የበረከት ስምኦን ከስልጣን በፈቃድ መልቀቅን ስሰማ የተለመደ የወያኔዋ አደናጋሪ ፕሮፖጋንዳ መስሎኝ ብዙም ጀሮ አልሰጠሁም ነበር። ያልተጠበቀ አይደለም በየግዜው አዲስ የሚሆነው ግን ድቃቅ ሰላዮች ለጌቶቻቸው ሁልግዜም ታማኝ በመሆን የሚመጣውን ይቀበላሉና ነው። መቸም ያልታደለችው አገራችን እና መከረኛው ሕዝባችን ለነጻነቱ ሲሉ የሚታገሉትን በግዜ በሞት እና በስደት ይለይና እኒያ ቀጥቅጠው የገዙት አገር ያፈረሱትን እፋረዳለሁ ብሎ ሲጠብቅ መጭውም ያው ብጤ መሰሉን ፈንቅሎ በቦታው ይሰየማል ፍትህን እና ፍርድን ለእርሱ በሚመች ስለሚሰራቸው ነጻነትም፣ ፍትህም፣ ዳኝነትም እንደጉም ተነው ይቀራሉ። 1991 የነበረው እርእሰብሄር አንድ ሰው እና አንድ መሳሪያ ብሎ ቃል እንዳልገባ ገና መንጋ ገንጣይ እና የቀን ጅብ አባይን ተሻገሩን ሲሰማ በጠራራ ጸሀይ ፈረጠጠን በዜና ሰማነው። የስንት እና ስንት የትውልድ ደም ያውም ብርቅ እና ድንቅ ዜጋ ጭዳ አድርጎ ማለት ነው። ከሁሉም ካስደመሙኝ የያን ሰሞን ዜናወች አንድ ቱባ ነፍሰበላ እና ፈላጭ ቆራጭ አሕያ እየነዳ ተያዘን በሰማሁ ግዜ ነበር። ስለአለፉ በአጭር ስለተቀጩ የለውጥ ተስፋወች ብዙ ብዙ ልንል እንችላለን የዛሬውን አንዲስ ትያትር ገና እየተከፈተ ነው እና ወደዚህ መዞሩ መልካም ነው።

መርከቧ እየሰጠመች ነው

ፈርጣጮችም የእኔ እቀድሙን ጀምረውታል። ልክ እነዚሁ ነፍሰበላ ዘረኞች እንደተኩት እነሱም እንደጉም ተነው ነበር የጠፉት የምንልበት ግዜ እሩቅ አይመስልም። እናም ብዙ ሰው ይሰጋል። ስጋቱ ተኪ ይኖር ይሆን በማለት ነው። እንደኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ ነው። መንግስት የማይፈልግ ጎረቤት ጎረቤቱን አቅፎና ተደጋግፎ ክፉ ቀንን የሚያሳልፍ። በአለም ላይ አሉ ተብሎ ቢቆጠር ሕዝባችንን ያህል ጨዋና ፍጹ ስልጡን አይገኝም። ይህን ደፍሬ ስናገር ከማስረጃ ጋር ስለሆነ ነው። 1991 ለዚህች አገር ጠላቶች ሰኔና ሰኞ ገጥሞላቸው ከየአለም ማእዘናቱ ተጠራርተው ነበር የወረሩን። ልክ እንደጀኔራል ቦዶሊዮ እና ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን የትፍረስ ፍርድም በአዋጅ ነበር የለፈፉት። ለብዙ ሽህ አመታት የተገነባን ባህላዊ ትስሥር ዶጋ አመድ አድርገው ሕዝብ ችላ ቢላቸውም በአርባ ጉጉ እና በበደኖ፣ በሌሎችም ሁሉ ብዙ ግፍ አሳይተውናል። የሰው ልጅን እስከነፍሱ በገደል እያስወረወሩም የቪዲዮ ምስል ቀርጸው ለአለም አቅርበዋል። እጣት የተጠቆመበት በእርግጥም ነፍጠኛው ይህችን ሀገር ከወገኖቹ ጋር ሆኖ አጥንቱን ከስክሶ፣ ደሙን አፍስሦ የገነባትን ዜጋ ነበር። ለሀገር መታጠቅ እና ዘብ መቆም ነውር የሆነበት፣ በሀገር ተመክቶ እና ለሕዝብ አለኝታ ሆኖ ወጥቶ ያደረን ነበር ጠላት ብለው እስከ ዛሬ የረገሙት። ሕዝብን እርስ በእርስ ለማባላት ነበር ጣት በአንዱ ሌላው እንዲቀስር የሰበኩት። ገጀራ ይዞም እዲተራረድ ነበር ተነስ ብለው ያወጁት። እስከ ኦጋዴን ድረስ ሄደው በለው ምንትጠብቃለህ ነበር ያሉት። ቆዳ ወፍራሞቹ ስለሕዝብ ቅንጣት አብሮነት የማይሰማቸው በመጨረሻዋም ሰአት የኦጋዴን ዜጎች በኦሮሞ ወገኖቻቸው እንዲጨክኑ መሳሪያ ያስታጠቁት። ደምም ያፋሰሱት። ዜጋ አገሩን ለቆ ወደማያውቀው እንዲባዝን ያደረጉት ነገ ጠዋት እንደጉም በነው የሚጠፉት ወያኔወች እና ባንዶቻቸው ናቸው ተነግሮለት የማያልቅ ብዙ ብዙ ግፍ እና በደል የፈጸሙት። ብዙ አገራዊ ወንጀል ባገር እና በሕዝብ ላይ የፈጸሙት።

ትናንት ሌላውን ሲገሉ ሲያስገድሉ የነበርሩት እንደነ አባዱላ ገመዳ አይነት ቢጭኗቸው ትንፍስ የማይሉቱ ሰጋር በቅሎወች ናቸው ይህን እጅግ ዘግናኝ ግፍ በቃን ያሉት። ከሁሉም ግፍ እና አገርን ለመግደል በተደረገው ሁሉ ዘመቻ ቀድመው የሰገሩቱ መርከቧ ስትሰጥም አብሮ መድፈቁን በአስራሁለተኛዋ ሰአት ያልቻሉት ልክ እንደጲላጦስ እጃቸውን ለመታጠብ የዳዳቸው። በረከት ስምኦን የዚህ ዘረኛ ስርአት ፊታውራሪ። የብዙ ዜጎችን ቤት የዘጋ፣ የብዞ ደሀ እናቶችን እና ደካማ አባቶችን አጋዥ ልጆች ደም ያፈሰሰ እና ያለጧሪ እና ቀባሪ ያስቀረው። ከቀንደኛው የኢትዮጵያ ጠላት መለስ ዜናዊ ጋር አብሮ ተባብሮ አገር ዶጋአመድ እንድትሆን፤ በኢትዮጵያ ትቢያ ላይ ታላቋን የትግራይ ትግሪኝን አላማ ሊያሳካ ደፋ ቀና ያለውን በረከት ስሞን ዛሬ ያረጋገጠው የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ለአመታት በይዞታ ከተተከለበት ተነስቷል። ሕወሐት ከሽፎባታል። ጀጀባውን ያዥው እንዳለው ባል እና እልከኛዋ ሚስት አረፋ ጨብጣ በሙላት እንደተበላችው ማለት ነው። ይህን ስርአት ለማትረፍ፣ አለያም አወጣጡ እንዲያምር ብለው ምክር የለገሱት የቀድሞ ወያኔ ሐርነት ትግራይ መሪወች ጻድቃን ገ/ተንሳይ እና አበበ ተ/ሐይማኖት ድርጅታቸውን ለማትረፍ ጀጀባውን ያዙ ካሉ አመት አስቆጥሯል። ደናቁርቱ የወያኔ መሪወች አሁንም እየሰመጠች ባለችው የስልጣን ጀልባቸው ሆነው የሚታያቸው ማሰር፣ መግደል፣ ሰጥ እና ለጥ አድርጎ ሕዝብን ስልጣናቸውን ማስቀጠል። አለያም የጠላት አገር የሚሏትን ከምንም በላይ የሚጠሏትን ኢትዮጵያን እርስ በእርስ አተራምሶ መሄድ ነው።

ይኸው እየሰጠመች ባለችው የስልጣን ጀልባቸው ላይ ተፈናጠው ዛሬ አረጋዊውን ምሁር ዶክተር መረራ ጉዲናን በእንበለ ፍርድ የሚያንገላቱት አሁንም የነገ ተነገ ወዲያን በነሱ እጅ ለመቆየቷ ባልተረጋገጠ ስልጣናቸው ተመክተው ነው። የሕወሐት ወንጀል ህልቆ መሳፍርት የለውም። ወያኔዋ ድርጅት በየካቲት 1967 ዓም ስትፈጠር ጀምራ የቋጠረችውን የዘረኝነት ጥላቻ እና ክፋት እስከ እለተ ሞቷ ተሸክማ ታልፋለች። 
በዚህ በማህበራዊ ገጽ አንድ ወጣት የጻፋትን ውስጥ አወቅ ጽሁፍ አነበብሁ። ጽሁፏ ስለበረከት መልቀቅ እና የበረከትን ባህርይ፣ ብሎም ከኢሓፓ ከከዱት መሰል ባንዶች ጋር ሆነው በሕወሀት ታጅበው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ባንድ ምሽት አማራ ሆነው ያማራ ድርጅት ተብሎ የተፈጠረውን የወያኔ መጋዣ በአዴን ውስጥ ስለነበረው ሚና ጽሁፏ ታብራራለች። በይበልጥም ሕዝባዊው ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ ሕዝቡ በበረከት ላይ ያደረሰበትን ጫናም ትዘረዝራለች ይህን የዳሰሰችዋ መጣጥፍ የእርሱን መልቀቅ ግን ቀለል አርጋው ታልፋለች። እናም ጸሀፊው ሀገር ውስጥ የሚኖር ሆኖ ሳለ እና ዛሬ በኦሮሚያ ዳግም የተቀሰቀሰው ንቅናቄ አዲስ አበባ ጫፍ ደርሶ ባለበት፣ ቱባ ባለስልጣናት ስራቸውን እየለቀቁ መሹለክ ላይ ባሉበት ሁኔታ የበረከትን መልቀቅ ነጠላ ማድረግ አይቻልም። ቢያንስ የአማራ ክልል ላይ ያለውን ስልጣን እና ለወያኔ የሚሰጠውን ልምዳዊ አስተዋጸኦ ማሳነስ ከባድ ጉድለት ይመስለኛል። ባጭሩ ስርአቱ በመፍረስ ላይ ነው። ስርአቱ ወደነበረበት ተመልሶ ሕዝብን ለመግዛት ከማይችልበት እንዲደርስ ያደረጉት ሁኔታወች ቀጣይ በመሆናቸው እና ድቃቋ የትግራይ ዘረኛ ልትመክተው፣ ልትቆቋመው ከማይቻላት ካለፈ የጻድቃን፣ እና የአበበ አወጣጣችሁን አሳምሩ የምትለዋ ምክር ምስክር ናት። ለምሳሌ ኳስሜዳ በሁለት ቲሞች በሚደረግ ውድድር ያንዱ ሌላውን ማቸነፍ ብዙውን የመንፈስ የበላይነት ማግኘት ውጤት ነው። የመንፈስ የበላይነት ዛሬ ያለው ሞት ወይንም ነጻነት ብሎ በተነሳው ሕዝባዊ ንቅናቄ ጎን እንጅ በአንድ ገዥ ጨቋን ድርጅት አይደለም።

ሕወሐት እና የመጋዦች ስብስብ የሆነው ኢሓዴግ ፈርሷል ወይንም በፍጥነት በመፍረስ ላይ ነው። ጥያቄው አሁንም በተቃዋሚው ላይ ይሆናል። የምንመኘው ነጻ ሀገር እና ዴሞክራሲን፣ ሰበአሚ መብትን፣ የሕግ የበላይነትን፣ እና እኩልነት የሰፈነበት ስርአት ለማምጣት ከሆነ ልዩነትን አጥቦ ተባብሮ የሀገሪቱን እድል መወሰን ነው። በራስ ሀገር የሌሎች እጅ ዘው ብሎ እንዲገባ መፍቀድ ልክ እንደ 1991 ዓም የለንደን ስብሰባ ማለት ነው አሁንም ለምንመኘው ነጻነት ሳይሆን ለምእራባውያኑ አራጊ ፈጣሪነቱን ሀላፊነት መስጠት ነው። እነርሱ ደግሞ ለኛ የሚጠቅም እንጅ ለሕዝብ የሚጠቅም የሚል ሀሳብ እንደማይኖራቸው መታወቅ አለበት። ነጻነትን ለማምጣት ኢትዮጵያውያን የቤታችንን ጉዳይ እኛው ብለው በአንድ መነሳት ይጠበቃል። በወያኔ ላይ የጀመረው ተቃውሞ ገና ከለንደን ሳይለቁ እንደሆነ ሁሉ። ችግራችንን ለመፍታት በጋራ እና በልበሰፊነት መነሳት ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!