18 ኦክተውበር 2017

የተፈናቃዮች በሐማሬሳ መጠለያ ውስጥየተፈናቃዮች በሐማሬሳ መጠለያ ውስጥ

ኢብራሂም አሊ አብደላ በኢትዮጵያየሶማሌ ክልል ቀብሪ ደሃር ከተማ ከ20 ዓመታት በላይ የኖረ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ነው። የተከሰተውን ሲያስታውስ፤ በወቅቱ እነደለመደው በጠዋት ተነስቶ ነበር።

በድንገት መጥተው በዱላና በድንጋይ ሲደበድቡኝ ወደ ሥራዬ ለመሄድ ፈረሶቼን አዘጋጅቼ ነበርይላል።

በዚያን ዕለት የክልሉ ወጣቶች በልዩ ፖሊስና በአካባቢው ባለሥልጣናት እየታገዙ ኦሮሞዎች ላይ ድብደባ መፈፀም እንደጀመሩ ይናገራል። ህይወታችንን ለማትረፍ ጋሪዬን ጥዬ ከቤተሰቦቼ ጋር ወደጫካ ሸሸሁኝይላል ኢብራሂም።

ኢብራሂም አሁን የሶማሌ ክልልን ለቀው በተለያዩ መጠለያዎች ካሉት 119 ሺህ ከሚደርሱ ተፈናቃዮች መካከል አንዱ ነው። ይህ ቁጥር የተገኘው ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአደጋ መከላከል ኮሚሽን ነው።

በሁለቱ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በኦሮሚያ በኩል ከ450 ሺህ በላይ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ይህ ቁጥር በፍጥነት ወደ 600 ሺህ እየተጠጋ መሆኑን ኮሚሽኑ ይናራል።

ኢብራሂም በአሁኑ ጊዜ በሐረር ከተማ በሚገኘው ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው የመጡ ከ4000 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ባስጠለለው ሐማሬሳ በተባለ ጣቢያ ውስጥ ነው።

በጣቢያው ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነና አንዳንዶችም ለህይወታቸው አስጊ ሁኔታዎች እንዳሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በመጠለያው ውስጥ ያለ ክሊኒክ

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተከሰተውን ግጭት የሚያብራሩ አምስት ነጥቦች

የመጠለያ ኑሮ፡ ስቃይና ተስፋ

በሐማሬሳ ጊዜያዊ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በሚገኘው ክሊኒክ ውስጥ ሙሉ ፊቷ የቆሰለ ሴት ተኝታለች። እሷ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት ናቸው በምትላቸው ሰዎች ለቀናት መደፈሯን ትናገራለች።

መጀመሪያ ከባለቤቴ ጋር ሆነን ያዙንትላለች። ወደ ጫካ ወስደው አስረው ክፉኛ ደበደቡኝ። ከዚያም ለተከታታይ ቀናት የሚፈልጉትን ከፈፀሙ በኋላ መንገድ ላይ ጥለውኝ ሄዱ። ከአማራ ክልል የመጣ አንድ ሰው አግኝቶ ነው ወደ ሃኪም ቤት በመውሰድ የረዳኝ።የምትለው ይህች ሴት እስካሁን ባሏ የት እንደደረሰ እንደማታውቅ ትናገራለች።

ሐማሬሳ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ለንግድ ተብሎ በብረት የተሠራ ትልቅ መጋዘን ነው።

አንዳንድ ተፈናቃዮች ሲናገሩ እዚህ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ልጅ ይዞ መጠለል እጅጉን ከባድ ነው፤ የምናገኘው ምግብ እና መጠጥ በቂ አይደለም ይላሉ።

የመፀዳጃ እና መታጠቢያ ስፍራ ጉዳይም እጅግ አሳሳቢ ነው። አሁን ላይ የምግብ እጥረት የለም። ነገር ግን ተፈናቃዮቹ እንደለመዱት ማቅረብ በጣም ከባድ ነውይላሉ የምስራቅ ሓረርጌ ዞን አደጋ መከላከል ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቶሌራ።

በሌላ በኩል እያደገ የመጣውን የተፈናቃዮች ቁጥር መመገብ እጅግ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ግርማ ዋታሬ ያስረዳሉ።

ከእነዚህ ተግዳሮቶች አለፍ ሲል ተፈናቃዮቹ ከወታደሮች የሚደርስባቸው ማስፈራራት እና ዛቻ ፈተና እንደሆነባቸው ለቢቢሲ ይናገራሉ።

የተፈናቃዮች ጣቢያውን ተዘዋውሮ የጎበኘው የቢቢሲ ሪፖርተር እንደታዘበው ጣቢያው በኦሮሚያ ፖሊስ ጥበቃ ስር ቢሆንም ሌሎች ወታደሮችን በዙሪያው መመልከት ችሏል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ስለጉዳዩ ለቢቢሲ ሲያስረዳ ተፈናቃዮቹ ስለየትኛው ማስፈራራት እንደሚያወሩ መረጃው የለንምብሏል።

እናቶችና ህፃናት በመጠለያው ውስጥእናቶችና ህፃናት በመጠለያው ውስጥ

በቀጣይ. . .

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ብቻ ወደ 72ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች መጀመሪያ ላይ በትምህርት ቤቶች እና ጊዜያዊ የመጠለያ ሥፍራዎች ነበር የሚገኙት።

አሁን ግን ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ክፍት በመሆናቸው ቅርብ ዘመድ ያላቸው ተፈናቃዮች ወደዚያ ሲያመሩ፤ የተቀሩት ደግሞ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተጠልለው ይገኛሉ።

/ሮ ራዉላ አዩብ በቀብሪ በያህ ከተማ ለ12 ዓመታት በነጋዴነት ተሰማርተው ቆይተዋል። ግጭቱ ከመከሰቱ በፊት ራውላ የኢትዮጵያሶማሌ ክልል ጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም ይኖሩ እንደነበር ያስውታውሳሉ።

በክልሉ ልዩ ኃይል የሚደገፉ ሰዎች ቤት ንብረታችንን አቃጠሉብን። ከዚህ በፊት እንደማያውቁን ሆኑብንይላሉ።

/ሮ ራዉላ በአሁኑ ወቅት ከባለቤታቸው እና ከሰባት ልጆቻቸው ጋር ፈዲስ አካባቢ እህታቸው በሰጠቸቻው አነስ ያለ ቤት ውስጥ ይኖራሉ። ነገር ግን እንደተፈናቃይ ተስፋ እየቆረጡ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አደጋ መከላከል ቢሮ እንዳስታወቀው ለተፈናቃዮቹ በፊት ከሚሠሩት ሥራ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሥራ ለማመቻቸት ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስከ ጥቅምት 3/2010 ድረስ ለተፈናቃዮች የተሳበሰበው ገንዘብ መጠን 166 ሚሊዮን ብር ደርሷል።