የኬንያ የምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ኃላፊ ሮዝሊይን አኮምቤ
አጭር የምስል መግለጫ የኬንያ የምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ኃላፊ ሮዝሊይን አኮምቤ

በጥቅምት 16 ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የኬንያ ምርጫ ተዓማኒነቱ እንደሚያጠራጥር በኬንያ የምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ሮዝሊይን አኮምቤ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ምርጫውን በበላይነት የሚመራው የምርጫ ቦርድ ውሳኔም ሆነ ስምምነት ላይ ለመድረስ ፖለቲካዊ መታፈን ደርሶበት ነበር።

ኬንያ በነበሩበት ወቅት ለህይወታቸው አስጊ የሆኑ ማስፈራሪያዎች ስለደረሳቸው በአሁኑ ወቅት ተቀማጭነታቸውን አሜሪካ አድርገዋል።

ባለፈው ሳምንት የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ከምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል።

ባለፈው ነሐሴ በተካሄደው ምርጫ ኡሁሩ ኬንያታ አሸንፈው የነበረ ሲሆን፤ ምርጫው በትክክል አልተካሄደም በሚል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

” ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ሊሆን ይችላል? ” በሚል የቢቢሲ የዜና ክፍል በጠየቃቸው ወቅት ሮዝሊይን አኮምቤ “በጭራሽ አይሆንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

“ባለፈው ምርጫ ወቅት የነበሩት ባለስልጣናት የሰሯቸው ስህተቶች በዚህም ምርጫ ላይ የመደገሙ እድል በጣም ከፍተኛ ነው። “ብለዋል

ምርጫ ቦርዱ በማያፈናፍን ሁኔታ ውስጥ በመቆየቱ ተዓማኒነት ምርጫ ያለው ለማድረግ አስፈላጊ ለውጦችን መተግበር አልቻለም ነው ያሉት።

ከዚህም በተጨማሪ የምርጫ ቦርዱ አባላት ችሎታን ሳይሆን ወገንተኝነትን ባማከለ መልኩ እንደሚመረጡ ጠቁመዋል።

የምርጫ ቦርዱ አስፈፃሚዎች ከፖለቲከኞችና ከተቃዋሚ ሰልፈኞች ማስፈራሪያ እንደደረሳቸውም ሮዝሊይን አኮምቤ ጨምረው ይናገራሉ።

እርሳቸውም ከማስፈራሪያ በተጨማሪ ከስራ ቦታቸው እንዲለቁ ግፊት እንደተደረገባቸውም አልደበቁም።

“በሀገሬ እንደዚህ አይነት ፍራቻ በህይወቴ ተሰምቶኝ አያውቅም” ብለዋል።

የምርጫ ቦርዱ ምንም አይነት ምላሽ ባይሰጥም ሮዝሊይን አኮምቤ ሀገሬ ተመልሸ ለመምጣት ለደህንነቴ ስለሚያስፈራኝ በቅርቡ አልመለስም ብለዋል።

የተቃዋሚው ናሳ መሪ ራይላ ኦዲንጋ
አጭር የምስል መግለጫ የተቃዋሚው ናሳ መሪ ራይላ ኦዲንጋ

የተቃዋሚው ፓርቲ ‘ናሳ’ (ናሽናል ሱፐር አሊያንስ) መሪ ራይላ ኦዲንጋ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት ” ከኬንያ ምርጫ ቦርድ በኩል ምንም አይነት የማስተካከያ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ እንዳልሆነ ማጠቃለያ ላይ ደርሰናል። ቀጣዩም ምርጫም ካለፈው የከፋ ይሆናል” ብለዋል።

ራይላ ኦዲንጋ በተከታታይ ምርጫ ቦርዱን በመቃወም የተቃውሞ ሰልፎችን አደራጅተዋል።

በተቃራኒው ኡሁሩ ኬንያታ ምርጫው በታቀደው መሰረት ለማካሄድ ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

“ወደ ምርጫው ለመመለስ ምንም አይነት ችግር የለብንም። ካለፈው በበለጠ ብዙ ድምፅ እንደምናገኝ እርግጠኛ ነን” ብለዋል።