“በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች እየተካሄደ ያለውን የተቃውሞ ሰልፍ ማን ነው የሚያስተባብረው?” የሚለው ጥያቄ ትልቅ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።

ዳኒኤል ብርሃኔ “የተቃውሞ ሰልፉ እየተመራ ያለው ከተጠበቀው በላይ ትልቅ በሆነ የህቡዕ ድርጅት” መሆኑን ገልፀጿል። እኔን የሚያሳስበኝ የዚህ ህቡዕ ድርጅት መፈጠሩና የተቃውሞ እንቅስቃሴውን መምራቱ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ መዋቅሩ በግልፅ ያልተለየ “ትልቅ የህቡዕ ድርጅት ተፈጥሯል” በሚል ሰበብ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሊፈፀም የሚችለው ግፍና በደል ነው።

ቀጥሎ ያለው ምስል የሁለት ፎቶዎች ቅንብር ነው። የመጀመሪያው ፎቶ ህዳር 25/2008 ዓ.ም ዕለተ ሐሙስ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ላይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎች በካምፓሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ ሲጀምሩ፣ ከዋናው መግቢያ በር ላይ ደግሞ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አድማ በታኞች ፖሊሶች ናቸው። ከታች ያለው ምስል ደግሞ ጥቅምት 03/2010 ዓ.ም ዕለተ ሐሙስ ከጠዋቱ 2፡00 ላይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ካምፓሱ ቅጥር ግቢ እየወጡ ያሳያል።

የተቃውሞ ሰልፍ በወሊሶ፦ ህዳር 2008 እና ጥቅምት 2010 ንፅፅርበዚህ ፎቶ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊሶች ወይም የከተማ ፖሊሶች ከካምፓሱ በር ላይ አይታዩም። ነገር ግን፣ በከተማው ዋና ዋና መንገዶች ላይ በብዛት ይታዩ ነበር። ከታች ባለው ፎቶ ላይ በግልፅ እንደሚታየው ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የከተማውና የኦሮሚያ ልዩ ፖሊሶች ስራቸውን በአግባቡ እየሰሩ እንደነበር ያሳያል። ከሁለት አመት በፊት የፖሊሶቹ ጥረት ተማሪዎቹና የአከባቢው ማህብረሰብ የተቃውሞ ሰልፍ እንዳያደርጉ በኃይል ለማስቆም ነበር። ባለፈው ሳምንት ሲያደርጉት የነበረው ደግሞ ተቃውሞ ሰልፉ ሁከትና ብጥብጥ እንዳይነሳ፣ በዚህም የሰዎች ህይወትና ንብረት እንዳይጠፋ መጠበቅ ነው።ባለፈው ሳምንተ በወሊሶ ከተማ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍከሁለት አመት በፊት ፖሊሶች የተቃውሞ ሰልፉን በኃይል ለመበተን ያደረጉት ጥረት ከሳምንት በኋላ ፈፅሞ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከ50ሺህ በላይ የወሊሶ ከተማ ነዋሪዎች ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ ወጡ። በዚህ ምክንያት፣ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ። ከከተማዋ አልፎ በመላው ኦሮሚያ የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር ተፈጠረ። በመጨረሻም በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አማካኝነት ህዝቡና ሀገሪቱ በወታደራዊ ቁጥጥር ስር ወደቁ።ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ግን ፍፁም ሰላማዊ ነበር። ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ላይ የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ ከ15ሺህ በላይ ሰዎችን ተሳትፈውበታል። ነገር ግን፣ ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ ግን ሁሉም ነገር ተጠናቅቆ ሰዎች በሰላም ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰዋል። በሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ፖሊሶች በኃይል ለመበተን ባይሞክሩ ኖሮ ዛሬ ከደረስንበት ደረጃ አንደርስም ነበር። በወቅቱ “ወሊሶ፡ ከሰላም ወደ ሱናሚ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፁኁፍ ላይ የተቃውሞ ሰልፉን ወደ አመፅና ብጥብጥ እንዲቀየር ያደረገውን ምክንያት እንዲህ ስል ገልጬ ነበር፡-

“ከዛሬ 50 አመት በፊት እንደነበረው ሁሉ፣ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ በኃይል ለመበተን የሚደረግ ጥረት ሁኔታውን ይበልጥ ከማባባስ የዘለለ ሚና የለውም። ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በተካሄደ ቁጥር ፖሊስ የተለመደ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ነገሩን ከማባባስ ይልቅ ዋና ተግባሩ በሆነው የሰውና የንብረትን ደህንነት በማስከበር ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሰራ የተሻለ ነው። የመንግስት ኃላፊዎችም በበኩላቸው የተነሳውን ተቃውሞ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በሚጥስ መልኩ የኃይል እርምጃ በመውሰድ አቋራጭ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የተነሳውን ጥያቄ በአግባቡ ተቀብለው ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ አለባቸው።”

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ እንዲሁም ባለፈው ሳምንት በወሊሶ ከተማ ከታየው ሰላማዊ ሰልፍ አንፃር፣ የተቃውሞ ሰልፉን ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚቀይሩት ሰልፈኞች፥ ፖሊሶች ወይም ማንነታቸው ያልታወቁ ፀረ-ሰላም ኃይሎች አይደሉም። ከዚያ ይልቅ፣ ሁከትና ብጥብጥ የሚነሳው በፖለቲካ መሪዎች የተሳሳተ ግምትና ውሳኔ ምክንያት ነው።ከሁለት አመት በኦሮሚያ አመፅና ተቃውሞ ሲቀሰቀስ የኢትዮጲያ መንግስት ኦነግና ግብፅን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች እየተካሄደ ያለውን የተቃውሞ ሰልፍ እየተመራ ያለው በጣም ትልቅ በሆነ የህቡዕ ድርጅት ከሚል የለየለት ቅዠት ውስጥ ገብቷል።ለሁለት አስርት አመታት “ኦነግ ሞቷል” እያለ ሲፎክር የነበረው የፖለቲካ ቡድን ከሁለት አመት በፊት ኦነግን ከቀበረበት መቃብር፣ ግብፅን ከገባችበት ችግር አውጥቶ “በኦሮሚያ አመፅና ተቃውሞ እየቀሰቀሱ ነው” በማለት የብዙሃን መሳቂያና መሳለቂያ የሆነ ምክንያት ሲያቀርብ ነበር። አሁን ደግሞ “ትልቅ የህቡዕ ድርጅት ተቋቁሟል” ከሚል ቅዠት ውስጥ ገብቷል። ይህ የፖለቲካ ቡድን ፈፅሞ መገንዘብ የተሳነው ነገር ቢኖር፣ የኦሮሞ ሕዝብ የተቃውሞ ሰልፍ እየወጣ ያለው በምንም ምክንያት፣ በማንም አሰስተባባሪነት ሳይሆን ያነሳቸው የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ ስላላገኙ ነው።ይህን እውነታ ተቀብሎ ተገቢ ምላሽ መስጠት የተሳነው ቡድን አንዴ “ኦነግና ግብፅ” ሌላ ግዜ “ህቡዕ ድርጅት” እያለ ሲቃዥ ይውላል እንጂ የሕዝቡን የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ማስቆም አይችልም። “የማሪያምን ብቅል የበላ ሲለፈልፍ ያድራል” እንደሚባለው ሁሉ የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ነፃነት የበላ መንግስት ኦነግ፥ ግብፅ፥ ህቡዕ፥…እያለ ሲለፈልፍ ያድራል!

https://ethiothinkthank.com/