ክልል ህዝባዊ የመብት ንቅናቄ በተፋፋመበት ወቅት አደባባይ ይዞት የወጣው ሰንደቅ አላማ አርማ የሌለው ስለሆነ እነዚያ ሰልፈኞች የድሮ ጨቋኝ ስርዓት ያሉትን መልሶ ለማምጣት የተደረገ ህዝባዊ ተቃውሞ ነበር ብለው ያምናሉ ማለት ነው።
አቶ ገብሩ ገ/ማርያም የድሮ ጨቋኝ ስርዓትን ለመመለስ የሚሞክሩ የሚሏቸው አካላት የሚያውለበልቡት ሰንደቅ አላማ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ የአፍሪካ የነፃነት አቀንቃኞች ምልክት መሆኑን ያወቁ አልመሰለኝም። የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሰንደቅ አላማቸው መሰረታዊ ቀለማቱ ከኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ አላማ የተወረሰ እንደሆነም የረሱ ይመስለኛል። በእርግጥም እሳቸው “የጭቆና” ምልክት የሚሏት ሰንደቅ አላማ ኢትዮጵያ ወራሪ ኃይልን መክታ ነጻነቷን ስታስጠብቅ የምታውለበልባት ምልክቷ ናት/ነበረች።
ኢትዮጵያ ወራሪ ጣሊያንን ስትመክት ይቺ ባዲራ ነበረች። የአሸናፊ ምልክት ሆናም ተውለብልባለች። የኢትዮጵያ አርበኞች ዱር ቤቴ ብለው ለነጻነት ከጠላት ጋር ሲዋጉ አርማቸው ይቺው ሰንደቅ ነበረች። የሶማሊያ ዚያድባሬ ወራሪ ጦር ድምበር ገፍቶ ሲመጣና ኢትዮጵያውያን ይህን ወራሪ ጦር አሳፍረው ሲመልሱ ይቺ ባንዲራ ነበረች፣ በነጻነት እንድትውለበለብም ተደርጓል።
ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ የሀገራቸን የውስጥ የፖለቲካ ችግር ለወለደውና ስልጣን ላይ በነበሩና ባሉ ከአብራካችን በወጡ አምባገነኖች ለተፈፀመ በደል ሰንደቅ አላማን የተለየ አካል የጭቆና ምልክት አድርጎ መውሰድ ትክክል አይደለም። ምናልባት አቶ ገብሩ እኔ የወደድኋትን ሰንደቅ አላማ መውደድ ላይጠበቅባቸው ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን እውነታውን ክዶ፣ አንተ የምትይዘው ሰንደቅ አላማ “የጭቆና” ነው፣ የእኔ ግን የነፃነት ነው የሚል ድምዳሜ መስጠት እንደሳቸው ካለ ለ”ነጻነት” ከሚታገል የፖለቲካ አመራር የሚጠበቅ አይደለም።
በመሰረቱ፣ እንዳለመታደል ሆኖ ሁላችንንም የሚያስማማ ሰንደቅ አላማ የለንም። ይህ በየለቱ የሚታይ ሀቅ ነው። ቀደም ብየ እንደገለፅሁት በአማራ ክልል በሚደረጉ ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ወቅት (አንዳንድ በዓላት ሲከበሩም ጭምር) ህዝቡ አደባባይ ይዞ የሚወጣው ምልክቱ/ሰንደቁ ንፁህ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ነው። በሌላ በኩል በኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት ደግሞ የምናየው ከዚህ የተለየ ነው። በሁሉም አካባቢዎች የሚታዩት ተቃውሞዎች መሰረታዊ የመብት ጥያቄን ያዘሉ ናቸው። ሆኖም አደባባይ ይዘውት የሚወጡት ሰንደቅ አላማ የተለያየ ነው። ይህም በሀገር ደረጃ ህዝብ የተስማማበት የጋራ ሰንደቅ አላማ የለም የሚለውን በተግባር ያሳየናል።
የሚገርመው በእነዚህ ህዝባዊ ተቃውሞዎች የምንመለከታቸው ሰንደቅ አላማዎች አንዳቸውም አሁን ላይ በህገ መንግስት የሰፈረውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሆኖ መሀሉ ላይ አርማ ያረፈበትን (በተለምዶ ባለኮከቡ) ሰንደቅ አላማን ይዞ የሚታይ አለመስተዋሉ ነው። ይህ ምናልባት አሁን ስራ ላይ ያለው ሰንደቅ አላማ በህዝቡ ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት እንደሌለው ያሳየን ነው ማለት እችላለሁ። በእርግጥ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆን አሁን ያለውን የፌደራሉን ሰንደቅ አላማ መቀበላቸውን የሚያመለክቱ ተግባራትን አናይም። ለምሳሌ፣ ፓርቲዎች ህዝባዊ ሰልፍ ሲያደርጉ ሰንደቅ አላማውን ይዘው አይታዩም። ይልቁንም የፓርቲያቸውን አርማ ብቻ ነው ሲያውለበልቡ የሚታዩት።
በሰንደቅ አላማ ላይ ያለን የተለያየ ፍላጎት የተለያየ አመንክዮ ሊኖረው ቢችልም፣ በጉዳዩ ላይ በቂ ውይይትና ክርክር አለማድረጋችን ግን በዋናነት የሚጠቀስ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ አሁን በስራ ላይ ያለውን የፌደራሉ ህገ መንግስት ከማርቀቁ እስከ ማፅደቁ ድረስ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ህገ መንግስቱ ሲፀድቅ በሰንደቅ አላማው ጉዳይ በቂ ውይይት አለመደረጉን ይመሰክራሉ።
“ትልቁ ጥያቄ የነበረው ሀገሪቱ ፌደራሊዝም ያስፈልጋታል አያስፈልጋትም የሚለው እንጂ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ድምፅ ከህዝብ አልተሰበሰበበትም። ለህዝብ ውይይትም አልቀረበም ነበር። እኔ እስከማስታውሰው ድረስ የህገ መንግስት ረቂቅ ሂደት ሲከናወን የሰንደቅ አላማ ጉዳይ አልተነሳም ነበር” ሲሉ ዶ/ር ነጋሶ አሁን ስራ ላይ ያለው ሰንደቅ አላማ እንዴት ህገ መንግስቱ ላይ እንደሰፈረ ይገልጻሉ።

እኔና አቶ ገብሩ ገ/ማርያም በሰንደቅ አላማ ጉዳይ ያለንን ልዩነት አጥቦ በጋራ ልንግባባበት የምንችለውን ሰንደቅ አላማ ለማፅደቅ የሚያስችል የፖለቲካ ምህዳርና ነፃነት አልነበረም። ዛሬም አለ ብየ አላምንም። ይህ በሆነበት ሁኔታ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት አመራርና ለተሻለ መብት መከበር እታገላለሁ ከሚል እንደ አቶ ገብሩ ገ/ማርያም አይነት ሰዎች “የአንተ ምልክት የጭቆና ስርዓትን” ነው የሚወክለው፣ አንተ ይህን ሰንደቅ አላማ የምትወደው “ጨቋኝ ስርዓትን” ለመመለስ “ድብቅ አላማ” ስላለህ ነው የሚል ፍረጃ መሰንዘር አላዋቂነት መሆን አለበት።

በበኩሌ ጭቆናን እፀየፋለሁ። አብሮነትን እፈልጋለሁ። ነጻነትን እሻለሁ። አቶ ገብሩ እንደሚሉት ሳይሆን የኔ የልብ እውነት ይህ ነው። እናም የእኔ የአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ አላማ መውደድ ነጻነትን የመምረጥ ጉዳይ ነው።