“ባልበላው ጭሬ አፈሰዋለሁ!” (To read in pdf, click here)

ቅጽ ፪ ቁጥር ፫ ማክሰኞ መስከረም ፲፩ ቀን ፪ሺ፲ዓ.ም.

“ባልበላው፣ ጭሬ አፈሰዋለሁ!” ይህ አባባል እኔ ካልተጠቀምኩበት፣ ሌሎች እንዳይጠቀሙበት አደረገዋለሁ፤ ለእኔ ካልሆነ፣ ለማንም እንዲሆን አልሻም፤ የእኔ መገልገያ ካልሆነ፣ ሌሎች ሊገለገሉበት እንዳይችሉ አበላሸዋለሁ፣አፈርሰዋለሁ፣ብለው ለሚያስቡ የጥፋት ሰዎች ዕይታ፣ በዶሮዋ ተመስሎ የተነገረ የብልሆች ዕውነት የማስጨበጫ ዘዴ ነው። አዎ ! ይህን አባባል በሌላ አባባልም አበው ይገልጹታል። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ሲሉ። እነዚህ አባባሎች እኔ ወይም እኛ ካልተጠቀምንበት፣ ለእኛ ካልሆነ ሌሎች ሊጠቀሙበት አይገባም ብለው የሚያስቡ ሰዎች የሕይዎት መርሕር እንደሆነ አባባሎቹ ያስረዳሉ። የትግሬ-ወያኔ አስተሳሰብና አጠቃላይ ዓላማ በነዚህ አባባሎች የተቃኘ ነው። የወያኔው ዘር የማይመራት ኢትዮጵያ መኖር የለባትም፣ እኛ ያልነው ካልሆነ፣ ኢትዮጵያ መበታተን አለባት ብለው በማመን፣ ባለፉት ፳፯ ዓመታት ግፈኛ አገዛዛቸው፣ ከቻሉ እነርሱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ማዕከል ላይ ለዘመናት መኖር የሚችሉበትን ፣ ካልቻሉ ኢትዮጵያን በነገድ ከፋፍለው ለመበታተን በሚቻልበት ሁኔታ ሢሠሩ መቆየታቸው ግልጽ ነው።

የአገሪቱ አስተዳደራዊ መዋቅር’ በመሬት ወረራና የዐማራን ነገድ ከቀየዉ በማፈናቀልና ዘሩን በመጨረስ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም መሆን፣ ሕገመንግሥት ተብየው አንቀጽ ፴፱ እና ፶፪ ማናቸውም የነገድ መንግሥት ነኝ ባይ በኢትዮጵያ አንድነት ማዕቀፍ ውስጥ መኖር አልችልም ብሎ ባሰበ ጊዜ መገንጠል እንዲችል ሠፊ በር የከፈተ መሆን፣ ወያኔ በሚሻው መልኩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አናት ላይ መቀመጥ የማይችልበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ ለምትገነጠለው ትግራይ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ ወታደራዊ፣ ባሕላዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መሠረት ለመጣል የአገሪቱን ሀብት ሥልጣንን መከታ በማድረግ እና በዘረፋ ወደ ትግራይ እንዲጓዝ ተደርጓል። ትግራይ ከማዕከላዊ መንግሥት ተብየው ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ፣ ሕገ-መንግሥታችን የሚሉትን በመጣስ ከውጭ መንግሥታት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስታደርግና የዲፕሎማሲ ልምምድ እንድታደርግ ሠፊ በር ተከፍቶ ይህኑ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።

በሌሎች ክልሎች ውስጥ የተቋቋሙትን ፋብሪካዎች በማቀጨጭ፣ ትግራይ የተገነቡትን ለማስፋፋት እና የምትገነጠለው ትግራይ በኢንዱስትሪ የበለጸገች ለማድረግ፣ ወያኔ በሽግግር ዘመን ተብየው፣”የልማት ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ ክልሎች” በሚል ሽፋን ለ፲ዓመታት ያህል ያገሪቱ ገንዘብ ለትግራይ ልማት እንዲውል ተደርጓል። በዚህም የባሕርዳር፣ የድሬደዋ፣ የአቃቂ፣ የኮምቦልቻ፤ የሞጆ ጨርቃጨቅ ፋብሪካዎችን የሚያከስር እና የነርሱን በጄት የቀማ “አልሜዳድ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ” የተሰኘ ግዙፍ ፋብሪካ ዐድዋ ላይ ገንብተዋል። የአዲስ አበባውን ፋርማኮ የመድኃኒት መቀመሚያ ፋብሪካ የሚያከስር “አዲግራት መድኃኒት ፋብሪካ” አዲግራት ውስጥ ገንብተዋል። የሙገርን፣ የድሬዳዋን፣ እና የአዲስ አበባውን የስሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያከስር “መሰቦ ስሜንቶ ፋብሪካ»፣ የተሰኘ መቀሌ ላይ ገንብተዋል። የአምቼን መኪና መገጣጠሚያ እና የብረታብረት ኢንዱስትሪ ፋብሪካን በሚያከስር መልክ፣ “መሥፍን ኢንጂነሪንግ” የተሰኘ የብረታብረት ፋብሪካ መቀሌ ላይ ገንብተዋል።

በማኅበራዊ ግንባታ ዘርፍ፣ በስምንቱም የቀድሞቹ የትግራይ ክፍለሀገር አውራጃዎች ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ገንብተዋል። በሁሉም ቀበሌዎች እና ወረዳዎች የአንደኛ፣ መለስተኛና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ሠርተዋል። ሦስት ታላላቅ ሪፈራል ሆስፒታሎች ሠርተዋል። በሁሉም አውራጃ ከተሞች ታላላቅ ሆስፒታሎች ገንብተዋል።

በመገናኛ ዘርፍ፣ መቀሌና አክሱም ላይ ዓለምቀፍ ደረጃን የጠበቀ አውሮፕላን ማረፊያ ሠርተዋል። ሁሉንም ወረዳዎችና ቀበሌዎች ከዋና ዋና ከተሞች የሚያገናኙ የክረምት በጋ አውራ ጎዳናዎች ሠርተዋል። መቀሌን ከጂቡቲና ከሱዳን የሚያገናኝ የባቡር ኃዲድ በመገንባት ላይ ይገኛል። ለነዚህ ሁሉ የኃይል ምንጭ እጥረት እንዳይኖር ተከዜ ላይ ከፍተኛ የሆነ የኃይድሮ-ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ተሠርቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው። በትግራይ የተገነቡት ፋብሪካዎችና የተከፈቱት ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች መበራከት የተነሳ፣ ከሌሎች ከተሞች እየተነቀሉ በየነጥብ ጣቢያዎቹ የተተከሉት(ለምሳሌ የጎንደር ከተማ የነበረው ተነቅሎ ብዘት ተተክሏል) ጄኔሬተሮችና የተከዜ ኃይድሮኤሌክትሪክ ማመንጫ አልበቃ በማለቱ፣ ከባሕርዳር የጣናን ውኃ በሚያደርቅ መልኩ በቦይ ተስቦ ኃይል እንዲያመነጭ በማድረግ፣ በደብረታቦር፣ ጋይንት፣ የጁና መሰል አውራጃ ከተሞች ላይ በተዘረጋ ኤሌክትሪክ ሽቦና በተተከሉ የኃይል ማሸጋገሪያ ምሰሶዎች ትግራይ እንዲገባ ተደርጓል።
ይህ ሁሉም ተደርጎ፣ የጥንቱ ትግራይ ክፍለሀገር የቆዳ ስፋቱ ጠባብ፣ የመሬቱ ለምነት የተሟጠጠ፣ የውኃ ሀብት የሌለው፤ መሬቱ ዛፍ አልባ የሆነ ደረቅ በመሆኑ፣ የትግራይ መገንጠልና እንደመንግሥት የመቀጠል ሁኔታ የማያስቀጥል መሆኑን የተገነዘቡት የትግሬ-ወያኔ መሪዎች፣ ከወሎ የራያና ቆቦን አውራጃ፣ ከሰሜን ጎንደር አምስት ወረዳዎች “ሠቲት፣ ጠገዴ፣ ወልቃይት፣ ጠለምትና ከፊል ታች አርማጭሆ ወረዳዎችን በመሣሪያ ኃይል የትግራይ አካል በማድረግ የትግሬ ገበሬ እያሰፈሩበት ይገኛል። በነዚህ ወረዳዎች ይኖሩ የነበሩ ዐማሮችን በልዩ ልዩ መንገድ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል በመፈጸም በቁጥር አናሳ አድርገዋቸዋል።

ወያኔ ይኸን ሁሉ አድርጎም ለ”ታላቋ ትግራ ረፐብሊክ” ቀጣይነት አስተማማኝ ሆኖ አላገኘውም። የታላቋ ትግራይ ረፐብሊክ ምሥረታና ግንባታ ሊሳከና ሊሰምር የሚችለው ትግራይ ከሱዳን ጋር ሠፊ የድንበር ወሰን ሲኖራት፣ የትግራይ ግዛት ከደደቢት ተነስቶ የምዕራብ ኢትዮጵያን ደንበር ከሰሜን ወደ ደቡብ አቅጣጫ በመሳብ ከጋንቤላ ጋር ማዋሰን እንዳለበት አመነ። ለዚህ እምነቱ ተግባራዊነትም ሁለት ሥራዎችን በተከታታይ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕምብርት ሳይወገድ መሥራት እንዳለበት ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። የመጀመሪያው በጥልቀት ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ከ፶ እስከ ፷ ኪሎ ሜትር፣ በቁመት ከሰሜን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ፩ሺ ፮መቶ ኪሎሜትር ርዝመት ያለው መሬት ለሱዳን በገጸ-በረከትነት በመስጠት የሱዳንን ወዳጅነት ማጥበቅ እንዳለበት አምኖ፣ ይህን ተግባራዊ አደረገ። የሚቀጥለው እርምጃ፣ የታላቋን ትግራይ ምሥረታ ከማንም ቀድሞ የሚቃወመው ኃይል ሊመጣ የሚችለው ከዐማራው እንደሆነ በመገንዘብ፣ ዐማራው ኃይል ሆኖ እንዳይወጣ ባለፉት ፳፯ ዓመታት ከሠራው የመከፋፈልና የማዳከም ሥራዎች በተጨማሪ፣ በጎጃም ክፍለ-ሀገር ውስጥ የሚኖሩትን አገዎች፣ በወሎ የሚኖሩትን ኦሮሞዎች እና በጎንደር የሚኖሩትን ቅማንቶች አደራጅቶ የየራሳቸው ክልል በመስጠት ዐማራውን በጠላትነት እንዲያዩት፣ የርሱም ቋሚ ጠላቶች ሆነው እንዲቆሙ የማደራጀትና የማሰልጠን ሥራን ሠራ። ይህም ዐማራው ወደ ውጭ እንዳያይ፣ በራሱ የውስጥ የኅልውና ጉዳይ ተወጥሮ በወያኔ የተወሰደበትን መሬት፣ ሀብት፣ የተጨፈጨፉ ወገኖቹን ማንነት እንዳያንሰላስልና ኃይሉን አፈርጥሞ በወያኔ ላይ እንዳይነሳ ከፍተኛ መሰናክል የመገንባቱን ተግባር ሌት ተቀን ሠራበት። የቅማንት ከጎንደር ማንነት መፋታት፣ እንዲሁም የጎጃም አገው ከጎጃም ማንነት መውጣት፣ ወያኔ የትግራይን ካርታ ጋምቤላ ድረስ ለማካለል ላቀደው እቅድ መደላድል ወይም መሰላል እንዲሆኑት ያዘጋጃቸውና በኋላም የታላቋ ትግራይ ረፐብሊክ አካል በማድረግ፣ ትግራይ ውስጥ እንዳሉት ኤሮፖች፣ ኩናማዎች፣ ዐማሮች፣ አገዎችና ኦሮሞዎች እጣ የሚገጥማቸው መሆኑን የቅማንትና የጎጃም አገው አቀንቃኞች የተረዱ አይመስሉም። ቢረዱም ተፈጥሮአቸው ባንዳነት ነውና አሻፈረን ሊል የሚያሰኝ ወኔ የሌላቸው እንደሆነ ሁኔታዎች ያሳያሉ።

ወያኔ ባለፉት ፳፯ የአገዛዝ ዘመኑ ባንድ በኩል በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ የወሳኝነት ቦታ ይዞ ለመቀጠል፣ በሌላ በኩል ይህ ዓላማው ባይሳካ ትግራይን ለመገንጠል የሚያስችለውን ሥራ ጎን ለጎን በማስኬድ፣ ዛሬ ከደረሰበት የውስጥና የውጭ ቀውስ ደርሷል። የውስጥ ቀውስ ለራሴ የሥልጣን መቆያ ይሆነኛል ብሎ ያደራጀው በመሬት ወረራና የዐማራን ነገድ ከቀየዉ በማፈናቀልና ዘሩን በመጨረስ ላይ የተመሰረተ የመንግሥት አደረጃጀት፣ የሕዝቡን ተዘዋውሮ የመሥራት፣ በፈለገው የሥራ መሥክ የመሠማራት፣ ባሻው መልክ የመደራጀትና ሀሳቡን በነፃ የመግለጽ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ መብትና ጥቅሞቹን የገፈፈ መሆን፣ በዘጠኙም ክልል ተብየዎች የቦታ ይገባኛል፣ ገፋኸኝ፣ ገፋኸኝ በሚሉ የመሬት ጥያቄዎች ዙሪያ በነገዶችና በክክል መንግሥታት ተብየዎች መካከል ተካታታይ ጦርነቶች እንዲካሄዱ አደረገ፤ እየተካሄዱም ነው። ለአብነት በሶማሊያና በኦሮሚያ፣ በትግሬና በዐማራ፣ በዐማራና በአፋር፣ በአፋርና በኦሮሞ፣ በሐረርና በኦሮሞ፣ በደቡብና በኦሮሞ ወዘተ መካከል ደም ያፋሰሱ ጦርነቶች ተደርገዋል። እነዚህ ጦርነቶችም የትግሬ ወያኔ ፈረሶች የሆኑትን የኦሕዴድ፣ የብአዴን፣የደኢሕዴግን ወዘተ ከፍተኛና ተራ አመራር አባሎች በትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ላይ ጥያቄ ከማንሳት ባለፈ “የለም? የወያኔ የበላይነት በዛ!” በማለት አመራሩን አንቀበልም ከሚል ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። በአዲስ አበባ የመስፋፋት ጥያቄ ኦሕዴድ የወሰደው አቋም፣ በወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ብአዴን የወሰደው አቋም፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን የውስጥ ቀውስ መገለጫዎች ናቸው። ከሁሉም በላይ ድርጅቱ ራሱ ደጋግሞ በሙስና ተዘፍቀናል፣ ለዚህም “ጥልቅ” ተሀድሶ እናደርጋለን ብሎ በአደባባይ የገባውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ ቀርቶ ሊያስበው አለመቻሉ፣ የሙስናው መሪ ተዋንያን የትግሬ-ወያኔ ቱባ ባለሥልጣኖች መሆን ፣ ማን ማንን ተጠየቅ ሊለው እንደሚችል ከነርሱ በላይ ሥልጣን ያለው አካል አለመኖር፣ የኢሕአዴግን የውስጥ ቀውስ ያባባሰ እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ በወያኔ መካከል ያለው የሥልጣን አያያዝና የሙስና ደረጃ በአመራሩና በተራው አባል፣ አልፎ አልፎም በትግራይ ሕዝብ መካከል የነበሩ አውራጃዊ ልዩነቶች እያሠፋው እንደመጣ ይስተዋላል። ወያኔ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የትናንቱ አይደለም። እንኳን የኢትዮጵያን ሕዝብ የትግራይንም ሕዝብ አስተባብሮ ለመምራት ከሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም። ለዚህም ነው ከፍተኛ ባለሥልጣኖቹ ዐባይ ፀሐዬና አርከበ ዕቁባይ ጓዛቸውን ጠቅለው ሰሞኑን ወደ ውጭ ማጭ ማለታቸው እየተሰማ ያለው።

ከውጭ ያለው ተጽዕኖም እንዲህ ቀላል አይደለም። ትናንት በገፍ ይረዷቸው የነበሩ መንግሥታት ዛሬ ጥያቄ ማንሳት ጀምረዋል። ወያኔ በያዘው የጉዞ መሥመር ሊቀጥል የማይችል መሆኑን ተረድተው። አማራጭ ብሔራዊ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ ቡድን እያሻተቱ ነው። ይህ ሁሉ ተደማማሮ፣ በመሐል፣ በምሥራቅ፣ በደቡብ፣ በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ለተከታታይ ሁለትና ሦስት ዓመታት የዘለቀው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ንቅናቄ፣ በሶማሊያና በኦሮሚያ ክልሎች ተብየዎች የተቀሰቀሰው የጎሳ ግጭት፣ በጎንደ,ር፣ በጎጃም፣ በወሎና በሸዋ የተቀጣጠለው በጎበዝ አለቆች የሚመራ ሕዝባዊ እንቢተኝነት፣ የትግሬ ወያኔን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዕምብርት ላይ የማይቆይ መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። ይህም በመሆኑ፣ ከፍተኛ የወያኔ ባለሥልጣን የሆኑትና ዕድሜአቸው የገፉት ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ዓይናቸውን በማማተር፣ ንብረታቸውን፣ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን በማሸሽ ላይ ይገኛሉ። ሌሎቹ ከመሀል አገር ያለ ንብረታቸውን ወደ ትግራይ እያጓጓዙ ይገኛሉ። የመከላከያውና የደህንነቱ ክፍል፣ ለምትገነጠለው ትግራይ ሊያገለግል የሚችልን ማናቸውንም ንብረት ወደ ትግራይ በማጓጓዝ ሥራ ላይ ተጠምደዋል። እግረ መንገዳቸውንም የጎሳ ግጭቶችን ሆን ብለው በመለኮስ ኢትዮጵያውያን ርስ በርሳችን በማናከስ የነርሱን ወደ ፈለጉት ቦታ ያላንዳች ችግር እንዲደርሱ የማበጣበጥ ሥራዎች እየሠሩ ነው። የቅማንት ከጎንደር ዐማራ የማጋጨት፣ የሶማሊያና የኦሮሞ፣ እንዲሁም የሐረሪና የኦሮሞ ግጭቶችና ጦርነቶች የዚህ አባባል ማሳያዎች ናቸው።

እነዚህ ድርጊቶችና ሁነቶች ተገጣጥመው ሲነበቡ የሚሰጥን ቁልጭ ያለ ሥዕል፣ ትግራይ ከኢትዮጵያ የመገንጠሏን የመጀመሪያው መጨረሻ ወቅት ላይ ያለን መሆኑን ነው። የትግሬ ወያኔ ጠቅሎ ወደ ጉሬው ሲገባ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የኃይል አቅርቦት ተቋሞች፣ የውኃ ጋኖችና መሥመሮች፣ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ የትምህርት ተቋሞች፣ የአስተዳደርና የማኅበራዊ ልማት ተቋሞችን መውሰድ የሚችለውን ወስዶ ቀሪውን አውድሞ የሚሄድ መሆኑ ከወያኔ ተፈጥሮ ልንረደው የምንችል ሐቅ ነው። ከዚህም አልፎ፤ ሕዝቡን ግራና ቀኝ አቁሞ እርስ በርሱ በማናከስ ቀድሞ የነበረውን የአብሮነት ስሜት ካለፉት የአገዛዝ ዘመኖቹ በከፋ ሁኔታ የሚጎዳው እንደሚሆን የሚታዩት አዝማሚያዎች ጉልህ ማሳያዎች ናቸው።

ይህ አጠቃላይ ሁኔታ በሚገባ ሲስተዋል አገራችን ከፍተኛ የሆነ የመበታተን አደጋ ውስጥ ያለች እንደሆነ ያሳያል። የወያኔም ፍላጎት ይኸው መሆኑ በግልጽ ይታወቃል። ይህ መጥፎ አጋጣሚ እንዳይሆን ቅንና አብሮነትን ከሚመኙ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ተግተው የማድረግ ሥራ ይጠበቅባቸዋል። የጥረታቸው ማጠንጠኛ ዲሞክራሲ፣ዕኩልነት፣ ፍትሕ፣ ነፃነት ወዘተ በሚሉት ዙሪያ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ከብተና እናድን! ኢትዮጵያን እንታደግ! የሚል መሆን አለበት። ለዚህ ጥሪ የነገድ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት እና የርዕዮተዓለም ልዩነት ቦታ ሊኖራቸው አይገባም። “እየየም ሲዳላ ነውና!” እነዚህ ልዩነቶች አገር ሲኖረን፣ ኢትዮጵያ ከብተና ስትድን፣ እንደ አገር ስትቀጥል፣ ሊነሱና በአገራችን ምድር ሁላችንም ተገቢ ቦታችን ስንይዝ የምናነሳቸው መሆኑን በማወቅ፣ አገር ለማዳኑ ተግባር ሁላችንም ያላንዳች ጠሪ ልንሰባሰብ ይገባል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓለዊነትና ብሔራዊ ጥቅም መከበር የፀና አቋም ያላቸው የተደራጁና ያልተደራጁ ኢትዮጵያውያን ጊዜ ሳይሰጡ የአገር አድን ግንባር ለመመሥረት ፈጥነው እንዲንቀሳቀሱ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ጥሪውን ያቀርባል። ወያኔ “ባልበላው ጭሬ አፈሰዋለሁ ” አለች እንደተባለችው ዶሮ፣ ኢትዮጵያን አፈራርሷት ከጉሬው ሳይገባ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ኃይል ግንባር በመፍጠር ኢትዮጵያን ከብተና ሊታደግ ይገባል።

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ኅብረት ተጠብቃ ለትውልድ ተሸጋገራለች!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!