welkait.com 

 

(ልጅ ዓምደጽዮን ምኒልክ)

ትናንት ምሽት በዛሚ ኤፍ.ኤም 90.7 ሬዲዮ ጣቢያ ላይ የሚተላለፈው ‹‹የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ›› ለ‹‹ውይይት›› ከመረጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ግዙፉን ጣና ሀይቅን የወረረው የእምቦጭ አረም ጉዳይ አንዱ ነበር።

በእምቦጭ አረም የተወረረው የጣና ሐይቅ

በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ተናጋሪ የነበረው ደግሞ ፍፁም ብርሃነ (ፌስቡክ ላይ በተደጋጋሚ ስሙ ሲነሳ የማየው ዳንኤል ብርሃነ የተባለው ግለሰብ ወንድም እና የህዋሃት አባል ነው) ነበር። ግለሰቡ ጉዳዩን አስመልከቶ ያቀረበው/የሰጠው ሃሳብ ስህተቶች የበዙበት ነበር።
ይህ ደግሞ ያገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የቁልቁለት/የኋልዮሽ ጉዟቸውን እያፋጠኑት እንደሚገኙ (አሳዛኝ) ማሳያ ነው። ከስህተቶቹ መካከል የተወሰኑትን ልጥቀስ።

ሀ). አቶ ፍፁም ብርሃነ ንግግሩን ሲጀምር ‹‹ … አቶ ሰለሞን ክብረት የተባሉ ሰው በአረሙ ላይ አተኩረው ለPh.D ጥናት የፃፉትን ጽሑፍ አንብቤዋለሁ›› አለ። ድርብ ውሸት!

ውሸት#1. ሰለሞን ክብረት ተብለው የተጠቀሱት ግለሰብ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና ‹‹Global Coalition for Lake Tana Restoration›› የተባለው ማኅበር መስራችና አባል የሆኑ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ሰው ናቸው። ስለሆነም ‹‹አቶ›› ተብለው ሊጠሩ አይገባም! … ዶክተር ሰለሞን ክብረት

ውሸት#2. ዶክተር ሰለሞን በነሐሴ 2009 ዓ.ም ‹‹Ethiopia’s Lake Tana is Losing the Fight to Water Hyacinth›› በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ ጽፈው ነበር። አቶ ፍፁም ያወሩትም ከዚህ ጽሑፍ የወሰዱትን ሃሳብ እንደሆነ ተናግረዋል። ነገር ግን ይህ ጽሑፍ ዶክተር ሰለሞን ለPh.D ጥናት የፃፉት ጽሑፍ ሳይሆን፣ የሐይቁ ህልውና አደጋ ላይ በመውደቁ ምክንያት ሙያዊ ማብራሪያቸውን የሰጡበት አጠር ያለ ማብራሪያ/ትንታኔ ነው።

ለ). አቶ ፍፁም ‹‹በጽሑፉ ላይ ከተጠቀሱት የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል ‹ከሁሉም የተሻለው ዘዴ ኬሚካል መጠቀም ነው› ይላል›› ብሏል። ውሸት!

በዶክተር ሰለሞን ጽሑፍ ውስጥ በመፍትሄ አማራጭነት ከቀረቡት ዘዴዎች መካከል ከሁሉም የተሻለው ኬሚካል (Herbicides) መጠቀም ሳይሆን ባዮሎጂካዊ ዘዴ (Biological Control) ነው።

ሐ). ‹‹ጽሑፉ ኬሚካል ተጠቅሞ አረሙን ለመቆጣጠር በዓመት 1.5 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሎ ይጠቅሳል›› ብሏል አቶ ፍፁም። ውሸት!
የዶክተር ሰለሞን ጽሑፍ ‹‹ሱዳን አረሙን ለመቆጣጠር በዓመት አንድ ሚሊዮን ፓውንድ ውጭ አድርጋለች›› ብሎ ይገልፃል እንጂ፣ ‹‹ኢትዮጵያ አረሙን ለመቆጣጠር በዓመት 1.5 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል›› አይልም።

መ.) ‹‹ጽሑፉ ‹በሐይቁ ላይ የተከሰተውን አረም በማሽን አጭዶ ለመጨረስ አስራ ስድስት ዓመታት ያስፈልጋሉ› ይላል›› ተብሎ በአቶ ፍፁም የተገለፀው ሃሳብም ስህተት/ውሸት ነው።

ዶክተር ሰለሞን በጽሑፋቸው ውስጥ ያብራሩት፣ በስፋቱ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም በሆነውና ታንዛኒያን፣ ኡጋንዳንና ኬንያን በሚያካልለው ቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ የተከሰተው አረም፣ በኬንያ ብቻ 60ሺ ሄክታር የሚሆነውን የሐይቁን ክፍል መሸፈኑን፣ ማሽኑ በቀን 10 ሄክታር ብቻ ማጨድ እንደሚችልና፣ የ60ሺ ሄክታሩን ብቻ ለማጨድ እንኳ ከ16 ዓመታት በላይ ሊጠይቅ እንደሚችል እንጂ ‹‹ጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን አረም አጭዶ ለመጨረስ አስራ ስድስት ዓመታት ያስፈልጋሉ›› ብለው አልፃፉም።

ሠ). አቶ ፍፁም ‹‹ጽሑፉ ባዮሎጂካዊ ዘዴ ተብለው የቀረቡትን መፍትሄዎች ጉዳት አልባ (Harmless) አድርጎ ነው ያቀረባቸው›› ብሎ ተናግሯል።

ዶክተር ሰለሞን አረሙን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስነ-ሕይወታዊ ዘዴዎች (Biological Control Measures) ‹‹ፍፁም ከጉዳት የፀዱ ናቸው›› አላሉም።
በእርግጥ ይህኛው ዘዴ ይህ ነው የሚባል የከፋ ጉዳት እንደሌለው በጽሑፋቸው ቢገልፁም፣ የቁጥጥር ዘዴው ጊዜ እንደሚፈልግና የሐይቁ ህልውና ደግሞ ፋታ የማይሰጥ በመሆኑ ስራውን/ሀይቁን ለመታደግ የሚደረገውን ትግል አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል።

አቶ ፍፁም ‹‹አረሙን ለማስወገድ የሁሉም ሰው ትብብር ያስፈልጋል … ይፈጃል የተባለው ገንዘብ (ገንዘቡ ግን ጽሑፉ ውስጥ የተጠቀሰው አይደለም) ከሐይቁ ጥቅም አንፃር ብዙ/ውድ የሚባል አይደለም›› ብሎ በተናገራቸው ሃሳቦች እኔም እስማማለሁ።
ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች ወደ ጣና ሐይቅ ተጉዘው ስለፈፀሙት አኩሪ ተግባር፣ ‹‹የወጣቶቹ ስራ ጥሩ ነው፤ መሄዳቸውን እደግፋለሁ፤ ነገር ግን ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም›› ብሏል። በዚህ ሃሳቡም እስማማለሁ!

በአጠቃላይ አቶ ፍፁም ብርሃነ ‹‹ጽሑፉን አንብቤያለሁ›› ብሎ ያቀረበው ገለፃ ከሞላ ጎደል (ሁሉም) ውሸት/ስህተት ነበር። ይህ ደግሞ ለቁጥር በሚታክቱ ችግሮች ተተብትቦ ለተያዘው ያገራችን መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ችግር አንድ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።

የዶክተር ሰለሞን ጽሑፍ ጣና ሐይቅ የተጋረጠበትን የሕልውና አደጋ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ትክክለኛ ሙያዊ/ምሁራዊ ማብራሪያ ነው። ጽሑፉን ለማንበብ የሚያስችለውን ማስፈንጠሪያ በአስተያየት መስጫ ቦታው (Comment Box) ላይ አስቀምጨዋለሁ።

https://theconversation.com/ethiopias-lake-tana-is-losing-the-fight-to-water-hyacinth-82947

ጣና ውሃ ብቻ አይደለም፤ጣና ብዙ ምስጢር አለው፤ጣና የዓለም ታሪክ ማኅደር ነው!

#ጣናንእንታደገው#XaanaaHaabaraarru#SaveTana

©ልጅ ዓምደጽዮን ምኒልክ