October 17, 2017 22:44

የትግራይ የገጠር አካባቢዎች ገዳማትም ጭምር ይመስላሉ፤
ብዙ ተዛዙሬ ባየሀዋቸው የትግራይ የገጠር ወረዳዎች በጣም በምያሳዝን ሁኔታ የወጣቱ የህ.ሰብ ክፍል አንሶ እና ተመናምኖ ነው ያየሁት። ባንፃሩ የአረጋውያን እና እመቶች ቁጥር ደግሞ በጣም ብዙ ነው… የአኗናር ዘዬኣቸው በጣም ያሳዝናል… የምያውሩት ሰው ይናፍቃሉ፤ ኑሮኣቸው በኣብዘሀኛው ከሙንክስና ህይወት ጋር ይመሳሰላል። ዝም ብለው መቁጠርያውን እየደጋገሙ መቁጠር፤ ኣሁንም መቁጠር።
ከታች የምታይዋቸው እናት 8ት ልጆች ነበርዋቸው። ነበርዋቸው ነው ያልኩት! አሁን የወላድ መሀን ናቸው።
መጀመርያ ወለዱ “ፈጣሪ ወሰደባቸው”። አሁንም ወለዱ አሁንም አልሆነላቸውም። ቀጠሉ መንታ ወለዱ፤ ሓድጋትና የዕብዮ ብለው ሰየምዋቸው። ነገር ግን ሓድጋት በ2ት ዓመቱ፤ የዕብዮ ደሞ 3ት ዓመት እንኳን ሳይሞላው የቀደሙትን እህቶቻቸው ዕጣ ደርሷቸው ከዚህች ዓለም ተከታትለው አለፉ። ማሕፀናቸው ግን አሁንም ሌላ “ሸል መቋጠ ይብቃህ አልተባለውምና” አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ መንታ ወለዱ፤ 9ኝ ጊዜ ዕልልልልልልልል ተባለ። 3ቱ ዕልልታ ለሴትዋ፤ 7ቱ ደሞ ለወንዱ መንትያዋ።
አዎ በ7ት ዕልልታ ታጅቦ ቤተሰቡን የተቀላቀለው ወንዱ ስም እንኳን ሳይወጣለት “ጠፋ”… ሞተ። የቀደሙትን “ተቀላለቀለ”!
ሴትዋ ያለ መንትያ ወንድምዋ መረስዒት ተብላ ስም ወጥቶላት እያደገች ነው።
ቀድሞውኑ “የወላድ መሀን” መሆናቸውን የተነገራቹ እናት የህይወት ታሪክ ስለሆነ እየተተረከላቹ ያለው… እችስ እስከ ስንት ዓመትዋ ትቆይ ይሆን? ሩጫዋስ ምን ድረስ ይሆን እያላቹ ማሰባቹ ኣይቀርም…
አዎ መረስዒት (መርሻ ማለት ነው) እያደገች ነው። በ3ት ዓመትዋም ወንድም ተወልዶላታል። ስሙም ሓረጎት ተብለዋል። እናት ሲናገሩ ትንሹ ሓረጎት ከሙቱ ታናሽ ወንድማቸው (ታጋይ ሓረጎት) ጋር በመልክ በጣም ይመሳሰላል። ለዛም ነው ሓረጎት ያሉት። ሓረጎት ማለት የ”ፈጣሪ ችሮታ” እንደ ማለት ነው፤ ባገራችን ባብዝሀኛው አከባቢ፣ በባህላችንም ጭምር “ልጅ የፈጣሪ ፀጋ ነው” ተብሎ ነው የሚታሰበው፤ እና ፈጣሪ ልጅ ይነሳል፤ ልጅ ይሰጣል ተብሎ በሰፊው ይታመናል። እማማ ካሕሳም ልጃቸው ሓረጎት ብለው ስም ያወጡለት ከፈጣሪ የተበደርኩት ብድሬ/አደራዬ (ልጄ) ብለው ነው። የወንድማቸውም ማስታወሻ ጭምርም ስለሆነ ሓረጎትን በጣም ይወዱታል፤ ስፍስፍ ይሉለታል፤ ሲይስነጥሰው ሆነ ሲያስለው እማማ ካሕሳ ጉንጫቸው ከዓይኖቻቸው እንደጎርፍ በሚወርደው እምባ እንደ ታጠበ ነው። ያከባቢው ሰው “አረ እማማ ይተው”። “አረ እንዲህ በትንሽ በትልቁ ሆድ አይባሶት፣ ልጅኮ እየወደቀ እየተነሳ፣ እየታመመ እየዳነ ነው የሚይድገው” ብለው ቢመክሯቸው በፍፁም አይሰሙም። ሰርክ ማንባት ነው፤ ወደ ፈጣርያቸው ማልቀስ ነው። ዕረፍት የለም።
እንዴት ያሳዝናሉ? እንዴት ይጨንቃል?
~
ሓረጎት 4ት ዓመት ሲሞላው ደስታን ተወለደችለት። ሌላ እህት አገኘ።
እማማ ካሕሳ ደስታቸው እየተመለሰ ነው መሰለኝ እችን ትንሽዋ እምቦቀቅላ “ደስታ” ብለው ሰይመዋታል።
አሜን። ሙሉ ደስታ ያድርግላቸው።
አሁን 3ት ልጆች አልዋቸው። ቤቱ ሙሉ ነው። ትልቅዋ መረስዒት፣ ቀጥሎ ሓረጎት አሁንም ደስታ አሉላቸው። እማማ ካሕሳ ይሁኑ ባላቸው ቀሲስ ምሩፅ አሁን ደስተኞች ናቸው። “ያለፈውን ረስተው” 3ቱ ልጆቻቸው በደስታ እያሳደጉ ነው።
~
ጊዜው እንዴት ይሮጣል? መረሰዒት 8ተኛ ክፍል ደርሳለች። ዘንድሮ ሚኒስትሪ ልትወስድ ነው። ሓረጎትም 5ተኛ ደርሷል። ደስትዬም ብትሆን 3ኛ ክፍል ነች….
ሁሉም የሚማሩበት ት.ቤት ማይ እሞሪ አንደኛ ደረጃ ት/ት ቤት ይባላል። እነሱ ከሚኖሩበት ቀዬ (ኾኾሎ) ወደ 4 ወይም 5 ኪ.ሜሮች ገደማ ይርቃል። በቀን በአማካኝ ለ8/9 ኪ.ሜሮች እየተጓዙ ነው የሚማሩት ማለት ነው…
ይከብዳል አ?
~
መረስዒት የ8ኛ ሚኒስትሪ ፈተና ተፈትና ልታልፍ አልቻለችም… በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ነው ነገሩ፤ ባመቱ የጠበቃትም ትዳር ነበር። ወጣት መረስዒት… ስንት ህልም የነበራት መረስዒት… ያንሁሉ ቀርቶ… እጣ ፈንታዋ: ሳታስበው… በጨቅላነትዋ “እማወራ” መሆን ሆነ…
መረስዒት ለ3ት ዓመታት በባልዋ ቤተሰቦች ከቆየች በኃላ እርጉዝ ሆና ወደቤትዋ ተመለሰች… “እናትዋ ቤት እንድትወልድ” ተብሎም ነው።
እማማ ካሕሳ የልጅ ልጅ ሊያዩ በፍፁም ደስታ ተውጦው የጦፈ ዝግጅት ላይ ናቸው… ያልተማፀኑት መልአክ፤ ያልተሳሉት ስለት የለም። ጎረቤት እና ወዳጅ ዘመድም ቢሆን ሁሉም እየመጣ እርጉዝዋን መረስዒት እያየ “ለቆታ እንጣጢዕ ይግበረልኪ” (እመቤቴ እርግዝናውን ታቅልልሽ፤ ከዓይን ያውጣሽ) “እንትፍ ትፍ ትፍ….” እያሉ መርቀዋት ይወጣሉ።
~
የመውለጃዋ ቀን ደረሰ… ምጥ መጣ… መረስዒት ትጮሀለች… እናት ድንጋይ ተሸክመው “ማርያም ማርያም” ይላሉ… አባት ቀበቷወቸው ፈተው ከበራፍ ርቀው “ፈጣሪዬ የዛሬውን እለፈኝ፣ ልጄን ማርልኝ” እያሉ ይማፀናሉ….
ከብዙ ፀጥታ በኃላ… ከማማጫው ክፍል ዋይታ ይሰማል… ትልቅ ጭሆት። ዋይታ። ወይኔ ልጄ መረስዒት… ወይኔ… ወይኔ…
~
አልሆነም።
መረስዒት ልጅ ልትሰጥ ብላ ህይወትዋን አለፈች። የስዋም የህፃኑም ህይወት “ሞት በለመደው” የእናትዋ ቤት አለፈ።
~
ደስታም ብዙ ሳትቆይ፤ “እንዲህ ሆነች” ሳይባል በጠራራ ፀሓይ “ሓድጊ ወቂዕዋ” (ምች መቷት) ተብሎ ሞተች።
~
ሓረጎት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ታጋይ ሆኖ ዘምቶ ንሮዋል በውግያው ተሰዋ።
አባት ቀሲስ ምሩፅ በኾኾሎ ወልደ ዮሀንስ ገዳም በምንኩስና ሲኖሩ አረፉ።
እማማ ካሕሳ ከታች በምስሉ እንደምታይዋቸው ጆሮኣቸው እና ዓይናቸውም ብዙም አይሰሙም፤ አያዩም…. ሀዘን፣ ድህነት እና የዕድሜ ጫና እያጎሳቀልዋቸው… “ምን ነው ፈጣርዬ እኔን ረሳሀኝ? ለምንስ ከልጆቼ ጋር አትወስደኝም?” እያሉ ማልቀስ እና ማንባት የዘወትር ኑሮኣቸው መገለግጫዎች ከሆኑ ሰነባብተዋል። ህይወታቸውም እንዲህቹ ለ”ነብሴ” ያለ እየረዳቸው ይገፋሉ።
~
ከእንዲህ ያለ መዓት ይሰውረን።
…….
ማንኛውም ተጨማሪ መረጃ የምትሹ ጓደኞቼ ልትጠይቁኝ ትችላላችሁ።