October 18, 2017 10:34

ተክሌ በቀለ

ተክሌ በቀለ

ሀብታሙ አያሌውን የተዋወኩት ዛሬ በስደት ላይ በሚገኘው ጠንካራው የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ በፀጋዬ አላምረው በኩል ነው፡፡ የባለ ራዕይ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት በነበረበት ወቅት ማለት ነዉ፡፡ መጀመሪያ ላይ ወደ አንድነት ፓርቲ ለመግባት ያለውን እቅድ ተቃውሜዉ ነበር፡፡ ህወሓት እንደሚያደርገው የሲቪክ ማኅበራትን እንዳናጠፋ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል የሚል ጽኑ እምነት ነበረኝ፡፡ የኋላ ኋላ ግን ህወሓትን ጨምሮ የተወሰኑ ፓርቲዎች የማኀበሩን ወጣቶች ሲቀራመቱ እኔም ተቃውሜዬን አነሣሁ፡፡ ከዚያም ሀብታሙ አያሌውና በርካታ ትንታግ ወጣቶች ፓርቲውን ተቀላቀሉ፡፡

የፓርቲያችን ዕድሜ ማጠሪያ ሊሆን እንደሚችል ብንረዳም ምርጥ ኢትዮጵያውያንን ከማሰባሳብ አልታቀብንም ነበርና ሀብታሙ አያሌውና ሌሎች የትግል ጓዶቹም ቤቱ ቤታቸው እንዲሆን ሁለገብ ሥራ ተሠራ፡፡ ሀብታሙ ገና ፊርማው ሳይደርቅ የፓርቲውን ከፍተት በየመስኩ በመሙላት በኩል ትልቅ አስተዋፅኦ አበረከተ፡፡ ይህ ድርጊቱ ግን ብዙ ተቃውሞ አስከተለበት፡፡ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ተባበሩበት፡፡ ነገር ግን ውስጡ ያለውን እውነተኛ የአገር ፍቅርና ሀቀኛ የትግል ስሜት ለመረዳት ያልተቸገርነው ከጎኑ ተሰልፈን ብርቱ ድጋፍ ማድረጋችንን ቀጠልን፡፡ እሱም በመጽሐፉ እንደተረከው በፓርቲው ውስጥ ከተፈጠረው የለውጥ ፍላጎት ጋር በአጭር ግዜ በመዋሃዱ የለውጡ ዋነኛ ኃይል ሆኖ ተገኘ፡፡ ሆን ተብሎ ለማጥፋት ታቅዶም ሆነ በስህተት የአሉባልታው ዘመቻ
በተፈለገው መድረክ ቢተረክበትም ከለውጥ ኃይልነቱ ሊያናጥቡት አልቻሉም፡፡ እንዲያውም የበለጠ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ግንዛቤ ተይዞ የተሻለ የኃላፊነት ቦታዎች እንዲሰጡት ተደረገ፡፡ የኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ካቢኔ ሲመሠረትም የሕዝብ ግንኙነቱን ክፍሉን በዋናነት እንዲመራ ተሰየመ፡፡ በሂደትም ‹‹የሚሊዮኖች ድምፅ ለነጻነት›› የሚባል ፕሮጀክት ተቀረፆ ተግባራዊ ሲደረግ በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ሀብታሙ ፕሮጀክቱን እንዲመራ፤ እኔ ደግሞ የግምገማና ክትትል ኃላፊ በመሆን አጠቃላይ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ሳምንታዊ ሪፖርት ለሥራ አስፈፃሚው እንዳቀርብ ተመደብን፡፡ የተበታተነው የፖለቲካ ፓርቲ የተቃውሞ ጎራው ወደ አንድ
ኃይልነት ለማሰባሰብ እኔና ሀብታሙ አያሌው በአንድ ምድብ ተመድበን ለመሥራት እድሉን አግኝተናል፡፡

አንድነት ፓርቲን ከመኢአድ እንዲሁም ከዓረና ትግራይና ከቀሪዎቹ የመድረክ አባላት (ግንባር) ጋር በማዋሃድ ትግሉን አንድ እርምጃ ለመውሰድ  ብዙ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገናል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በደሴ ከተማ የተከናወነውን በሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ሰላማዊ ኮሚቲ  የእስር እርምጃ መወሰዱን ለመቃወምና ገበሬው የመሬት ባለቤት እንዲሆን ለመጠየቅ ሰላማው ሰልፍ ለመምራት በስራ ኣስፈፃሚዉ እንድመራ ስመደብም ሀብታሙ አያሌው የቀኝ እጅ ነበረና በጋራ ሰፊ እድል አግኝተን ስለ አገራችን አውግተናል፡፡ ከሁሉም በላይ ባሕሪይው የሚከብድ ነገር ስለሌለው ስለ አገር ሆነ በግል ጉዳያችን ብዙ ለመመካከር እድል አግኝተናል፡፡ እናም ሀብታሙ አያሌውን በቅርብ አውቀዋለሁ፡፡ ሁለገብ ችሎታ ያለው በወገንና በአገር ፍቅር የተለከፈ ከዕድሜው በላይ የበሰለ ውድ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከምር ሕይወታቸውን አስይዘው ፖለቲካ ከሚሠሩ ሰዎች አንዱ እንደ ሆነ እውነተኛ ምስክር ነኝ፡፡

ከኢህአዴግ ጋር ለሁለት ዓመታት እንደመኖሩ የገዥውን ፓርቲ ባሕርይ በደንብ ተረድቷል፡፡ በተለያየ ምክንያት ልሳናቸው ‹በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት› ስም ታፍነው በኢህአዴግ ውስጥ በቁዘማ ጊዜያቸውን ለሚያቃጥሉ ወጣቶች ሀብታሙ አያሌው ትልቅ አርአያ እንደነበረ በኢህአዴግ ቤት ሚንስትር ዴኤታ የነበረው አቶ ኤርምያሰ ለገሰ ‹የመለስ ቱሩፋት› በሚለው መጽሐፉ ብዙ እንደተረከልንም እናስታውሳለን፡፡ የፖለቲካ ትብተባ ሰንሰለትን በጣጥሰው ወደ ተቃውሞ ጎራ ከመጡ ወጣቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን አመለካከትን በአመለካካት ከመመከት በቀር ጥላቻ ብሎ ነገር አልፈጠረበትም፡፡ ሕዝብና ፖለቲካ ፓርቲን ከለዩ ጉምቱ ፖለቲከኞች አንዱ መሆኑን በርግጠኝነት መመስከር እችላለሁ፡፡ ‹ከህወሓት ሰማይ ሥር› የሚለው የአሁኑ መጽሐፉም ይህንኑ
ጽኑ እምነቱን በሚገባ ያስረዳል፡፡

ኣንድነት ፓርቲ የለዉጥ ሃይሎች ማእካል እንዲሆን የሚፈልጉ ወገኖች የሃሳብ ቀያሽ የሆነዉ ኣካላት  ከሁለት ሰይፍ ጥቃት ጥበቃ ለማድረግ የምንችለውን ሁሉ የታገልነዉም ለዚሁ ነበር፡፡ የሆነው ሆነና ከህወሓት ኢህአዴግ
የግፍ እስር ልንታደገው አልቻልንም፡፡በቀለኞች ተበቀሉት፡፡ እርሱ ለእስር ቢዳረግም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት የተጀመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ውህደት በማጠናቀቅ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲገነባ ለማድረግ የቦዘነ አመራር አልነበረም፡፡ በህወሓት ኢህአዴግ የሴራ ፖለቲካ የተፈበረከ መጠነኛ የነበረ የውስጥ ቅራኔ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ለ2007 ዓ/ም አገራዊ ምርጫ ብቁ ኃይል ሆኖ ለመውጣት ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡

ህወሓት ኢህአዴግ ግን ጫና በመፍጠር ማንበርከክ ሲሳነው እንደ ልማዱ ከሕግ በላይ በመሆን የወታደራዊ አቅሙን በመጠቀም ብቻ ፓርቲያችንን ቀማን፡፡ንብረቱ ተዘረፈ፤ሃብታሙ አያሌውም(እንደሌሎቹ ታጋይ ጓዶች ሁሉ) በወህኒ ቤት እንዳለ ፓርቲ አልባ ሆነ፡፡

የህወሓት የጉልበተኛነት ውጤት ግን ዛሬ የምናየውን ሁኔታ አስከተለ፡፡

ሃብታሙ ከሃያ በላይ ከተሞች ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባብሮአል፡፡ ሞንታርቦ ይዞ ለነጻነት ጮኋል የህወሓት ጉጅሌዎች ግን ሁሉን ነገር በአፈና ያለፉት ቢመስላቸውም ዛሬ ግን በኢትዮጵያችን ሺህ ሀብታሙዎች ተፈጥረው የሚያቆማቸው ኃይል ጠፍቶ እዚህ ደረጃ ተደርሶ ስመለከት አገሬ መጪው ግዜዋ ብሩህ ሊሆን እንደሚችል ይሰማኛል፡፡

ይህን አስተያየት በምጽፍበት ወቅት ሀብታሙ አያሌው ወኅኒ ቤት በተፈጸመበት ግፍ ሕይወቱ አደጋ ላይ ነበር፡፡ ቂመኞች ማየት የሚሹትም ሞቱን ቢሆንም ፈጣሪ ግን ከሱ ጋር ሆኖ ከታሪክ ሠሪዎች መሐል እንደምናገኘው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በመጨረሻም አንድ ነገር ልበል ሀብታሙ አያሌው ለብዝኀነት ክብር አለው፡፡ የጎበጠውን ለማቅናት እንጂ ተጨማሪ ጉዳት ለማድረስ የሚያስችል የሞራል ሁኔታ የለውም፡፡ በሆነ ወቅት በሆነ አጋጣሚ አንድነት ፓርቲ በጋራ ይሠራበት ከነበረው ግንባር ጋር ለማላተም የፈለጉ ቡድኖችም ተፈጥረው ነበር፡፡ በወቅቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ሴራ ታሪክ ጊዜ የሚፈታው ቢሆንም ሀብታሙ አያሌው ፓርቲዎች የትኛውም የአደረጃጀት መሠረት ይኑራቸው ማንነትን መሠረተ ያደረገ ተቃውሞ ይሁን ጥላቻ የለውም፡፡ ይህንንም ሐሳቡን በውብ ቋንቋ በዚህ መጽሐፍ ክሽን አድርጎ አውግቶናል፡፡  እንኳንም ለዚህ አበቃህ ሀብትሽ፡፡

በሃብታሙ ኣያሌዉ መፅሃፍ ዉስጥ ግለሰቦች ኣለያም ተቋማት በኣወንታዊም ይሁን በኣሉታዊ ጎን ተወስተዉ ሊሆን ይችላል፡፡ከነበረበት ዉስን ሁኔታ በቂ መረጃ ካለመኖር የትንታኔ ክፍተት ሊፈጠር ይችል ይሆናል፡፡ለሚፈጠረዉ ክፍተትም ደራሲዉ ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡ተነካን የሚሉ  ብቻም ሳይሆን ሌሎች ባለድርሻ ኣካላትም የመሰላቸዉን ሃሳብ ይዘዉ ደራሲዉን የመተቸት መብት ይኖራቸዋል፡፡ክብሬ ተነክቷልና የደራሲዉን ክብር በመንካት ብድሬን እመልሳለሁ የሚል ስሌት ዉስጥ ከተገባ ኦሪታዊ እይታ ይመስለኛል፡፡በተለይም በከፍተኛ የፖለቲካ የስልጣን እርከን ላይ ተቀምጠን ትግሉን ለማስተባበር ስንተጋ ከነበርን ኣካላት የሚደመጥ ክብር የለሽ ሃሳብ ሁሉንም የሚነካና ትዝብት ዉስጥ የሚጥል ይሆናል፡፡ይህን እድል ያስገደደኝ የቀድሞዉ ኣንድነት ፕ/ት ኢ/ር ግዛቸዉ ሽፈራዉ ስለመፅሃፉና ስለ ኣቶ ሃብታሙ ኣያለዉ በፅሁፍ ያሰቀመጡት ኣስተያየት ነዉ፡፡በእዉነት እንነጋገር ከተባለና ሁሉን ነገር የኣደባባይ እናድረገዉ ካልን በመፅሃፉ ዉስጥ እሳቸዉ የተነሱበት ሃሳብ በጣም ትንሽና ያልተተነተነ ሆኖ ይገኛል፡፡በመድረክ-ኣንድነት፤በመኢኣድ-ኣንድነት፤በኣንድነት-ዓረና….ባጠቃላይ በፓርቲዎች ህብረትና ዉህደት በጠባብ ፍላጎት መነሻነት ብዙ ግፍ ተፈፅሟል፡፡የሰዎች ስም ጠፍቷል፤ኃላ-ቀር ኣስተሳሰቦች ተራምደዋል፡፡የመርህና የደንብ ጥሰቶች ከመኖራቸዉም በላይ ኣፀያፊ ደርጊቶችም ተከናዉነዋል፡፡ከገዥዉ ፓርቲ ሰዎችም በጓሮ በር ለመሞዳሞድ ተሞክሯል፡፡መሞዳሞዱ ኣጠቃላይ ትግሉንና ኣንድነት ፓርቲንና ሰላማዊ ትግሉን ኣጣብቂኝ ዉስጥ ስለሚከት በወቅቱ ተቃዉሞ በማቅረቤ ተቋርጧል፡፡

በግላቸዉ ከፈለጉ መቀጠል እንደሚችሉ መብታቸዉ መሆኑንም ነግረናቸዋል፡፡የሚፈይደዉ ነገር ባይኖርም ራሱን የቻለ መፅሃፍ ይወጣዋል፡፡እሳቸዉ ከመሰረቱት ካቢኔ ኣምስት የስ/ኣስፈፃሚ ኣባላት ከሃለፊነት ለመልቀቅ ያበቃንን ዉሰኔ እስከዛሬም ድረስ ለየትኛዉም ሚዲያ ኣልገለፅንም፡፡ለትግሉ የሚጨምር እንጂ ትግሉን የሚያቀዛቅዝ ነገር መጨመር የሚያሰችለን የቅንጦት ሁኔታ ላይ ኣይደለንምና ነዉ፡፡እሳቸዉ በዚህ ኣቀራረብ ሃሳባቸዉን መሰንዘራቸዉ መብታቸዉ ሆኖ ይበልጥ ያስከብረኛል፤የኣንባቢን ጀሮም በመሳብ የፖለቲካ ትርፍ ኣገኛለሁ ብለዉ ካሰቡ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸዉ ከማለት ዉጪ የምለዉ ኣይኖረኝም፡፡

ኣሁንም እግረ መንገዳቸዉን የኔን የስራ ቦታ በማዛባት ስም ለማጥፋት መሞከራቸዉ ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቄስ ኣይለቅም የሚለዉ ብሂል ኣእምሮየ ላይ ይመጣል፡፡እኔ የምሰራዉ መንግስታዊ ላልሆነ(ለፋይናንስ ሴክተሩ በተለይም ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከኣለም ኣቀፍ ኣጋሮች ጋር በመሆ በስልጠናና ምርምር የተሰማራ) ኣገር በቀል ድርጅት ሲሆን እሳቸዉም ባንድ ወቅት በትርፍ ሳአቴ ኣስተምርበት በነበረዉ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ነዉ የሚሰሩት፡፡በኢትዮጵያችን ያሉ ተቋማት ሁሉ የህወሓት እያሉ መፈረጅም ትክክል ኣይመስለኝም፡፡ ለኔ ፍረጃ ያረጀ ኣስተሳሰብ ነዉ፡፡የተቃዋሚዉ ጎራ ኣንዱ ችግር ኣደባባይ ላይ አስኪበቃዉ ይዘራጠጥና በኃላ ኣብሮ ለመስራት ሲተናነቀዉ እናያለን፡፡እናም ከዚህ ወዲህ ከሳቸዉ ጋር እሰራለሁ የሚል እቅድ ባይኖረኝም እለፊ ላለመናገር እተወዋለሁ፡፡ ያማለት ግን ሃብታሙ ፍፁም ነዉ ማለት ኣይደለም፡፡ግድፈቱ ለኔ ኣልታየኝም፡፡ ኣለበት ከተባለ በስርኣትና በክብር ነዉ መተቸት ያለበት፡፡

ይህን ካልኩ ዘንዳ ኣንድ እዉነት ልናገር፡፡ኢ/ር ግዛቸዉ ወደ ፕ/ትነት የመምጣት ፍላጎት ቢኖራቸዉም “ተለምነዉ” ጭምር ነዉ የመጡት፡፡እኔም ስህተት እንደፈፀምኩ ለመረዳት ግዜ ባይወስድብኝም ሙሉ ድጋፌን ሰጥቻለሁ፡፡በወቅቱ ኣምኘባቸዋለሁ፡፡ኣሁን ለመክሰስ እንደሚሞክሩት ሳይሆን በልዩነትም ኣብረን ያወራነዉን ሚስጢር ጠብቄኣለሁ፡፡ኣንድነት ፓርቲ የፈረሰዉ በፖለቲካ ዉሳኔ ነዉ፡፡እሳቸዉ ለገዥዉ ፓርቲ ሚድያ የሰጡት ኣስተያየት ለህዝብ በማደናገሪያነት እንዲቀርብ የተፈለገ ምክያት ነዉ፡፡ባጭር ኣገላለፅ ኣብሬ በሰራሁባቸዉ ወራት የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር ኢ/ር ግዛቸዉ የተገነባን ግንኙት ለማፍረስ የማይሳሱና ችኩል  ለመገንባት ትግስቱና ግዜዉ የሌላቸዉ በበጎች መሃል የሚኖሩ ጉልበታም ፈረስ ናቸዉ፡፡ኣዙሮ የማየት ችሎታዉን ያልታደሉ በጣም መካኒካል ሰዉ ሲሁኑ መርህና የፓርቲ ዲስፒሊን የሚባሉ ነገሮች የሉዋቸዉም፡፡

ትንሽም ቢሆን የምትጠቅማቸዉ ከመሰላቸዉ ያምኑሃል፤ሰማይ ይሰቅሉሃል፡፡ከተቃወምክና ከጠሉህ ምንም ይኑርህ ምን ባዶ ኣድርገዉ ያራቁቱኃል፡፡የልጅ ልጃቸዉ የሚሆነዉን ሃብታሙ ኣያሌዉን ከመኮትኮትና ለማስተካከል ከመጣር ይልቅ በሆነ ወቅት ወያኔ ነዉ ላባርረዉ ነዉ እንዳላሉን ሁሉ በሌላ ወቅት (ከባህርዳር ሰልፍ በኃላ ደግሞ) ደግሞ ላይኔ እሳሳለታሉ እንዳላሉ ባደባባይ እንዲህ ለማራቆት መነሳታቸዉ ይኸዉ ባህሪያቸዉ መገለጫ ነዉ፡፡

በዚህ ስብእናቸዉ የመንግስት ስልጣን እጃቸዉ ላይ ቢገባ የምንፈልገዉን ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ ላያመጡ ይችላሉ ከምላቸዉ ሰዎች ዉስጥ ኣንዱ ናቸዉ፡፡ፕ/ር መስፍንን ጨምሮ ከ26 ባላይ የሚልቁ ኣመራሮችን ከኣንድነት ያባረሩበትን ሁኔታ ሁሌም በስብሰባዎች ሳይቀር በኩራት ሲያወሩት እጅግ ኣፍር ነበር፡፡በዚህ ሳይፀፀቱ ስለቀጣይ ሃብታሙንና ሌሎች ኣመራሮችን ማባረር ያልሙ ነበር፡፡ደግነቱ የቆሙበት ም/ቤት ጠንካራ ስለነበርና ለሁለታችንም ም/ፕሬዝደንቶች ሚዛን ስለነበራቸዉ ከስህተት ታድገናቸዋል ብየ ኣምናለሁ፡፡

በዚህ ግዜ የዚህ ኣይነት የመጠላለፍና የመዘላለፍ ተቃዋሚ ነኝ ከሚል ሰዉ መፃፉም ግርምትን ኣጭሮብኛል፡፡ባለፈ ነገር ተጎትቸ በመግባቴና ሃሰብ ለመስጠት በመገደዴ ቅር የሚያሰኝ ሃሳብ ሰንዝሬ ከሆነ ምንም ማድረግ ኣልቻልኩምና ኣንባቢን የከበረ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡