ወገኖቸ በእርግጠኝነት ልነግራቹህ የምችለው ነገር ቢኖር ሕዝባዊ ትግሉ በወያኔ ላይ ይሄንን ያህል ጫና ለማሳደር መቻሉን ነው እንጅ አቶ በረከት በውስጣዊ ሽኩቻው ስለተሸነፉ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደው ሥልጣን ለቀቁ!” የሚለውን ወሬ አትመኑ፡፡

ይሄንን ስል ግን ከአቶ መለስ ሞት በፊትም ሆነ በኋላ ውስጣዊ ሽኩቻ በወያኔ ውስጥ የለም አልነበረም!” ማለቴ አይደለም፡፡ የፈለገውን ያህል የዓላማ አንድነት ቢኖራቸውና ለዚህ ዓላማቸውም የፈለገውን ያህል ጽናት ቢኖራቸውም ሰዎች ናቸውና ሽኩቻ አያጣቸውም፡፡ በእርግጠኝነት ልነግራቹህና እናንተም ልታውቁት የሚገባው ቁም ነገር ግን በተለይም ወያኔ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በወያኔ ውስጥ ያሉ ሽኩቻዎች የበላይነትን ከማግኘት ያለፈ አለመሆኑንና በፍጹም አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ወይም ለመጉዳት ከመፈለግ አንጻር እንዳልሆነ፣ ሆኖም እንደማያውቅ፣ ወደፊትም እንደማይሆን ነው፡፡

የወያኔዎችን መሠሪነት የምታዩት በፀባቸው ውስጥም ያላቸውን ስምምነትና አንድነት ስታዩ ነው፡፡ ወያኔዎች በፀባቸው ውስጥ የተፈጠረውን ውጤት ሌላ ኃይል እንዲጠቀምበት ማናቸውም አይፈቅዱም፡፡ ይልቁንም ለፖለቲካቸው ይጠቀሙበታል እንጅ፡፡ የአቶ በረከትን፣ ቀደም ሲልም የአቶ አባዱላን፣ ከዚያም በፊት የእነ ስዬ አብርሃንና የሌሎችንም ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ወጡ፣ ተባረሩ፣ ተለዩ የተባሉ ሰዎች ወጥተውም፣ ተሸኝተውም የሙሉ ጊዜ ሥራቸው ባሉበት ሁኔታ ሆነው ወያኔን ማገልገል ነው እንጅ ወጡ ተባረሩ ወይም በአቋምና በዓላማ ልዩነት ሳቢያ ለቀቁ የተባሉ ሰዎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቆመው ወያኔን ተቃርነው ወያኔን ለማጥፋት ሲታገሉ ታይተው ተሰምተው አይታወቁም፡፡

እነ አቶ ገብሩ ዐሥራትን ትጠቅሱልኝ ይሆናል፡፡ ልብ ብላቹህ አይታቹህ እንደሆነ ግን እነ አቶ ገብሩ እየሠሩ ያሉት ለትግራይ ሕዝብ አማራጭ መስለው በመቅረብ የትግራይ ሕዝብ ከወያኔያውያን ውጭ ወደሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች እንዳይሔድ የመከላከል ሥራ ነው እየሠሩ ያሉት፡፡ ለዚህም ነው ተለዩ ከተባሉ በኋላ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) የሆነ የአቋም ልዩነት የማያንጸባርቁት፣ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር መልሰው በአንድነት የሚቆሙት፣ ወጡ የተባሉ ሰዎች ድርጓቸው ወይም የመተዳደሪያ ወጪያቸው ከድርጅቱ የሚሰጣቸው፡፡

በመሆኑም የአቶ በረከት ስምኦን መልቀቅም ሕዝባዊ ትግሉ በድርጅቱ ላይ ከፈጠረው ውጫዊና ውስጣዊ ጫና ጋር በተያያዘ ወያኔ ሊሠራው የፈለገውን የፖለቲካ ሥራ ለመሥራት አቶ በረከት ይሄን እንዲያደርግ ተደረገ ወይም አደረገ እንጅ አቶ በረከት በፍጹም በፍጹም ወያኔን ለማሳጣት ወይም በመክዳት ወይም በመሸሽ በግል ተነሣሽነቱ ወይም ፍላጎቱ ይሄንን እርምጃ አልወሰደም!!! አቶ በረከት ይሄንን ከሚያደርግ እራሱን ቢያጠፋ ይመርጣል፡፡ ይሄንን እውነት አቶ በረከት ከዚህ በኋላ በተለየ ሁኔታ ለወያኔ ከመሥራቱና የመተዳደሪያ ገቢውንም ከወያኔ እያገኘ ከመቀጠሉ ወዘተረፈ. ነገ የምታረጋግጡት ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ ቆይ ታያላቹህ ብዙም ሳይቆይ ወያኔ በአቶ በረከትም ሆነ በአቶ አባዱላ ሌላም በተመሳሳይ መንገድ ለቀቀ የሚባልም ካለ እሱንም ጨምሮ በእነሱ ላይ ሊሠራው የፈለገውን ፖለቲካዊ ሥራ ከሠራ በኋላ ቅሬታቸው ስለተቀረፈ ተመለሱ!” ብሎ ወደ ቦታቸው ሲመልሳቸውም ታዩ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ወጣም ወረደ ወያኔ ለማስመሰልም ቢሆን ይሄንን እያደረገ ያለው ትግልህ ካሳደረበት ከባድና አስጨናቂ ጫና የተነሣ ነውና ይሄ ላንተ ታላቅ ድል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ድልህ ፍጻሜ ማግኘት አለበት! በመሆኑም ወያኔ መራሹ አገዛዝ ድራሹ እስኪጠፋ ድረስ ክፍተትህን እየሞላህ ትግልህን አጠናክረህ ቀጥል!!! “ከወያኔ በኋላስየተዘጋጀ ኃይል ስለሌለ ችግር ላይ አንወድቅም ወይ?” የሚለው ሐሳብ ፈጽሞ አያሳስብህ! እመነኝ ወያኔ የፈለገውን ያህል ሸፍጥ ቢፈጽምም ለዚያው ሰሞን ጥቂት ግርግር ከመፍጠጥ ባለፈ ዘላቂ የሆነ ችግር የመፍጠር አቅም አይኖረውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ ጭንቅላት የሚያስብበትን ዕድል ካገኘ እጅግ ኃላፊነት የሚሰማው ሕዝብ ስለሆነና የጥፋት ኃይሎች በፈጠሩበት ቀውስ የተሰላቸ፣ አደገኝነቱንም የተረዳ ስለሆነ ምንም አይመጣም አትሥጋ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com