(Miky Amhara)

ህወሃት አበክሮ ከሚሰራዉ ነገር አንዱ የአማራ ገበሬ ሀብት እና ንብረት አፍርቶ ከድህነት ተላቆ እንዳይኖር ማድረግ ነዉ። በትግራይ ክልል ዉስጥ በባለፉት አስር አመታት ከ68 በላይ (ከ48 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው) መካከለኛና ከፍተኛ የመስኖ ግድቦችና የወንዝ ጠለፋ ተካሂዶ በሚሊየን የሚቆጠር የትግራይ ገበሬ እራሱን በምግብ ችሎ በዚህ ሁለት አመት ከተከሰተዉ ከፍተኛ ድርቅ እንኳን ተላቋል። ይህ ይበል የሚያሰኝ ነዉ። ማንም ቢሆን በረሃብ መሞት የለበትምና። ችግሩ ግን ይህ የተቀናጀ የግብርና ፓሊሲ የሚሰራዉ ትግራይ ላይ ብቻ መሆኑ ነዉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዞችና ለሰፋፊ የግብርና ፕሮጀክቶች አመች የሆነ መሬት ኢትዮጵያ ዉስጥ አንደ አማራ ክልል ያለው የለም። ግን ምን ዋጋ አለዉ በጠላትነት ተፈርጀን ምንም ነገር እንዳይሰራ ሁኗል፡፡

ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ፕሮጀክቶች ማየት እንችላለን።ተጀምረዉ የቀሩና ከተጀመሩ ደግሞ 10 አመት ያለፋቸዉ ናቸዉ አብዛኞቹ፡፡

1. የርብ ፕሮጀክት
***************
በወረታ አካባቢ በሚገኝ ወንዝ ላይ የተጀመረዉ ግድብ እድሜዉ ከወያኔ መንግስት ጋር አብሮ እየነጎደ ነዉ። የግድቡ ጥራት ደግሞ አጠያያቂና ለጣና ሃይቅ እራሱ አስጊ የሚሆን ግድብ ነዉ። በዚህ ግድብ ላይ የግድቡ አካል የሆነ ግንባታ ተደርምሶ ከ10 በላይ ሰዎች እንደጨረሰ ባለፈዉ አመት አይተናል።

2. የመገጭ ግድብ
************
ይህ የመስኖ ግድብ በጎንደር አካባቢ የሚገኝ ሲሆን መጀመሪያ የተመደበለትን በጀት አንድ የህዎሃት ድርጅት ይዞት ስለጠፋ እንደገና በባለፈዉ አመት ሌላ በጀት ተመድቦለት ለመስራት እየሞከሩ ነዉ። እድሜዉ ራሱ የማቱሳላን ሊያክል ምንም አልቀረዉም። ይህ የመስኖ ግድብ ባግባቡ ካልተያዘ ሌላኛዉ የጣና ሃይቅ ስጋት ነዉ። ምክንያቱም ትልቅ የጣና ሃይቅ ገባር ወንዝ ስለሆነ።

3. የአጓት ዉሃ ግድብ
****************
ይህ በስማዳ አካባቢ ያለ ለመስኖ ስራ የሚዉል ግድብ ሊስራበት ተብሎ በጀት ተይዞለት በጀቱ እንኳ የት እንደገባ አይታወቅም። ህዝቡ ሲያማርር ሰሞኑን ደግሞ እንደገና እንሰራዋለን ብለዋል።

4. የጀማ ወንዝ መስኖ ፕሮጀክት
************************
በአንጎለላና ጣራ ወረዳ-ሰሜን ሸዋ የሚገኘዉ ወንዝ ግድብ ሊሰራበት ተብሎ ጥናት ተካሂዶበት ስንት ብር ወጥቶበት የዉሀ ሽታ ሁኖ ከቀረ አመታት ተቆጠሩ። በቅርብ ደግሞ በ2 ቢሊየን ብር እንሰራዋለን ብሎ ብአዴን የፕሮፓጋንዳ ንፋሱን ለቋል። የምናየዉ ይሆናል።

5. የሽንፋ ወንዝ ፕሮጀክት
********************
በሰሜን ጎንደር ቋራ/መተማ አካባቢ የሚገኝ ትልቅ ወንዝ ሲሆን የመስኖ ግድብ ሊሰራበት ተብሎ ከታቀደ ዘመናት አልፈዋል። እንዲያዉም የአካባቢዉን ገበሬ መሬት ሁሉ ለመስኖ የሚሆን ብለዉ ከገበሬዉ ከወሰዱት ቆይተዋል። የተጀመረ ግን ምንም ነገር የለም።

6. የመና ወንዝ ፐሮጀክት
*********************
ይህ ወንዝ እጅግ በጣም ትልቅ ወንዝ ሲሆን በበለሳና ሰቆጣ/ዋግ መካከል ያለ የተከዜ ገባር ወንዝ ነዉ። ትልቅ የመስኖ ፕሮጀክት ታስቦበት በጀት ሁሉ ተመድቦለት አንድም ነገር ሳይሰራ ቆሞ አለ። የበለሳና ሰቆጣ ገበሬ ግን ሴፍቲ-ኔት ተብሎ ስንዴ በወያኔ እየተሰጠዉ ተረጅ ሆኖ ተቀምጧል። እዚህ ወንዝ ላይ ወያኔ ምንም አይነት ፐሮጀክት አይሰራም ብሎ የከለከለ ሲሆን የከለከለበት ምክንያትም የተከዜን ግድብ ይጎዳል በሚል ነዉ።

7. የበለስ የመስኖ ፕሮጀክት
**********************
ይህ የመስኖ ፕሮጀከት በጎጃም አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ብዙ ገንዘብ ወቶበት የተሰራዉ የመስኖ ስራ ማህበረሰቡን እንዳይጠቅም ሆኖ ከስራ ዉጪ ከሆነ ቆይቷል።

8. የአበርገሌ-ዝቐላ ተከዜ ተፋሰስ መስኖ ፕሮጀክት
************************************

የዋግ አካባቢ ገበሬወችን በየጊዜዉ ከሚከሰተዉ የአካባቢው ድርቅ ይታደጋል ተብሎ የተጀመረዉ የመስኖ ፕሮጀክት ይሄዉ እንዲሁ እየተንበላወሰ የአካባቢዉ ገበሬም በችጋር እያለቀና እየተሰደደ ይገኛል፡፡

እነዚህ የመስኖ ፕሮጀክቶች በሚሊየን የሚቆጠር አማራ የሚጠቅም በመሆኑና ከህወሃት ጭቆና ለመዉጣት ደግሞ የጠነከረ ማህበረሰብ ስለሚያስፈልገን ጫና ልናደርግ ይገባል። በኢኮኖሚ ጠንካራ ማህበረሰብ ስንፈጥር የወያኔን መንግስት እድሜ እንደምናሳጥረዉ ሳይታለም የተፈታ ነዉ። ለአንድ ማህበረሰብ የፖለቲካ ነጻነት የኢኮኖሚ ጥንካሬዉ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ሁሌም ቢሆን ባርነት የሚመጣዉ ደግሞ ከድህነት ነዉ።

አማራን በኢኮኖሚ መጨቆን ይብቃ!

**********************

በተያያዘ ዜና

**********************

ሰሞኑን በአማራ ክልል ከ10 አመት በፊት ተጀምረዉ ያላለቁ ከ 7 በላይ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች አዉጥተን ነበር፡፡ እኛን ተከትሎ የአማራ ክልል ቴሌቪዥን በተወሰኑት ግድቦች ላይ ዝርዝር ዘገባ ይዞ ወቷል፡፡ ዘገባዉ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነዉ፡፡

አለም ባንክ ለግድቦቹ ማጠናቀቂያ የመደበዉ ገንዘብ መንግስት ባለመጠቀሙ ሰሞኑን ወደ 90 ሚሊየን ብር ለባንኩ ተመላሽ ያደርጋል፡፡ ህዝቡ በግድቡ ዉሃ በመከበቡና በመንገድ አጦት እየተሰቃየ መሆኑን በዚህም ምክንያት ትምህርት ቤትና ገቢያ መሄድ እንዳልቻሉ ሁሉ ይናገራሉ፡፡

11 ቢሊየን ብር የወጣባቸዉ የመገጭ፤ ሰራባና ርብ ግድቦች ስራቸዉ እኳን ግማሽ አልሆነም፡፡ 11 ቢሊየን ብር ግን የት እንደገባ አይታወቅም፡፡ ገበሬወች የተከፈላቸዉ ካሳ የለም፡፡ አሳዛኝ ነዉ፡፡ በስንቱ ጮኸን እንደምንዘልቀዉ፡፡ ለማንኛዉም አማራን በኢኮኖሚ ለማድቀቅ እየተሰሩ ያሉ ወንጀሎችን እየተከታተልን እናወጣለን፡፡

ከዚህ በታች ዝርዝሩን ማንበብ ይቻላል፡፡ ምንጭ፡ Amhara Mass Media Agency

የርብ መስኖ ግድብ ግንባታ ከ6 ዓመት መጓተት በኋላ ተጠናቀቀ::
ባህር ዳር፡ መስከረም 29/2010 ዓ/ም (አብመድ)

• የመስኖ አውታር ግንባታው 45 በመቶ ላይ ነው
• መገጭ ግድብ ከ50 በመቶ በታች ሲገኝ ሰራባ በዓመቱ መጨረሻ ያልቃል
• ፕሮጀክቶቹ ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ጠይቋል

ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድርና እርዳታ እንዲሁም በፌዴራል መንግሥት የውስጥ በጀት እየተገነቡ የሚገኙት የርብ፣ የመገጭና ሰራባ የመስኖ ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ ከሚገኙ ግዙፍ የመስኖ ብሮጀክቶች በቀዳሚነት ይቀመጣሉ:: በተለይም የመገጭና ርብ የመስኖ ግድቦች በሀገሪቱ ካሉ የመስኖ ግድቦች ውሰጥ በዓይነታቸውና በመጠናቸው የመጀመሪያዎቹ መሆናቸው ይነገራል::

ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነቡ የሚገኙት እነዚህ ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ የመስኖ እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎም ይጠበቃል:: ነገር ግን ፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ በነበረባቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው የፕሮጀክቶችን መልክ አጠይሞታል:: የዓለም ባንክም “በዓለም ላይ ካሉ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች በጣም የተወሳሰበ ችግር ያለባቸው” ሲል እነዚህን ፕሮጀክቶች ይገልፃቸዋል:: በአሁኑ ወቅት ከእነዚህ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል የርብ ግድብ ከተያዘለት ጊዜ በስድስት ዓመት ዘግይቶ በ10 ዓመቱ ለመጠናቀቅ ችሏል:: ነገር ግን የመጀመሪያው ምዕራፍ የመስኖ አውታር (ካናል) ግንባታው 45 በመቶ ላይ ነው:: ይህ ማለት ግድቡ ውሀ ከመያዝ ውጭ በመስኖ ማልማት የሚችልበት ሁኔታ ላይ አይደለም ማለት ነው::

በተመሳሳይ የመገጭና ሰራባ ፕሮጀክቶች ለመጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቀዋል::
ለመሆኑ እነዚህ ፕሮጀክቶች ለምን ዘገዩ? እያሳያደሩት ያለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጽዕኖስ ምንድን ነው? በትንታኔያችን እንመለከታለን::
ፕሮጅክቶቹ ለምን ተጓተቱ?

በሰሜን ጐንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ እየተገነባ የሚገኘው የሰራባ መስኖ ፕሮጀክት በጥር ወር 2008 ዓ.ም ይጠናቀቃል ቢባልም በወቅቱ ግንባታው ገና 50 በመቶ ላይ መሆኑን በኩር ጋዜጣ ዘግቦ ነበር:: ይህ የጣናን ውሀ በአምስት ትላልቅ የውሀ መግፊያ መሳሪያዎች በመግፋት (ፓምፕ በማድረግ) ከአራት ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በማልማት ከ12 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ፕሮጀክቱ ዘገባው ከተሰራ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላም ያከናወነው 40 በመቶን ብቻ ነው:: የፕሮጀክቱ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ባዩ ኑሩ ለፕሮጀክቱ መጓተት የዲዛይንና የመሬት አቅርቦት ችግርን በምክንያትነት ያነሳሉ::

“በአሁኑ ወቅት ችግሮቹ ተፈትተዋል” የሚሉት አቶ ባዩ የቀረው የአንድ ሣይት የካናል ስራ መሆኑንና እርሡ ካለቀ ፕሮጀክቱ እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል::
የሰራባ ዋና የመስኖ ካናል (ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ) ሥራ በቻይና ኩባንያ እየተከናወነ ይገኛል:: አራተኛው( ወደ ማሣ የሚገቡ የውሀ ካናሎች) ደግሞ በአማራ መልሶ መቋቋም ድርጅት (አመልድ) እና አማራ ውሀ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት (አውስኮድ) አማካኝነት እየተገነቡ ነው:: አቶ ባዩ እንደሚሉት እነዚህ ሥራዎች እስከ ሰኔ 2010 ዓ.ም ድረስ የሚጠናቀቁ ናቸው:: በአጠቃላይ ፕሮጀክቱን በዚህ ዓመት ሰኔ ወር ላይ አጠናቅቀን ለማስረከብ እየሰራን ነው ብለዋል::

የመገጭ ግድብ ሥራ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ይርጋሸዋ ዘለቀ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የዘገየው በጥሬ እቃ አቅረቦት እጥረት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል:: በተለይ የአሸዋ አቅርቦት በቅርብ አለመገኘት ዋና ችግር እንደነበር አስረድተዋል:: ከዚህ በተጨማሪም ዋናው ግድብ የሚያርፍበት የመሠረት ቁፋሮ፣ ዘግይቶ መጀመር በሌሎች ሥራዎች ላይ ጫና አሣድሯል ብለዋል::

“በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ 46 ከመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሥራውን ለማፈጠን ጥረት እያደረግን ነው:: ቀሪውን 54 በመቶ በሁለት ዓመት ውስጥ ለመጨረስ አቅደናል” ብለዋል::

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የውሀ መሠረተ ልማት ዘርፍ እየተገነባ የሚገኘው የመገጭ የንፁህ መጠጥና የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅ የነበረበት ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ነው:: ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ግንባታው ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ተራዝሟል:: ሆኖም ፕሮጀክቱ ካሉበት ቀሪ ግዙፍ ሥራዎች አንፃር በተባለው ጊዜ ለመጠናቀቁ እርግጠኛ መሆን አይቻልም::

በሌላ በኩል የርብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት እየተገነቡ ካሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል ለረዥም ዓመታት የተጓተተ ፕሮጀክት ነው:: በኩር ጋዜጣ ታህሳስ 11/ 2008 ዓ.ም በሰራው ዘገባ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስትር ዲኤታው አቶ ከበደ ገርባ ‹‹ግድቡን በ2008 ዓ.ም እናጠናቅቃለን›› ማለታቸውን ዘግቦ ነበር::

ነገር ግን በ2000 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት ከ10 ዓመት በኋላ በአሁኑ ወቅት የግድብ ሥራው ቢጠናቀቅም ለመስኖ ልማት የሚሆነው የአውታር (ካናል) ዝርጋታ ገና አልተጠናቀቀም::
በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚገነባው ይህ የመስኖ ካናል ከዋናው ግድብ አምስት ኪሎ ሜትር ያህል ውሀው ከተጓዘ በኋላ ለሁለት ተከፍሎ የሚጓዝበት ነው:: በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነውና ሦስት ሺህ ሄክታር ሊያለማ የሚችለው ባለ 23 ኪሎ ሜትር የካናል ሥራ ከዓለም ባንክ በተገኘ 50 ሚሊዮን ዶላር እየተገነባ ይገኛል::
የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሀንዲስ አቶ ዳንኤል አሰፋ እንደሚሉት የካናል ግንባታው 2007 ዓ.ም መጀመሩንና በተገባው የውለታ ጊዜ መሠረት በ2010 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ነው:: በአሁኑ ወቅትም ግንባታው 45 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን እስከ ሚያዚያ አጋማሽ 2010 ዓ.ም ይጠናቀቃል ብለዋል::

ነገር ግን ከ36 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለውና ከ10 ሺህ በላይ ሄክታር ሊያለማ የሚችለው የምዕራፍ ሁለት የካናል ስራ መቼ ሊጀመር እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም::
የፕሮጀክቶቹ ባለቤት የሆነው የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ በበኩላቸው የፕሮጀክቶቹ መዘግየት የሚያከራክር አይደለም ይላሉ:: “ሥራዎቹ በወጉ መሠራት የጀመሩት ከ2007 ዓ.ም ወዲህ ነው:: በእነዚህ ጊዜያት ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው መጠን እየተገነቡ ይገኛሉ::
“ከእነዚህም ውስጥ የርብ ፕሮጀክት የግድብ ሥራው ተጠናቅቋል፤ አሁን በየትኛውም ጊዜ መመረቅ ይችላል:: ነገር ግን ሌሎች የዘገዩ ፕሮጀክቶችን ለማካካስ እየሠራን እንገኛለን:: በተለይ መገጭና ሰራባ ከነበሩባቸው ችግሮች መሻሻል አሳይተዋል” ብለዋል::
መዘግየቱ ምን ተፅዕኖ አመጣ?

በኢትዮጵያ የመስኖ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ከ40 በመቶ በታች መሆናቸውን የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ:: በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሀብታሙ ሀይሉ እንደሚሉት የሚዘገዩ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች፣ መጠቀም ያለባቸውን ዜጐች እየጐዷቸው ይገኛሉ:: ከዚህ አንፃር ወጪያቸውና ጥቅማቸው ተመጣጣኝ አይደለም ይላሉ:: በተጨማሪም ፕሮጀክቶቹ በከፍተኛ ወጪ ከመገንባታቸው አንፃር ቶሎ ወደ ሥራ ባለማስገባት ሊፈጠር የሚችለው የኢኮኖሚ ጫና ከፍተኛ ነው:: እንደ እርሳቸው አባባል አንዳንዶቹ “ሳይገነቡ ቢቀሩ” የሚያሰኙ ናቸው ሲሉ ይገልፁታል::

በአማራ ክልል እየተገነቡ የሚገኙት ሦስት የመስኖ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ ወጫቸው 11 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ሲሆን ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ያህሉ ገንዘብ ከመዘግየትና ተያያዥ ችግሮች በመነጨ ወጪ የተደረገ ነው::

በተለይም የርብና መገጭ ፕሮጀክቶች ወጪ ከተያዘላቸው የግንባታ ወጪ ከእጥፍ በላይ ያሻቀበ ነው:: የውሀ፣ የመስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ ግን ከአጥፍ በላይ የመጨመሩ ጉዳይ በዝርዝር መታየት ይኖርበታል ይላሉ:: “በደፈናው በእጥፍ የጨመረ ነው ተብሎ መወሰድ የለበትም:: ለመጨመሩ ምክንያቶች አሉት:: በተለይ የዲዛይኖቹ ሥራ በትክክል የተጠኑ ስላልነበሩ ክለሣ ተደርጓል:: በየጊዜው የሚለዋወጠው የግንባታ ቁሳቁስና ጥሬ እቃ ዋጋ መናር እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረትም ምክንያት ነው:: ከዚህ ባሻገር ግን ቀድሞ የነበረው የፕሮጀክት ዋጋ ዝቅተኛ ሥለነበር ማሻሻያ አስፈልጓል:: ገንቢ ድርጅቶች ኪሣራ ውስጥ መግባት ስለሌለባቸው የዋጋ ለውጥ ተደርጓል” ነው ያሉት::

ከዚህ በፊት የእነዚህ የመስኖ ፕሮጀክቶች መጓተትና ከፍተኛ ወጪ ዋናው ችግር የግንባታ ንድፍ (ዲዛይን) ሥራው መሆኑን በኩር ሚኒስትር መስሪያ ቤቱን ጠቅሦ ዘግቧል:: የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ከበደ ገበርባ ከዓመት በፊት ከጋዜጣው ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ዲዛይኑን የሠራው የእስራኤሉ ታህል ኩባንያ ጥናት ከፍተኛ ችግር የፈጠረ እንደነበር ገልፀዋል:: ኩባንያውንም በህግ ለመጠየቅ ዝግጅት መደረጉን በወቅቱ ገልፀው ነበር:: ሆኖም ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ ግን ስለክሱ “የማውቀው ነገር የለም” ሲሉ ነው የገለፁት::

በሌላ በኩል የግንባታ ሥራዎቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገድብ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው የዓለም ባንክ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች የመድበው 90 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት በጊዜው መጠቀም ባለመቻሉ በጥቅምት ወር 2010 ተመላሽ ይደረጋል:: ይህንን ክፍተት መንግሥት ከራሡ ካዝና ይሸፍናል ተብሎም ይጠበቃል::

ያልተመለሱ ማኅበራዊ ጥያቄዎች

በፕሮጀክቶቹ ዙሪያ የካሳ ክፍያ መዘግየትና የውሀ መከበብ ሥጋቶች ዋነኛ ማህበራዊ ጥያቄዎች ናቸው::

አቶ ላቀው ማኔ በርብ ግድብ አቅራቢያ በሚገኘው የጃራ ሽክራ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ከክረምቱ መግቢያ ጀምሮ ከባድ ጊዜን አሳልፈዋል:: እርሳቸው የሚኖሩበትን ቀበሌ ጨምሮ በሌሎች ሁለት ቀበሌዎች ለሚኖሩ ከሦስት ሺህ በላይ አባውራዎች ዋና መተላለፊያ የነበረው መንገድ በግድቡ ውሀ በመያዙ እጅግ መቸገራቸውን ይገልፃሉ:: “መንገድ የሚባል ነገር ጠፍቷል:: ልጆቻችን ከትምህርት ቤት አቋርጠው የሚውሉት ቤት ነው:: ገበያ መሄድና ወላድ ወደ ጤና ጣቢያ ማድረስ አልቻልንም፤ ልክ አዋሽ ወንዝ ሞልቶ ነዋሪዎች በሄሊኮብተር ወጡ ሲባል እንደምንሰማው አይነት ነው የሆነብን:: መንግሥት አታሎናል በውሀው ትጠቀማላችሁ ሲለን ቆይቶ ይሄው ውሀ አስበላን” ሲሉ በምሬት ይገልፃሉ::

ከዚህ ቀደም ነዋሪዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ለግድቡ ዋና ተፋሰስ የሆኑትን የርብና የሐሙስ ወንዞች በማቋረጥ ነው:: ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በግድቡ ምክንያት ወንዞቹ ወደኋላ ተገፍተው ሌላ መልክ በመያዛቸው የነዋሪዎች እንቅስቃሴ ተገድቧል:: ነዋሪዎች እነዚህን አገልግሎቶች ለማግኘት ከ10 ሰዓት በላይ በእግር መጓዝ ግድ ሆኖባቸዋል::

የተቀናጀ የገጠር ልማት አማካሪ የሆኑት አቶ ዳኘ ምናሉ እንደሚሉት የክልሉና የፌዴራል መንግሥት ችግሩን በፍጥነት መፍትሔ ካልሰጡት አስከፊ ማኅበራዊ ቀውስ ይፈጠራል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ::

“በእኛ በኩል አማራጭ በሆነ ቦታ ላይ ድልድይና መንገድ መገንባት እንዳለበት እናምናለን:: የዚህን ጥናትም ለዓለም ባንክና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቅርበናል:: ነገር ግን እስካሁን ምንም ተጨባጭ እርምጃ አልተወሰደም” ብለዋል::
በሌላ በኩል ደግሞ የካሣ አከፋፈሉ ወጥነት እንደሌለው ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ሥራ መሬታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮች ይገልፃሉ:: በሰራባ ዳውሎ ቀበሌ የሚኖሩት አቶ ቸርነት ስዩም ለመስኖ ልማት ተብለው ለተነሱ አርሦ አደሮች ከሦስት ዓመት በላይ ካሣ ሳይከፈል እንደቆየ ተናግረዋል:: “መንግሥት በተለያየ ጊዜ የገባውን ቃል አልተገበረም” የሚሉት አቶ ቸርነት የአካባቢው ህዝብ ቅሬታው ከፍ እያለ መምጣቱን ገልፀዋል::

በተመሳሳይ በፋርጣ ወረዳ ከርብ ግድብ ጋር በተያያዘ ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ የካሣ ክፍያ አለመፈፀሙን ወረዳው ቅሬታ አቅርቧል::

በርብ ግድብ መሙላት ምክንያት የተፈጠረውን ማኅበራዊ ጫና መፍትሔ ለመስጠት “ድልድዮችንና መንገዱን ማን ይስራው?” በሚል የክልሉና የፌዴራል መንግስት ሙያተኞች መገፋፋት ያሳዩ ቢሆንም ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ችግሩን በስፍራው ተገኝተው ከተመለከቱ በኋላ ሁለት ድልድዮችና ከዋናው መንገድ ጋር የሚያገናኝ የጥርጊያ መንገድ በፌዴራሉ መንግስት እንዲገነባ ውሳኔ ሰጥተዋል::

ከካሣ ጋር በተያያዘ ለተነሡ ችግሮችም ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ ሂደቱ የፈጠረው ክፍተት በመሆኑ ሁሉንም ለማጠናቀቅ ጥረት ይደረጋል ብለዋል::

በፕሮጀክቶቹ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “የርብ ግድብ ተጠናቀቀ የሚለውን ዜና በመስማቴ ደስ ብሎኛል” ብለዋል:: ነገር ግን “አሁንም ከምጥ ያልወጣንባቸው” የመገጭ፣ ሰራባና የርብ የመስኖ አውታር ስራዎች በቀጣይ ሌላ ጥያቄ እንዳይፈጥሩ የበለጠ ትኩረት እንዲሠጣቸው አሳስበዋል::

አብርሃም አዳሙ

በኩር ጋዜጣ የሰኞ መስከረም 29/2010 ዕትም

Source    –   welkait.com